[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጠዋት ቤታቸው መጥቷል]
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንክ?
- አርፍደው ተነሱ፡፡
- ማን በጠዋት ና አለህ?
- እርስዎ ነዎታ፡፡
- ማን እኔ?
- ማታ ወይኗ ናት እንዴ ያዘዘችኝ?
- ወይኗ ማናት ደግሞ?
- ማለቴ ሠርግ ቤት የጠጧት?
- አንተ ግን ከእኔ ጋር በጣም ተደፋፍረናል፡፡
- ኧረ እርስዎ አይደፈሬ ነዎት፡፡
- ምን?
- ለማንኛውም ዛሬ እረፍት ቢሰጡኝ ደስ ይለኛል፡፡
- ምን ተገኘ?
- በጣም የሚገርም ቁርስ በልቼ ቁንጣን ይዞኛል፡፡
- ማለት?
- ክቡር ሚኒስትር ቁርስ ቢሉ ቁርስ መሰለዎት?
- ምን በላህ?
- ቅቤ ፍርፍር፣ ቱና ፍርፍር ቢሉ የቲማቲም ፍርፍር፡፡
- እ. . .
- ቂንጬውም ቀይ ቢሉ ነጭ፡፡
- እሺ፡፡
- እንቁላሉ ራሱ በዓይነት ነው፡፡
- ማለት?
- እንቁላል ቁጭ ቁጭ፣ እንቁላል ብድግ ብድግ፣ እንቁላል በሥጋ ኧረ ምን ቅጡ፡፡
- ሌላስ?
- ኬኩስ ቢሉ ከፓን ኬክ ጀምሮ እስከ ጣፋጭ ኬክ ድረስ፡፡
- እ. . .
- ጁሱም የሚገርም ነበር፡፡
- ማለት?
- ከብዛቱ የተነሳ ያልተጨመቀ የአትክልት ዓይነት ሁሉ አልነበረም፡፡
- እ. . .
- የካሮት ጁስ ራሱ አልቀረም፡፡
- እኔ ጠፋሁ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ ደመወዝህ ስንት ነው?
- ደመወዜማ ከግማሽ ኩንታል ጤፍ እንደማታልፍ ያውቋታል፡፡
- እኔም እኮ ገብቶኛል፡፡
- ምንድን ነው የገባዎት?
- ኪራይ ሰብሳቢ መሆንህ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ኪራይ ሰብሳቢ ብሆን እንኳን በአንዴ እንዴት እንዲህ ዓይነት ቁርስ ልበላ እችላለሁ?
- እኔም እኮ ገርሞኝ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ጥያቄው መሆን ያለበት ሌላ ነው፡፡
- ምንድን ነው መሆን ያለበት?
- የትኛው ኪራይ ሰብሳቢ ቤት ነው የበላኸው? የሚለው ነዋ፡፡
- እና ከእኔ ውጪ ለሌላ ሰው መሥራት ጀምረሃል እንዴ?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ የት ነው ቁርስ የበላኸው?
- እርስዎ ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሴት ልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]
- መሮኛል ዳዲ፡፡
- ምን ችግር አለው ታዲያ?
- እንዴት ችግር የለውም?
- ጣፋጭ ነገር መብላት ነዋ፡፡
- ውስጤን ነው የመረረኝ፡፡
- ምን ሆነሽ?
- መብቴ ተገድቧል፡፡
- ምን ሆንሽ?
- ባለፈው ማምሸት አትችይም አልከኝ፡፡
- ማምሸትም አትችይም፡፡
- ቤት ገብቼ ግን መዝናናት አልቻልኩም፡፡
- ለምን?
- የቲቪ ቻናሉ ተዘግቶብኛል፡፡
- ኢቢሲ ተዘጋ እንዴ?
- ዳዲ ደሞ?
- ምነው?
- ኢቢሲ እንዳይ ነው የምትጠብቀው?
- ምን ችግር አለው?
- አንተን የማወራህ ነው እኮ የሚመስለኝ፡፡
- እንዴት?
- ሁሌ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ፀረ ልማት፣ አፍራሽ ምናምን ነዋ የሚሉት፡፡
- እና ምንድን ነው ማየት የምትፈልጊው?
- ዲኤስቲቪ፡፡
- አንቺ በጣም ሞልቃቃ ነሽ፡፡
- እንዴት?
- የቀድሞውን ሕይወታችንን ረሳሽው እንዴ?
- ማለት?
- ያኔ እኔ ሥልጣን ላይ ሳልወጣ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ቲቪ እንኳን አልነበረንም፡፡
- እሱማ አዎ፡፡
- ሰው ቤት እየሄድሽ አልነበረ እንዴ የልጆች ጊዜ የምታይው?
- ልክ ነው፡፡
- ለዚያውም በብላክ ኤንድ ዋይት ቲቪ?
- ለምንድን ነው ይኼን ያነሳኸው?
- ቀበጥ ነሽ ለማለት ፈልጌ ነዋ፡፡
- ማለት?
- ከቀድሞ ሕይወትሽ ጋር ሲነፃፀር አሁን የምትጠይቂው ጥያቄ የቅብጠት ነው፡፡
- እንዴ ዳዲ ዘመን እኮ ቆሞ አይጠብቅም ይለወጣል፡፡
- ማለት?
- ከቀድሞ ዘመን ጋር አወዳድረህ ይበቃሻል ማለት አትችልማ፡፡
- ለዚህ ነው እኮ ሞልቃቃ ነሽ ያልኩሽ፡፡
- እ. . .
- ቀበጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወንድ ልጃቸውን አስጠሩት]
- አቤት ዳዲ፡፡
- እህትህን እንዳታይ የከለከልካት ቻናል አለ እንዴ?
- አዎን ዳዲ፡፡
- የምን ቻናል ነው?
- የፋሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሴት ልጃቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]
- ቀበጥ ነሽ ብዬሽ ነበር፡፡
- እንዴት ዳዲ?
- የፋሽን ቻናል ተዘግቶብሽ ነው መብቴ ተገፏል የምትይው?
- እህሳ?
- ለመሆኑ የፋሽን ቻናሉ ስለኢትዮጵያ ልብሶች ያሳያል?
- ስለፓሪስ፣ ሚላን፣ ቶኪዮና ኒውዮርክ ነው እንጂ፡፡
- ስሚ እኔ እምቢ ብላቸው ባንቺ መጡብኝ አይደል?
- እነማን ናቸው?
- ኒዮሊብራሎቹ፡፡
- ጀመረህ ደግሞ ዳዲ፡፡
- ምንድን ነው የጀመረኝ?
- ከዚያም በላይ መብቴ ተገፏል፡፡
- እኮ ምን ተደርጎ?
- መኝታ ቤቴ ተበርብሮ በርካታ ዕቃ ጠፍቶብኛል፡፡
- እንዴት ማለት?
- በጣም የምወዳቸው ልብሶች ጠፍተዋል፡፡
- እ. . .
- ባለፈው ለሾፒንግ ፓሪስ ልከኸኝ አልነበር?
- አዎን ልኬሽ ነበር፡፡
- ከዛ የገዛኋቸውና በጣም የምወዳቸው ልብሶች በሙሉ ተወስደውብኛል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወንድ ልጃቸውን በድጋሚ ጠሩት]
- አቤት ዳዲ፡፡
- መኝታ ቤቷን በርብርሃል እንዴ?
- አዎና ዳዲ፡፡
- ለምን?
- ባለፈው ሙሉ ሥልጣን እሷ ላይ ሰጥተኸኛል አይደል እንዴ?
- እንድትከታተላት ነዋ፡፡
- አዎ እኔም ስከታተላት አላስፈላጊ ልብሶቿን በርብሬ ወስጃቸዋለሁ፡፡
- እ. . .
- በቃ ከእኛ ባህል ውጪ የሆኑ ልብሶቿን ወስጃቸዋለሁ፡፡
- እና ምን አደረግከው?
- በቃ ለሴት ጓደኞቿ ሸጥኩላቸው፡፡
- ምን?
- አዎን ዳዲ፡፡
- ይኼማ ወንጀል ነው፡፡
- ምን አደረግኩህ?
- ከፈቀድኩልህ በላይ ነው የሄድከው፡፡
- ምን አጠፋሁ?
- ዘረፍክ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ምን እያደረግክ ነው?
- ፈተና አለብኝ?
- የምን ፈተና?
- እያጠናሁ ነው አልኩሽ፡፡
- እኮ ምንድን ነው የምታጠናው?
- ይኸው ተመልከቺው፡፡
- እንዴ እንዴ በስተርጅና?
- ምን አለበት?
- መንጃ ፈቃድ ልታወጣ ነው?
- አዎን፡፡
- ምን ያደርግልሃል? ሾፌር አለህ አይደል እንዴ?
- ጊዜው ጥሩ ስላልሆነ አይታወቅም፡፡
- እና ራስህ እየነዳህ ልትሄድ?
- ምን ችግር አለው?
- እኔ ግን ፈተናውን የምታልፍ አይመስለኝም፡፡
- እኔ ሁሌ ፈተናዬን እንዳለፍኩ ነው፡፡
- እስቲ እሺ ሳምፕል ፈተናውን ልፈትንህ፡፡
- ፈትኚኝ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ መቶ የሳምፕል ጥያቄ ሠሩ]
- ኪኪኪ. . . .
- ምን ያስገለፍጥሻል?
- ኪኪኪ. . .
- ደፈንኩት እንዴ?
- መድፈን ፓርላማ ቀረ፡፡
- ስንት አገኘሁ?
- አሥራ አምስት፡፡
- ከመቶ?
- አዎን፡፡
- ለነገሩ ችግር የለውም፡፡
- ምን ልታደርግ?
- መንጃ ፈቃዱን አስመጣዋለሁ በቃ፡፡
- እንደዛማ ከሆነ መንጃ ፈቃድ አይሆንም፡፡
- ታዲያ ምን ይሆናል?
- መፍጃ ፈቃድ!