Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ የኅትመት ዘርፍ በውጭ ድርጅቶች መዋጡ ጥያቄ አስነሳ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የኅትመት ዘርፍ በውጭ ድርጅቶች እየተዋጠ መሆኑ ጥያቄ አስነሳ፡፡ የመንግሥትና የግል ተቋማት ለኅትመት ወደ ውጭ ድርጅቶች እያመሩ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ አሳታሚዎችና አታሚዎች እየተጎዳን ነው አሉ፡፡ የአሳታሚዎችና የአታሚዎች ማኅበር ባዘጋጀው ውይይት ላይ፣ የአገር ውስጥ ተቋማት ለማንኛውም ዓይነት ኀትመት የውጭ ድርጅቶችን መምረጣቸው እንዳሳሰባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡

ሐሙስ ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም በሸራተን አዲስ በተካሄደው አገር ዓቀፍ የአሳታሚዎችና የአታሚዎች የውይይት መድረክ፣ በርካታ ባለሙያዎች መንግሥት ለኅትመት ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጠው ገልጸዋል፡፡ ለዘርፉ አንዳችም ድጋፍ ካለመደረጉም በተጨማሪ፣ መንግሥት ከፍተኛ በጀት ላላቸው የኅትመት ሥራዎች የውጭ የኅትመት ድርጅቶችን ብቻ ማማተሩ ተገቢ አይደለም ተብሏል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርን የመሰለ መንግሥታዊ ተቋም ጨረታ ሲያወጣ፣ የአገር ውስጥ አታሚዎችን በማማከል መሆን እንዳለበት ተጠይቋል፡፡

በጄነራል ኢዱኬሽን ኳሊቲ ኢምፕሩቭመንት ፓኬጅ ሥር ትምህርት ሚኒስቴር የሚያሳትማቸው የመማሪያና የማስተማሪያ መጻሕፍት ጨረታን በተመለከተ በርካታ ባለሙያዎች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ የሚኒስቴር ኅትመት በአጠቃላይ የተሰጠው ለውጭ ድርጅቶች በመሆኑ፣ መንግሥት የአገሪቱ አታሚዎችም ዕድሉን የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት እንደነበረበት ተገልጿል፡፡ የአገር ውስጥ አታሚዎች በተናጠል ባይችሉ እንኳን በጋራ የፕሮጀክቱ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነበር ተብሏል፡፡

የአገሪቱ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከውጭ የኅትመት ድርጅቶች ጋር መሥራታቸው የዘርፉ አንድ ተግዳሮት ሲሆን፣ ሌሎችም በርካታ ችግሮች እየተፈታተኗቸው እንደሚገኙ ባለጉዳዮቹ ተናግረዋል፡፡ የአሳታሚዎችና የአታሚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አባዲ እንደገለጹት፣ የኅትመት ዘርፉን መንግሥት ዘንግቶታል፡፡ ‹‹መንግሥት ለዘርፉ በቂ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ተደራራቢ ታክስም አለብን፡፡ የተማረ የሰው ኃይልና የዘመናዊ መሣሪያዎች እጥረትም አለ፡፡ ዘርፉ በመከራ ላይ ያለና መድኃኒት የሚያስፈልገው ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የኅትመት ኢንዱስትሪ ችግሮች፣ ሥጋቶችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርዕስ ጥናት የሠሩት አቶ ጌታቸው በለጠ፣ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት መካከል 95 በመቶው መንግሥት ለዘርፉ ተገቢ ትኩረት እንዳልሰጠው ያምናሉ ብለዋል፡፡ በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ ስለኅትመት ዘርፉ የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ መንግሥት ዘርፉን እንደዘነጋው ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ዋነኛ ተግዳሮት የሆነባቸው ተደራራቢ ታክስ እንደሆነም አክለዋል፡፡ ‹‹15 በመቶ ቫት ከመጻሕፍት ኅትመት ላይ መነሳቱ መልካም ሆኖ ሳለ ወረቀት፣ ቀለምና ሌሎችም ለኅትመት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቫት ዘርፉን ይፈትነዋል፤›› ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ ማተሚያ ቤቶች ዘመን ባለፈባቸው መሣሪያዎች እንደሚገለገሉ፣ ዘመናዊ መሣሪያ እንዳያስገቡ ከፍተኛ የቀረጥ ክፍያ ችግር እንደተጋረጠባቸው አቶ ጌታቸው በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ ዘርፉን የተማረ ሰው ኃይል እጥረትም እየተፈታተነው እንደሆነ አክለዋል፡፡ በኅትመት ዘርፍ የሚያስተምር ተቋም ባለመኖሩም ማተሚያ ቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመስጠት ተገደዋል ብለዋል፡፡

ሌላው የዘርፉ ችግር የጥራት ደረጃ አለመኖሩ ነው፡፡ ዘርፉ ደረጃ ያልወጣበት በመሆኑ በቂ የኅትመት መሣሪያ የሌላቸውም ዘርፉን እንደሚቀላቀሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አታሚዎችና አሳታሚዎች ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ ደረጃ ወጥቶለት ፈር እንዲይዝም ጠይቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የተገኙት ተወካይ በበኩላቸው፣ በኅትመት ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማት ደረጃ የሚወጣበትን ልኬት አዘጋጅተው ካቀረቡ ደረጃ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ የደረጃ ማውጫ መሥፈርቶች በዝርዝር ተዘጋጅተው እንዲቀርቡም ጠይቀዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለመንግሥት ለቀረቡ ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ ‹‹በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ ኅትመት የራሱ ምዕራፍ የለውም ማለት መንግሥት ትኩረት አልሰጠውም ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በሰነዱ የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደተቀመጡና በኅትመት ዘርፉ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከመጻሕፍት ኅትመት ላይ 15 በመቶ ቫት ተነስቷል፡፡ ይህ ለሌሎቹ የኅትመት ግብዓቶች የማይሠራበት ምክንያት የለም፤›› ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥ ኅትመቶች ወደ ውጭ ድርጅቶች የመወሰዳቸውን ጉዳይ በተመለከተ፣ አሳታሚዎችና አታሚዎች የጥራት ደረጃ ማሻሻል ላይ ካተኮሩ የአገር ውስጥ ኅትመት እንደሚያድግ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች በተሻለ ጥራት በመሥራት ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡ ‹‹ትንንሽ ሥራ እየተሠራ የኅትመት ኢንዱስትሪው ማደግ አይችልም፡፡ በሚገኘው ቀዳዳ ሁሉ በተሻለ ጥራት መሥራት አላባችሁ፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ሥራ ከተሠራ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ፕሮጀክት ማግኘት ትችላላችሁ፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች