Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሥነ ፍጥረትየዝሆን አማካይ ዕድሜ 80 ዓመት ነው የብሔራዊ ፓርክ ዕድሜ ስንት ይሆን?

የዝሆን አማካይ ዕድሜ 80 ዓመት ነው የብሔራዊ ፓርክ ዕድሜ ስንት ይሆን?

ቀን:

በሰለሞን ወርቁ በያዝነው ዓመት የዓለማችን ዕድሜ ጠገቡ ብሔራዊ ፓርክ የአሜሪካው የሎው ስቶን 100ኛ ዓመቱን ከመቸውም በላይ አምሮበት ለማክበርና የቀጣዩን ክፍለ ዘመን መፃኢ ዕድል በር ለመክፈት እየተሰናዳ ባለበት ወቅት፣ ሩሲያ እ.ኤ.አ. 2017ን የፓርኮች ዓመት ሆኖ እንዲከበር ወስና ከወዲሁ በርበሬ እየቀነጠሰች ባለበት በዚህ ወቅት የእኛው አዋሽ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉ መቃረቡን አስቦ ተክዟል፡፡ በአገራችን የዱር እንስሳት ሀብት ጠቀሜታ መኖሩ ልብ የተባለው በ1936 ዓ.ም. በእርሻ ሚኒስቴር ሥር በተቋቋመው የአደን ፈቃድ ሰጪ ቢሮ አማካይነት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አደንና የመሬት ሕገ ወጥ ይዞታ መስፋፋት ምክንያት አዲስ ሐሳብ ተወለደ፡፡ የዱር እንስሳት ሀብትን በዘላቂ ሀብትነት ለመጠበቅ ከተፈለገ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ከአጠቃቀም ጎን ለጎን መኖሩ ተገቢነቱ ታምኖበት የአትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ድርጅት በ1962 ዓ.ም. በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል ሆኖ በእርሻ ሚኒስቴር ሥር ተቋቋመ፡፡ አዋሽና የዕድሜ አቻው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ብሔራዊ ፓርኮች ሆነው በነጋሪት ጋዜጣ ደንብ ቁጥር 57 እና 54 በ1961 ዓ.ም. ተቋቋሙ፡፡ ይህ ከመሆኑ ስድሳ ዓመታት ቀድሞ አውሮፓውያን ረግጠውት የማያውቁትን ሥፍራ ለመዳሰስና የጉዞ ማስታወሻውን በኢትዮጵያ ዙሪያ ለመጻፍ በማሰብ ከአገረ እንግሊዝ በ1891 ዓ.ም. ገደማ ተነስቶ የዘጠኝ ወር ቆይታ አድርጎ በሦስተኛው ዓመት መጽሐፉን ያሳተመው ፖውል ኮቶን ነበር፡፡ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ላይ የሰፈረው የማስታወሻው መሪ መግለጫ ‘‘ለጥ ካለው የአዋሽ ሜዳ እስከ በረዷማው ሰሜን አደን ከዝሆን እስከ አይቤክስ’’ የሚል ነበር፡፡ የአዋሽና የሰሜን የተፈጥሮ ፀጋ ልግስና ያኔ ፍፁም ግሩም የሚባል ነበር፡፡ አዋሽን በዛሬ ገጽታው ሳይሆን የዝሆንና የጎሽ መናኸሪያ እያለ ያየው ፖውል ኮቶን የቢለን ፍል ውኃን፣ የአዋሽ ወንዝን ድምቀት የሳላና የግሬቪ አህያን መንጋ፣ የሰጎንና የቆርኬን ብዛት ገልጾ በመጽሐፉ /A SPORTING TRIP THROUGH ABYSSINIA/ አስፍሮታል፡፡ በ50 ዓመቱ እርጅና የተጫነው አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ አዋሽ ከተቋቋመበት 1961 ዓ.ም. ጀምሮ የዳግም ክለላ እስኪደረግለት ድረስ 752 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት 590 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ተከልሎ ይገኛል፡፡ ፓርኩ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች የተፈጥሮ ሀብቱ እንዲመናመን ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሲያደርሱበት ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያውን ሰው ሠራሽ ከባድ ጫና ያስተናገደው በተቋቋመ በስድስት ዓመቱ ገደማ የንጉሡ ሥርዓት መፍረስን ተከትሎ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግም በነጋሪት ጋዜጣ በታወጀው የ1970 ዓ.ም. ደንብ መሠረት በፓርኩ ዙሪያ በሚኖሩ አርብቶ አደሮች የሚደርስበት ጫና መቀነስ ተችሏል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በርካታ የአገሪቱን አካባቢ ተዳርሶ የነበረው የ1977 ዓ.