Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስና የቴሌኮም ተቋማት ዕድል ያልሰጧቸው ደንበኞች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ባዘጋጀው ዓመታዊ ሲምፖዚየም ላይ የተገኙ ባለሙያዎች ባንኮችም ሆኑ የሞባይል ኦፕሬተሮች እንዲሁም የቴሌኮም ተቋማት ከዚህ ቀደም ሲመሩበት በነበረው አካሄድ አሁንም እየተጓዙ እንደሚገኙ በመጥቀስ ከዘመኑ ጋር እንዲጓዙ መክረዋል፡፡

ዓለም በሞባይል ስልክ አማካይነት ክፍያ ከመፈጸም ባሻገር ብድር በሚያገኝበት፣ በሞባይሉ አማካይነት ልዩ ልዩ የንግድ ግብይቶችን በሚፈጽምበት በዚህ ወቅት ባንኮች ቅርንጫፍ በማስፋፋት፣ የኤቲኤም ማሽኖችን በየሥርቻው በመትከል ውድ ጊዜና ገንዘብ እያባከኑ ነው በማለት ከሚገልጹት መካከል ጋቪን ክሩገል አንዱ ናቸው፡፡ ክሩገል በደቡብ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን ያደረገው ዲጂታል ፍሮንቲየርስ ኢንስቲትዩት የተባለውን ተቋም በአጋርነት በመመሥረት፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ይመራሉ፡፡

ክሩገል ባለፉት 20 ዓመታት ካካበቱት የዲጂታል ፋይናንስ ተሞክሯቸው በመነሳት እንደገለጹት፣ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት መነሻው ከ15 ዓመታት በፊት በአፍሪካ ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሞባይል ክፍያ ሥርዓት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከየትኛውም አካባቢ ይልቅ መስፋፋቱንና በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ የኬንያው ኤም-ፔሳ ከ40 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን በሞባይል ክፍያና እንዲፈጽሙ፣ ግብይት እንዲያከናውኑ ቢያስችልም ሲጀመር ጀምሮ በኬንያ ባንኮች ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱን ያስታውሳሉ፡፡

ኤም-ፔሳ በእንግሊዙ የተራድዖ ድርጅት (ድፊድ) አማካይነት የአነስተኛ ገንዘብ ተቋማት ደንበኞች እንዲገለገሉበት ተብሎ የተጀመረ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ነበር፡፡ ይሁንና ሳይታሰብ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገበ ተጠቃሚ መገኘቱ፣ የሞባይል ኦፕሬተሮችንም የአየር ሰዓት ተጠቃሚነት ከሚገመተው በላይ በማሻቀቡ፣ መደበኛ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ወደ መሆኑ እንደተሸጋገረ ይጠቀሳል፡፡

ይህም ሆኖ ግን መደበኞቹ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙና በሌላው ዓለም እንደሚታየው የተራቀቁ የግብይት ሥርዓቶችን በሞባይል ስልኮች ለማስተናገድ ዳተኛ ሆነው እንደሚታዩ ክሩገል ያምናሉ፡፡ ‹‹ባንኮች ሞተዋል፤ ረጅም ዕድሜ ለባንክ አገልግሎት፤›› የሚሉት ክሩገል፣ ተቋማቱ ደንበኞች በሚፈልጉት መጠንና በደንበኞቻቸው ባህሪይ መሠረት መንቀሰቀስ እየቸገራቸው እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እንደሚታየው ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የንግድ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን እንዲያስፋፉ በዚህም የቁጠባ መጠን እንዲጨምር እንዲያደርጉ ይጠይቃል፡፡ ባንኮቹ ቅርንጫፍ ከማስፋፋት ባሻገር የኤቲኤም ማሽኖችን በመትከል ሥራ ተጠምደው፣ ለዚህም ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ላይ እንደሚገኙ ይታያል፡፡

በአንፃሩ በሌላው የዓለም ጽንፍ እንደ ‹‹አፕል ፔይ››፣ ‹‹ዛፐር››፣ ‹‹ሞባይል ዋሌት››፣ ‹‹ስኴዌር ዋሌት›› የመሳሰሉ የደመወዝ መክፈያዎች፣ ግብይት መፈጸሚያዎችና ልዩ ልዩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂዎች በምዕራቡ ዓለም ሳይስፋፉ ቀድሞ፣ ከ20 ዓመት በፊት በአፍሪካ የዲጂታል ሥርዓት ተዘርግቶ ሥራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ወደ ራስ ከማየት ይልቅ ወደ ምዕራቡ ዓለም ማማተር ይቀናቸዋል በማለት የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ተችተዋል፡፡

