በአሳምነው ጎርፉ
በብዙዎች የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት አገሮችን ኢኮኖሚ አሳድጓል፡፡ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚያቸው መሠረት ነው፡፡ በእጅጉ ሰላምና መረጋጋትን ቢፈልግም የፖለቲካ ልዩነትም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ተገዳዳሪነት ሳይገድብ የሰው ልጅን ወዲያ ወዲህ የሚያስብል መስክ ነው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው፡፡
ቱሪዝም ለሚባለው መስክ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (United Nations World Tourism Organization – UNWTO) የሰጠው ትርጉም አለ፡፡ ቱሪዝም ጎብኚ ተብለው በተለዩ ሰዎች የሚፈጸም ክንዋኔ ነው፡፡ ጎብኚ ደግሞ በመደበኝነት ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስቶ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ቆይታ በዓልን ማክበር፣ ጊዜ ማሳለፍና መዝናናትን የሚያዘወትረውን ነው፡፡ እንዲሁም ሥራን፣ ሕክምናን፣ ትምህርትን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ሌላ መዳረሻ የሚጓዝን ሰውም ይመለከታል፡፡
ባሳለፍነው የመስከረም ሁለተኛ ሳምንት ላይ የዓለም ቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ ሲከበር በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውኗል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 157 አገሮችን ያቀፈው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት መሪ ቃሉን ‹‹ቱሪዝም ለሁሉም ዓለም አቀፈ ተደራሽነት!›› በሚል ነው የሰየመው፡፡ በዚሁ በዓል ላይ የተለያዩ ዓውደ ርዕዮችና ዓውደ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡
የታጨቀው ሀብትና ያልተጋገረው ዳቦ
ኢትዮጵያ ዕምቅ የቱሪስት መስህብ ባለቤት ነች፡፡ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ ሳይሆን፣ በእንግዳ ተቀባይ፣ በሰላም ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቧ፣ እንዲሁም ታሪኳና ሃይማኖታዊ ዳራዋ ለቱሪስት ቀዳሚ ተጠቃሽ አፍሪካዊት አገር ነች፡፡ በዩኔስኮ የተመዘገቡ 11 ቅርሶች የያዘች መሆኗም ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡትን ብናይ የአክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥት፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች፣ የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የኮንሶ ሰው ሠራሽ የመሬት አቀማመጥ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ወዘተ. ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በማይጨበጥ ቅርስነት ደግሞ በቅርቡ ያከበርነው የደመራና የመስቀል በዓል፣ የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፌቼ ጨንበላላ ናቸው፡፡
ሌሎች በምዝገባ ሒደት ላይ ያሉ ቅርሶችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሺክ ሁሴን መስጊድ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የጌዲዮ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መልክዓ ምድር፣ የመልካ ቁንጡሬ የአርኪዮሎጂ ሥፍራ፣ ከባህላዊ ቅርሶች ደግሞ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት፣ የትግራይና የአማራ (ሰቆጣ) የአሸራዳ/አሻንዲዬ በዓላት ይገኙበታል፡፡
