– ከነዳጅ ሽያጭ ከሚሰበበስበው ተጨማሪ እሴት ታክስ ግማሹ ለፈንዱ ተፈቀደ
የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ለ2009 በጀት ዓመት ለመንገድ ጥገና እንዲውል ያቀረበወ ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት ፀደቀ፡፡ ከነዳጅ ሽያጭ ከሚሰበሰበው ተጨማሪ እሴት ታክስ ግማሹ ለመንገድ ፈንድ እንዲገባ ተፈቀደ፡፡ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ለበጀት ዓመቱ ተጠይቆ የነበረው 1.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የመንገድ ፈንድ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ስብሰባ ለበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፈንድ ጥገና የሚውለው በጀት ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲሆን ወስኗል፡፡
ለመንገድ ጥገናው የተፈቀደው ይህ በጀት ጽሕፈት ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ለመንገድ ጥገና እንዲውል የፀደቀ ከፍተኛው በጀት ነው፡፡ ከተጠየቀው በጀት በላይ ሊፈቀድ የቻለው በበጀት ዓመቱ ለጽሕፈት ቤቱ የሚገባ ተጨማሪ ገቢ በመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ለመንገድ ጥገና ተፈቅዶ የነበረው በጀት 1.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 65 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሚወስድ ሲሆን፣ ቀሪውን ከተሞችና የክልል መንገድ ባለሥልጣኖች የሚከፋፈሉት ነው፡፡
የመንገድ ፈንድ ለመንገድ ጥገና የሚያውለውን ገንዘብ የሚያሰባስበው ከነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ፣ ከዓመታዊ ተሽከርካሪዎች ፈቃድ ማሳደሻ ክፍያና የጎረቤት አገር ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከሚከፈለው የኮቴ ክፍያ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእነዚህ የገቢ ምንጮች በተጨማሪ ፈንዱን ለማሳደግ የነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበው የተጨማሪ እሴት ታክስ ወደ ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ እንዲገባ የተጠየቀው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱም ታውቋል፡፡ ጥያቄው የነዳጅ ሽያጭ በሙሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢው ለፈንዱ እንዲገባ ቢሆንም፣ መንግሥት ግማሹን ሊፈቅድ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይኽም የጽሕፈት ቤቱን የገቢ ምንጭ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ በሚመደበው በጀት ከ25 እስከ 30 ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