Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየተማረ ሰው ኃይል እጥረት የሚፈትነው ሆቴልና ቱሪዝም

  የተማረ ሰው ኃይል እጥረት የሚፈትነው ሆቴልና ቱሪዝም

  ቀን:

  የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በተማረ የሰው ኃይል እጥረት እየተፈተነ መሆኑ ተገለፀ፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩ ሠራተኞች መሀከል አብዛኞቹ በልምድ በመታገዝ እንደሚሠሩና በሙያው የሠለጠኑ ሰዎች በብዛት በሥራው አለመሰማራታቸው ዘርፉን እየጎዳው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል አምና በሠራው ጥናት መሠረት፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ሰዎች ወደ 77 በመቶ ያህሉ በሙያው ያልሠለጠኑ ናቸው፡፡ በዘርፉ ከተሰማሩት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት ከሙያው ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ሥልጠና ሳይወስዱ ዘርፉን ተቀላቅለዋል፡፡ 27 በመቶው ደግሞ ዘርፉን ከተቀላቀሉ በኋላ ቀጣሪዎቻቸው መጠነኛ ሥልጠና እንዲወስዱ ያደረጓቸው ናቸው፡፡ ሥልጠናው ግን የጥቂት ቀናት በመሆኑ የጎላ ለውጥ ማምጣት ይችላል ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ስላለው የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የተገለጸው የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል፣ ጥቅምት 4 እና 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ነበር፡፡ ማዕከሉ ከ1961 ዓ.ም. ጀምሮ በዘርፉ ሥልጠና ቢሰጥም፣ ከማዕከሉ ተመርቀው ከሚወጡት ተማሪዎች ምን ያህሉ በዘርፉ ይሰማራሉ የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ብዙ ክፍት የሥራ ቦታ ቢኖርም፣ ቀጣሪዎች በሙያው የሠለጠኑ ሰዎችን ሲቀጥሩ አይስተዋልም፡፡ በተቃራኒው ብዙዎቹ በትውውቅ መቅጠርን ይመርጣሉ፡፡ በውይይቱ ይህ አካሄድ በብዙ አስተያየት ሰጪዎች የተተቸ ሲሆን፣ በዘርፉ ለሠለጠኑ ባለሙያዎች ቦታ መሰጠት እንዳለበትም ተመልክቷል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ኃላፊዎችና የሆቴልና ቱሪዝም ተቋሞች ኃላፊዎች በውይይቱ የተሳተፉ ሲሆን፣ በዘርፉ ያሉ ባለሃብቶች በሙያው የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ካልቀጠሩ፣ ተመራቂዎቹ ሥራ አጥ ከመሆናቸው ባሻገር ሌሎች ግለሰቦች በዘርፉ ለመሠልጠን ያላቸውን ፍላጎት ይቀንሰዋል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝሙ ካለው የተማሩ ባለሙያዎች እጥረት በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ለሙያተኞቹ የሚሰጠው አነስተኛ ግምትም ተግዳሮት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ብዙዎች በዘርፉ ለመሰማራት የጥቂት ጊዜ ልምድ ብቻ በቂ እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ ይህን የተዛባ አመለካከት መቅረፍ ለዘርፉ እድገት የራሱ አስተዋጽኦ አለውም ተብሏል፡ ማዕከሉ ባዘጋጀው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ጥናት ያቀረቡት የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታግሎ ካሳ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሆቴልና ቱሪዝሙ ያሉ ተቋሞች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ የሰው ኃይል ፍላጎትም እየናረ መጥቷል፡፡ በአንፃሩ በዘርፉ ካሉት ሠራተኞች አብዛኞቹ በሙያው ያልሠለጠኑ ወይም የጥቂት ቀናት ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይኼ መቀየር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲሁም የሆቴሎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎቱም በዛው ልክ ከፍ ይላል፡፡ ይህን ፍላጎት ለማርካት ያስፈልጋሉ ካሏቸው መካከል የወደፊቱን የትኩረት አቅጣጫ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ይገኝበታል፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባትም ማዕከሉ የአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃም፣ ለተማረ የሰው ኃይል እጥረትና ሌሎችም የዘርፉ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ሐሳቦች በፍኖተ ካርታው ተካተዋል፡፡ በየጊዜው የሚጨምረውን የዘርፉን የተማረ ሰው ኃይል ፍላጎት በማርካት ረገድ ማዕከሉ አስተምሮ የሚያወጣቸው ባለሙያዎች መፍትሔ እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡ የገበያውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር የአሠልጣኞችን አቅም ማሳደግም ተነስቷል፡፡ በፍኖተ ካርታው የአሠልጣኞችን ብቃት ለማሻሻል የተያዙ እቅዶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ ሲገልፁ፣ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው የአሠልጣኞች ሙያዊ ብቃት ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለማሠልጠን የሚመለመሉ መምህራን በዘርፉ ከተወሰነ ደረጃ ያለፈ ትምህርት ሲያገኙ አይታይም፡፡ ሙያዊ ብቃታቸው ውስን ሲሆን ደግሞ የሠልጣኞች ችሎታን የማሳደጋቸው ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ሊሻሻል የሚችለው ዘርፉን የሚያሳድግ የተማረ የሰው ኃይል ሲኖር ነው፤›› ብለዋል፡፡ መምህራን በአገር ውስጥም ይሁን ውጪ አገር ከፍተኛ ትምህርት የሚያገኙበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ባለሃብቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው፡፡ ‹‹ባለሀብቶች ካልሠለጠኑ በዘርፉ ሙያዊ ሥልጠና ለወሰዱ ሰዎች ቦታ ሊሰጡ አይችሉም፤›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ሌሎችም አስተያየት ሰጪዎችም ዘርፉ በዘፈቀደ የሚገባበት እንዳይሆንና በትምህርት የተደገፈ አካሄድ አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ ሥልጠና ባያገኙም ለዓመታት የሠሩና ልምድ ያካበቱ ሰዎችን ትምህርት በመስጠት ብቃታቸውን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የተናገሩ ግለሰብም ነበሩ፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ሙያዊ ብቃት ጉዳይ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ብዙዎች ዘርፉን ወደኋላ ከሚጎትቱ ችግሮች በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጡት የተማረ የሰው ኃይል እጥረትን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሙያው የሠለጠኑ ሰዎች ሥራ አጥተው ተቀምጠዋል ይባላል፡፡ ተቃርኖው የተፈጠረው በባለድርሻ አካሎች መሃከል ጠንካራ ትስስርና የመረጃ ልውውጥ ባለመኖሩ ነው የሚሉ አካሎች አሉ፡፡ በውይይቱም ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡም ነበሩ፡፡ በፍኖተ ካርታው ከተካተቱ እቅዶች መሃከል ማዕከሉ ከሌሎች ዘርፉ ተቋሞች ጋር ያለውን አጋርነት ማጠናከር ይገኝበታል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ዕቅዱ ከጽሑፍ ባለፈ ምን ያህል በተግባር ይውላል? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ከጠቀሷቸው ተግዳሮቶች አንዱ የዘርፉ ተቋማት ትስስር መላላት ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት በሆቴልና ቱሪዝም በተለያየ ደረጃ ሥልጠና የሚሰጡ የግልና የመንግሥት ተቋሞች ቢኖሩም፤ ማን ምን እየሠራ እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁን ነው፡፡ በተያያዥም በተቋሞችና ቀጣሪዎች መሃከል ያለውን ክፍተት ማንሳት ይቻላል፡፡ ገበያው የሚፈልገው የተማረ ሰው ኃይል ታውቆ፣ ግለሰቦች ሠልጥነው ወደየት መሄድ እንዳለባቸው በግልጽ የሚያመላክት ነገር ያስፈልጋል፡፡ አቶ ታግሎ እንደገለጹት፣ በአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታው ማዕከሉ የድኅረ ምረቃና ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት የመጀመር እቅድ ተካቷል፡፡ በአፍሪካ ካሉ አምስት የሆቴልና ቱሪዝም ተቋሞች አንዱ መሆንም ታስቧል፡፡ ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ እንቅስቃሴዎች ማድረግ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና የተሻለ አስተዳደራዊ መዋቅርም ታቅዷል፡፡ መምህራንን በዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ማሳተፍ፣ ሞዴል ሆቴል መገንባትና የሠልጣኞች የብቃት ምዘና ሥርዓት መዘርጋትም ይጠቀሳሉ፡፡ በውይይቱ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች፣ እቅዶቹ መሬት ላይ ወርደው ካልተተገበሩ ፍኖተ ካርታው ትርጉም እንደማይኖረው አስረግጠዋል፡፡ በተለይም ብቁ አሠልጣኞችን በክልል ከተሞች የማሠማራት ነገር ሊታሰብበት ይገባል ተብሏል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ በዘርፉ ያሉ ተቋሞች በየፊናቸው ሳይሆን በጥምረት እንዲሠሩ አሳስበው፣ ከሙያ ብቃት ጎን ለጎን የሥነ ምግባር ጉዳይ ታሳቢ ይደረግ ብለዋል፡፡ በዘርፉ ካሉ አመራሮች ጀምሮ ሙያተኞችም ሙያዊ ሥነ ምግባር መላበስ ግድ ይላቸዋል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ በብቃት ምዘና ላይ አተኩረው ተናግረዋል፡፡ በሙያው የሠለጠኑ ሰዎች በአግባቡ መመዘን እንዳለባቸውና ካልሠለጠኑ ሰዎች በተሻለ በዘርፉ ሊስተናገዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በሙያው የሠለጠኑ ሰዎች በየጊዜው ችሎታቸውን የሚያሻሽሉበት ትምህርት ማግኘት አለባቸው፡፡ በየጊዜው ዓለም አቀፉን የሆቴልና ቱሪዝም ደረጃ በመከተል የብቃት ማሻሻያ ሥልጠና መስጠትም ያሻል፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች ጋር በቁርኝት የሚሠራ እንደመሆኑ ሠልጣኞች ከሆቴልና ቱሪዝም ጋር ስለሚያያዙ ሙያዎች ማወቅም አለባቸው፡፡ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፍኖተ ካርታው ተቋሙ አቅሙን የሚያሻሽልበትና በአገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ብዙ ሠልጣኞች የሚወጡበት ነው፡፡ ‹‹ብቃት ያለው ሙያተኛና ምርጥ ቴክኖሎጂ ለኢንዱስትሪው ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ ተቋሞች መቀናጀት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ተቋሞች ዘርፉ የሚፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል ለማቅረብ ተገቢ ሥልጠናዎች በመስጠትና የሙያተኞችን ብቃት በመመዘን ረገድ የየድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ለዚህም በየክልሉ የሆቴልና ቱሪዝም ሥልጠና የሚሰጡ ክላስተር ማዕከሎች እንደሚቋቋሙ ተናግረዋል፡፡ በየክልሉ ያለውን የሰው ኃይል ፍላጎት በመለየት በማዕከሎቹ ሥልጠና ይሠጣል፡፡ የሙያ ብቃት ምዘና በማድረግም ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ‹‹ክላስተር ማዕከሎቹ ወደ ተግባር ሲገቡ በዘርፉ የበቃ ሰው ኃይል እናፈራለን፡፡ ባለው ጥናት መሠረት በዘርፉ ከሚሠሩት 23 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡ ሙያዊ ሥልጠና ያገኙት ከአዳዲስ ሠልጣኞች ጎን ለጎን ያለሥልጠና በልምድ የሚሠሩ ግለሰቦችም ተመዝነው በተሻለ ሁኔታ መሥራት ይችላሉ፤›› ይላሉ፡፡ ሙያተኞችን በማሠልጠን ረገድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ጋር በመተባበርና ከኢትዮጵያ ውጭ ያለውን ልምድ ተሞክሮ በመውሰድ እንደሚሠሩ አቶ አሸብር ገልፀዋል፡፡ ከሐዋሳ፣ አክሱምና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የመጀመርያ ዲግሪ ሞዴል ሥርዓተ ትምህርት መቅረጻቸውንና ይህም ከሠልጣኞች ጎን ለጎን የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው አክለዋል፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል በመቅጠር ጉዳይ ባለሃብቶችን ያማከለ ሥልጠና የመስጠትም ዕቅድ አላቸው:: በየክልሉ ላሉ የሆቴሎችና አስጎብኚ ድርጅቶች ባለቤቶች በዘርፉ ስላላቸው ድርሻ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ለሆቴሎች የሚሠራው ደረጃም የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በደረጃ ምደባው አንድ ሆቴል ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይል ብዛት ከግምት ስለሚገባ፣ የሠለጠኑ ግለሰቦችን የመቅጠር ነገር እየተሻሻለ እንደሚሄድ ያምናሉ፡፡ ‹‹በዘርፉ ያሉ ተቋሞች የሰው ኃይል እጥረት አለ ይላሉ፤ እኛ ደግሞ የሠለጠነው ሰው ወደ ኢንዱስትሪው እየገባ አይደለም እንላለን፡፡ ይህንን ለማስታረቅ አዲስ ሥርዓት እየዘረጋን ነው፡፡ ሥርዓቱ ስለ ሠለጠነው የሰው ኃይል መረጃ ለዘርፉ ተቋሞች የሚያሳውቅና ትስስር የሚፈጥር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...