በዚህ ላይ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛነቷ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ባስቆጠረችው የሉሲ (ድንቅነሽ) አፅም ተረጋግጦላታል፡፡ የአረቢክ ቡና ዝርያ መገኛ የመሆናችን ሚስጥርም ተነግሮ የከረመ ሀቅ ነው፡፡ የዓለም ረጅሙን ወንዝ ዓባይን ጨምሮ ኢትዮጵያን ‹‹የውኃ ጋን›› ያስባሏት በርካታ ወንዞችና ሐይቆች ይገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ የታሪክና የሃይማኖት ቅርሶቻችን ተነግረው የማያልቁ ቱባና ዕምቅ ሀብቶች ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ ሊጎበኝ የሚገባውና የሚያስደምም ሀብት ያላት አገር ግን በቱሪዝም በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ከጎረቤት ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያም አንሳ 17ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ነች፡፡ ከዓለም ደግሞ 121ኛ ተርታ ላይ ነው ያለችው፡፡ ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶችን ስንመለከት ደገሞ በ2004 ዓ.ም. አፍሪካን ከጎበኙ 52.3 ሚሊዮን ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከ597 ሺሕ የማይበልጡት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የአፍሪካ ጎብኚዎች የተገኘው 34 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ያገኘችው ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ራሱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያረጋገጠው መረጃ ያስገነዝባል፡፡
የተለያዩ ጥረቶች ታክለውበት በ2006 ዓ.ም. እስከ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ቢገኝም ዕድገቱ እንደተገመተው ፈጣን መሆን አልቻለም፡፡ በእርግጥ በ2008 ዓ.ም. ክረምት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በተጠቀሰው ዓመት አንድ ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለመሳብ ታቅዶ 900 ሺሕ መምጣታቸውንና 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ቢባል በዚያ አገሪቱ ያላትን ዕምቅ ሀብት ያህል የሚያረካ ጎብኚ አላገኘችም፡፡ በተለይ እየተሻሻለ ከመጣው የኢኮኖሚ ዕድገትና ለማሳደግ እየተሞከረ ካለው የገጽታ ግንባታ አንፃር፣ መዲናችን አዲስ አበባ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከል እንደሆነች ከመምጣቷ አኳያ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ወጣቶች በዘርፉ ማሰማራትም ይቀራል፡፡
በእርግጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሎጆችና የእንግዳ ማረፊያዎች ተገንብተዋል፡፡ አስጎብኚ ድርጅቶችና የተሽከርካሪ አከራዮችና ትራንስፖርተሮችም አሉ፡፡ ያለጥርጥር ለእነዚህ የተፈጠረ ምቹ ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህም በላይ ግን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲዎች እየተመረቁ ‹‹ሥራ አጥ›› ከሚሆኑ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል ከፊሉን እንኳን ዘርፉ መቀበል ይኖርበታል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ እንደተገለጸውም በቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ከመስኩ የሚጠበቀውን ያህል ባለመጠቀሙ፣ የቱሪዝም ቅርሶችና መሠረተ ልማቱን እንደ ራሱ ሀብት እየጠበቀ አይደለም፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯም እንደተናገሩት በትልልቅ ፓርኮች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ጥንታዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ መስህቦች አካባቢ የተጠናከረ የማኅበረሰብ ተኮር የልማት ሥራዎችን ማስፋፋት ካልተቻለ፣ መስህቦችን በቋሚነት መንከባከብም ሆነ ዘርፉን ማሳደግ አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡
በዚህ ረገድ በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸው ባይካድም በላሊበላን፣ በጎንደር (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀዝቀዝ ቢታይም)፣ በአክሱምና የደቡብ ክልል ልዩ ልዩ መስህቦች አቅራቢያ የሚኖሩ ወጣቶች በተደራጀ መንገድ ሥራ አልተፈጠረላቸውም፡፡ በዚህም የአገርን ጥቅም በማስቀደምና በሥነ ምግባር እንግዶችን ማገልገል ላይ የጎላ ችግር እየታየባቸው ነው፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በአግባቡ ባለመመራቱ ለሚያጋጥሙ የማኅበራዊ ቀውስ አደጋዎች መጋለጥም እየታየ ነው፡፡ በተለይ ‹‹Sex Tourism›› ለሚባለው የምዕራባዊያኑ ወረርሽኝ የተጋለጡ ለጋ ወጣቶችና የተሻለ ንቃት የሌላቸው ዜጎችን በጥናት ማግኘት ይቻላል፡፡ ልመናና ሌሎች የውርደት ገጽታዎችን ለመመከት የሚቻልበት ግልጽ አሠራርና ትግበራ አለመታየቱንም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚተቹት፡፡ በድምሩ አገሪቱ ያላትን የታመቀ ሀብትና መስህብ ያህል ቱሪዝሙ ገና በቂ ዳቦ አልተጋገረበትም፡፡
ቱሪዝም መሻሻል ቢያሳይም አልተመነደገም
የአገራችንን የቱሪዝም ሀብት ስፋት በማነፃፀር በቂ ውጤት አልተገኘበትም ብንልም፣ መስኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ለመካድ ያዳግታል፡፡ በቅርቡ ከተቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ጀምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ የሚሠሩት ሥራ ቀስ በቀስ ፍሬ እያመጣ ነው፡፡ አንድ አብነት እንኳን ብንወስድ በ2008 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባከናወነው የቱሪዝም ዲፕሎማሲና የገጽታ ግንባታ ሥራ 104 ዓለም አቀፍ አስጎብኝ ድርጅቶች ኢትዮጵያን የቱሪዝም ፓኬጃቸው ውስጥ ማስገባታቸው ተነግሯል፡፡ ምንም እንኳን የሚጠበቀውን ያህል ጎብኝ መላክ ባይችሉም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ሰው ሠራሽ እሴቶቻችንም ብዙዎችን የመሳብ ዕድላቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በቅርቡ እንደታየው ያለ መደነቃቀፍ ካልገጠመው ‹‹ድህነትን የማሸነፍ ተምሳሌት›› ሆነን በሌላ ገጽታ መፈለጋችንም አይቀርም፡፡ ልክ የጎረቤት ስደተኞችን በመቀበልና የሰላም ማስከበር ዓለም አቀፍ ተልዕኮ ላይ እንዳለን ስም ማለት ነው፡፡
ያም ሆኖ ለቱሪዝም መስኩ መመንዳና እንደ እንቅፋት የሚወስዱ ተግዳሮቶችን መመርመሩ ተገቢነት ይኖረዋል ብዬ በማመን አንድ በአንድ ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ፡፡
- ዘርፉ በፌዴራል፣ በክልሎች ደረጃም ሆነ በከተማ አስተዳደሮች በሙያው በሠለጠኑ፣ ብቃት ባላቸውና በተወዳዳሪነት እየተመራ አለመሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ እዚህ ላይ ምንም እንኳን በጥናት ላይ ሳንመሠረት ያሉትን ኃላፊዎች በጅምላ መተቸት ቢያዳግትም፣ በአብዛኛው በ‹‹ፖለቲካ ታማኝነት›› እና በብሔር ውክልና የተቀመጡ ኃላፊዎች ከምሕንድስና፣ ከስፖርት ከመምህርነት፣ ከግብርና ባለሙያነት፣ ወዘተ. የተሰበሰቡ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በሚጠይቀው ዘርፍ ውስጥ እንደ ሙሴ ‹‹ባህር ሰንጥቆ›› የማለፍ ብቃትን ቢመኙትም ሊያገኙት አይችሉም ባይ ነኝ፡፡
- በተመሳሳይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተመደቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙያተኞች ምንም እንኳን የቋንቋ፣ የሥነ ጽሑፍ የባህል (ፎክሎር) ትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም በሌላው ዓለም ያለው ዓይነት ብቃት እያሳደጉ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በግብፅ በመንግሥት ከተቀጠሩ 1,500 የታሪክ፣ የባህልና የሃይማኖት ሊቅ የሆኑ የቱሪዝም ኤክስፐርቶች ብቻ በአሥር ቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገቢ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሙያተኞች በጥናት ላይ በተመሠረተ ዕውቀት፣ በተተነተነና በዳበረ መረጃ የአገራቸውን ገጽታ ለዓለም ያሠራጫሉ፡፡ ጎብኚዎች የሚስተናገዱበት፣ የሚመሩበትና ሀብት የሚያመነጩበት አሠራር ዘርግተው ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ አስጎብኚዎች ተልዕኮአቸውን እንደወሰዱና የአገራቸውን ገጽታ ከፍ እንዲያደርጉ ያነሳሳሉ፡፡
