Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከየመኑ ኮንትራክተር የተነጠቀውን መንገድ ለመገንባት የቻይናው ኩባንያ አነስተኛ ዋጋ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ግንባታውን ለማስጀመር የአፍሪካ ልማት ባንክ ውሳኔ ይጠበቃል

የየመኑን ኮንትራክተርና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንን ሲያወዛግብ የቆየው የጩኮ ይርጋጨፌ መንገድ ፕሮጀክትን ለሌላ ኮንትራክተር ለመስጠት በተካሄደ ጨረታ ሲኖ ሃይድሮ የተባለ የቻይና ኮንትራክተር አነስተኛ ዋጋ ማቅረቡ ተጠቆመ፡፡ የቀረበው ዋጋ ቀድሞ ኮንትራት ከተፈረመበት በላይ ሆኗል፡፡  

ሐዋክ ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮንስትራክሽን ሊሚትድ ከተባለው የየመን ኮንትራክተር በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታውን ማካሄድ አልቻለም በሚል የፕሮጀክቱ ሥራ በሌላ ኮንትራክተር እንዲሠራ በወጣው ጨረታ መሠረት አምስት ኮንትራክተሮች ተፎካካሪ ሆነው ቀርበው ነበር፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ የየመኑ ኮንትራክተር ጀምሮት የተወውን ሥራ ለማጠናቀቅ ቀረበ የተባለው ዝቅተኛ ዋጋ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ከየመኑ ኮንትራክተር እስኪነጠቅ ድረስ ከጠቅላላ የፕሮጀክቱ ሥራ ከ45 በመቶ ተጠናቋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ኮንትራክተሩን ግን 60 በመቶ ስለመድረሱ ገልጾ ነበር፡፡ አሁን በተካሄደው ጨረታ ሲኖ ሃይድሮ ባቀረበው ዋጋ መሠረት ሥራው ከተፈቀደለት የሚከፈለው፣ የየመኑ ኮንትራክተር ጀምሮ ያልጨረሰውን የፕሮጀክቱ ክፍል ይሆናል፡፡

ከየመኑ ኮንትራክተር ጋር ተገብቶ በነበረው ውል 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን መንገድ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ ነበር፡፡ ሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ሥራው መጠናቀቅ ነበረበት፡፡ ኮንትራክተሩ በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ ሳይችል በመቅረቱ፣ ባለሥልጣኑ ውሉን ማቋረጡን አስታውቋል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት፣ ግንባታው ከተቋጠ በኋላ ግንባታውን ለማስጀመር የተለየ አካሄድ እንደተከተለ ታውቋል፡፡

ይህም በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት በተደገፈ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን ኮንትራክተሮች በጨረታ በመጋበዝ የተከናወነ ነው፡፡ አምስቱ ተፎካካሪ ኩባንያዎችም በዚህ መንገድ ተመርጠው ዋጋቸውን በማቅረብ የተወዳደሩ ናቸው፡፡

አሁን አነስተኛ ዋጋ አቀረበ የተባለውም ኮንትራክተር ሥራው የሚፀድቅለት መጀመሪያ የፋይናንስ ድጋፍ ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ሲያፀድቀው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በባለሥልጣኑና በየመኑ ኮንትራክተር መካከል የተፈጠረው ያለመግባባት በግልግል እንዲፈታ አደራዳሪ ቦርድ ተሰይሞ ጉዳዩን እየተከታተለ ነው፡፡ አደራዳሪ ቦርዱ ሊያስተላልፍ የሚችለው ውሳኔ ለውጥ አያመጣም እየተባለ ሲሆን፣ ኮንትራክተሩ ደግሞ በኮንትራት ውሉ መሠረት ግንባታውን ያላጠናቀቀው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ችግር ነው በማለት ሲከራከር ቆይቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ግን ሊደረግለት የሚገባው እገዛ ተደርጐለታል ይላል፡፡

ሆኖም ግን በፕሮጀክቱ ላይ ስለተፈጠረው አለመግባባት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና ሐዋክ የተለያዩ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ዕርምጃውን የወሰድኩት ለኮንትራክተሩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰጠሁ በኋላ ነው ሲል፣ ኮንትራክተሩ ደግሞ ግንባታውን ለማከናወን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሊፈጽማቸው ይገቡ የነበሩ ተግባራት ሊፈጸሙ ባለመቻላቸው የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑ ይገልጻል፡፡ በተለይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ባለሥልጣኑ ለግንባታው እንቅፋት የሆኑ እንደ የኤሌክትሪክ ምሰሶና የመሳሰሉትን ግንባታዎች ማንሳት ባለመቻሉ ጭምር ነው ይላል፡፡ ይህም የፈጠረውን ችግር በመገንዘብ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ የግንባታ ማራዘሚያ ጊዜ እንዲሰጠው ጥያቄ ቢያቀርብም፣ አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘቱን፤ ይህም በኮንትራት ውሉ መሠረት ለሥራው እንቅፋት በመፈጠሩ ቀድሞ የውል ማቋረጫ ደብዳቤ በማስገባት የኮንትራት ውሉ መቋረጥ ዕርምጃን የወሰድኩት እኔ ነኝ ይላል፡፡

በባለሥልጣኑና በኮንትራክተሩ መካከል የተፈጠረውን ያለመግባባት ለመሸምገል የተሰየመው አደራዳሪ ቦርድ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑ እየታወቀ፣ የቦርዱ ውሳኔ ሳይታወቅ ግንባታውን ለሌላ ኮንትራክተር ሊሰጥ መሆኑንም ይቃወማል፡፡

ውሉ መቋረጡና ለሌላ ኮንትራክተር መሰጠቱ የመንገድ ግንባታ ወጪውን ይጨምራል የሚለው እምነት በሁለቱም ወገኖች በኩል ተጠቅሶ የነበረ ሲሆን፣ እንደ አዲስ በተካሄደው ጨረታ ቀረበ የተባለው አነስተኛ ዋጋ ቀደም ብሎ የነበረውን ሥጋት በተጨባጭ ያረጋገጠ ሆኗል፡፡

ከሰሞኑ እንደታወቀውም ቀሪውን የመንገድ ግንባታ ለማከናወን የቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት 60 ኪሎ ሜትሩን መንገድ ለመገንባት ተሰጥቶ ከነበረው ዋጋ በላይ ሊሆን ችሏል፡፡

ሐዋክ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 786.7 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ የኮንትራት ውሉ ሚያዝያ 2005 ዓ.ም. ሲፈረም ሐዋክ ግንባታውን በሦስት ዓመት አጠናቅቆ ሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ለማስረከብ ተስማምቶ የገባበት ቢሆንም፣ በውሉ መሠረት በተያዘለት ጊዜ ሊያጠናቅቀ አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች