Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትየአገራችን የፖለቲካ ቀውስ መንስዔና መፍትሔ - በምክንያታዊ ዓይን

  የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ መንስዔና መፍትሔ – በምክንያታዊ ዓይን

  ቀን:

  የመጨረሻ ክፍል

  በልደቱ አያሌው

  ባለፈው ሳምንት በክፍል አንድ በቀረበው ጽሑፍ አገሪቱ ወደተካረረ ቅራኔ የገባችበትን ምክንያቶች በዝርዝር በማውሳት፣ በአሁኑ ወቅት የተጋረጠውን አደጋ በመሻገር ወደ ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ ለማስገባት የሚረዳ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት የሚረዱ ችግሮች ተወስተዋል፡፡ የመጨረሻ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

  ልማታዊ መንግት አስተሳሰብ ህፀፆች

  አሁን አሁን የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ ያጡ አንዳንድ የአፍሪካ መንግሥታት የልማታዊ መንግሥትን ቀዳሚ ትርጉም ለራሳቸው በሚጥም መንገድ እየቀየሩ ሊጠቀሙበት ቢሞክሩም፣ በአብዛኛው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች እንደታየው  የልማታዊ መንግሥት ዋና መገለጫ ባህሪ መንግሥት ራሱን ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር አድርጎና የፖለቲካ መብቶችን ደፍቆ፣ ጠንካራ ዲሲፒሊን ባለው ቢሮክራሲ አማካይነት ፈጣን የኢኮኖሚና የልማት ዕድገትን ማምጣት ነው፡፡ የልማታዊ መንግሥት ትክክለኛ መገለጫው ይህ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ አስመሳይ (Pseudo) ዴሞክራሲ ያላቸው አንዳንድ አገሮች ‹‹ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ነን›› በማለት ራሳቸውን በመጥራት፣  ልማታዊ መንግሥትነት ዴሞክራሲንም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን በጣምራ ማምጣት የሚያስችል ሥርዓት ነው በማለት አዲስ ግን ትርጉም የለሽ አስተሳሰብ ይዘው መጥተዋል፡፡

  ትርጉም የለሽ የሚሆንበት ምክንያት አንድ መንግሥት ዴሞክራሲንና የኢኮኖሚ ዕድገትን በጣምራ ማምጣት ከቻለ በአብዛኞቹ የምዕራብ አገሮች እንደሚታየው የዚያ ዓይነቱ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ወይም የካፒታሊስት ሥርዓት ተብሎ ይጠራል እንጂ፣ በተለየ ሁኔታ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ተብሎ መጠራት አያስፈልገውም፡፡ ምክንያቱም በ1970ዎቹ ለመጀመርያ ጊዜ ይህ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› የሚለው መጠሪያ የተፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይኖራቸው በአምባገነናዊ መንግሥት እየተመሩ ትክክለኛ ነው ተብሎ ከታመነበት መንገድ ውጪ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያመጡ ያሉ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮችን ምን ብለን እንጥራቸው? ለሚለው የወቅቱ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ተብሎ ቻልመርስ ጆንሰን በተባለ ሰው የወጣ ስያሜ ነው፡፡ አንዳንድ ቦትስዋናን የመሰሉ አንፃራዊ ዴሞክራሲ ያላቸው አገሮች መንግሥታቸው በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ቁጥጥር ያለው ከመሆኑ አንፃር  ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› እየተባሉ በተለምዶ ቢጠሩም፣ ይህ መጠሪያ በዋናነት ጥቅም ላይ የዋለው ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳይኖራቸው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላመጡ የእስያ አገሮች ነው፡፡ ኢሕአዴግም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ (በሕወሓት መፈረካከስ ወቅት) ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ አጥቶ ሲውረገረግ በአቶ መለስ ዜናዊ አማካይነት በድንገት ጠልፎ የያዘው ስያሜ ነው እንጂ፣ ልማታዊ መንግሥትነት ከመጀመርያው በበቂ ጥናትና ትንታኔ ተደግፎ በድርጅት ውሳኔ የተያዘ መስመር አይደለም፡፡

  ዞሮ ዞሮ ቀደም ሲል ኢሕአዴግ ምን ያህል ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ ያለው ድርጅት መሆኑን ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ እንደ ብዙዎቹ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመድፈቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማምጣት እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘበት ወቅት የቀዝቃዛው ጦርነት በምዕራቡ ዓለም አሸናፊነት የተደመደመበት ወቅት ስለነበረና እሱን ተከትሎ የመጣው የዓለም የኃይል አሠላለፍ የማያመች ሆኖበት እንጂ፣ ኢሕአዴግ በውስጣዊ ዕምነቱ ከቻይና የተለየ አመለካከት ያለው ድርጅት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በየዕለቱ በሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ምዕራባውያንን ሲያንቋሽሽ የሚውለው፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ሲያፍን የሚውለው፣ የፓርቲ የንግድ ድርጅት አቋቁሞ የሚነግደው፣ ከካድሬ እስከ ጋዜጠኛና ባለሀብት ያለው ኅብረተሰብ በሙሉ ልማታዊ መሆን አለበት ብሎ ጫና የሚፈጥረው በእርግጥም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ቻይናዊ ልማታዊ መንግሥት ስለሆነ ነው፡፡ በቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲና በኢሕአዴግ መካከል ያለው መሠረታዊ  ልዩነት- የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ያለምንም ማስመሰል በአሁኑ ወቅት ለቻይና ሕዝብ የሚያስፈልገው የኢኮኖሚ ዕድገት እንጂ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት አይደለም ብሎ በግልጽ ይናገራል፡፡ ኢሕአዴግ ግን በተግባር ላይፈጽመው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ የሞት የሽረት ጥያቄ ነው እያለ ያስመስላል፡፡

  ይህ የኢሕአዴግ የተንሻፈፈ አመለካከት ያስከተላቸው ችግሮች (ወረድ ሲል እናያቸዋለን) መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በኢኮኖሚ ዕድገትና በልማት መስፋፋት ረገድ ኢሕአዴግ ባለፉት 20 ዓመታት ያስመዘገበው ውጤት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በተለይም በመሠረተ ልማትና በትምህርት መስፋፋት ረገድ (የጥራት ጉድለቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) በኢሕአዴግ ዘመን የተሠራው ሥራ እንደ ትውልድ ሁላችንንም ሊያስደስትና ሊያኮራ የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚ ዕድገትና የልማት መስፋፋት ጉዳይ ከድህነት የመላቀቅና የመበልፀግ ጥያቄ በመሆኑ፣ ለፖለቲካዊ ደኅንነታችንም ሆነ ለአገራችን ህልውና መቀጠል ያለው ፋይዳ ከፍተኛና የማይተካ ነው፡፡ በኢኮኖሚው ዙሪያ የሚታየው ዕድገት በአንድ በኩል የሥራ ዕድልና የኑሮ መሻሻል ተስፋ በመፍጠር አንፃራዊ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖረን ያደረገ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እየተፈጠረ ያለው የመሠረት ልማት መስፋፋት ሕዝቡ እርስ በርሱ እንዲተሳሰርና የመሀሉና የዳሩ አገር ሕዝብ እንዲቀራረብ በማድረግ አንፃራዊ አንድነት እንዲኖረን አድርጓል፡፡

  ላለፉት 25 ዓመታት የአንድነት ሳይሆን የልዩነት ፕሮፖጋንዳ ያለማቋረጥ ሲነዛ የመኖሩን ያህል ተስፋ ሰጪ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በአገራችን ባይኖር ኖሮ ከነ ችግሮቹም ቢሆን ዛሬ በአገራችን የሚታየው አንፃራዊ የፖለቲካ መረጋጋትም ሆነ የአገር አንድነት ጭራሹንም ላይኖር ይችል ነበር፡፡ ስለሆነም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ማንም ይሁን ማን፣ እንውደደውም እንጥላውም የኢኮኖሚ ዕድገት ከአጠቃላዩ ህልውናችን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ቁም ነገር ስለሆነ ለአፍታም ሳይቋረጥ የሞት የሽረት ትግል ተደርጎ መቀጠል አለበት፡፡ 

