Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ቀን:

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ዓመት በድርጅቱ የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ አፈጻጸም በዝርዝር መገምገም ጀምሯል፡፡

በኢሕአዴግ የቆየ ባሕል መሠረት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያካሂደው የትግል ሒደት የሚያጋጥሙትን ጉድለቶች ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ በጥልቀት ይገመግማል። ግምገማውን መሠረት በማድረግም ራሱን በራሱ ያርማል። እነሆም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የነበሩና የተተኩ ነባር ታጋዮችን ባካተተ አግባብ ከታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ኢሕአዴግ የኅብረተሰቡን ለውጥ የሚመራ ድርጅት ሲሆን፣ አስተማማኝ የለውጥ መሪ የሚሆነውም ራሱንም እየለወጠ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡ ሁሌም ራሱን እየገመገመ ከነባራዊው ሁኔታ የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ለመያዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አቅጣጫ ወደፊት እየገሰገሰች እንደምትገኝ መላ የአገሪቱ ሕዝቦችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር በገሃድ የመሰከሩት ሃቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በመታየት ላይ የሚገኙት በዋነኛነት ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮች የማያዳግምና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ የሚሰጡ ይሆናል። እስካሁን በተደረጉት ግምገማዎችም የችግሮቹን ዓይነተኛ ባህሪዎችና ዋነኛ መንስዔዎች አስመልክቶ ዝርዝር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በአመራሩ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኋን የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ተችሏል። የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሠረት በመሆኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደወትሮው በላቀ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ፊቱ ላይ በደቀኑት ሥጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንዳለ በትክክል ይገነዘባል። ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተጀመረውን ፈጣን ዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ካሁን በፊት የነበረው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሠረተ አንድነት በቦታው ላይ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ያምናል። ሥራ አስፈጻሚው እስካሁን ባደረገው ግምገማ በአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበት መሆኑን በጥብቅ ተገንዝቧል። በዚህ ላይ ተመሥርቶ በተደረገው ሰፊና ጥልቅ ውይይት በዚህ ረገድ የታዩ ችግሮችን በስፋት መርምሮ የቆየውን የሐሳብና የተግባር አንድነት ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል።

ሥራ አስፈጻሚው በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቱ ኢሕአዴግ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካታ አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሰን ወደ አዘቅቱ መመለስ መጀመራችንን በትክክል አስቀምጧል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባል። አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የድርጅቱ በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚሁ ድክመት ተጋሪ ቢሆንም፣ ሥራ አስፈጻሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መግባባት ላይ ተደርሷል።

የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ በድርጅቱ ውስጥ ያለበት ደረጃ ከፍተኛ ድክመት የሚስተዋልበት መሆኑንና ኅብረተሰባችን ውስጥ ጤናማ ዴሞክራሲያዊ ሕይወት በመፍጠር ረገድ ያደረሰውን ተፅዕኖ ሥራ አስፈጻሚው በሚገባ ይረዳል።

እስካሁን በተደረገው ጥልቅ ግምገማ ከስኬት ጎዳና እያራቁን የሚገኙ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መታጣት፣ የእርስ በርስ መጠራጠር፣ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ዕጦትና የሕዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር ተገቢ ውይይት ተደርጎባቸው የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የሰላም ጥያቄዎችን በሚገባ ለመመለስ በሚያስችሉን አቅጣጫዎች ላይ መግባባት ተደርሷል። ከምንም ነገር በላይ በአገሪቱ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመፍታትና የፌዴራል ሥርዓቱን ከአደጋ ከመታደግ አንፃር የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መንገድ የተጠናከረ ሥራ መሥራት እንዳለበት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የጋራ አቋም ይዟል።

የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ለአገሪቱ ሕዝቦች ጥያቄ በተሟላ መንገድ መመለስና ለፌዴራል ሥርዓቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለዚህ ግብ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን የተሳካ ውይይትና መተጋገል በፅናት ቀጥሎበት በቅርብ ጊዜ በድል የሚጠናቀቅ ይሆናል። ሒደቱንም ለመላው የአገሪቱ ሕዝቦችና ለኢሕአዴግ አባላት በተከታታይ የሚገልጽ መሆኑን ያስገነዝባል።

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...