Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሜቴክና ጥረት ለዲጂታል ቴሌቪዥን ማሠራጫ ቴክኖሎጂ እንዲያመርቱ ተመረጡ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  – ለስድስት የግል ቴሌቪዥንና ኤፍኤም ጣቢያዎችም ፈቃድ ተሰጥቷል

  የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አካል የሆነው ሀይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና የጥረት አካል የሆነው ጣና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የዲጂታል ቴሌቪዥን ማሠራጫ ቴክኖሎጂ (ሴት ቶፕ ቦክስ) እንዲያመርቱ ተመረጡ፡፡

  ቴክኖሎጂውን ለማምረት አራት ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ ለአምስት ሚሊዮን የቴሌቪዥን ባለይዞታዎች በሽያጭ እንደሚከፋፈል ታውቋል፡፡ አገልግሎት ላይ የሚገኘውን የአናሎግ ቴሌቪዥን ሥርጭት ወደ ዲጂታል የሚቀይረውን ቴክኖሎጂ እንዲያመርቱ የተመረጡት ሁለቱ ድርጅቶች፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደማምረት እንደሚገቡ ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተዘጋጀው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

  የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም እንዳሉት፣ ድርጅቶቹ የተመረጡት በብሮድካስት ባለሥልጣን አስተባባሪነት የወጣውን ጨረታ በማሸነፍ ነው፡፡  በአገር ውስጥ አምራቾች እንዲመረት የተፈለገውም የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠርና በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲዳረስ ተብሎ ነው ብለዋል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነው የአናሎግ ቴሌቪዥን ሥርጭትን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሒደትን ለማሳካት የሚረዱ የመሠረተ ልማት አውታሮችን የማዘጋጀት ሥራው የተጀመረው ከዓመታት በፊት መሆኑን አቶ ዘርዓይ አስረድተዋል፡፡

  ‹‹ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር በአግባቡ ካልተመራ በስተቀር ብዙ ኪሳራዎችና ውጣ ውረዶች ይኖራሉ፤›› ያሉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ናቸው፡፡ ሒደቱ እንዳይደናቀፍ ማድረግ የሚችል ኮሚቴ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው የሌሎች አገሮችን አሠራር መነሻ በማድረግ ሽግግሩን ቀላል ሊያደርግ የሚችል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የተመረጠው የሴት ቶፕ ቦክስ ቴክኖሎጂም በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ እየተጠቀመባቸው የሚገኙትን የአናሎግ ቴሌቪዥኖች ከጥቅም ውጭ እንደማያደርግ ተገልጿል፡፡

  ‹‹ማኅበረሰቡ እየተጠቀመባቸው የሚገኙትን አናሎግ ቴሌቪዥኖች መጠቀም ካልቻልን ሽግግሩ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው የተሻለ የአውሮፓ ቴክኖሎጂ የሆነውን ሴት ቶፕ ቦክስ የመረጥነው፡፡ ነባሮቹን ቴሌቪዥኖች መወርወር ሳይሆን መጠቀም ይቻላል፤›› በማለት ቴክኖሎጂው በሥራ ላይ የሚገኙትን ቴሌቪዥኖች ከጥቅም ውጪ እንደማያደረግ አስረድተዋል፡፡

  በዕለቱ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ የቴሌቪዥን ማሠራጫ ፈቃድ ያገኙት ናቸው፡፡ በሬዲዮው ዘርፍ ደግሞ ሉሲ ዋን ላቭ ብሮድካስቲንግ፣ አሀዱ ኤዲስቴለር ትሬዲንግና አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ የማሠራጫ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሬዲዮ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ቁጥርም ወደ አሥር ከፍ ብሏል፡፡

  ድርጅቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል በሚደረገው ሽግግርም ጥሩ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በማቅረብና የተሻለ የመረጃ አማራጭ በመሆን ስኬታማ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል ተብሏል፡፡ አዲስ የሚዲያ አዋጅና የሲግናል ዲስትሪቡተር ድርጅት ማቋቋሚያ ደንብ መዘጋጀቱንና በባለድርሻ አካላት ፀድቆ በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚውል አቶ ዘርዓይ አስታውቀዋል፡፡

  ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በብሮድካስት አዋጁ መሠረት ቴሌቪዥን ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንዲሆን ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማትም ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ፈቃድ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን፣ ሰላምና መቻቻልን የሚያስተምሩ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በማስተላለፍ ለአገር ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አቶ ዘርዓይ አክለዋል፡፡   

  አመልካቾች በማስታወቂያ ተጠርተው በብሮድካስት አገልግሎት አዋጁና በግል የቴሌቪዥን ፈቃድ መመርያ መሠረት ብቁ የሆኑ ተወዳዳሪዎች ተመዝነው ፈቃዱ እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆናቸውንና አማራጭ የመረጃና የመዝናኛ አውታር እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

  የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚባል መጠሪያ በ1964 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሦስት ቋሚ ጣቢያዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ኢቢሲ አንድ ሲሆን በባህል፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ለ24 ሰዓታት ያስተላልፋል፡፡ ኢቢሲ ሁለት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን ለሕዝቡ ያቀርባል፡፡ ሌላው ኢቢሲ ሦስት ሲሆን ድራማዎች፣ ኑሮና የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞች ያሠራጫል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰባት ኤፍኤም የሬዲዮ ጣቢያዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች