Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተስተጓጎሉ ሠርጐች

የተስተጓጎሉ ሠርጐች

ቀን:

የሠርጉ አስተዋዋቂ “ከዚህ በመቀጠል ሙሽሪት የመረጠችውን ሙዚቃ ተጋበዙ፤” አለና ሙሽሪት ሠርገኞች መሀከል ገባች፡፡ ሙሽራዋ የመረጠችው “የሕይወቴ ሕይወት” ወይም “ሙሽራዬ” የተሰኙ የሠርግ ዘፈኖችን አልነበረም፡፡ ዲጄው በቅርቡ የተለቀቀውን የይሁኔ በላይ “ሰከን በል” ዘፈን ከፈተ፡፡ ሙሽራዋ ግጥሙን እየተከተለች ስትዘፍን እጃቸውን በተቃውሞ ምልክት ያጣመሩ ጥቂት ሠርገኞች አጅበዋት ይታያል፡፡ ይህ ሠርግ የተከናወነው ከጥቂት ቀናት በፊት አሜሪካ ውስጥ ሲሆን፣ ከሠርጉ ቪዲዮ ወደ ስምንት ደቂቃ የሚሆነው ተቀንጭቦ ቪዲዮው ኢንተርኔት ላይ ተለቋል፡፡ ዩቲዩብ ላይ 198,249 ተመልካቾች ያገኘ ሲሆን፣ የወቅቱ መነጋገሪያም ሆኗል፡፡

ከቪዲዮው ስር በርካታ አስተያየቶች ሠፍረዋል፡፡ ከአስተየያየት ሰጪዎቹ አብዛኞቹ ሙሽራዋን ሲደግፉ፣ የነቀፉም አሉ፡፡ “በሠርግሽ ቀን የወገንሽ ጥቃት ተሰምቶሽ ይኼን በማድረግሽ እግዚአብሔር ትዳርሽን ይባርከው፣ ሆዴን አባባሽው፡፡ አቦ ዘርሽን እንደ አሽዋ ያብዛልሽ” የሚለውን አስተያየት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሙሽራዋን “አስተዋይ፣ አንበሳ” እያሉ ያሞገሡም ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ፣ ሙሽራዋ የሀገሪቱ ሁኔታ ሳያሳስባት ሠርግ ደግሳ እየተደሰተች ሳለ፣ ዘፈኑን በመዝፈን ያዘነች መምሰሏ ተገቢ አይደለም ሲሉ የተቿትም ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ሆኖ የፈለጉትን አስተያየት መስጠት ቀላል እንደሆነ የገለጹም አሉ፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ለወትሮው ከፖለቲካ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው የሚታመኑ መድረኮች ዛሬ ዛሬ የተቃውሞ ድምፅ ማሰሚያ ሲሆኑ እየታየ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የኦሎምፒክ ስፖርታዊ ውድድሮችንና ከላይ የተጠቀሰውን ሠርግ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኢሬቻ በሚከበርበት መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. የተከሰተውም ይጠቀሳል፡፡ የኢሬቻ በዓል መጀመሪያ በሕዝባዊ ተቃውሞ ወደ ማገባደጃው ደግሞ የብዙዎች ሕይወት በመቀጠፉ ሳይከበር ቀርቷል፡፡ ኢሬቻ ላይ በአባገዳዎች ምርቃት የሚካሄድ ጋብቻ የተባረከ እንደሆነ ስለሚታመን ብዙ ሙሽሮች ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወደ ቢሾፍቱ ያቀናሉ፡፡ ዘንድሮ በሆራ አርሰዲ ሐይቅ የተገኙት ግን በጣት የሚቆጠሩ ሙሽሮች ነበሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሙሽሮቹ በሕዝባዊው ተቃውሞ ወቅት መድረክ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከሕዝቡ በደረሰባቸው ግፊት ግን ከመድረክ ወርደው ወደ ሕዝቡ ተቀላቀለዋል፡፡ ሪፖርተር ሠርጋቸው ሳይከናወን ቀርቶ ቬሏቸውና ሱፋቸውን እንደለበሱ መንገድ ዳር ተቀምጠው የነበሩ ጥንዶችን አስተውሏል፡፡

ዲላ ከተማ ውስጥ ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የታቀደ ሠርግ ላይ ሚዜ የነበረ ግለሰብም፣ ኦሮሚያ ክልል ያለው አለመረጋጋት አስግቶት ከአዲስ አበባ ወደ ዲላ በምን መንገድ እንደሚሄድ ተጨንቆ እንደነበር አጫውቶናል፡፡ የኋላ ኋላ ግን በከተማዋ ባለው አለመረጋጋት ሳቢያ ሠርጉ መሰረዙን ሙሽራው ገለጸለት፡፡ በተመሳሳይም ኢሬቻ በዋለ በሳምንቱ ቢሾፍቱ በሚገኝ አንድ ሪዞርት ለመጋባት አስበው የነበሩ ጥንዶች የሠርጋቸውን ዕለትና ቦታ ለመቀየር መገደዳቸውን የቅርብ ጓደኛቸው ትናገራለች፡፡

