‹‹የ13 ወር ፀጋ›› የተሰኘውና ለዘመናት የኢትዮጵያ ቱሪዝም መገለጫ የነበረው መለያ (ብራንድ) በ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› የተተካው በቅርቡ ነው፡፡ መለያው በይፋ ሥራ ላይ ውሎም የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ መለያው በምን መንገድ እንደተመረጠና ለቱሪዝሙ ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ ለጋዜጠኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ጥቅምት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ያዘጋጀው መድረክ፣ የቱሪዝም መለያው ጥቅም ላይ ሲውል መጠበቅ ያለባቸው መርሆዎችንም ዳሷል፡፡
‹‹አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለያ መሪ ቃል ምንነት፣ አስፈላጊነትና አጠቃቀም›› በሚል መርህ ጥናት ያቀረቡት አቶ ሲሳይ ጌታቸው፣ የቱሪዝም መለያው ኢትዮጵያ ያሏትን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች በማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎችን የሚጋብዝ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን የገለጹትም ከቀድሞው የቱሪዝም መለያ ጋር በማነፃፀር ነበር፡፡ የቀድሞው የቱሪዝም መለያ ለዘመናት ጎብኚዎችን የሳበ ቢሆንም፣ የአገልግሎት ዘመኑን አጠናቋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመለያው ቃል የተገባው ኢትዮጵያ ያልተበረዘ ባህል፣ ተስማሚ አየር፣ ማራኪ መልከዓ ምድርና ሌላም ሀብት እንዳላት ነው፡፡ ነገር ግን መለያው በረዥም ጊዜ ሒደት ስለ አገሪቷ ከተገነባው የተበላሸ ገጽታ ጋር ተያይዟል፤›› ብለዋል፡፡ ብዙዎች ስለኢትዮጵያ ሲነገር አያይዘው የሚያነሷቸው አሉታዊ ገጽታዎችን በበጎ ለመለወጥ አዲስ መለያ ያስፈለገውም ለዚህ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሳ ከረሃብና ድህነት ጋር ብቻ አያይዘው አገሪቷን የሚገልጹ እንዳሉና ይህን ስያሜ ለውጦ በነባራዊው ሁኔታ ለመተካት አዲሱ መለያ ያግዛል፡፡
በጥናታቸው ይህን ቢሉም፣ የ‹‹13 ወር ፀጋ›› መለያን የቀመሩትና ‹‹የቱሪዝም አባት›› በሚል የሚታወቁት አቶ ኃብተሥላሴ ታፈሰ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢው ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ በጋዜጠኞች ተመልክቷል፡፡ አቶ ኃብተሥላሴ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ጅማሮ እንዲሁም የዓመታት ጉዞው የማይዘነጋ ውለታ መዋላቸውን ከግምት በማስገባት ምሥጋና እንዲቀርብላቸውም ተጠይቋል፡፡
አጥኚው፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የቱሪዝም መለያ መስቀል የዘመነ ደርግ ደግሞ የአንበሳ ምልክት እንደነበራቸው አስታውሰዋል፡፡ መስቀል መላው ኢትዮጵያዊያን እንደማይወክልና አንበሳም የሁለቱ ሥርዓቶች መገለጫ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አዲሱ መለያ ላይ ያለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተሳሰሩበት ዛፍና ዛፉ ያረፈበት ሰማያዊ ቀለም ከአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ባሻገር የሕዝቦችን እርስ በርስ መተሳሰር፣ ተስፋና ብልፅግናንም ያንፀባርቃል ብለዋል፡፡
አዲስ መለያ ላይ ያለው ምልክት ጥያቄ ባያስነሳም፣ ብዙ ጋዜጠኞች የአንበሳ ምልክት የፖለቲካዊ ሥርዓቶች መገለጫ ነው የሚለውን ድምዳሜ ተቃውመዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንበሶች (ባለ ጥቁር ጐፈር አንበሳ) እንደ እንስሳ ከሚሰጣቸው ትልቅ ሥፍራ ባሻገር፣ የአንበሳ ምልክትም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ያለው ቁርኝት ተነስቷል፡፡ አንበሳ ከማኅበረሰቡ ታሪክ ጋር ከመተሳሰሩ ባሻገር በሥነ ቃል፣ በምርቃትና በንግግር መካከልም ስለ አንበሳ ማጣቀስ የሰላምታ ያህል በተለመደበት አገር አንበሳን ከአንድ ሥርዓት ጋር ብቻ ማያያዝ እንደማይገባም ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ለዱር እንስሳት የሚሰጠው ቦታ እንዲሻሻልና ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ›› ሲባል የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ አንበሶችንም ስለሚያመላክት ክብር እንዲሰጣቸው ተጠይቋል፡፡
አቶ ሲሳይ እንደገለጹት፣ መለያው ሲዘጋጅ ኢትዮጵያውያን ስለ ራሳችን ምን እንላለን? የውጭ አገር ሰዎች ኢትዮጵያን እንዴት ይመለከቷታል? በቱሪዝም ረገድ ኢትዮጵያን የሚፎካከሩ አገሮች ኢትዮጵያን በምን መንገድ ይገልጻሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ተጠይቀው የተገኘውን ምላሽ መሠረት በማድረግ መለያው ተመርጧል፡፡
‹‹የቱሪዝም መለያ ለጎብኚዎች ቃል የምንገባበት ነው፡፡ በአዲሱ መለያ ቃል የምንገባው ኢትዮጵያ የብዙ ነገሮች መሠረትና የዘመናት ታሪክ ባለቤት መሆኗን እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቷና ባህሏን ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አገሪቷን ልዩ ከሚያደርጓት ሀብቶች መካከል የሰው ዘር፣ የቡና፣ የእንሰት፣ የጤፍና የያሬዳዊ ዜማ ኖታ መነሻ መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ አቶ ሲሳይ ስለ አገሪቱ ሀብቶች በቱሪዝም መለያው የሚሰጠው መረጃ በእውን የሚታይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ቱሪስቶች በመለያው የተገባላቸውን ቃል ወደ አገሪቱ ሲመጡም ማግኘት አለባቸው፡፡
በዚህ ረገድ የጋዜጠኞች ጥያቄ የነበረው ቱሪስቶች ኢትዮጵያ የብዙ ነገሮች መነሻ ናት ብለው ለመጎብኘት በሚመጡበት ወቅት፣ አገሪቱ የምትኮራባቸው ሀብቶች መገኛ አካባቢዎች ላይ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል? የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተጠቀሱት ሀብቶች መነሻነቷን የሚገልጹ ጥናቶችን ከማቅረብ ጎን ለጎን በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ስለ ሀብቶቹ በቂ መረጃ መቅረብ መቻል አለበት፡፡
በተያያዥ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያለውን ሀብት ጠብቆ የማቆየት ጉዳይንም ማንሳት ይቻላል፡፡ በቱሪዝሙ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መካካል የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የመዳረሻ አካባቢዎች አያያዝ ጉድለት ይጠቀሳል፡፡ የበርካታ ባለሙያዎች የዘወትር እሮሮ ቢሆንም አንዳች መፍትሔ ያልተበጀለት የፓርኮች አያያዝ ደግሞ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎች ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ለማስቻል የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆኑም ይተቻል፡፡
በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያለው ማኅበረሰብ ከቱሪዝሙ የሚያገኘው ዝቅተኛ ጥቅምና ስለቱሪዝሙ ያለው ግንዛቤ ውስንነትን እንደ ችግር የሚያነሱም ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ማኅበረሰብ ስለ አዲሱ የቱሪዝሙ መለያም መረጃ የሚያገኝበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት የተናገሩ ነበሩ፡፡
የቱሪዝም መለያው በይፋ ሥራ ላይ ከዋለ ጥቂት ጊዜው ቢሆንም፣ ወጥ የአማርኛ ትርጓሜ አልተሰጠውም፡፡ ይህም የተለያዩ አካሎች በተለያየ መንገድ ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ››ን እየተረጐሙ እንዲጠቀሙ አድርጓል፡፡ መለያውን በእንግሊዝኛ ብቻ አስተዋውቆ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛው መመለስ ጐን ለጐን መሔድ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
መለያውን በማስተዋወቅ ረገድ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ልዩ ልዩ መንገዶችን መጠቀም እንዳለበትም ተገልጿል፡፡ ‹‹የ13 ወር ጸጋ›› የሚለውን መለያ በድረ ገጽ፣ በመጽሔትና በሌላ መንገድም አሁንም ድረስ የሚጠቀሙ ተቋሞች እንዳሉና አዲሱን መለያ ሁሉም በወጥነት እንዲጠቀም በማድረግ ድርጅቱ ኃላፊነት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡
መለያው ጥቅም ላይ ሲውል ተጠቃሚው አካል መከተል ያለበትን መርሆች አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ በመለያው ያሉት ጥቁር፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይና ሰማያዊ ቀለም በመለያው ከሰፈሩበት የቀለም ኮድ ውጪ መጠቀም አይቻልም፡፡ በመለያው ፊደላት መካከል ካለው ርቀት፣ ከመለያው ርዝመትና በምልክቶቹ መካከል ያለው ርቀት ውጪም መጠቀም አይቻልም፡፡ መርሁ የወጣው በድርጅቱ ሆኖ ሳለ፣ ድርጅቱ ባሳተማቸው አንዳንድ ብሮሸሮች መርሁ እንደተጣሰና የመለያውን ወጥ አጠቃቀም ድርጅቱ በተምሳሌትነት ማሳየት እንዳለበት ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ከጋዜጠኞች ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ፣ ብዙ ጋዜጠኞች ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ አተኩረው ከሚሠሩ ጋዜጠኞች ድርጅቱ አብሮ ቢሠራ ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ መለያው ፀድቆ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ስላለፈ ነገር ማንሳት ጥቅም ባይኖረውም፣ በመለያው ዝግጅት ወቅት ጋዜጠኞች መሳተፍ ነበረባቸው ብለው የተናገሩ ነበሩ፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀርም፣ ከዚህ በኋላ ድርጅቱ ከጋዜጠኞች ጋር ተቀራርቦ መሥራት አለበት ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ከድር፣ መለያውን በማስተዋወቅ ረገድ ድርጅቱ ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቀው ገልጸዋል፡፡ መለያው በስፋት ካልተዋወቀ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ጥቅም ማግኘት እንደማይቻልም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ለመሸጥ መለያው አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ መለያውን የአገሪቱ መገለጫ ከሆኑ ልዩ ልዩ ነገሮች ጋር በማያያዝ መጠቀም እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ታላቁ ሩጫን ሲሆን፣ ‹‹ላንድ ኦፍ ኦሪጅንስ››ን ከተለያዩ አገላለጾች ጋር በማዋሀድ መጠቀምና አገሪቱን ማስተዋወቅ እንደሚቻል አክለዋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ጐብኚዎችን ለመሳብ የቱሪዝም መለያው ብቻውን ሳይሆን፣ የቱሪዝም ዘርፉ መልማት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