ም. ድርቅ አዋሽንም ጎብኝቶ ነበር፡፡ በዚህም አካባቢው ለሁለት ዓመት ያህል የዝናብ ጠብታ ሳይጎበኘው በመቆየቱ ምክንያት ደቡባዊ የፓርኩ ቀጣና ፈንታሌ እንዲሁም ምዕራባዊው የፓርኩ ግማሽ አካል ሳቡሬ ሜዳ ለአርብቶ አደሩ ማረፊያና የግጦሽ መሬትነት ተሰጠ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በአርብቶ አደሩ ጥያቄ መሠረት በተጨማሪም ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት ይውል ዘንድ ሳቡሬ ላይ የውኃ ገንዳ ተገነባ፡፡ የ1983 ዓ.ም. የመንግሥትን ለውጥ ተከትሎ ፓርኮች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ አዋሽም የዚህ ዕጣ ሊደርሰው ሦስት ተከታታይ ሙከራዎች የተቃጡበት ቢሆንም አካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተካሄደ ውይይት መሠረት ከአደጋው ማዳን ተችሏል፡፡ ከዚያ ሁሉ በኋላ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አሁን አዋሽ አንጀት ርቆታል፡፡ ሆደባሻ ሆኗል፡፡ ከባዶ ማፅናናት ባሻገር ከጎኑ የሚቆምለት የሚደግፈው ይሻል፡፡ እርግጥ ነው በቀደመው ዘመን የነበረውን የተፈጥሮ መልክ መልሶ መፍጠር አይቻልም፡፡ ዓለማችን በለውጥ ላይ ናት፣ የሰው ልጅም የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ ነው፣ ተፈጥሮም እንደዚያው፡፡ ቁምነገሩ ግን የአገራችን የተፈጥሮ ፀጋ በተገቢው መልኩ ለማስተዳደርና ከጥፋት ለማዳን መትጋት እንዳለብን ቆም ብለን የምናስብበት ጊዜ አሁን መሆኑን ማወቁ ላይ ነው፡፡ ከሩብ ምእት ዓመት በፊት አካባቢውን የቃኙት ዶ/ር ጀሲሲ ሂልማን የሰጡት ምክረ ሐሳብ ለጥቅስ የሚበቃ ነው፡፡ ‹‹ምንም እንኳ በተፈጥሮ ተቆርቋሪ ዓይን አዋሽን የበርካታ የዱር እንስሳት መከማቻ ስፍራነቱ እኛ ብንረዳውም ሌሎች የሚያዩበት መነጽር እንደሚለይ መዘንጋት የለብንም፡፡ ውኃማና ለጥ ያለ ለእርሻ ምቹ ሥፍራ፣ ገደብ የለሽ የአርብቶ አደር ቀጣና፣ ወሳኝ የመገናኛ መስመር፣ መንገድ፣ የባቡር መስመር፣ የውኃ፣ የስልክና የኤሌክትሪክ መስመሮች ሁሉም በዚህ ዘመን የምንፈልጋቸው መሠረተ ልማቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ሁሉ ዘርፎች በተለያየ መልኩ አንዱ አንዱን ተፅዕኖ ላይ በማይጥልበት መልኩ ተገናዝበው የጋራ ጥቅም በማስቀደም ተጣጥመው የሚሄዱበት ዘዴ መታሰብ ይኖርበታል::›› ሂልማን የጠቆሙት የመቻቻል ሐሳብ ታስቦበት አንዱ ዘርፍ ከሌላው ተጣጥሞ ሄዶ ቢሆን ኖሮ እያልን ቁጭት ይውረሰን፡፡ በእነዚህ መቻቻል በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መቻቻል ስላልተቻለ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለን ስለ ጥንቱ አዋሽ እያወራን እንገኛለን፡፡ አዲስ ሊገነባ የታሰበው የፍጥነት መስመር፣ በቀጣናው ሊገነቡ የታሰቡ የውኃ ጉድጓዶች፣ በፓርኩ አቅራቢያ ያለው የአዋሽ ከተማ ማስተር ፕላን ሌላ ቁጭት ሊያወርሱን ምንም አይነት መጣጣም ላይ ሳይደርሱ ወደፊት እየፈረጠጡ ይገኛሉ፡፡ መሠረተ ልማቶቹ ለእኛ የኑሮ ሸክም ቅለት ያላቸው ፋይዳ እጅግ የሚባል ነው፡፡ የአዋሽ ሕይወትና የእኛ ሕይወትም መሳ ለመሳ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከወዲሁ ልብ ካልተባሉ በቋፍ ላይ ያለውን አዋሽ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርክ እዚህ አካባቢ ነበር እያልን በባቡር ተሳፍረን ስናልፍ የምንተርክበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ አዋሽ፣ የዱር እንስሳትንና የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለማየት ሲባል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበትና ለመዲናችን አዲስ አበባ በመቅረቡ ምክንያት አገሬው የሚጎበኘው ብቸኛው ብሔራዊ ፓርክ ነበር፡፡ የዝሆኖች ፍልሰትና ባቢሌ ‘የዝሆኖች’ መጠለያ ከአዲስ አበባ ወደ ጅግጅጋ መስመር 557 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው ባቢሌ ከተማ፣ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ባለው በደን የተሸፈነ ክፍል የሚኖሩ ዝሆኖች እንዲጠለሉበት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ ምንግሥት በ1962 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ‹‹ክልላችሁን እንጠብቃለን መጠለያችሁንም ባቢሌ ብለነዋል›› ማለታቸውም ይነገራል፡፡ ዝሆኖቹ ቀድመው ይኖሩ በነበረበት በዚህ የባቢሌ መጠለያ ከትውልድ ትውልድ ሲወራረሱ በየዘመናቱ የሰዎች በአካባቢው መኖር እየተበራከተ መጥቶ እነሆ ዛሬ መጠለያቸውን ለከብት፣ ለግመል፣ ለፍየልና ለባለቤቶቻቸው መጠለያና እርሻ ለቀው በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንጠብቃችኋለን ያሏቸውም ክንዳችንን ተንተርሰን ራሳችሁን አውጡ የሚሉበት ጊዜ የመጣ ይመስል በግራ መጋባትና በትካዜ ተውጠው መጨረሻውን ይጠባበቃሉ፡፡ ዝሆኖቹ ሠልፍ ወጥተው እየሄዱ ነው፤ መጠለያውንም 1,500 ለሚሆኑ አርብቶ አደርና አርሶ አደር ሰፋሪዎች ወደፊትም ለሚገቡት ጭምር አስረክበው እየለቀቁ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. በሰኔ ወር ገደማ አንድ በመጠለያው ምዕራባዊ ክፍል በጎበሌ ሸለቆ ይኖር የነበረ ዝሆን ከሞቀ መጠለያው ለቆ 30 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ሐረር ከተማ በሶፍ ወረዳ ሲደርስ ከቀየው ያሰደደው የሰው መንደር ውስጥ በመግባቱ ግራ ይጋባና አንድ ሰው ለህልፈት ሲዳርግ፣ አንድ ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጎ በአካባቢው ሰዎች ርብርብ ወደ መጠለያው ዳግም ሊመለስ ችሏል፡፡ ይህ ከሆነ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ከኤረር አካባቢ የተገፋ የዝሆን መንጋ መጠለያውን ለቆ የባቢሌ ከተማ ዋና መንገድ ላይ በመውጣት ሳምንት ቆይቶ ሲመለስ በሰዎች አማካይነት በደረሰበት አደጋ አንዱ አውራ ከመንጋው ተነጥሎ ቀርቷል፡፡ እንዲያው በውል ይታወቃል በሚባለው እንኳን ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ስድሳ ሦስት ዝሆኖች በሰዎች ተገድለዋል፡፡ የሰባቱ ዝሆኖች ጥርስ በተለያየ መንገድ የተያዘ ሲሆን የቀሪዎቹ ግን መዳረሻው ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ አሁን ባቢሌ እንደ ቀድሞው የዝሆኖች ብቻ መጠለያ አይደለም፤ የሰዎችና የቤት እንስሳትም ጭምር እንጂ፡፡ መጠለያም ብቻ አይደለም የሰፋፊ እርሻዎችና የበርካታ የቤት እንስሳት የግጦሽ ቦታም ጭምር እንጂ፡፡ በአሁኑ ወቅት 1,125 ስኩየር ኪሎ ሜትር የሚገመት የመጠለያው ክፍል በሰዎች ተይዞ ይገኛል፡፡ በመጠለያው ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚያገለግል የገበያ ቦታዎች ተመሥርተዋል፡፡ በዚያም ወተት፣ ጫትና ሌሎች ለዕለት ፍጆታ የሚያስፈልጋቸውን ግብአት ይሸምታሉ፡፡ ባቢሌ ‘የዝሆኖች’ መጠለያ በ6,987 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋቱ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልል ተንሰራፍቶ የሚገኝ ሲሆን በ2007 ዓ.ም. በተደረገ ቆጠራ 250 የሚሆኑ ዝሆኖች እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ ዝሆን ለጥርሱ ሲባል በሕገ ወጥ መንገድ በመታደኑ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ በዚህም መልኩ ከቀጠለ በቅርብ ዓመታት ከምድረ ገጽ ሊጠፋ እንደሚችል ይታመናል፡፡ የባቢሌ ዝሆኖች ሕገ ወጥ አደን እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ የመጣ ሲሆን፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ሠፈራው ደግሞ ለዚህ እክል ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ለከሰልና ለእርሻ ቦታ ፍለጋ በሚደረግ ምንጣሮ ምክንያት መተኪያ የማይገኝላቸው በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ አገር በቀል ዛፎች ደብዛቸው እየጠፋ ሲሆን መጠለያው አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሊ ዶል በባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ለአሥራ ሦስት ዓመት በቁጥጥርና ጥበቃ ሠራተኝነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አሁንም በዚያው እያገለገለ ሲሆን መጪውን ጊዜ ሲያስብ ግን ፊቱ ላይ ፍርኃት ይነበባል፡፡ አሊ ዶል ምን አለ? እንዲህ አለ ‹‹አቦ ባቢሌ 2009 ዓ.