ሠርጉን ወደ አዲስ አበባ አዞሩት፡፡ ካለው የጊዜ ጥበት አንፃር ግን አዳራሽና ሌሎችም ነገሮች በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ሙሽሮቹ የሠርጉ ቦታና ቀን መቀየሩን ለሚዜዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው አሳውቀው ሠርጉ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚያደርጉት ሠርግ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኑረው አይኑረው አያውቁም፡፡

ጓደኛቸው እንደምትለው፣ ሁኔታው ከሙሽሮቹ ቤተሰቦችና የሠርጉ ታዳሚዎች በበለጠ የሙሽሮቹን ስሜት ይነካል፡፡ ‹‹ከአገር የሚበልጥ ነገር ስለሌለና ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ስለሆነ ሁሉም ተረድቷቸዋል፤›› ትላለች፡፡ ሙሽሮቹ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄደውን ሠርግ ማታ የማድረግ ዕቅድ ቢኖራቸውም ሰው አይመጣም በሚል ሥጋት ቀን ለማካሄድ ተገደዋል፡፡ አሁንም ሠርጉ ስለመከናወኑ እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት ሁኔታ የለምና ቢያንስ በወሳኝ ኩነቶች ተፈራርመው ለመጋባት አስበዋል፡፡

ሠርግ ከጥንዶች ባሻገር የዘመድ አዝማድና አብሮ አደጎች የደስታ ቀን ነው ይባላልና በሠርግ አስደሳች ነገሮችን ማካተት የተለመደ ነው፡፡ የሠርግ ሽርጉድ ቀደም ብሎ ተጀምሮ በተቻለው መጠን የሠርጉን ቀን ልዩና ደማቅ ለማድረግም ይሞከራል፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ድባብ ሠርጎች ላይ ያጠላ ይመስላል፡፡ በወቅታዊው ሁኔታ በማዘን አልያም አንዳች ነገር ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት ሠርጋቸውን የሠረዙ ሠዎች ገጥመውናል፡፡ ለወደፊት ነገሮች የተሻሉ ይሆናሉ በሚል የሠርጋቸውን ቀን የለወጡም አሉ፡፡

ቤተሠብና ገፋ ሲልም በጎረቤት ትብብር የሚደገሰው ሠርግ ከጊዜው ጋር ተለውጦ፣ ለሠርግ ዝግጅት የተለያዩ ተቋሞች ይቀጠራሉ፡፡ ወቅታዊው ሁኔታ ታዲያ ጥንዶችን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ተቋሞችም እየተፈታተነ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ በዋነኛነት የሠርግ ወቅት የሚባለው ጥርና ሚያዚያ ቢሆኑም፣ ጾም በሌለባቸው ሌሎች ወራትም ሠርግ ይከናወናል፡፡ ከነዚህ ወራት መካከል መስከረምና ጥቅምትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 2009 ዓ.ም. ከገባ ጀምሮ በነበሩት ሳምንታት የተካሄዱ ሠርጎች ቢኖሩም፣ ካለፉት ዓመታት አንጻር ቁጥሩ እንደቀነሰ የሚገልጹ አሉ፡፡

ወቅቱ ጉልህ የሠርግ ወቅት አለመሆኑ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተደማምሮ የሙሽሮችን ቁጥር እንደቀነሰው፣ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የተሰረዙ ሠርጎች እንዳሉ የገለጹልን ነበሩ፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ የተስተዋለው ከመስከረም 2009 ዓ.ም. ወዲህ እንደሆነ ከሠርግ ዝግጅት ጋር የተያያዘ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋሞች ባለቤቶችና ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡ የሠርጎች መቀዝቀዝ የሠርግ ተኮር ቢዝነሶችን ሠንሰለት ተከትሎ ሥራቸውን እንዳዳከመውም ያክላሉ፡፡

በሠርግ ዝግጅት ወቅት መጠነኛ ከሚባሉ ሠርጎች ትልቅ በጀት እስከተመደበላቸው ድረስ፣ ጥንዶቹ ለሠርጋቸው አስፈላጊ ያሏቸውን ተቋሞች ይቀጥራሉ፡፡ እነዚህ ሥራቸው ከሠርግ ጋር የተያያዘ ተቋሞች ወደ 30 ይደርሳሉ፡፡ ፎቶና ቪዲዮ አንሺዎች፣ የመኪና፣ የሠርግ አዳራሽ እንዲሁም የዕቃ አከራዮች፣ ኬክ አቅራቢ፣ የሙሽራና ሚዜ ልብስ መደብር፣ ምግብ፣ መጠጥና መስተንግዶ አቅራቢ፣ የሠርግ መጥሪያና የምስጋና ካርድ አሳታሚዎች፣ ፖስት ካርድ አዘጋጆች፣ ባንዶች፣ ዲጄዎች፣ የወንድና ሴት የውበት ሳሎኖች፣ የሥጦታ ዕቃ አቅራቢዎች፣ የጫጉላ ሽርሽር መዳረሻ አካባቢዎች፣ የዳንስና እስክስታ አሠልጣኞች እንዲሁም አፈራራሚ ተቋማት በሠርጎች መቀዝቀዝ ሊጎዱ ከሚችሉ ተቋሞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የሠርግ ፎቶ በማንሳት ዓመታትን ያስቆጠረው ባለሙያ፣ ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት በተለየ የሠርጉ ድባብ መቀዛቀዙን ተናግሯል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ሠርግ የሚደግሱ ዳያስፖራዎች የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትለው ሠርጋቸውን ለመሰረዝና ላልተወሰነ ጊዜ ለማስተላለፍ መወሰናቸውን፣ ለሠርግ ፎቶ እንዲያነሳቸው ከወራት በፊት ካስመዘገቡ መካከል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተማክረው ሠርግ ለመሰረዝ የወሰኑ ዳያስፖራ ጥንዶችን እንዳገጠሙትም ያክላል፡፡ የሙሽራዋ እናትም የአገሪቱ ሁኔታ ስላሠጋቸው ሳይሠርጉ ይኖሩበት ወደነበረው አገር ተመልሰዋል ይላል፡፡

