Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ የግል ጦር መሣሪያ ለመንጠቅ የወጣ ነው ተብሎ...

‹‹የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ የግል ጦር መሣሪያ ለመንጠቅ የወጣ ነው ተብሎ የሚሠራጨው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው››

ቀን:

አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ ጠቅላይ ዋና ዓቃቤ ሕግ

ሰሞኑን በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲደረግ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም በኮማንድ ፖስቱ የተዘጋጀውን መመርያ በተመለከተ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግርታ በፈጠሩ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ማብራሪያ ሰጡ፡፡ በዋናነት አነጋጋሪና ግርታ ፈጥረዋል ከተባሉ ጉዳዮች መካከል የመሣሪያ አያያዝ፣ የሰዓት ዕላፊ ገደብ፣ የተጠርጣሪዎች አያያዝና ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ ብርበራ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተለይ በመሣሪያ አያያዝ በኩል የወጣው መመርያ አንቀጽ 13 ማንኛውንም የጦር መሣሪያ፣ ስለት፣ እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ወደ ገበያ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሕዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት ቦታ፣ በአጠቃላይ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው ይላል፡፡

መመርያው ይፋ ከተደረገ በኋላ ይህ አንቀጽ የተለያዩ መላምቶች እየተጨመሩበት ውዥንብር የፈጠረ ሲሆን፣ በተለይ መንግሥት ትጥቅ ሊያስፈታ ነው የሚል አስተያየት ተሰምቶ ነበር፡፡

ነገር ግን አቶ ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ የግል ጦር መሣሪያ ለመንጠቅ የወጣ ነው ተብሎ የሚሠራጨው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ግጭት ለመግታት በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን አዋጅ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. አውጥቷል፡፡ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የወጣው መመርያ በአገሪቱ የተፈጠረውን ችግር ከሥሩ ለመፍታት ዘጠኝ ቦታዎችን ለይቶ ቀይ ዞን ብሏቸዋል፡፡

እነዚህም ከአዲስ አበባ ጂቡቲ፣ ከአዲስ አበባ ሻሸመኔ፣ ከአዲስ አበባ ሐረር፣ ከአዲስ አበባ ዲላ፣ ከአዲስ አበባ ነገሌ፣ ከአዲስ አበባ ጋምቤላ፣ ከአዲስ አበባ አሶሳ፣ ከአዲስ አበባ ገብረ ጉራቻ፣ ከጎንደር መተማ፣ ከጎንደር ሁመራ ያሉት መስመሮች ናቸው፡፡

አቶ ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ በእነዚህ መስመሮች ግራና ቀኝ 25 ኪሎ ሜትር ቀጣና (ራዲየስ) ድረስ ማንኛውም ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ‹‹በዚህ አካባቢ የሚኖር ግለሰብ የግል ጦር መሣሪያ ካለው ቤቱ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ወይም በራሱ ይዞታ ላይ ብቻ ይዞ መገኘት ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ሕገወጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሰዓት ዕላፊ ጉዳይም አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በመመርያው አንቀጽ 22 ላይ በኢኮኖሚ አውታሮች፣ በመሠረተ ልማቶች፣ በኢንቨስትመንት ተቋማት፣ በእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎችና በመሰል ተቋማት አካባቢ ከቀኑ 12፡00 አንስቶ እስከ ንጋቱ 12፡00 ድረስ ከተፈቀደለት ሠራተኛ በስተቀር ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ አይችልም ይላል፡፡ አንቀጽ 23 ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰው በኮማንድ ፖስቱ ውሳኔ የሰዓት ዕላፊ በይፋ በሚገለጽበት ቦታና ጊዜ የሰዓት ዕላፊ ክልከላን በመተላለፍ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይፈቀድም ይላል፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ በዘጠኙ ቀጣናዎች በተለይም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ማንኛውም ሰው ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

ሌላው ጉዳይ የዕርምጃ አወሳሰድና የፍርድ ሒደት ነው፡፡ በመመርያው አንቀጽ 31 ላይ በሕጉ መሠረት በኮማንድ ፖስቱ ከሚደረጉ የተሃድሶ ዕርምጃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ለፍርድ መቅረብ ያለበት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ ሁለተኛው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተፈጸሙ ሁከቶችና በብጥብጦች ላይ በቡድን ወይም በግል የተሳተፈና በጦር መሣሪያ ወይም በማንኛውም መንገድ የግልም ሆነ የመንግሥት ንብረት የዘረፈና የዘረፈውን መሣሪያና ንብረት ይህ መመርያ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በአሥር ቀናት ውስጥ በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ የመለሰና እጁን የሰጠ፣ ከዚህ በፊት ለሕገወጥ ተግባራት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገና ይህ መመርያ በወጣ በአሥር ቀናት ውስጥ ለፖሊስ እጁን የሰጠ፣ ወረቀት በመበተንና አድማ በማድረግ የተሳተፈና ያነሳሳ ይህ መመርያ በወጣ በአሥር ቀናት ውስጥ ለፖሊስ ጣቢያ እጁን የሰጠ፣ ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠለ፣ ወንጀል የፈጸመ ይህ መመርያ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአሥር ቀናት ውስጥ ለፖሊስ እጁን የሰጠ፣ እንደ ወንጀል ተሳትፎው ቀላልና ከባድነት ዋና ፈጻሚና አባሪ ተባባሪ መሆኑ ታይቶ በኮማንድ ፖስቱ የተሃድሶ ትምህርት ተሰጥቶት እንዲለቀቅ ይደረጋል ይላል፡፡

ይህ አንቀጽ በኅብረተሰቡ ዘንድ መነጋገሪያ በመሆኑ፣ ሰው የገደለና ንብረት ያወደመ እንዴት የተሃድሶ ሥልጠና ተሰጥቶት ይለቀቃል የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

አቶ ጌታቸው ሰው የገደለና ፋብሪካ ያቃጠለ በተሃድሶ ሥልጠና ሊለቀቅ አይችልም፣ እንደ ወንጀሉ ተሳትፎ እየታየ ለፍርድ የማቅረብ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ ‹‹አድማ ያስነሳና ወረቀት የበተነ ሰው ከገደለ፣ ፋብሪካ ካቃጠለ ጋር እኩል ሊዳኝ አይችልም፣›› ሲሉ ኅብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ ግር ሊሰኝ እንደማይገባ አስታውቀዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን በቦርዱ አማካይነት የት እንዳሉ፣ የሠሩት ወንጀልና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ ሌላው ሥጋት የሆነው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረግ የቤት ብርበራ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ ብርበራ የሚካሄደው በአካባቢው የሚገኙ የማኅበረሰብ ፖሊስ ባሉበት የአካባቢ ሰዎች በተወከሉበት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ በኩል ችግር እንዳይፈጸምና ማንኛውም ሕጋዊ ያልሆነ አካል የፀጥታ ኃይሎችን ዩኒፎርም መልበስ፣ ይዞ መገኘት፣ ቤት ማስቀመጥ፣ አሳልፎ መስጠትና መሸጥ ክልክል ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ አገሪቱ ወደ ቀድሞ ሰላሟ ተመልሳለች፡፡ ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሷን ለማሳየት የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለአብነት አንስተዋል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መጓጓዝ ሥጋት የፈጠረባቸው ሰዎች በአውሮፕላን ለመጓጓዝ ተገደው እንደነበር ሲገልጹ፣ ‹‹ከአዲስ አበባ የአራት ሰዓት ጉዞ ብቻ የሚወስደውን ወደ ሐዋሳ ከተማ የሚደረግ ጉዞ፣ ሰዎች በአውሮፕላን ለመጓዝ አንድ ሳምንት ወረፋ ለመጠበቅ ተገደዋል፤›› በማለት የሁከቱን ወቅት አስከፊነት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበት ነዳጅ መንገድ በመዘጋቱ ነዳጅ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች መተማ ከተማ ለመቆም ተገደው ነበር በማለት የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ለታላቁ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች መንገድ ተዘግቶ ለአንድና ለሁለት ቀናት መጓዝ ሳይችሉ ቀርተዋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ በተወሰዱ ዕርምጃዎች አገሪቱ ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሷን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...