በአፍሪካ ያለው ነባራዊ ሁኔታን መሠረት በማድረግ እንዳብራሩትም፣ የሞባይል ኦፕሬተሮችና የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የዳታ መለዋወጫ ዋጋዎችን በማናራቸው ሳቢያ እንዲህ ያሉ አገልግሎቶችን ማዳረስ ከባድ ሆኗል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም 70 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎችን ለማዳረስ የሚያስችል የመሠረተ ልማት መገንባት እንደቻለ ይገልጻል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ከመቶ ሚሊዮን በላይ ለማድረስ መነሳቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የሞባይል አገልግሎት ስለመዘርጋቱም ሆነ በሞባይል አማካይነት በሌላው ዓለም እንደሚደረገው ከየትኛውም ዓለም የፋይናንስ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ፣ ግዥ ለመፈጸም፣ ደመወዝ በስልክ ለመክፈል የሚያስችሉ አሠራሮችን ስለመዘርጋቱ ሲናገር አይደመጥም፡፡

የኢንተርኔት ዳታ ልውውጥ ዋጋ በአፍሪካ ውድ በመሆኑ የተነሳ በርካታ የዲጂታል ኩባንያዎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከባንኮችም ከሞባይል ኦፕሬተሮችም የላቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የሚያመላክቱ ፕሮጀክቶች በሩዋንዳው የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጉባዔ ወቅት ታይተዋል፡፡ በዘረጉት ፕሮጀክት አማካይነት የገንዘብ ሽልማትም አግኝተዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ ኤም-ኮፓ የተሰኘውና የሶላር ኢነርጂን ለተጠቃሚዎች በሞባይል ክፍያ አማካይነት የሚያቀርበው ኩባንያ ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያውን የመሠረቱትና በምርት ዘርፍ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት ኒክ ሒውጅስ እንደሚገልጹት፣ ኩባንያው በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ25 ሚሊዮን ያላነሱ ኬንያውያን ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ኤም-ኮፓ በፀሐይ ብርሃን የሚሠሩና ባትሪያቸው ቻርጅ የሚደረጉ የቤት መብራቶችን፣ ሬዲዮኖችን፣ የእጅ ባትሪዎችንና የመሳሰሉትን ያቀርባል፡፡ ከተመሠረተ ስድስት ዓመታት ያስቆጠረው ኤም-ኮፓ የኬንያን የላምባ ጋዝ ፍጆታ ወጪ ለመቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ኬንያ በየዓመቱ ለላምባ ጋዝ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ፣ የኩባንያው ደንበኞች በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ምርቶችን በመጠቀማቸው እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ማዳን መቻላቸውን ሒውጅስ ይናገራሉ፡፡

ሌላኛው ኩባንያ በደቡብ አፍሪካ የተመሠረተውና ስደተኞችን ዋና ደንበኞቹ ያደረገው ‹‹ሔሎ ፔሳ›› የተባለው የሞባይል ክፍያ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያውን የመሠረተው የ34 ዓመት ወጣቱ አህመድ ካሲም የፈጠረው ይህ ኩባንያ፣ በሐዋላ ገንዘብ ከውጭ ወደ አገር ቤት ለመላክ የሚጠይቀውን የ20 ከመቶ ወጪ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ማድረግ አስችሏል፡፡

የሐዋላው ገንዘብ በሞባይል አማካይነት የሚከፈል ከመሆኑም ባሻገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚላክለት ሰው እንደሚደርስ ሥራው በተጀመረ በ18 ወራት ውስጥ 200 ሚሊዮን ዶላር የሐዋላ ገንዘብ ማላላክ እንዳስቻለ ካሲም አስታውቋል፡፡ 200 ሺሕ የተመዘገቡ ደንበኞች ያሉት ሔሎ ፔሳ፣ ዘንድሮ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የቀረበውን የ150 ሺሕ ዶላር የሽልማት ገንዘብ ለማግኘት በቅቷል፡፡

በኢትዮጵያ የዲጂታል ወይም የሞባይል አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ኤም-ብር፣ ሔሎ ካሽ ያሉ ኩባንያዎች ብቅ ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ክፍያ የተባለው የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያም ከዚህ ቀደም ጊዜና ገንዘብ የሚያባክኑ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃና የስልክ ክፍያዎችን በቅርቡም የቴሌቪዥን አገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል ሥርዓት በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡ ኩባንያው በአፍሪካ ዕውቅና እያገኘ ስለመሆኑም ከተሳታፊዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በቅርቡም ‹‹ፋይናንሺያል ሰርቪስስ ዲፕኒንግ›› ከተባለው ተቋም ለጊዜው መጠኑ ያልተገለጸ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ሪፖርተር ከተቋሙ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ልዩ ልዩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች የታዩበት የሩዋንዳው የማስተር ካርድ ፋንዴሽን ጉባዔ፣ በዓለም ላይ ከሁለት ቢሊዮን በላይ የተገለሉ ሕዝቦች እንዳሉና ከመደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተቆራርጠው እንደሚገኙ አሳይቷል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በመደበኛው የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉም የፋውንዴሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡ በዓለም ላይ በድህነት ውስጥ ከሚኖሩ አባወራዎች መካከል ግማሹ የባንክ ሒሳብ ደብተር የሌላቸው ሲሆኑ፣ ግማሽ ያህሉ ደግሞ የሒሳብ ደብተር ኖሯቸውም ቢሆን የማይጠቀሙበት መሆናቸውን አመላክቷል፡፡

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ኪጋሊ ሩዋንዳ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች