Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሥጋት ለመውጣት

ከሥጋት ለመውጣት

ቀን:

ካለፈው ዓመት (2008 ዓ.ም.) ኅዳር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰተው ተቃውሞ፣ ለጥቆም በክረምቱ በአማራ ክልል የተደገመው ከ2008 ዓ.ም. በባሰ በ2009 ዓ.ም. ላይ የጎላ ተፅዕኖውን አሳድሯል፡፡ ሲጠረቃቀም ከርሞ አሁን ላይ ለተከሰተው ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና፣ በፖለቲካ አመለካከት አለመወከል እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ይመደባሉ፡፡

መንግሥትም እነዚህንና ሌሎች ችግሮች እንዳሉበት በማመን ‹‹ጥልቅ ተሐድሶ›› እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ሆኖም በተለይ በመስከረም 2009 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በነበሩ ክስተቶች የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ኢንቨስትመንት ተስተጓጉሏል፣ ሰዎች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡

መንግሥትም በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች መስመር ሳይስቱና ለሕዝብ እልቂት ለአገሪቱም ውድቀት ምክንያት ሳይሆኑ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት ያህል ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት አስመልክተው መግለጫ ሲሰጡ፣ የሕዝብ ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሕዝቡንና አገሪቷን ካለመረጋጋት ለማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወሳኝ መሆኑን፣ ከዚህ ጎን ለጎንም የሕዝቡን ጥያቄ የመመለስ ሥራም እንደሚከናወንም አሳውቀዋል፡፡ ሰዎች በሥጋት ቢሸበቡ ምን ያጣሉ? አገራቸው ላይስ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይፈጥራል?

በንግድ ሥራ የተሰማሩት ግለሰብ ትዳር ከመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ ዘመን መለወጫ፣ ከባለቤታቸው ቤተሰቦች፣ መስቀልን ደግሞ ከሳቸው ቤተሰቦች ጋር በመሆን ያከብራሉ፡፡ በትዳር በቆዩባቸው 10 ዓመታት ያፈሯቸውን ልጆች፣ እንዲሁም የቤት ሠራተኛቸውን ይዘው መጓዛቸውም የተለመደ ነበረ፡፡ በ2009 ዓ.ም. ግን ይህንን አላደረጉም፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ቤተሰባቸውን ይዘው ለመውጣት ሠግተው ነበር፡፡  “በመንገድ ምን እንደሚገጥመን አላውቅም፣ ልጆቼን ይዤ ስጓዝ ችግር ቢገጥመኝስ ብዬ ስለሠጋሁ በዓልን ከቤቴ ማሳለፍን መርጬ ነበር፤” ይላሉ፡፡

አምና መስቀልን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያከብሩ፣ የዘንድሮውን ግን ከቤተሰብ በተጨማሪ ለጎረቤቶቻቸው ባህሉን ለማሳየት ይዘው ለመሄድ፣ አባታቸውንም ለማስደሰት አቅደው የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም፡፡ ለዚህም ደግሞ ምክንያቱ በአገሪቱ አንዳንድ ስፍራዎች መረጋጋት ስላልነበረ ችግር ቢገጥመኝስ ከሚል ሥጋት ነው፡፡

በተለይ 2009 ዓ.ም. ከገባ ወዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከታወጀበት ጊዜ ድረስ ሰዎች መሞታቸውና ንብረቶች መውደማቸው፣ ይችን አገር ወዳልታሰበ እልቂት ይመራት ይሆን? የሚል ሥጋት ወስጥ እንደከተታቸው፣ ግራ እንደተጋቡና፣ ነገሮች ግልፅ እንዳልሆነላቸው ይገልፃሉ፡፡  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ ማለት አገሪቷ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አለመኖሩ ስለተረጋገጠና የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ሥጋት ስላለ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣

“ውስጤ በተፈጠረው ሥጋት ራሴን፣ ከጎረቤት፣ ከጓደኛ ወደ ማግለሉ ገብቻለሁ፣  ቤተሰብ በሰላም ወጥቶ ይገባ ይሆን? አገሪቷ ሰላሟ ተረጋግጦ ወደነበረው ሰላማችን እንመለስ ይሆን? የሚለው እንደሚያሳስባቸው ይናገራሉ፡፡

እስካሁን ድረስ በግላቸው የገጠማቸው ችግር ባይኖርም፣ ሊሆን ወይም ሊከሰት ይችላል ብለው በአእምሮዋቸው የሚመላለሰው ሥጋታቸው ግን ኑሮዋቸውን በጭንቀት የተሞላ እንዳደረገውም ያክላሉ፡፡

የኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተው ሞት የባሰው ታዳሚው ከመነሻው በውስጡ ሥጋት ስለነበረውና እያንዳንዷ ድርጊት ውስጡን ታስጨንቀው ስለነበረም ነው ያሉን በአስመጭነት የተሰማሩ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በአገሪቷ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ሁሉንም በየዘርፍ እንደሚያውከው ሁሉ የኤክስፖርት ገበያውን ከጎዳው፣ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለሚገጥማቸው ሥራቸውን መከወን ያቅታቸዋል፡፡ እሳቸውም አንዱ እንደመሆናቸው፣ ለአገሪቱ ሊያበረክቱ የሚችሉትን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከመጉዳቱ ባለፈ ለቤት ኪራይ፣ ለሠራተኞች የሚከፍሉት አይኖራቸውም፡፡ ቤተሰባቸውንም ለማስተዳደር ይቸገራሉ፡፡

አሁን መረጋጋቱ እየመጣ ስለሆነ ከዚህ ቀደም የነበራቸው ሥጋት ቢቀንስም፣ ከውስጣቸው እንዳልወጣና ከዚህ ቀደም የነበራቸው የውስጥ ሰላም እንደተናጋ ይህም የመሥራት ፍላጎታቸውን እንደቀነሰው፣ ከጎረቤቶቻቸውም ሆነ ከጓደኞቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነትም እንዲገደቡ፣ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡

“አገር ሰላም ሲሆን ሁሉ ነገራችን ነፃ ነው፡፡ እንደፈለግን እንናገራለን፣ እንቀልዳለን፡፡ አሁን ግን ይህንን ትቻለሁ፡፡ ይልቁንም ምን ተናገርኩ? ሰው አስከፍቼ ይሆን? ከማን ጋር ላውራ? እያልኩ እሠጋለሁ፤” ይላሉ፡፡

መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጎን ለጎን ያጋጠሙ ችግሮችን በመቅረፍ ሰላም እንዲሰፍንና አገሪቷም ተረጋግታ ሕዝቡ ያለሥጋት እንዲሠራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃሉ፡፡ ሕዝቡም በተረጋጋ መንፈስ ለአገሪቱ ሰላም እንዲተጋም ያክላሉ፡፡

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሥጋት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሰውን ተናግሬ አስቀይሜ ይሆን? የተናገርኩት አካል ያጠቃኝ ይሆን? የገጠመኝ ሕመም ይገድለኝ ይሆን? የሚሉና ከዕለት ዕለት መስተጋብራቸው ጋር ተያይዞ በገጠማቸው ወይም ይገጥመኛል ብለው በሚያስቡት አሉታዊ ጉዳይ ሥጋት ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ አገር ውጥረት ውስጥ ስትገባ ዜጎቿ በሥጋት ይወጠራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ማኅበራዊ፣ አካላዊና አእምሮአዊ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ ኢኮኖሚያዊ እድገትንም ያስተጓጉላል፡፡

በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የሥነልቦና መምህሩ አቶ እስጢፋኖስ አበራ፣ ሥጋት የሰው ልጅ ጠላት ነው ይላሉ፤ ሰው ወደ ስኬት መድረስ እየቻለ ተደናቅፎ ለመቅረትም ሥጋት አንዱ መንስዔ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ተጨባጭ ያልሆኑ ሥጋቶች ማለትም የሆነ ጉዳት ይደርስብናል፣ ወደፊት ያጋጥመናል በማለት መረጃ ሳይኖር አእምሮ የሚፈጥራቸው ሲሆኑ፣ ለዚህ ምንጩ ስለሚባለው ነገር ግልፅ የሆነ መረጃ ማጣት ነው፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ በቂ መረጃ አለመገኘት ግለሰቦች ስለ ጉዳዩ በራሳቸው ተንትነው ችግር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡

ተጨባጭ የምንለው ደግሞ ድርስና ቅርብ፣ ሊመጣ እንደሚችል፣ ወይም መምጣቱ እንደማይቀር አውቀን የምንሠጋው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥጋት ይመጣል ወይም መምጣቱ አይቀርም፡፡ ሲመጣ ግን ምን ይዞ እንደሚመጣ አለመታወቁ ሥጋት፣ ፍርሃትንና የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ይፈጥራል፡፡ ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ግንኙነትን ያበላሻል፡፡  በሥራ አካባቢም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡

አቶ እስጢፋኖስ እንደሚሉት፣ ሥጋት ሰዎች በማኅበራዊ ግንኙነታቸው መደበኛ የሆነውን የቀን ተቀን ሕይወታቸውን በአግባቡ እንዳይመሩ ጫና ያሳድራል፡፡ ከጓደኛ፣ ከቤተሰብና ከጎረቤት ጋር ያሉ መልካም ግንኙነቶችን ያላላል፡፡ የሥራ ተነሳሽነትንም ይቀንሳል፡፡

እንደ አገር ሲታይ ደግሞ፤ በአንድ አገር ላይ አለመረጋጋት ሲኖር ሰዎች ሥጋት ውስጥ የሚገቡት በቂ መረጃ በአግባቡ ስለማያገኙ ነው፡፡ ስለጉዳዩ በራሳቸው ተንትነው ያልሆነ ውሳኔ ላይ የሚደርሱትም ውስጣቸው ያለው ሥጋት በሚፈጥርባቸው ግምታዊ ሁነት ነው፡፡

“በዚህ እንግዲህ ሆነ፣ በዚያ እንዲህ ሆነ” ሲባል ሰዎች ወደ ጥርጣሬና አለመረጋጋት ይገባሉ፡፡ በአገር ደረጃ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲከሰት፣ እንዲሁም ወረርሽኝ ሲገባ ወይም ሊፈጠር ይችላል የሚባለው ነገር ሲነገር፣ ሕዝቡን ማረጋጋትና ከሥጋት ማውጣት የሚቻለው በቂ መረጃ በመስጠት እንደሆነም አቶ እስጢፋኖስ ይገልፃሉ፡፡ በቂ መረጃ የታጠቀ ማኅበረሰብ ከሥጋት ይድናል፣ አንዱ አንዱን እየተጠራጠረ እንዳይኖር መተማመን እንዲሰፍን ፣ ወደ አልሆነ ድምዳሜም እንዳይደርስ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ጭንቀትና ሥጋት ማኅበራዊ ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ተፅዕኖም አለው፡፡ ሰዎች በፈሩና በሠጉ ቁጥር የሚያመነጩት የተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች አሉ፡፡ እነዚህ ጤናን ያውካሉ፡፡ ሥጋት አእምሮአዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድርም ራስን እስከማጥፋት ያደርሳል፡፡

ሥጋትን እንዴት መቅረፍ ይቻላል?

አንድ ማኅበረሰብ በተለያዩ ምክንያቶች ሥጋት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ሥጋትና ፍርሃት ውስጥ የገባን ማኅበረሰብ እንዴት ወደ መተማመን ደረጃ ማምጣት ይቻላል የሚለው ሰፊና ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ አቶ እስጢፋኖስ እንደሚሉት፣ አገሪቷ ከገባችበት አለመረጋጋት ለማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበር እንደተጀመረው ሁሉ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ እርስ በርስ እንዲተማመን (Trust management) መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ሥጋት ውስጥ የገባውን ማኅበረሰብ ከሥጋቱ ለማውጣት ከታች ጀምሮ በሥነልቦናና ተዛማጅነት ባላቸው ባለሙያዎች የታገዘ ውይይት ማድረግና ኅብረተሰቡን ወደመተማመን ደረጃ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

በፖለቲካው በኩል ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ማኅበረሰቡ ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለሱስ በባለሙያ መረዳትና መረጃ ማግኘት አለበት ሲሉም አቶ እስጢፋኖስ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...