- የዜጎች አገራዊ ስሜትና ብሔራዊ መግባባት ተጠናክሮ አለመውጣት፡፡ ይህ አባባል ከላይ ከላይ ሲመለከቱት ፖለቲካዊ ይምሰል እንጂ በተለይ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ያለው ፋይዳ የሚናቅ አይደለም፡፡ እዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነው በራሳችን በአገር ውስጥ ያለው የአገር ውስጥ የጉብኝት ባህል ነው፡፡ ስንቶቻችን ከምንኖርበት ወደ ሌላ አካባቢ ሄደን (የተሻለ ገቢ እንኳን ቢኖር) ለመጎብኘትና ለመደመም እንመኛለን፡፡ ከራሳችን መንደር ወጥተን በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ቅርሶችን ማወቅና ማስተዋወቅ ላይስ በምን ደረጃ ላይ እንገኝ ይሆን? የኢትዮጵያን አዲሱን የቱሪዝም መለያ ‹‹ኢትዮጵያ የሁሉ መገኛ ምድር (Ethiopia Land of Origins)›› ከልብ አውቆ ተንትኖ ማብራራት ያልቻለ ምሁርም ይባል ዲፕሎማት ወይም ነጋዴ ወይም ወታደር ሌሎች አገሮች የደረሱበት ለመድረስ ቢመኙ ዋጋ አይኖረውም፡፡
- ከአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ጋር በሚያያዘው ልክ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ማበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የሰላምና ደኅንነትም ጉዳይ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሰላም መታወክ ካሳለፍነው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ክልል (ኮንሶ አካባቢ) በመታየቱ ብቻ አይደለም የሚገለጠው፡፡ ይልቁንም የአገሪቱ መንግሥት የሚከተለው የአገዛዝ ሥርዓት (ዴሞክራሲያዊነትና ሕዝቡን አሳታፊ መሆኑ) የሚያሳድረው በጎ አስተዋጽኦ አለ፡፡ (ለዚያ ለዚያማ ኤርትራን ወይም ሰሜን ኮሪያን ማን ጓጉቶ ሊጎበኝ ይችላል?) ስለዚህ የሰላም መደፍረስ በጦርነት ውስጥ መሆን ወይም በሽብር በመጠቃት ብቻ አይደለም፡፡ ዝርፊያ፣ ውንብድና የጠባብነትና የዘረኝነት ችግር፣ ቅጥ ያጣ ድህነት፣ የኃይል ዕርምጃ አለመኖርንም ይሻል፡፡ ስለዚህ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተሟላ ገጽታ ግንባታ ታጅቦ እንዲመነደግ የሰላምና ደኅንነት ብሎም የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ጉዳይ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ (በነገራችን ላይ በቅርብ ጊዜው አገራዊ ግጭትና ሁከት እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና አንዳንድ አገሮች መግለጫና ማስጠንቀቂያ ማውጣታቸው የመስቀል በዓልን እንኳን የውጭ ቱሪስቶች ጭር እንዲሉበት ሆኗል፡፡)
- የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ አንዱ አማራጭ ለስብሰባ፣ ለሥልጠናም ሆነ ለጉብኝት የሚመጡ የውጭ ሰዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ የውጭ ጎብኚዎች አማካይ የቆይታ ጊዜ ስድስት ቀናት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አምስት ቀናት እንደሆነ የመስኩ ጥናት ያመለክታል፡፡ ይህን ቢያንስ ወደ ሰባትና ስምንት ቀናት ለማድረስ የተቀናጀ የቱሪዝም አገልግሎትና የጉብኝት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ የቱሪስቱን ደኅንነት ለማስጠበቅና የመስኩን ባለሀብቶችም ለማበረታታት መንግሥት የጎላ ሚናውን ሊጫወት ይገባል፡፡ ይህ እንግዲህ ከመሠረተ ልማትና ከማኅበረ ኢኮኖሚው ጉዞ በተደማሪነት የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሰብሳቢዎች የሚያርፉባቸውና የሚጎበኙዋቸው ድንቃ ድንቅ ሀብቶችን ማስተዋወቅ፣ አመቺ ማድረግና ጎብኚዎችን ማማለል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መስክ ነው፡፡ ያም ሆኖ የተነገረለትን ያህል ያልፈካና ተጠቃሚ ያላደረገን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ብቻውን ከመጣጣር ወጥቶ የአገሪቱ ዜጎች በፖለቲካ፣ በብሔር ወይም በሃይማኖት ሳይለያዩ እንዲሠሩበት የሚያደርግ አብዮት ሊቀሰቅስ ይገባዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ለአገሪቷ አጠቃላይ ምርት (GDP) እዚህ ግባ የማይባል አስተዋጽኦ ነው ያበረከተው፡፡ ሌሎች አገሮች ግን በውስን መስህብ ተዓምር እየሠሩባት ነው፡፡ ስለዚህ በዕውቀት፣ በጥናትና በብልጠት የታገዘ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ውስጥ መግባት መቻል አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ቱሪዝማችንን በሚገባ ልንታደገው ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