ም ካለፈ ምናልባት ተስፋ ይኖረዋል፡፡›› አሊ ብዙ መጥፎ ጊዜያትን ከባቢሌ ዝሆኖች ጋር እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡ ያሁኑ ግን አስፈሪ ነው ይላል፡፡ ‹‹ለራሳችን መሥጋት ጀምረናል፡፡ እኛ ብንሞት ቤተሰባችን ይበተናል፣ ስለሆነም መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ያ ካልሆነ ግን እኛ ባለን አቅም ችግሩን መፍታት አንችልም ከአቅማችን በላይ ነው፤›› ሲልም አክሏል፡፡ ሥጋት ከወዴት መጣ ቢሉ? በ2008 ዓ.ም. በመጋቢት ወር በመጠለያው ቀጣና በተፈጠረ ግጭት የመጠለያው ሠራተኛ የነበረው አብዱላጢፍ ረሽድ በመጠለያው ውስጥ ለቁጥጥር ሥራ ተሰማርቶ ባለበት ጊዜ በሕገ ወጥ መንገድ በመጠለያው ውስጥ በገቡ ሕገ ወጦች በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አልፏል፡፡ ይህን ያየ ዓይን እንዴት ችግርን ገፍቶ ይጋፈጥ፡፡ አብዱላጢፍ የስምንት ልጆች አባት የቤቱ አባወራ ነበር፡፡ ቀሪዎቹ የመጠለያው የቁጥጥርና ጥበቃ ሠራተኞች ይህንን አይተው ቢበረዩ ነገን የልጆቻቸው አባት እንደሆኑ መቆየት ቢሹ የሚገርም ነገር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ በሰባት የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታዎችና በሁለት የጥብቅ ደኖች ውስጥ ዝሆኖች ያሏት ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ብቸኛው ዝሆኖችን ለመጠበቅ ሲባል የተቋቋመ መጠለያ ነው፡፡ የመጠለያው ስፋትና የሥነ ምህዳሩ ምቹነት ዝሆኖችን ትርጉም ባለው መልኩ ለመጠበቅ በእጅጉ የሚመረጥ ቦታ ነው፡፡ እና ምን ይሻላል? የሚሻለው ከፍተኛ ኃላፊነት የተጣለበት ባለሥልጣኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሁለቱ ክልሎች ጋር በመነጋገር ሰፋሪዎቹን ማስወጣት እርሻና በመጠለያው ውስጥ የሚካሄዱ ማንኛውም ዓይነት ሕገ ወጥ ተግባራት ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ የመጠለያው ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን ለመፍታት ብቻውን አንድ ዕርምጃ እንኳን ወደፊት መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ አቶ ጀማል የመጠለያው ዋርደን እንዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩን በተደጋጋሚ ለዋናው መሥሪያ ቤት አሳውቀናል፣ እስካሁን ግን ያገኘነው ምላሽ የለም፣ አሁንም ከእኛ ጥረት የሚታከል ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ ይሆናል፡፡›› ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለመምከር በ2008 ዓ.ም. ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አማካይነት፣ በድሬዳዋ ከተማ የምሥራቅ እዝን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም በባቢሌ ከተማ መጠለያውን ከሚያዋስኑት ወረዳዎችና ሁለት ዞኖች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ ሆኖም ግን እስካሁን መሬት ላይ የወረደ ምንም ተግባር አለመኖሩን አቶ ጀማል የመጠለያው ዋርደን የገለጹ ሲሆን፣ እንዲያውም አዲሱን ዓመት አጆ አካባቢ በሕገ ወጥ አዳኞች በተገደለ ዝሆን ችግሩ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሁሉም ነገር መፍትሔ ሳይበጅለት ከቀጠለ መጭው ትውልድ ባቢሌን በዝሆኖቿ ሳይሆን ዝሆን በሚያካክሉ ተደራራቢ ድንጋዮቿ እየተማረከ ይጎበኛታል፡፡ የሟች ተቆርቋሪ ከተገኘ ደግሞ በአውራ መንገዷ መሀል የቁጭት ሐውልት ያቆምላታል፡፡ ግዙፍ የዝሆን ሐውልትንም የሚያይ መጪው ትውልድ ትናንትን ይረግማል፡፡ ቅድመ አያቶቹንም ሲወቅስ ይኖራል፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...