Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም አሥር ቀናት 1,670 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም አሥር ቀናት 1,670 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

ቀን:

– የተዘረፉ የጦር መሣሪያዎች እየተመለሱ ነው

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተከሰተውን ሁከትና መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመት ለመግታት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአሥረኛ ቀኑ፣ ለክስተቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 1,670 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የተዘረፉ የጦር መሣሪያዎች መመለሳቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬቴሪያት አስታውቃል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴርያት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ሁከት በቡድን ወይም በግል የተሳተፈ፣ የጦር መሣሪያ፣ የግልና የመንግሥት ንብረት የዘረፈ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ፣ ወረቀቶች በመበተን አድማ ያደረገ፣ የተሳተፈና ያነሳሳ፣ ሰው የገደለ፣ ንብረት ያቃጠለና፣ ወንጀል የፈጸመ በአዋጁ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት እጅ እንዲሰጥ አስታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሆነ በአሥር ቀናት ውስጥ በርካታ ተጠርጣሪዎችንና በርካታ የጦር መሣሪያዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ መከላከያ ሚኒስቴር ከሚገኘው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚሰጠው በመላው አገሪቱ የሚገኘው የፀጥታና የመከላከያ ኃይል በአጭር ቀናት በድምሩ 1,670 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቄለም አካባቢ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ሲመሩና ሲያስተባብሩ ነበሩ የተባሉ 110 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል፡፡ በዚሁ ቄሌም አካባቢ፣ ደምቢዶሎ ከተማና ደሮ ወረዳ ዙሪያ ከተለያዩ ቦታዎች የተዘረፉ 70 የጦር መሣሪያዎችን የፀጥታ ኃይሉ መረከቡን ኮማንድ ፖስቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በምዕራብ አርሲ ዞን በተፈጠረው የንብረት ውድመት ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ ከተባሉት መካከል 1,120 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ 450 ተጠርጣሪዎች ሻሸመኔ ከተማ የተያዙ ናቸው፡፡ በሻሸመኔ ከተማ ተከስቶ በነበረው ጥፋት ከተዘረፉ 162 ጦር መሣሪያዎች ውስጥ 88 ያህሉ የተመለሱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ጉጂ ዞንም እንዲሁ ከተዘረፉ የጦር መሣሪያዎች ውስጥ 32 ክላሽኒኮቭ ጠመንጃዎች፣ ኮምፒዩተሮች፣ ሞተር ብስክሌቶች፣ የቢሮ ቁሳቁሶችና የመሳሰሉ ዕቃዎች ተመልሰዋል፡፡ በአካባቢው ለተፈጠረው ሕገወጥ ክስተት ዋነኛ አስተባባሪ ነበሩ የተባሉ 302 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆናቸውን ሌሎች 20 የሚሆኑ አስተባባሪዎች ደግሞ በመመርያው በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት በፈቃዳቸው እጃቸውን ለመስጠት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ፣ ቦራ ሎሜ፣ ሊበን፣ ጭቁላ፣ አዳማ ቦስትና አዳቢ ቱሉ ወረዳዎች በተፈጠረው ችግር ከተለያዩ የፀጥታ አካላት፣ ግለሰቦችና ተቋማት የተዘረፉ 100 ዘመናዊና ኋላቀር የጦር መሣሪያዎች ተሰብስበዋል፡፡ ለተፈጠረው ችግር ቀንደኛ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት በድምሩ 513 የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች የተዘረፉ ሲሆን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሆነ በአሥር ቀናት ውስጥ 384 የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎች እንዲመለሱ መደረጉ ተመልክቷል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ጎንደር ከተማና አካባቢው ሸፍተው ጫካ የገቡና ከአሸባሪ ኃይሎችና ታጣቂዎች ጋር ሲገናኙ ነበሩ ከተባሉት ውስጥ 93 ሰዎች እጃቸውን መስጠታቸው ታውቋል፡፡ እጃቸውን ከሰጡት ውስጥ 45 የሚሆኑት ከነሙሉ ትጥቅ፣ 38 የሚሆኑት ደግሞ ያለ ትጥቅ እጅ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

በጎንደር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 13 ተጠርጣሪዎች፣ የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ውስጥ ውስጡን ሲቀሰቅሱ ነበሩ የተባሉት 13 ተጠርጣሪዎች፣ የመማር ማስተማሩን ሒደት ለማደናቀፍ የሞከሩ ሦስት መምህራን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡

በባህር ዳር ከተማ የንግድ ሱቆቻቸውን በመዝጋት አገልግሎት ለማቋረጥ የተንቀሳቀሱ 35 ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ስድስቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቀቃቸውንና የቀሪዎቹ 29 ነጋዴዎች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተፈጠረው ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ሁከት ምክንያት ተጠርጣሪዎች በሕዝብ ጥቆማና በተጠርጣሪዎች በጎ ፈቃድ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሆነ፣ ኮማንድ ፖስቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ባስተላለፈው ጥሪም ሰው የገደሉ፣ ንብረት የዘረፉና ያወደሙ ተጠርጣሪዎችን ኅብረተሰቡ አሳልፎ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...