  የተማረና መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አመች ሁኔታ የሚፈጥረው፣ ሕዝቡን በመሠረተ ልማት ግንባታ በማስተሳሰርና በማቀራረብ የዳር አገሩን መሀል በማድረግ የሕዝብና የአገር አንድነትን በከፍተኛ ፍጥነት ማጠናከር የሚችለው ከምንም ነገር በላይ የኢኮኖሚና የልማት ዕድገት ጉዳይ ስለሆነ በአገሪቱ ያለው ሥርዓት አምባገነናዊ በሆነበትም ሁኔታ ሳይቋረጥ መቀጠል ያለበት ነው፡፡  የልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት በሒደት መብቱን የመጠየቅና ጥቅሙን የማስከበር አቅም ያለው ጠንካራ ሕዝብ በመፍጠር የአምባገነናዊ ሥርዓትን ዕድሜ የሚያሳጥር እንጂ፣ አንዳንድ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች እንደሚሉት የአምባገነኖችን ዕድሜ የሚያራዝም አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ትግል ስም ኢንቨስትመንትን በአገራችን እንዳይስፋፋ የሚደረገውን ቅስቀሳና ንብረትን በማቃጠልና በማውደም እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ መቃወም ያለብን፣ ከቅርቡ የኢኮኖሚ ጥቅማችን አንፃር ብቻም ሳይሆን ከሩቁ የፖለቲካ ጥቅማችን ጭምር አንፃር ነው፡፡ ነገር ግን ከልማታዊ መንግሥት አመለካከት ጋር በተያያዘ በኢኮኖሚው ዘርፍም ለሕዝቡ ብሶት መባባስ ተጨማሪ ምክንያት የሆኑ ችግሮች በአገራችን አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች እንደሚከተለው እርስ በርስ ተዛማጅ በሆኑ በሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

  ከገደብ ያለፈ የኢኮኖሚ ቁጥጥርና ጣልቃ ገብነት

  ከፍ ሲል ከአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ኢሕአዴግ ፖለቲካውን ለመቆጣጠር ኢኮኖሚውን መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ከሚለው አመለካከቱ ጋር በተያያዘ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ቁጥጥርና ጣልቃ ገብነት ያለው መንግሥት ነው፡፡ በፓርቲ ድርጅቶች፣ በመከላከያ ሠራዊቱና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አማካይነት በከፍተኛ የንግድ ሥራ ውስጥ የገባ ከመሆኑም በላይ፣ ሲያስፈልገውም ተራ የሸቀጣ ሸቀጦችን ዋጋ እስከመተመን በሚደርስ ተግባር የኢኮኖሚ ገበያውን ለመቆጣጠር የሚሞክር ድርጅት ነው፡፡ በዚህ የተዛባ አስተሳሰብ ምክንያት በልማት ሥራና በሥራ ቀጣሪነት ከፍተኛ ሚና ሊጫወት የሚገባው የአገራችን የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚገባውን ያህል ማደግና መስፋፋት አልቻለም፡፡ ከዕዝ ኢኮኖሚ ወጥተን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ገባን ከተባለ 25 ዓመታት የሆነን ቢሆንም፣ በአገራችን ዋናው አልሚና ሥራ ቀጣሪ አሁንም መንግሥት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥትና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የሰው ኃይል በከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የሙስና ተግባር ውስጥ የተዘፈቀ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ዋና ሥራ ቀጣሪ ሆኖ መቀጠሉ ሥራ ተቀጣሪነትን ከፓርቲ አባልነትና ደጋፊነት ጋር በማያያዝ የፖለቲካ ሙስና እንዲፈጽም አድርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ወጣቶች ሥራ እንዲያገኙ የሚደረገው የአገሪቱ ዜጋና የሥራ ብቃት ያላቸው ስለሆኑ ሳይሆን፣ በዋናነት የፓርቲ አባልና ደጋፊ ለመሆን ባላቸው ፈቃደኝነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እውነተኛ አመለካከታቸውን ደብቀው የኢሕአዴግ አባል ለመሆን የሚገደዱት ወጣቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ እምነታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት በመወሰን ከሥራ ዕድል ተገልለው የሚቀሩት ወጣቶች ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡

  ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ኢሕአዴግ ለወጣቱ ሥራ ለመፍጠር በዋናነት የተነሳሳው ወጣቱ ተቃዋሚዎች ለሚቀሰቅሱት አመፅና ነውጥ ዋና ተቀጣጣይ ኃይል ነው ብሎ በማመኑ ቢሆንም፣ እነዚህ ያለእምነታቸው መስለው ለመኖር ሲሉ ሥራ የተቀጠሩትም ሆኑ የፓርቲ አባል አንሆንም ብለው ከሥራ ተገልለው የሚቀሩት ወጣቶች አመቺ ሁኔታ ሲያገኙ የአመፅና የነውጥ ተባባሪ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ያለፍላጎታቸው ሥራ ለማግኘት ሲሉ የፓርቲ አባል እንዲሆኑ የተገደዱትም ሆኑ በእምነታቸው ምክንያት ሥራ አጥ እንዲሆኑ የሚደረጉት ወጣቶች፣ ለሥርዓቱ የሚኖራቸው ጥላቻና ንቀት ልዩነት አይኖረውም፡፡ ያለፍላጎቱ አባል እንዲሆን የተገደደው ወጣት ሥራ አጥ እንደሆኑት ወጣቶች በይፋ ከተቃዋሚው ጎራ ጋር መሠለፍ ባይችል እንኳን በየመሥሪያ ቤቱ ተሰግስጎ ሕዝብን በመልካም አስተዳደር ዕጦት እያማረረ  መንግሥትና ሕዝብን ማጣላቱ አይቀርም፡፡ ባለፉት አሥርት ዓመታት መንግሥት በዋናነት ሥራ የመፍጠር ሙከራ እያደረገ ያለው በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች አማካይነት ቢሆንም፣ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በአብዛኛው ከኮንስትራክሽን ሴክተሩ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ቋሚና በሒደት ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋጋሪ ለመሆን አልቻሉም፡፡ እንደስማቸው ሁሉ አነስተኛና ጥቃቅን ሆነው ቀርተዋል፡፡ በዚህም ሆነ በሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድልም ከወጣቱ አጠቃላይ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ በሥራ ቀጣሪነቱ ለሚታወቀው የማኑፋክቸሪንግ ሴክተር ተገቢ ትኩረት ሳይሰጥ በመኖሩም፣ አገራችን የማምረቻ ፋብሪካዎች ሳይሆን የሱቅና የቢሮዎች አገር ሆናለች፡፡

  በተለይም ኢሕአዴግ ሲያራምደው በኖረው የእርሻ መር የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ምክንያት አገሪቱ ዛሬም የኋላ ቀር እርሻ ጥገኛ ሆና ቀጥላለች፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ 85 በመቶ ገበሬ የነበረው ሕዝብ አሁንም ከ25 ዓመት በኋላ 83 በመቶ  ሕዝብ ገበሬ ሆኖ በመቀጠሉ ከመሬት ጥበት ጋር በተያያዘ አብዛኛው የገጠር ወጣት ሥራ አጥ ለመሆን ተገዷል፡፡ ይህም በመሆኑ ኢሕአዴግ ሲፈራው የነበረው የከተማ ወጣት ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግ እንደ አጋር ይቆጥረው የነበረው የገጠሩ ወጣትም የአመፅና የነውጥ ተቀጣጣይ ኃይል እየሆነ መምጣቱን በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ በግልጽ እያየነው ነው፡፡ መንግሥት በአገራችን ትልቅ የሀብት ምንጭ በሆነው በመሬት ላይ ብቸኛ የባለቤትነት መብት ይዞ መቀጠሉም ተደራራቢ ችግሮችን እያስከተለ መጥቷል፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ ከመሬት ጋር ተጣብቆ እንዲኖርና ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ሴክተሮች እንዳይገባ በማድረግ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንቅፋት የሆነ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከመሬት ጋር የተያያዘው ዘረፋና የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ መንግሥትን በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ረገድ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ከመሬት ጋር  በተያያዘ እየተከሰተ ያለው የሕገወጥ ግንባታ፣ በልማት ምክንያት የሚፈጠር የዜጎች መፈናቀልና የካሳ ክፍያ ጉዳይ የሕዝቡን ብሶትና ምሬት በማባባስ ረገድ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የመሬት ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ዋና ፖለቲካዊ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን እያየን ነው፡፡ በአገራችን የመሬት ባለቤት ዜጎች ሳይሆኑ መንግሥት  የመሆኑ ጉዳይ  ‹‹የመሬት ላራሹ›› ጥያቄ ከመፈክር አልፎ በተግባር ያልፈታቸው ችግሮች ዛሬም እንዳሉ በገሃድ እያየን ነው፡፡

  በእኔ አመለካከት በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች የጥያቄ አቀራረቡ ወጥነትና ግልጽነት የሌለው ቢሆንም፣ ‹‹መሬት ለዜጎች›› የሚለው ጥያቄ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ጥያቄ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በኦሮሚያ ክልልና በአገራችን ከተሞች ዙሪያ እንደምናየው መንግሥት መሬትን እርባና በሌላው የካሳ ክፍያ ከሕዝቡ እየቀማ እሱ ግን በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ የገንዘብ መጠን እየቸበቸበው  ነው፡፡ ቢያንስ ለመኖሪያ  ቤትና ለእርሻ ሥራ በዜጎች እጅ የሚገኘው መሬት ከነሙሉ  መብቱ የዜጎች መሆን ሲገባው፣ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በመያዙ የፖለቲካ ቀውስ፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት መፈልፈያና የሕዝብ ብሶት ዋና ምንጭ እየሆነ ነው፡፡ በእኔ አመለካከት ኢሕአዴግና አንዳንድ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ቆመናል የሚሉ የኦሮሞ ድርጅቶች፟ ‹‹ነፍጠኞችን›› ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል በሚል የተሳሳተ ግምት መሬት  የመንግሥት እንዲሆን ሽንጣቸውን ገትረው ቢሟገቱም፣ ከማንም በላይ የኦሮሞን ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርገው የሚችለው አጀንዳ ግን ‹‹የመሬት  ለዜጎች›› ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት በሞኖፖል የያዘውን የመሬት ባለቤትነት መብት ቢያንስ በከፊል ለዜጎች ካላካፈለ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት መልኩን ቀይሮም ቢሆን የባላባትና የጭሰኛ ግንኙነት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

  ኢኮኖሚን እንደ ብቸኛ የአገር ግንባታ መሪያ ማየት

  ሌላው ከኢሕአዴግ የልማታዊ መንግሥትነት የተዛባ አስተሳሰብ ጋር የተያያዘው ችግር ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንና ዕድገትን ብቸኛ የአገር ግንባታ (Nation Building) መሣሪያ አድርጎ ማየት ነው፡፡ ከአጠቃላዩ የኢሕአዴግ የፕሮፓጋንዳ ቅኝት በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው፣ ኢሕአዴግ በግልጽ ባይናገረውም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማምጣት የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል ከቻልኩ የሕዝቡን የፖለቲካ የመብት ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ደፍቄ መቆየት እችላለሁ የሚል ቻይናዊ አቋም አለው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በግልጽ ባይናገረውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን የሚገኝበት የሶሽዮ ኢኮኖሚ የዕድገት ደረጃ ዴሞክራሲንና የብዙኃን ፓርቲን ለመተግበር ብቁ አያደርገውም ብሎ ያምናል፡፡ የኢሕአዴግ እውነተኛ እምነት ለመጭዎቹ 20 እና 30 ዓመታት ያለምንም ትርጉም ያለው ተቀናቃኝ ኃይል በሥልጣን ላይ መቆየትና በኢኮኖሚ ዕድገት አማካይነት መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ በቅድሚያ ፈጥሮ በሒደት ዴሞክራሲንና የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓትን ለመፍጠር ነው የሚያስበው፡፡ ከዚህ አስተሳሰቡ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ህዳሴ ዕውን ለማድረግም ሆነ አንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችለኝ ዋናው ወኪል (Agent) በፖለቲካ ግርግር የማይደናቀፍና የማይታወክ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው ብሎ አምኗል፡፡ ለሕዝቡ በይፋ ባይናገረውም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሪ ካድሬዎቻቸውን ሲያስተምሩ የሚውሉት ይህንኑ ነበር፡፡

  በእኔ አመለካከት ከልቡ እስካመነበት ድረስ ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ መያዙ ችግር አለው ብዬ አላምንም፡፡ በብዙ ታዳጊ አገሮች ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንደ አንድ አዋጭ የዕድገት አማራጭ ሐሳብ ተደርጎ ስለሚቀነቀን ኢሕአዴግ የዚህ አቋም አራማጅ ቢሆን ችግር የለውም፡፡ መብቱም ነው፡፡ ችግሩ ያለው ኢሕአዴግ ይህንን አቋሙን ለሕዝብ በግልጽ አቅርቦ ለማሳመን መሞከር ሲገባው፣ ከኢኮኖሚውና ከልማቱ ባላነሰ ዴሞክራሲም ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የህልውና ጉዳይ ነው እያለ  የማያምንበትንና በተግባር ሊያውለው የማይፈልገውን ሐሳብ እምነቱ አስመስሎ ለማሳመን መሞከሩ ነው፡፡ ይህ የኢሕአዴግ አስመሳይነት በተቃዋሚው ጎራና በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው ሕዝብም በግልጽ የሚታወቅ ሀቅ ሆኗል፡፡ ኢሕአዴግ የሚያስበውን የማይናገር፣ የሚናገረውን የማያደርግ ሴረኛና አስመሳይ ድርጅት ሆኖ በሕዝቡ እንዲታይ ያደረገውም ይህ ዓይነቱ በቃልና በግብር  የተለያየ ድርጅት የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ የቱንም ያህል ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ሊያሳምን የሚችለው ሕዝብ የለም፡፡ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ ያለው አማራጭ በግልጽ ዴሞክራሲና መድበለ ፓርቲ ለአገራችን አይበጁም ብሎ ሕዝቡን ለማሳመን መሞከር፣ ወይም ዴሞክራሲም የልማትን ያህል አስፈላጊ ነው የሚለውን እምነቱን መሬት ላይ በተግባር ማሳየት ነው፡፡

  በኢሕአዴግ የአስመሳይነት ባህሪ ምክንያት የሕዝቡ ብሶትና ጥላቻ የበለጠ የሚባባስ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋናው ቁም ነገር ግን የኢትዮጵያ  የአገር  ግንባታ ሒደት የፖለቲካ መብት ተደፍቆ በኢኮኖሚ ለውጥ  ብቻ የሚመጣ አለመሆኑ ነው፡፡ ሕዝቡ የኢኮኖሚ ለውጥ መጥቶ ኑሮው እስከተሻሻለ ድረስ ለፖለቲካ መብት መከበር ብዙም ደንታ አይኖረውም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ እንዲያውም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለፖለቲካ መብት ጥያቄ የበለጠ ቀናዒ ሆኖ ለውጥ እንዲመጣ እየታገለ ያለው፣ በኢኮኖሚ አቅሙ በአንፃራዊነት የተሻለ ደረጃ ላይ ያለው ኅብረተሰብ ነው፡፡ በዚህ መንግሥት ዘመን ሠርተው የከበሩ ባለሀብቶች ሳይቀሩ ለሥርዓቱ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ፣ አመፅና ጦርነትም ቢሆን ተቀስቅሶ ይህ መንግሥት እንዲወድቅ ሲመኙ የሚውሉ ናቸው፡፡ ደሃው ሕዝብማ ቁርስና ራቱን  በልቶ ማደርም ፋታ የማይሰጥ የዕለት ተዕለት አጀንዳ ስለሆነበት ስለመንግሥት ለውጥ የማሰብ ዕድልም የለውም፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚያስበው በልማት ተጠቃሚ መሆን ብቻውን የአገር ግንባታ አጀንዳን የሚያሳካ ቢሆን ኖሮ፣ በአሁኑ ወቅት በኢሕአዴግ ዘመን በተሠራው አውራ ጎዳና ላይ በሺዎች እየተመሙ፣ የተሠራውን ልማት እያቃጠሉና እያፈረሱ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ጥላቻ የሚገልጹ ወጣቶችን ባላየን ነበር፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በራሳችን ጎረቤት አገሮች ከተከሰተው የዓረብ የፀደይ አብዮት መማር ከቻልን፣ እነ ሙባረክንና ጋዳፊን ጠራርጎ ከሥልጣን ያስወገዳቸው ወጣት ኃይል በእነሱ ዘመን በተሠራ ሥራ ለተሻለ የኑሮ ደረጃ የበቃ ትውልድ ነው፡፡

  ስለዚህ የኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሒደትም ሆነ የኢሕአዴግ የአገር ህዳሴ ፕሮጀክት ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ የዜጐችን ፖለቲካዊ መብት በማክበርና የተሟላ የአገር ባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማትን በማምጣት ብቻ አይደለም፡፡ በአገሪቱ አስተማማኝ የፖለቲካ መረጋጋት ኑሮ በዜጐች ልቦና ውስጥ ትርጉም ያለው ሰላም ከሌለ፣ የአገር ግንባታው ሒደትም ሆነ የኢትዮጵያን ህዳሴ የማሳካቱ ፕሮጀክት በቀላሉ ሊሳካ አይችልም፡፡ የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ የሚያረጋግጠውም ይኼንኑ ዕውነታ ነው፡፡

  በአጠቃላይ እነዚህ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው አብዛኛዎቹ ችግሮች ኢሕአዴግ እንደሚለው ከአፈጻጸም ጋር ብቻ የተያያዙ ችግሮች ሳይሆኑ ከተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫ የሚመነጩ ችግሮችም ናቸው፡፡  ኢሕአዴግ በዚህ ደረጃ የችግሩን መሠረታዊ ምንጭ መረዳትና አምኖ መቀበል ሲችል ብቻ ነው የመፍትሔው አካል መሆን የሚችለው፡፡

  በአጭሩ ኢሕአዴግ፡-

  • የተሳሳቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎቹን በተገቢው ጊዜና ሁኔታ ከማረም ይልቅ፣ በኮሙዩኒስታዊ የማስረፅ ሥልት በሕዝቡ ላይ ለመጫን የሚጥር፣
  • የሙያ፣ የዕውቀትና የሥነ ምግባር ብቃት ሳይሆን የፓርቲ ታማኝነት ያላቸውን ደካማ ካድሬዎች በዙሪያው በመሰብሰብ ፖሊሲዎቹን የመፈጸም ብቃት ያጣና በመልካም አስተዳደር ዕጦት ሕዝብን እያሰቃየ የሚገኝ፣
  • ተቃዋሚ አስተሳሰብንና ተቃዋሚ ድርጅቶችን በማዳከምና በማጥፋት ፀረ ዴሞክራሲ አቋም የሚያራምድ፣
  • የአገሪቱን ችግሮች የማወቅም ሆነ መፍትሔ የማምጣት ብቃት ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ የሚል የትምክህተኛነት ባህሪ የተጠናወተው አምባገነናዊ ድርጅት ነው፡፡
  • የፖሊሲ ስህተቶችን፣ የአፈጻጸም ብቃት ማነስን፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ፀረ ዴሞክራሲነትንና ትምክህተኝነትን ችግሮቹ አድርጐ የማይቀበል የኢሕአዴግ ተሃድሶ የሥልጣን ዕድሜ ከማራዘም ያለፈ ለወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ችግር አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ለወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ ቀዳሚና ግማሹ መፍትሔም እስካሁን የተሰሩ ስህተቶችን በግልጽና በድፍረት አምኖ መቀበል መሆኑን ኢሕአዴግ መረዳት አለበት፡፡

  ተቃዋሚው ጎራ በወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ ያለው ሚና

  ከዚህ በላይ በዝርዝር የቀረቡ የኢሕአዴግ ድክመቶችና አሉታዊ ድርጊቶች ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞና ጥላቻ እንዲኖረው ያደረጉ ዋና ምክንያቶች ቢሆኑም፣ ይህ የሕዝብ ምሬት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሳይሆን በኃይልና በነውጥ ጭምር እንዲገለጽ በማድረግ ረገድ ግን ተቃዋሚው ጎራና ተቃዋሚውን ጎራ የሚደግፈው ሕዝብ ድክመት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የወቅቱ የሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደ ጥሩ የለውጥ ማግኛ ዕድል ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ህልውናና ደኅንነት ላይ የባሰ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ክስተት እንዲታይ ያደረገው በእኔ አመለካከት በተቃዋሚው ጎራና በደጋፊው ሕዝብ ዙሪያ ያለው ድክመት ነው፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ግልጽና የተብራራ አማራጭ ሐሳብ ቀርፆ፣ ሕዝቡን በሐሳብ የበላይነት አሳምኖና በዙሪያው አደራጅቶ ከገዥው ፓርቲ የሚቃጣበትን አፈናና ተፅዕኖ በብቃት ተቋቁሞ ሰላማዊውና ሕጋዊውን ትግል በብቃት መምራት ባለመቻሉ፣ የወቅቱ የሕዝብ ትግል ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብና የድርጅታዊ አመራር ክፍተት ተፈጥሮበታል፡፡ የወቅቱ ትግል ጠንካራ አማራጭ ሐሳብና ድርጅታዊ መዋቅር ባለው የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን በአካባቢ የጎበዝ አለቃ፣ በውጭ አገር በሚገኙ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ፣ በፌስቡክ ጥሪና በአሉባልታ ዘመቻ ጭምር የሚመራ በመሆኑ አገሪቱን ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዳት የማይታወቅ ትግል ሆኗል፡፡

  በትግሉ ዙሪያ ተሳትፎ እያደረገ ያለው ሕዝብ ኢሕአዴግ እንደሚለው የተሃድሶ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ለውጥ የሚፈልግ መሆኑ በግልጽ እየታየ ቢሆንም፣ የሚፈለገው ለውጥ ኢሕአዴግን ከሥልጣን ከማውረድ ባሻገር ከኢሕአዴግ የተሻለ መንግሥትና ሥርዓት እንዴትና በምን ሁኔታ ሊያመጣ እንደሚችል ግን በግልጽ የተቀመጠ አቅጣጫ የለውም፡፡  ይኼም በመሆኑ የትግሉ እንቅስቃሴ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ዕድልና አጋጣሚ ሳይሆን የባሰ አገራዊ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል አደጋ በሥጋት እየታየ ነው፡፡ የአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእንዲህ ዓይነት ግራ ቀኙን ገደል ባደረገ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ያደረገው አንዱ ምክንያት የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አለመኖር ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት በተቃውሞ ትግሉ ዙሪያ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡን በስሜትና በምሬት እየመሩ ከሚገኙት የአካባቢ የጎበዝ አለቃዎች የተሻለ ሚና ያላቸው ባለመሆኑ፣ በወቅቱ የሕዝብ ትግል እንቅስቃሴ የወረቀት መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ቦታና ሚና የሌላቸው (Irrelevant) ኃይሎች ሆነዋል፡፡

  ስለወቅቱ የአገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በድፍረትና በሀቅ መነጋገር ካለብን የመንግሥት ሥልጣንን ተረክቦ አገርን በብቃት ማስተዳደር ይቅርና ከገዥው ፓርቲ የሚቃጣበትን ጥቃት በአግባቡ ተቋቁሞ፣ የራሱን ህልውና አስጠብቆ መቀጠል የሚችልም ሆነ የሕዝቡን ትግል በአግባቡ አቅጣጫ አስይዞ ሊመራ የሚችል አንድም ጠንካራ ድርጅት በአገራችን የለም፡፡  ኢሕአዴግ ላለፉት 25 ዓመታት በብቸኝነት አንቀጥቅጦ የገዛንም ሆነ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ያለ ድርጅታዊ አመራር በተበታተነና ባልተቀናጀ ሁኔታ በመንግሥት ላይ ለማመፅ የተገደደው ያለምክንያት ሳይሆን፣ በድርጅታዊ ጥንካሬውና በአስተሳሰብ ጥራቱ እስካሁን ሕዝብ በሙሉ ልቡ አምኖ የተቀበለው ፓርቲ ባለመኖሩ ነው፡፡  የቱንም ያህል የኢሕአዴግን ስህተትና ኃጢያት ስንቆጥር ብንውል፣ የቱንም ያህል ኢሕአዴግ ሥልጣኑን እንዲያጣና አዲስ የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ስንመኝና ስንጠይቅ ብንውል ያለጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ መኖር ሊመጣ የሚችል አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ አይኖርም፡፡

  በእኔ አመለካከት የተቃዋሚው ጐራ መሠረታዊ ድክመት የሚመነጨው ከሦስት አቅጣጫ ነው፡፡ አንደኛ የሕዝቡንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ያገናዘበ ጥራት ያለው አማራጭ ሐሳብ ካለመኖር፣ ሁለተኛ ከተሳሳተ የትግል ሥልትና አቀራረብ፣ ሦስተኛ ጠንካራ ድርጅት ለመፍጠር የሚያስችል ሁለንተናዊ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ካለመሆን የሚመነጭ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እስካሁን እንደሚያደርጉት ራሳቸውን ጠንካራና ሀቀኛ አስመሰለው ለሕዝብ በማቅረብ ያለ አግባብ ከመመፃደቅ ይልቅ ውስጣቸውን በሀቅ ገምግመውና ድክመታቸውን አርመው በአዲስ መልክ ተጠናክረው መውጣት አለባቸው፡፡  ከስሜታዊነት፣ ከጭፍን ጥላቻ፣ ከእወደድ ባይነት፣ ከዘረኝነትና ከአሉባልታ የፀዳ ዝርዝርና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በአግባቡ የተገነዘበ አማራጭ ሐሳብ በማቅረብ ሰላማዊ ትግሉ በጉልበት፣ በጊዜ፣ በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በአካልና በሕይወት ጭምር የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በፅናት በመክፈል ተቃዋሚው ጎራ በአዲስ ተነሳሽነት ተጠናክሮ መውጣት አለበት፡፡ በቅድሚያ ራስን ሳያበቁና ሳያዘጋጁ መንግሥት ሥልጣኑን እንዲያጣ መፈለግ፣ ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት ቅደም ተከተሉን የሳተ ሥልት መሆኑን በመገንዘብ የተቃዋሚው ጎራ የወቅቱ አጣዳፊና አሳሳቢ አጀንዳ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ በአገር ውስጥ መፍጠር መሆን አለበት፡፡ ተመሳሳይ አደረጃጀትና የፖለቲካ ፕሮግራም ያላቸው ፓርቲዎች ኅብረት ወይም ውህደት በመፍጠር፣ ይህንን ማድረግ የማይችሉ ፓርቲዎች ራሳቸውን በተናጠል በማጠናከር፣ ይኼንንም ማድረግ ካልተቻለ በበቂ ቅድመ ዝግጅት አዲስ ፓርቲ ጭምር በማቋቋም ተቃዋሚው ጎራ በወቅቱ የአገራችን ፖለቲካ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቃዋሚው ጎራ በአስቸኳይ ተጠናክሮ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የተበታተነና ያልተቀናጀ የሕዝብ ትግል በአግባቡ አቅጣጫ አስይዞ መምራት የማይቻል ከሆነ፣ በኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ›› ተሃድሶም ሆነ በሕዝቡ የተናጠል ትግል የሚመጣ አስተማማኝና ዘላቂ ለውጥ ሊኖር አይችልም፡፡ እንዲያውም የወቅቱን የተበታተነ የሕዝብ ትግል በብቃትና በኃላፊነት ስሜት በአግባቡ መምራት የሚችል ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሳይፈጠር ወይም  ኢሕአዴግ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከልቡ ተቀብሎ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሳይወስን፣ የወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ እየተባባሰ ከመጣ ማናችንም ልንገምተው በማንችለው ፍጥነት አገራችን ህልውናዋን ወደሚፈታተን ቀውስ ልትገባ ትችላለች፡፡

  እንዲህ ዓይነቱ አደጋ በእኛ አገር አይከሰትም ብሎ መገመት በሕዝባችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየተባባሰ የመጣውን የጥላቻና የጽንፈኛነት ስሜት በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ እንኳንስ ለ25 ዓመታት ልዩነት ሲሰበክባት በኖረችዋና በውስጧ በርካታ የአስተሳሰብ፣ የብሔርና የሃይማኖት ቅራኔን አርግዛ በምትገኘው በእኛ አገር፣ አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት ባላቸው አገሮች በዓረብ የፀደይ አብዮት አማካይነት የተቀሰቀሱ ብጥብጦች አገሮችን ምን ያህል ወደ መንግሥት የለሽነትና ወደ ዘግናኝ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳስገቡ ማየት ችለናል፡፡ ስለሆነም ተቃዋሚው ጎራ በኃይልና በነውጥ እንቅስቃሴም ሆነ በሌላ አቋራጭ መንገድ ሥልጣን ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ፣ በአገሪቱ ትርጉም ያለው ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲፈጠርና የፖለቲካ ምኅዳሩ ትርጉም ባለው መጠን እንዲሰፋ በመንግሥት ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ መፍጠር አለበት፡፡ ኢሕአዴግ በጠንካራ የሕዝብ ትግል እንጂ በጥያቄ ሊለወጥ የማይችል ፀረ ዴሞክራሲ አምባገነናዊ መንግሥት መሆኑን በመገንዘብም፣ ተቃዋሚው ጎራ ሕዝቡን በዙሪያው በማደራጀትና ጠንካራ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በማካሄድ ሥርዓቱ ወደደም ጠላም የሕዝቡን ጥያቄ ለመቀበል የሚገደድበትን ትግል አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

  ተቃዋሚው ጎራ ከእስካሁኑ ድክመቱ በአግባቡ ተምሮ ራሱን በአጭር ጊዜ አጠናክሮ መውጣት ከቻለ በአሁኑ ወቅት በሥርዓቱ ዙሪያ የሚታየው ሁለንተናዊ ድክመትም ሆነ፣ በሕዝቡ ውስጥ እየታየ ባለው ከፍተኛ የለውጥ ፍላጐት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይሆንለታል፡፡ ይህንን ዕድል በአግባቡ ከተጠቀመበት ተቃዋሚው ጎራ በመጪው የ2012 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ሲቻል የመንግሥት ለውጥ፣ ካልተቻለም ከፍተኛ የፓርላማና የክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ በማሸነፍ ራሱን ትርጉም ወዳለው የፖለቲካ ኃይል ማሸጋገር ይችላል፡፡ በ2012 ዓ.ም. ይኼንን ዓይነቱን ውጤት ለማሳካትም ከፊታችን በ2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ በበቂ ዝግጅት በመሳተፍ፣ ምርጫውን በሕዝቡ ውስጥ አዲስ የሰላማዊ ትግል ተነሳሽነት ለመፍጠርና ለ2012 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ የላቀ ውጤት የመስፈንጠሪያ  ሒደት አድርጐ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡  ይህንን የአዲስ አበባ ምርጫም ኢሕአዴግ ከዚህ ሁሉ የሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴና ‹‹ጥልቅ›› ብሎ ከጠራው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በኋላ ምን ያህል በተጨባጭ መለወጥ እንደቻለ አንድ የመፈተሻ መድረክ አድርጐ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ይህንን ዓይነት ቀጣይነትና ትርጉም ያለው የሕዝብ ተሳትፎ የሚታይበት ጠንካራ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ዝግጅቱ ነገ ሳይሆን ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ተቃዋሚው ጎራ ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚችል ከሆነ፣ የሕዝባችን የለውጥ ፍላጐት ኢሕአዴግን ከሥልጣን በማውረድ ብቻ ሳይሆን ከኢሕአዴግ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማምጣት ሊሳካ ይችላል፡፡

  የተቃዋሚው ጐራ ደጋፊ የሆነው ሕዝብም ብዙ በደል የተሸከመና ለውጥ ፈላጊ  ሆኖ እያለ ተደራጅቶ የመታገልን የማይተካ ጠቀሜታ በአግባቡ ባለመገንዘቡ እስካሁን ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር አልቻለም፡፡ ሕዝቡ ሥርዓቱን ከማማረርና ለውጥ ፈላጊ ከመሆን ባሻገር ለራሱና ለአገሩ ጠቃሚ አማራጭ ሐሳብ ባላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ በመደራጀት ሐሳቡን፣ ጉልበቱን፣ ገንዘቡን፣ ዕውቀቱንና ጊዜውን በአግባቡ ቢያዋጣ ኖሮ ዛሬ የተበታተነ የትግል እንቅስቃሴውን በአግባቡ አቀናጅቶ የሚመራ/የሚመሩ ፓርቲዎች በኖሩት ነበር፡፡  ሕዝቡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊፈጠር የሚችለው ከየትም ሳይሆን ከራሱ ተጨባጭ ተሳትፎና የትግል ውጤት መሆኑን ባለመገንዘብ ከሩቅ ሆኖ ድክመታቸውን በመዘርዘር ሲተቻቸውና ሲያማቸው ስለሚውል ተጠናክረው ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ከሁሉም በላይ በራሱ በሕዝቡ ውስጥ ሆነው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉትን ፓርቲዎች አቅፎና ደግፎ ከማጠናከር ይልቅ፣ ሩቅ ናፋቂ በመሆን በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ተቃዋሚዎች መጥተው ነፃ እንዲያወጡት ሲናፍቅ ስለሚውል፣ የኢሕአዴግን አፈና ተቋቁሞና ትግሉን በአግባቡ መርቶ ለድል የሚያበቃ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ በአገር ውስጥ መፍጠር አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከእውነተኛ የሕዝብ ብሶትና የለውጥ ፍላጎት የመነጨውን የወቅቱን የሕዝብ ትግል አሉባልታና የጥላቻ አመለካከት በማሠራጨት ሊመሩት ሲሞክሩ የሚታዩት አገር ውስጥ የሚገኙት ሳይሆኑ፣ ከአትላንቲክ ማዶ የሚገኙት ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ሆነዋል፡፡  በእኔ አመለካከት ሕዝቡ የቱንም ያህል በሥርዓቱ ላይ ጥላቻ ቢኖረው፣ ከጥላቻም አልፎ የቱንም ያህል ለትግል ተነሳስቶ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ቢወስን የሚያካሂደው ትግል የጠራ አመለካከትና ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ባለው በአገር ውስጥ በሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲ እስካልተመራ ድርስ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡

  በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን በተለያዩ ተፅዕኖዎችና የአፈና ድርጊቶች እያሰቃየው የሚገኘው ገዥው ፓርቲም ሆነ ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት በአግባቡ ታግለው መለወጥ ያቃታቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከየትም የመጡ ሳይሆኑ፣ ከዚሁ ሕዝብ የተፈጠሩና የሕዝቡ የፖለቲካ የአስተሳሰብ ደረጃና ባህል መገለጫዎች ናቸው፡፡  በአንድ አገር ጥሩ ሥርዓት ሲኖር የሚጠቀመው፣ መጥፎ ሥርዓትም ሲኖር የሚጐዳውና ዋጋ የሚከፍለው ሕዝብ ነው፡፡ ይኼም በመሆኑ በአንድ አገር የሚገኙ ፓርቲዎችን የመመሥረት፣ ከመሠረተም በኋላ የማጠናከርና ለመንግሥት ሥልጣን የማብቃት፣ አልጠቀሙኝም ብሎ ሲያምንም ከሥልጣን የማውረድና በሌላ የመተካት ኃላፊነት ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡ አንድ ሕዝብ ጠንካራና አገልጋይ የሆነ ሥርዓት ሲኖረው የሚኮራውንና የሚመካውን ያህል፣ ደካማና ጨቋኝ ሥርዓት ሲኖረውም በዚያው መጠን ሊያፍርና ሊቆጭ ይገባዋል፡፡ አንድን ሕዝብ እንደ ሕዝብ መተቸት በተለምዶ የፖለቲካ ስህተት ተደርጎ ቢታይም፣ ሁልጊዜ ጨቋኝ ሥርዓቶች በጫንቃው ላይ እየተፈራረቁ የሚገዙትና እነዚህን ጨቋኝ ሥርዓቶች የሕዝብ አገልጋይ በሆነ ሥርዓት መተካት የተሳነው ሕዝብ ያለጥርጥር የለውጥ ኃይል መሆን የተሳነው ደካማ ሕዝብ ነው፡፡ የለውጥ ኃይል ለመሆን የበቃ ሕዝብ ግን ጌታውን ሳይሆን አገልጋዩ የሚሆነው ሥርዓት ይፈጥራል፡፡  በእኛ አገር ያለውን ተጨበጭ ሁኔታ ስናይ ግን ሕዝብ እስካሁን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የለውጥ ኃይል አልሆነም፡፡  ባለፉት 40 ዓመታት ሦስት ገዥዎችን መቀያየር ቢችልም፣ እስካሁን ገዥዎችን በገዥዎች እንጂ ገዥዎችን በአገልጋይ ሥርዓቶች መቀየር አልቻለም፡፡ 

  በአሁኑ ወቅትም ተቃዋሚውን ጐራ በሚደግፈው ሕዝብ ውስጥ ያለው ትኩረትና አዝማሚያ መንግሥትን በሌላ መንግሥት የመቀየር እንጂ፣ ገዥን በአገልጋይ የመቀየር አይመስልም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከሥልጣን እንዲወገድ በሕይወቱ ጭምር ዋጋ እየከፈለ ያለው ሕዝብ ወደፊት ኢሕአዴግን ተክቶ ሥልጣን የሚይዘው ፓርቲ ማንና ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይቅርና ማሰብም የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ነገር ግን ተተኪ የፖለቲካ ኃይል በአግባቡ ባልተዘጋጀበትና የሕዝቡ ትግል የሚሠራውን በሚያውቅ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት በማይመራበት ሁኔታ በስሜትና በአመፅ ብቻ አንድን ሥርዓት ማፍረስ መንግሥት የለሽነትንና መቋጫ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነትን በመቀስቀስ ገዥ ፓርቲን ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያፈርስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡  ይህ ዓይነቱ አደጋ ከፊታችን ያለ ቢሆንም ሕዝቡ ግን በአፈና ካማረረው ሥርዓት ለመገላገል ስለቸኮለ ብቻ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን የባሰና አስከፊ ጣጣ ሊረዳው ቀርቶ ሊያስበው አልቻለም፡፡ 

  በሕዝቡ ውስጥ ያሉ የጥላቻ ስሜቶች ከአግባብ በላይ በመለጠጣቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ‹‹ቅኝ ተገዥዎችና ሁለተኛ ዜጋ ሆነናል›› በሚል እየተፈጠረ ያለው የከረረ ስሜትና በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎች ‹‹የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመብን ነው›› በሚል እየተሠራጨ ያለው አደገኛ ፕሮፓጋንዳ ወዴት አቅጣጫ ሊወስደን እንደሚችል ለመረዳት ከሞከርን፣ አገራችን ሶማሊያ ወይም ሩዋንዳ ልትሆን አትችልም ብሎ መደምደም የሚቻል አይመስለኝም፡፡  አገራችን ወደዚህ ዓይነቱ በቀላሉ መውጣት የማይቻልበት አደጋ ውስጥ እንዳትገባና በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ከተፈለገ፣ ሕዝቡ ቢያንስ የሚከተሉትን አራት ኃላፊነቶች በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡

  1. አንድ ሕዝብ የቱንም ያህል ግፍና ጭቆና ቢደርስበትና ከዚያ ግፍና ጭቆና ለመላቀቅ ቢፈልግ፣ ትግሉን በድርጅት ዙሪያ ያላስተባበረ ሕዝብ ፍላጐቱን ሊያሳካ እንደማይችል በመገንዘብ በአስቸኳይ በፓርቲዎች ዙሪያ መደራጀት አለበት፡፡  ሕዝቡ አሁን በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሆነ ተዓምር ለውጥ ያመጡልኛል ብሎ ዳር ቆሞ ከመጠበቅ ይልቅ፣ በውስጣቸው እየገባ ሊፈትሻቸውና ሊያጠናክራቸው ይገባል፡፡ ሕዝቡ ራሱን በፓርቲ መሥራችነት፣ በፓርቲ አባልነት፣ በፓርቲ አመራርነትና በምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪነት ተሳታፊ በማድረግና የተደራጀባቸውን ፓርቲዎች በጉልበቱ፣ በጊዜው፣ በዕውቀቱና በገንዘቡ በመርዳት ትርጉም ባለው መጠን ሊያጠናክራቸው ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሕዝቡ ትግል ዙሪያ የተፈጠረውን የድርጅት የአመራር ክፍተት በመረዳትና ድርጅት በአንድ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ያለው ሚና የማይተካ መሆኑን በመገንዘብ የጠንካራ ድርጅት መኖርን ጉዳይ ወቅታዊና ቀዳሚ አጀንዳው ሊያደርገው ይገባል፡፡
  2.  እስካሁን በነበረው የፖለቲካ ትግል ሒደት አብዛኛውን ጊዜ ሕዝብ ፓርቲዎችን  ሲደግፍ የሚታየው የግለሰቦችን ዕውቅናና ዝና፣ ስሜታዊ ቅስቀሳንና ጊዜያዊ ጀብደኛነትን መመዘኛ አድርጐ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እስካሁን ከሁለትና ከሦስት ዓመት በላይ የሕዝቡን ትኩረት ስበው ተጠናክረው መውጣት የሚችሉ ፓርቲዎች ማግኘት አልቻለም፡፡  ይህ ሁኔታ ተለውጦ ሕዝቡ የጠንካራ ፓርቲ ባለቤት መሆን ከፈለገ ብቸኛ መመዘኛው፣ ፓርቲዎቹ ለአገርና ለሕዝብ ያላቸው አማራጭ ሐሳብና ሐሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ያላቸው ጥንካሬና ቁርጠኛነት መሆን ይገባዋል፡፡
  3. ኢሕአዴግ ያለጠንካራ የሕዝብ ትግል ሥልጣኑን ለመልቀቅ ወይም ለማጋራት ፈቃደኛ የማይሆን ድርጅት መሆኑን በመገንዘብ፣ ሕዝቡ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ነገር ግን በአንድ በኩል ሊካሄድ የሚገባው ትግል ፍፁም ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ የትግል ሥልት መመራት ያለበት፣ በሌላ በኩል በአገራችን የፖለቲካ ትግል ተጨባጭና ዘላቂ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት በውጭ አገር እየኖሩ የነውጥና የትጥቅ ትግል ሥልትን የሚሰብኩ አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች ሳይሆኑ፣ አገር ውስጥ ሆነው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች መሆናቸውን ከልቡ አምኖ ሊቀበል ይገባል፡፡  ከአሁን በኋላ በአገራችን የፖለቲካ ሥልጣን በሕዝብ ምርጫ ካርድ ብቻ እንጂ በጠመንጃ አፈሙዝና በሌላ አቋራጭ መንገድ መያዝ እንደሌለበት ከማንም በላይ አምርሮ መቃወምና መታገል ያለበት ሕዝቡ ነው፡፡
  4.  በአገራችን መምጣት ያለበት ለውጥ ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝቦች ያሳተፈና በውጤቱም ሁሉንም የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆን ይኖርበታል፡፡  የሕዝቡ አጀንዳና ፍላጐት በተከፋፈለበት ሁኔታ በሥርዓቱ ላይ ተገቢውን ጫና ማሳደር ስለማይቻል፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸው አጀንዳዎች ከአባቢያዊ ጉዳዮች ይልቅ አገር አቀፋዊ ይዘት ያላቸው፣ አንድን ሕዝብ ወዳጅ ሌላውን ሕዝብ ጠላት አድርገው የማያዩ፣ የፖለቲካ ፓርቲንና ሕዝብን ለያይተው የሚያዩ፣ ከአሉባልታ፣ ከዘረኝነትና ከጥላቻ ቅስቀሳና ድርጊት ፈጽሞ የፀዱ፣ የመንግሥትንም ሆነ የግለሰቦችን ንብረት ከማውደም የተቆጠቡ መሆን ይገባቸዋል፡፡

  የምንታገለውን ሥርዓት የምናይበት መንገድ ጭምር ምክንያታዊና ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባዋል፡፡  የምንታገለው ኢሕአዴግን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ለማጥፋት ሳይሆን፣ በነፃና በፍትሐዊ የሕዝብ ምርጫ እየተዳኘ የአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሒደት አካል ሆኖ እንዲቀጥል መሆኑን፤ ትግላችንም ለሰላምና ለእኩልነት እንጂ ኢሕአዴግንና አባላቱን ለመበቀልና ለመቅጣት አለመሆኑን ከወዲሁ ማረጋገጥ አለብን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ከስሜታዊነት የፀዳ ሥልት የትግሉን ሒደትም ሆነ የውጤቱን ይዘት ዘላቂና አስተማማኝ ያደርገዋል፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሁላችንንም የጋራ አሸናፊዎች ያደርገናል፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝብ እነዚህን የየበኩላቸውን ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት ከቻሉ አገራችንን ከእርስ በርስ ጦርነትና ከመንግሥት የለሽነት አደጋ መታደግ ብቻ ሳይሆን፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት እንድንሆን ማድረግ ይቻላል፡፡

  ማጠቃለያ

  የወቅቱን የአገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት የያዘው አቋም የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ ያልተረዳና የችግሩን ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫም ያልያዘ ነው፡፡ የወቅቱ ችግር በዋናነት ከተሳሳቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ ከከፍተኛ የአፈጻጸም ብቃት ማነስ፣ ከፀረ ዴሞክራሲና የትምክህት አመለካከት የመነጨ መዋቅራዊ (Systemic) ችግር ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ግን የችግሩን ምንጭ ከመጠን በላይ አሳንሶና አኮማትሮ በዋናነት ከሙስናና ከቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ ጋር የተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግር አድርጎ አቅርቦታል፡፡ የችግሩን መፍትሔ በተመለከተም ኢሕአዴግ በራሴ ላይ ‹‹ጥልቅ›› የተሃድሶ ዘመቻ በማካሄድና እንደገና ተጠናክሬ በመውጣት ችግሩን ራሴው እንደፈጠርኩት ራሴው እፈታዋለሁ እያለ ነው፡፡  ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተፈጠረውን ችግር በእርግጠኛነት ለመፍታት ከፈለገ በእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ያለውን አቋም በአግባቡ መርምሮ ማስተካከል አለበት፡፡ 

  የችግሩ ምንጭ ሙስናና የአፈጻጸም ብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን በዋናነት የፖሊሲ ስህተትና የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ጭምር መሆኑን፣ ችግሩን ለመፍታት የሚቻለውም በኢሕአዴግ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ጋር በጋራ በመምከርና በመተባበር መሆኑን ከልቡ አምኖ መቀበል አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ እስካሁን በመጣበት መንገድ አገሪቱን በተረጋጋ ሁኔታ እየገዛ ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል እየተሟጠጠ መምጣቱን በመገንዘብ፣ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር እየተመካከረ፣ እየተደራደረና እየተባበረ ለመሥራት መወሰን አለበት፡፡ የአገሪቱ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በእኔ መንገድ ብቻ ነው ከሚለው የፀረ ዴሞክራሲና የትምክህተኛነት አመለካከት ተላቆ ሌሎችንም የአገሪቱ ችግሮች የመፍትሔ አካላት አድርጎ መቀበል አለበት፡፡ መቀበልም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁኔታዎች እንዲለወጡ የሚያስችል ተጨባጭ ዕርምጃ በፍጥነትና በግልጽነት መውሰድ አለበት፡፡ በእኔ አመለካከት ኢሕአዴግ የወቅቱን የአገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ከልቡ ለመፍታት ከፈለገ ይህንን ፍላጐቱን የሕዝብ እምነትና ሕጋዊነት ባለው መንገድ ለማስፈጸም የሚከተሉትን ሦስት ዕርምጃዎች በአስቸኳይ መውሰድ አለበት፡፡

  1.  ኢሕአዴግ ከልቡ ሊለወጥ ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለው ጥያቄ በጥያቄነት  መቀጠሉ የማይቀር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአሁኑ ወቅት ከልቡ ለመለወጥ ቢወስን እንኳ የሕዝቡን ተቀባይነት በቀላሉ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ የችግሩን ክብደት በአግባቡ የተረዳው ባይመስልም ላለፉት 25 ዓመታት ያራመደው የተሳሳተ የፕሮፓጋንዳ ሥልት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን እምነት በቀላሉ እንዳይጠገን አድርጎ በጣጥሶታል፡፡ መንግሥት ከእንግዲህ ውሸትና የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ በማሠራጨት ብቻ ሳይሆን እውነትም ተናግሮ የማይታመንበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ ሁኔታ ተለውጦ ኢሕአዴግ ስለሚሠራውና ስለሚናገረው ነገር በሕዝቡ መታመንና መደመጥ ከፈለገ በቅድሚያ ላለፉት 25 ዓመታት የተጠቀመበትን የፕሮፓጋንዳ ሥልት መቀየር፣ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተቆጣጠራቸውን መገናኛ ብዙኃን አሠራር መሠረታዊ በሆነ ደረጃ መለወጥ አለበት፡፡  የመገናኛ ብዙኃኑን አሠራር ብቻም ሳይሆን በእነዚህ መገናኛ ብዙኃን ለዓመታት ተሰግስገው በተሳሳተና አሰልቺ በሆነ የፕሮፓጋንዳ ሥልት መንግሥትንና ሕዝብን የማራራቅ ሚና ሲጫወቱ የኖሩትንና  የሕዝብ ዓይነ ጥላ (Allergy) እየሆኑ የመጡ ካድሬ ጋዜጠኞችን ጠራርጐ ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ ዕርምጃ በመውሰድ ያልተዛባና ያልተጋነነ መረጃ በማቅረብ በቅድሚያ የሕዝቡን እምነት ማግኘት ካልቻለ፣ የወቅቱን የፖለቲካ ቀውስ በዘላቂነት ማረጋጋትም ሆነ ሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚሆንበት የለውጥ ሒደት ውስጥ አገሪቱን ማስገባት አይችልም፡፡
  2. ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ የውይይት፣ የምክክርና የድርድር ሒደት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ በዚህ ሒደትም አሁን ለምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ ያበቁን ችግሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ማስቀመጥና ወደፊት የፖለቲካ ምኅዳሩን በሚፈለገው መጠን ለማስፋትና ሕዝቡን በምርጫ አማካይነት እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ መሻሻል የሚገባቸው ሕጎችና ተቋማት የትኞቹ እንደሚሆኑ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የጋራ መተማመን ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
  3. በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች ድርድር የሚገኘውን ውጤት ሕጋዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመፍታትና በመንግሥትና በሕዝብ፣ በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ያለመተማመን ክፍተት ለማጥበብ ከተፈለገ መንግሥት ሁለት ፖለቲካዊ ኃላፊነቶችን ሊያስፈጽም የሚችል አንድ ገለልተኛ ኮሚሽን በአዋጅ ማቋቋም አለበት፡፡  የሚቋቋመው ኮሚሽን ከገዥውም ፓርቲ ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለልተኛ ሆኖ የሚደራጅና የሚከተሉትን ሁለት ዓላማዎች ለማስፈጸም የሚቋቋም ኮሚሽን መሆን አለበት፡፡

  አንደኛው ዓላማ እስካሁን በአገራችን በተከሰተው የግጭትና የአለመግባባት የፖለቲካ ሒደት ቅራኔ ውስጥ የገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የፖለቲካ ኃይሎችን በማቀራረብና በማግባባት፣ በአገራችን ጠንካራ የሆነ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንዲፈጠር ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓላማ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚደረስበትን የድርድር ውጤት መሠረት አድርጎ በ2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማና በ2012 ዓ.ም. በአገራችን የሚካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ በአገራችን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይሆናል፡፡ የሚቋቋመው ኮሚሽን ዝርዝር ቅርፅና ይዘትም በገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ምክክር የሚወሰን መሆን አለበት፡፡ 

  የዚህ ኮሚሽን ዓላማዎች በአግባቡ ተፈጻሚነት አግኝተው ሕዝቡ በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ የሥልጣን ባለቤትነቱ እንዲረጋገጥ ከተፈለገም፣ ኢሕአዴግ ለመጪዎቹ 20 እና 30 ዓመታት አገሪቱን እየገዛ ለመቀጠል ያለው ፍላጎት ከወቅቱ የአገራችን ሕዝብ ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የማያዋጣ የከሸፈ ምኞት መሆኑን ተገንዝቦ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት ባለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠናክሮ መውጣት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ከፊታችን በሚመጡት አገራዊ ምርጫዎች ሕዝቡ የሚሰጠውን ውሳኔ በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን፣ ምንም ዓይነት ብዥታና ጥርጣሬ በማይፈጥር ሁኔታ ከወዲሁ በተግባር ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከእንግዲህ የኢሕአዴግ ጭንቀት እንዴት አድርጌ የሥልጣን ዘመኔን ላራዝመው የሚል ሳይሆን መምጣቱ የማይቀረውን የለውጥ ሒደት እንዴት አድርጌ ለአገሪቱም ሆነ ለራሴ የወደፊት ህልውና ዋስትና በሚሰጥ መንገድ እንዲካሄድ ላድርገው የሚል መሆን አለበት፡፡ አሁን አገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ከነበረው ሁኔታ በውስጥ ፖለቲካዊ የኃይል አሠላለፍ፣ በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፣ በሕዝቡ የዲሞግራፊክ ስብጥርና ዕድገት፣ በአጠቃላይም ከሕዝቡ ጥቅምና ፍላጎት አኳያ በብዙ ርቀት የተለወጠ መሆኑን በማመን ጊዜውንና ትውልዱን ለሚመጥን ለውጥ መዘጋጀት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ካለፉት የአገራችን ሥርዓቶች በተለየ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ቀጣይ ህልውና እንዲኖረውም ሆነ በበጎ ታሪክ እንዲወሳ ከፈለገ፣ ብቸኛው መፍትሔ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመተባበርና በመመካከር ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ቅድመ ሁኔታ በአግባቡ አመቻችቶ የሕዝቡን ውሳኔ ያለምንም ማቅማማት መቀበል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከእንግዲህ አድርባይ ካድሬዎች የሚያቀርቡትን መረጃና የራሱን ጩኸት በራሱ መገናኛ ብዙኃን እያዳመጠ የሕዝብ ድጋፍ አለኝ በማለት ራሱን እያታለለ መኖሩን ማቆም አለበት፡፡

  ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን ያላቸው ድርጅታዊ ጥንካሬ የወቅቱን የሕዝብ ትግል በአግባቡ አቅጣጫ አስይዞ ለመምራትም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ ይህንን ሰፊና ውስብስብ ችግር ያለበት አገር ለመምራት እንደማያስችላቸው አምነው በመቀበል፣ ቀዳሚ ትኩረታቸውን የራሳቸውን ድርጅታዊ ጥንካሬ በመፍጠር ላይ ማድረግ አለባቸው፡፡ ተቃዋሚዎች ተገቢውን ድርጅታዊ ጥንካሬ ፈጥረውና አሳማኝ አማራጭ ሐሳብ አቅርበው በሕዝብ በመመረጥ ለሥልጣን ሊበቁ የሚችሉትም ሆነ የሚያስተዳድሩትና አገርና ሕዝብ ሊኖራቸው የሚችለው የአገሪቱ ሰላም፣ አንድነትና ህልውና ተጠብቆ ሲቀጥል ብቻ መሆኑን በመረዳት ራሳቸውም ሆኑ ሕዝቡ የሚያካሂደው ትግል ፍፁም ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን የማይተካ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ በአገራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቅራኔ እጅግ ውስብስብ መሆኑን በመረዳት፣ አገራችንም በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝበት ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በብዙ ችግሮች የታጠረ መሆኑን በመገንዘብ በአገራችን የሚካሄድ ማንኛውም የሥልጣን ሽግግር የአገር ህልውናን ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ መንገድ ብቻ እንዲካሄድ ማድረግ የተቃዋሚው ጎራ ኃላፊነትም መሆን አለበት፡፡

  ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግ የአገራችን ችግሮች ብቻ ሳይሆን የዛሬውና የወደፊቱ የአገሪቱ ችግሮች የመፍትሔ አካል መሆኑንም አምነው በመቀበል ከስሜታዊነትና ከጽንፈኛነት በፀዳ መንፈስ ከኢሕአዴግ ጋር በመወያየትና በመደራደር፣ ሕዝቡ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሥልጣኑ ባለቤት የሚሆንበትን ዕድል ለማመቻቸትና በመጨረሻም ሕዝቡ የሚሰጠውን ውሳኔ ያለማቅማማት ለመቀበል መወሰን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎች ከታሪክ መማራቸውንም ሆነ ከኢሕአዴግ የተሻሉ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንደተለመደው በኃይል ወይም በሌላ አቋራጭ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት ሳይሆን፣ ሕዝቡ በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ብቻ የራሱ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን በሚያደርጉት ትግል መሆን አለበት፡፡ የተደራጁ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የአገሪቱ ባለቤት የሆነውና ፓርቲዎችን በመደገፍና በመቃወም የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርገው ሕዝብም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝቡ ይህች አገር በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ወደ መንግሥት የለሽነት ወይም የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ብትገባ ዋናው ተጎጂ ራሱ መሆኑን በመገንዘብ ከማንም በላይ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ተቆርቋሪና ጠበቃ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ተረጋግቶ የፖለቲካ ኃይሎች በሰከነና በተረጋጋ መንገድ የመወያየትና የመደራደር ዕድል ካላገኙ በስተቀር ሕዝቡ ዞሮ ዞሮ የሚፈልገውን ለውጥ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በተለይም ተቃዋሚውን ጎራ የሚደግፈው ሕዝብ ፍላጎቱንና አስተሳሰቡን የሚወክል ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እስካልፈጠረ ድረስ መንግሥትን ከሥልጣን በማስወገድ ብቻ ምኞቱን ሊያሳካ አይችልም፡፡ ይህንን እውነታ በውል በመረዳት በአንድ በኩል ለሰከነ ፖለቲካዊ ውይይትና ድርድር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥር ሰላምና መረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍላጎቱንና ጥቅሙን የሚወክልለት ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት መፍጠርን ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

  እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ በግርግርና በነውጥ ሊመጣ የሚችል የመንግሥት ለውጥ መንግሥት የለሽ የመሆንና መቋጫ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ፣ ፖለቲካዊ ቀውሱን ከሚያባብሱ ከማናቸውም ዓይነት ድርጊቶች ራሱን መቆጠብና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችም ከተመሳሳይ አውዳሚ ድርጊት ተቆጥበው ትግላቸውን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያራምዱ አስፈላጊውን ጫናና ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ የሕዝቡ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት የሚለካው አገራዊ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርገውን ጥረት አስቀድሞ በተገቢው ጊዜና ሁኔታ በመፈጸም ነው እንጂ በሶማሊያ፣ በሩዋንዳ፣ በዩጎዝላቪያ፣ በሊቢያ፣ በየመንና በሶሪያ ሲሆን እንዳየነው አደጋው ከተፈጠረ በኋላ የታሪክ ተፀፃች በመሆን አይደለም፡፡ ከ1966 እና ከ1983 ዓ.ም. የአገራችን የመንግሥት ለውጥ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በአግባቡ ተምረን ከሆነም ‹‹ኢሕአዴግ ይውደቅ እንጂ የመጣው ይምጣ›› የሚለው ስሜታዊ መፈክር የትም አያደርሰንም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስሜታዊ አስተሳሰብ ተመሳሳይ ታሪክ መድገም ብቻ ሳይሆን እስካሁን ዓይተነው ለማናውቅ የባሰ አደጋ ሊዳርገን ይችላል፡፡ በእኔ አመለካከት የወቅቱ ችግር ሊፈታ የሚችለው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና የዕርቅ ስሜት በመፍጠርና ሕዝቡ በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን በማድረግ እንጂ፣ በኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶም ሆነ በጠመንጃና በአመፅ ግርግር አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ፣ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ ከፍ ሲል በተጠቀሰው መሠረት የየበኩላቸውን ኃላፊነት የአገርና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ከተወጡ፣ አገራችንን ከከፋ አደጋ ከመታደግም ባለፈ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት እንድትሆን ልናበቃት እንችላለን፡፡ የወቅቱን ሥጋትና አደጋም ወደ አንድ ጥሩ የለውጥ ዕድል ልንቀይረው እንችላለን፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  
   

   

                       

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...