Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አገሪቱ ከሐር ምርት ማግኘት ያለባትን ጥቅም አለማግኘቷ ተነገረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተሻለ ሐር የማምረት አቅም ቢኖራትም የተማረ የሰው ኃይል ዕጥረት፣ ተፈላጊው ቴክኖሎጂ አለመኖር፣ የዘር ማራቢያና ማሠራጫ ማዕከላት እጥረት፣ ከባለድርሻ አካላት በኩል ያለው አብሮ በጋራ የመሥራት ችግርና የመሳሰሉት ምርቱ እንዳይስፋፉ ማነቆ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

  ሐሙስ ጥቅምት 10 ቀን በፍሬንድሺፕ ሆቴል በተዘጋጀ ዓውደ ጥናት፣ በአገሪቱ 700 የሚሆኑ የሐር ጥጥ (ኩኩን) የሚያመርቱ በአነስተኛ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮች አሉ ተብሏል፡፡ ከእነዚህ አርሶ አደሮች በዓመት 100 ቶን ኩኩን የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት በዓመት የሚገኘው ከሁለት ቶን ያልበለጠ እንደሆነ፣ የሐር ምርምር አስተባባሪው አቶ ዓብይ ጥላሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  በሐር ምርት ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ የምትይዘው ቻይና ስትሆን እ.ኤ.አ. በ2015 ኤክስፖርት ያደረገችው ሐር 170,000 ሜትሪክ ቶን ነበር፡፡ ከሌሎቹ ጨርቃ ጨርቅ ኤክስፖርት በተሻለ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትም ነው ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ዓብይ ገለጻ አንድ ኪሎ ኩኩን (የሐር ጥጥ) በ100 ብር ይሸጣል፡፡ እሴት ሲታከልበት ደግሞ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል፡፡ አንድ ኪሎ የሐር ክር በ1,200 ብር ይሸጣል ብለዋል፡፡

  አገሪቱ ባላት ለሐር ምርት የተመቸ የአየር ፀባይ እንደ ቻይና ባይሆንም ከፍተኛ ምርት በማምረት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደምትችል፣ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ባሉት ችግሮች አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የነበረባትን እያጣች እንደሆነ አቶ ዓብይ አክለዋል፡፡ ምንም እንኳን በየዓመቱ የሚገኘው የምርት መጠን ዝቅተኛ ቢሆንም የተገኘውን ወደ አሜሪካ፣ ካናዳና መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚላክ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ከ4,500 ዓመታት በፊት በቻይና እንደተጀመረ የሚነገርለት የሐር ምርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1970ዎቹ በጣሊያኖች አማካይነት እንደነበር፣ ነገር ግን ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም ነበርና በዚያው መቅረቱ፣ በመሆኑም ጉዳዩ ወደ ጐን ተብሎ ቆይቶ እንደገና በ1993 ዓ.ም. ምርቱን በአገሪቱ ለማስፋፋት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይነገራል፡፡

  የሐር ትሎቹን ለማራባት የሚያስፈልጉ ለምግብነት የሚውሉ እንደ እንጆሪ፣ ካሳቫና የጉሎ ቅጠሎች ለምተው ወደ ሥራው ተገብቶ እንደነበር፣ ነገር ግን አርሶ አደሮቹን የሚያበረታታ የገበያ ሁኔታ ባለመፈጠሩ እንደገና መቀልበሱም ይነገራል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ለኢንዱስትሪው መስፋፋት ደግሞ በቂ የሆነ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት መኖር ወሳኝ ነው፤›› የሚሉት የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ስለሺ ጌታሁን፣ ኢንዱስትሪው በግብዓትነት ከሚጠቀምባቸው አንዱ ሐር እንደሆነ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

  አገሪቱ በሐር ልማት ዙሪያ እያጋጠሟት ያሉትን ማነቆዎችና ያላት ዕምቅ አቅም ላይ ትኩረቱን አድርጐ በተዘጋጀው በዚህ የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት ላይ ከጃፓን የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግና ዓውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት በአገሪቱ ላለው ለሐር ልማት የበኩሉን እየሠራ መሆኑን የድርጀቱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ጌታቸው መላኩ ገልጸዋል፡፡    

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች