የወገብ ሕመም የጀመረው ገና ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ነገር ግን ታክሞ አያውቅም፡፡ ብዙም ግድ የሚሠጠውም አይመስልም፡፡ ‹‹መታመም የጀመርኩት ለማትሪክ ፈተና ዝግጅት ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ እያጠናሁ ሣድር በነበረበት ወቅት ነው›› ሲል ለሕመሙ መንስኤ ነው ብሎ የሚያስበውን ከመናገር ባለፈ ወደ ሕክምና መስጫ ሄዶ ለመታከም ጥረት አድርጎ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡ ጀርባው መዛል፣ ጫንቃው ላይ የመወጠር ስሜት ሲሰማው ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ትከሻውን በማንቀሳቀስ ህመሙን ለማስታገስ ይሞክራል፡፡
ነገር ግን ይህ መፍትሔ ስለማይሆንለት ብዙም ባለበት ሆኖ መቁነጥነጥ ይጀምራል፡፡ እጁን ወደ ጀርባው በመስደድ ራሱን በራሱ ለማሸት ይጥራል፡፡ ሕመሙ በተለይ በቦርሳው ላፕቶፕ ይዞ የተንቀሳቀሰ ቀን ይብስበታል፡፡ ማጅራቱ አካባቢ የማቃጠል ስሜት ይሰማዋል፡፡ ክንዱም እንደ መዛል ይላል፡፡ አልፎ አልፎ ሕመሙ ብዙም ሳይቆይ የሚሻለው ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን በቀላሉ አይታገሠውም፡፡ ‹‹ጠዋት ጠዋት ጀርባዬ በእግር መታሸትና የተያያዙ አጥንቶቼን ማንቃቃት አለበት፡፡ አለዚያ ቀኑን ሙሉ እንደከበደኝ ነው የምውለው›› የሚለው ሠለሞን ፈቃዱ ሕመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የመጣ ቢሆንም ቦታ የሠጠው አይመስልም፤ የመታከም ሐሳብም የለውም፡፡
በሰው ልጆች የአካል ክፍል ውስጥ የሚገኙት 206 አጥንቶች ዋነኛ ሚና ሰዎች ተፈጥሯዊ የሆነውን አካላዊ መዋቅር እንዲይዙ ማድረግ ነው፡፡ አጥንት ከፕሮቲን፣ ቫይታሚን እና እንደ ካልሽየም ካሉ ንጥረ ነገሮች የሚሠራ ሲሆን በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ኮርቲካል በመባል የሚታወቀው ጠንካራው የላይኛው የአጥንት ክፍል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለስላሳና ሥሥ የሆነ ከውስጥ የሚገኘው ትሬብኩላር የተሰኘው ነው፡፡ በውስጡ የተለያዩ ሚና ያላቸው አራት ሴሎችም አሉ፡፡
በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ አስፈላጊ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የዳበሩ ምግቦችን አለመመገብ፣ የጉልበት ሥራዎችን ማብዛት እና ሌሎችም የአጥንትን ጤና ከሚሸረሽሩ ነገሮች መካከል ናቸው፡፡ ከተለያዩ የአጥንት በሽታዎች መካከል ኦስቲኦፕሮሲስ የተሰኘው የአጥንት ሕመም በተለየ መልኩ በዓለም ላይ በስፋት መሰራፋቱን ዓለም አቀፉ ኦስቲኦፕሮሲስ ተቋም ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች አጥንት በሚሳሳበት ወቅት የሚከሰተው ይህ በሽታ በተለይ በሴቶች ላይ በብዛት ይከሰታል፡፡ የአጥንት ፍሬም ጠባብ (ቀጭን) ሲሆን፣ ዕድሜ ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፣ በየትኛውም የማረጫ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች፣ ከቤተሰብ መካከል በአንዱ ተከስቶ የሚያውቅ ሲሆንና በአጥንት ውስጥ የካልሲየም እጥረት ሲኖር ሰዎች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል፡፡
የጀርባ ወይም አጥንት ሕመም የአከርካሪ መጉበጥ፣ የአጥንት በቀላሉ መሠበር እና አጥንት ውስጥ የሚሠማ የሕመም ስሜት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴቶች ከወንዶች በተለየ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ከ50 በላይ ከሆኑ ሦስት ሴቶች አንዷ በበሽታው ትጠቃለች፡፡ ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑ አምስት ወንዶች መካከልም አንደኛው የችግሩ ሠለባ ነው፡፡ ለዚህም ሴች በተፈጥሮ አጥንታቸው ቀጭን መሆኑና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዳቸው ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 200 ሚሊዮን ሴቶች የአጥንት መሳሳት በሽታ ተጠቂ ናቸው፡፡
እንደ ሠለሞን ያሉ የአጥንታቸው ጤንነት ብዙም የማያስጨንቃቸው ሰዎች ባሉበት አገር ውስጥ ደግሞ የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጠርም፡፡ እከሌ አንገት ደፊ ጨዋ ነው በሚባልበት ቀና ቀጥ ብሎ መሄድ ከዓይናውጣነት በሚቆጠርበት፣ አድካሚ የጉልበት ሥራዎች በሰው ጉልበት በሚሰራበት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ባልተለመደበት፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ብርቅ በሆነበት ሁኔታ ችግሩ በምን ያህል መጠን ሊኖር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
በርካቶች ጀርባዬን አመመኝ፣ ማጅራቴን ጨመደደኝ፣ ሰውነቴ ተሳሰረ እያሉ ራሳቸውን ከማስታመም ባለፈ ህመሙ እንደ ሌላ ማንኛውም በሽታ ሕክምና እንደሚያስፈልገው አይረዱም፡፡ በአሁኑ ወቅት እግራቸው እና የዳሌ አጥንታቸው ጋር በሚፈጠር ችግር የሚያነክሱ ሰዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ለመታከምም ሆነ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው፡፡
ለሰዓታት አቀርቅረው ልብስ የሚያጥቡ፣ እንጨት ለቅመው በመሸጥ የሚተዳደሩ እና በመሠል የጉልበት ሥራዎች በተሠማሩ ሴቶች ላይ ደግሞ የአጥንት ችግር የመፈጠር ዕድሉ እጅግ የሠፋ ነው፡፡
በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በአከርካሪ ሕመም ይሰቃያሉ፡፡ በሌላው ዓለም ሕክምናው በበቂ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ ‹‹በአገሪቱ የካዮፕራክቲክ ሕክምና ትምህርት አይሰጥም፡፡ በአገሪቱ ያለነው ሦስት ባለሙያዎች ብቻ ነን›› የሚሉት ካይሮፕራክተሯ ዶ/ር ሠላም አክሊሉ በሽታው የበርካቶች ችግር ቢሆንም እስካሁን ሕክምናው ተደራሽ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
80 በመቶ የሚሆነው የአከርካሪ ሕመም የሚፈጠረው በጡንቻና በጅማት ላይ በሚፈጠር ችግር ሲሆን በአቋቋም፣ በአቀማመጥ፣ በአተኛኝ ችግሮች የሚከሰት ነው፡፡ 20 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለቲቪ፣ ለካንሰር ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶችን በመጠቀም የሚከሰት ነው፡፡ ‹‹በሰውነታችን ከራስ እስከ እግር ጥፍራችን የሚገኙት ነርቮች ሁሉ በአከርካሪ የሚያልፉ ናቸው፡፡ ስለዚህም አከርካሪያችን ሲጎዳ ሌላ የአካል ክፍላችን ሊታመም ይችላል፡፡ ለዚህም ነው የዲስክ መንሸራተት ያጋጠማቸው ሰዎች እግሬን አቃጠለኝ የሚሉት›› በማለት ሕመሙ ተጓዳኝ በሽታዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ስለችግሩ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ለጉዳት ከመዳረጉ በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ ከተጎዳም በኋላ ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት የሚሞክሩ ጥቂቶቸ ናቸው፡፡ አስገዳጅ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር ሕክምና ማድረግ አልተለመደም፡፡ አልፎ አልፎ የሚመርጧቸው የሕክምና ዓይነቶችም ፈውስን በመሥጠት ፋንታ ሌላ መዘዝ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
ወድቆ የመሰበር አደጋ ከሚያጋጥማቸው መካከል አንዳንዶቹ ወደ ባህላዊ ሕክምና የሚሄዱ ሲሆን የሚደረግላቸው ሕክምና በሣይንስ ያልተደገፈ ሊሆን ስለሚችል አልፎ አልፎ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ዶ/ር ሰላም ይናገራሉ፡፡ በአንዲት እናት ላይ ያጋጠመውንም ዶክተሯ ሲገልጹ ‹‹የተሰበረው እጃቸው በቀርከሀ ታስሯል፡፡ ስቃዩ ግን አልቀነሰላቸውም፡፡ እጃቸውን ወደነበረበት እንዲመልስ ታስቦ በእጃቸው ዙሪያ የታሠረው ቀርከሀ የደም ዝውውራቸውን ዘግቶታል፡፡ በስተመጨረሻም የሴትየዋ እጅ ተቆረጠ›› ሲሉ ሁኔታውን አስታውሰዋል፡፡
በከተማው ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ማሳጅ ቤቶች የሚሠሩ ነገር ግን በተገቢው ሙያ ያልሠለጠኑ ሰዎች መኖርም ማሣጅ የዜጎችን ጤንነት አደጋ ላይ እየጣለው እንደሚገኝ ዶ/ር ሰላም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሙያው ትምህርት ያስፈልገዋል፡፡ ነርቮች ከየት ተነስተው የት እንደሚደርሱ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ማሳጅ ቤቶች አሠራር ግን ትምህርት የጎደለው ነው›› ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ከሚያጋጥሟቸው ኬዞች መካከል፣ የጎድን አጥንታቸው የተሰበረ፣ መታሸት የሌለበት ቦታ ታሽተው ለሌላ በሽታ የተጋለጡ፣ እንደ ቲቢና ካንሰር ሕመም ያለባቸው ማሣጅ የተደረጉ በዚህም ለከፋ በሽታ የተጋለጡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹በዚህ ምክንያት መንቀሳቀስ አቅቷቸው በዊልቸር እየተገፉ የመጡ ሴትዮ ሰሞኑን አጋጥመውኝ ነበር›› ብለዋል ዶ/ር ሰላም፡፡
ዶክተር ሠላማዊት አሰፋ በከተማው በሚገኙ እንጨት ለቅመው በሚተዳደሩ ሴቶች ዙሪያ በሚሰራው ባዮ ኢኮኖሚ አፍሪካ የተባለው ድርጅት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ ውስጥ 17,000 ሴቶች እንጨት ለቅመው በመሸጥ ይተዳደራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም ድርጅቱ 400 የሚሆኑትን በተለያዩ ሙያዎች በማሠልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል፡፡
‹‹ቢሯችን ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነው፡፡ ሴቶች እንጨት ለቅመው ሲመለሡ ሁሌም እናያቸዋለን፡፡ በጭነቱ እስከ ጉልበታቸው ጎብጠው ነው የሚራመዱት፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው›› የሚሉት ዶክተር ሠላማዊት እንጨት በመልቀም የሚተዳደሩት ሴቶች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት በመነሳት ወደ እንጦጦ እንደሚያመሩና ያገኙትን እንጨት በጀርባቸው ተሸክመው ቀን አምስት ሠዓት ገደማ እንደሚመለሱ፣ ጭነቱ ለሠዓታት በጀርባቸው እንደሚቆይ ይናገራሉ፡፡ አደገኛ በሆነው በዚህ ሥራ ከሚገጥማቸው መደፈር፣ የመደብደብ አደጋ በተጨማሪ በየቀኑ በጀርባቸው አዝለው ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው የሚጓዙበት ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የጤና ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል፡፡
በድርጅቱ ከታቀፉት ሴቶች መካከል ጥቂቶቹ በሥራው ሦስት ዓመታት ያህል የቆዩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን ከሦስት ዓመታት ከዚያ በላይና እስከ አሥር ዓመት የቆዩ ናቸው፡፡ ለረጅም ጊዜ ጭነት በመሸከማቸውም ከወገባቸው ጎብጠው የቀሩ፣ የተጣመሙ እንዲሁም የሚያነክሱ ብዙ ናቸው፡፡ የደረሰባቸው የጤና ጉዳት በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የማሕፀን መገልበጥ ያጋጠማቸው አሉ፡፡
‹‹ጉዳቱ ለረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ በሕክምና የሚድን አይደለም፡፡ ነገር ግን መሻሻሎች እንዲኖሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ በቂ እረፍት እንዲያገኙ እናደርጋቸዋለን፤ የሕመም ስሜት በሚሰማቸው ጊዜም ማስታገሻ እንዲወስዱ እናደርጋለን›› በማለት ሕመሙ በቆየ መጠን የመዳን ዕድሉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት 80 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን የአጥንት ህመም አለባቸው፡፡ ለዚህም አገሪቱ ለሕክምና በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች፡፡ በሽታው በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች በአራት እጥፍ የሚጨምር ሲሆን ይህም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ለአገሪቱ ተጨማሪ ፈተና ሆኗል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሕክምናውን ተደራሽነት በተመለከተ ዶ/ር ሰላም እንደገለጹት፣ የባለሙያዎች ቁጥር ውስን መሆኑና የሕክምናው ዋጋ ከፍተኛ መሆን ሕክምናው ለሰፊው ሕዝብ ተደራሽ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ለኤምአርአይና ሲቲስካን ምርመራ ብቻ ከ1,500 እስከ 2,500 ብር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ዲስክ መንሸራተት ያሉ ሕክምናዎች ደግሞ እስከ 5,000 ድረስ ይፈጃሉ፡፡ አቋቋምን ማስተካከል፣ ቀጥ ብሎ መቀመጥ፣ አብዝቶ አለመቀመጥ፣ ትምባሆ አለማጨስ፣ በቀን ቢያንስ ለአሥር ደቂቃ ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ከአላስፈላጊ ሥቃይ እና ወጪ ነፃ ያደርጋል፡፡
በዶ/ር ሰላም አስተባባሪነት ባለፈው ሳምንት በሚሊኒየም አዳራሽ የዓለም የስፓይናል ቀን ተከብሮ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ላይ ስለአከርካሪ አጥንት ጤና አጠባበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡ አሥር ለጤና በሚልም የአሥር ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማደረግ ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል፡፡