“ፎቶ አንሺዎችና ሌሎችም በሠርግ ዝግጅት ያሉ ጓደኞቼ እየደወሉልኝ ‹አንተጋ አየሩ እንዴት ነው ብለው ይጠይቁኛል፡፡ የኔ ቢዝነስ እንደነሱ መቀዛቀዙን እነግራቸዋለሁ፤” ይላል፡፡ ጥንዶችን ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የተፈጥሮ (ላንድስኬፕ) ፎቶ ማንሳትም አለመቻሉን ይናገራል፡፡ የላንድስኬፕ ፎቶ በብዛት የሚነሳባቸው አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ፣ ቢሻን ጋሪ ሎጅና ሲምቦ ቢች ሪዞርት ሎጅ በተቃውሞ ሳቢያ መቃጠላቸው ነገሮችን አባብሷቸዋል፡፡ ላንድስኬፕ ፎቶ ከአዲስ አበባ ውጪ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ መንገድ ላይ ባለ ግርግር ምክንያት የተስተጓጎሉ ሙሽሮችም አሉ፡፡

“አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ፎቶ ለማንሳት ሄጄ ከጥንዶቹ ጋር በተመለስኩ ቀን ማግሥት፣ ክለቡ በከፊል መቃጠሉን ሰማሁ፡፡ በጣም ያስደነግጣል፡፡ ማንም ሙሽራ ልቡ ተረጋቶ ይደግሳል ማለት አልችልም፤” ሲል ይገልጻል፡፡ ከደኅንነት ሥጋት በተጨማሪም በአገሪቱ ሁኔታ በማዘን ሠርጋቸውን የተቃውሞ መግለጫ ያደረጉ ሙሽሮች መኖራቸውን መነሻችን ላይ የጠቀስናትን ሙሽራ ምሳሌ አድርጎም ይናገራል፡፡ “በሠርግ የሠርግ ዘፈን ሳይሆን የፖለቲካ ይዘት ያለው ዘፈን የሚከፈተው ሰው ልቡ ስለተነካ ነው፡፡ ለወደፊት የሚሆነው ባይታወቅም፣ ከዓመት በፊት ለፎቶ ቡክ ያደረጉ ሠዎች ከሰረዙ፣ አሁን ላይ ሆኖ ለወደፊት ቡክ የሚያደርግ ላይኖርም ይችላል፤” ይላል፡፡

መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ገጽ የተነበበው ዜና በኦሮሚያ ክልል ከ130 በላይ ኢንቨስትመንቶች መውደማቸውን ያትታል፡፡ ከነዚህ መካከል በምዕራብ አርሲ ጎልጀታ አካባቢ የሚገኘውና በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ኢኮ ሎጅ እንደሆነ የሚነገርለት  ቢሻንጋሪ ሎጅ ነው፡፡ ሎጁ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የሎጁ ባለቤት አቶ ዑመር ባገርሽ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም ሲምቦ ቢች ሪዞርት ሎጅ በከፊል የቃጠሎ አደጋ እንደደረሰበት የሎጁ መሥራች አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችን መዝናኛዎች ለሠርግና ለጫጉላ ሽርሽር ከዚህ በኃላ ወደ ሥፍራዎቹ ለመሄድ ጥንዶች ሊሠጉ ይችላሉ በማለት የገለጸልን ስሜ አይጠቀስ ያለን ሌላ ፎቶ አንሺ ነው፡፡

ፎቶ አንሺው መደበኛ ሥራው የሠርግ ፎቶ ማንሳት ባይሆንም፣ በሠርግ ወቅቶች ከተለያዩ ፎቶና ቪዲዮ ቤቶች ጋር በመስማማት ይሠራል፡፡ እንደገለጸልንም፣ ከሠርግ እንዲሁም ከጫጉላ ሽርሽር ጋር በተያያዘ ቢዝነስ ውስጥ ያሉ ተቋሞች ሥጋት ሸብቧቸዋል፡፡ “ባለፉት ዓመታት መስከረም ውስጥ ባሉ ሳምንታት ቅዳሜና እሑድ ሠርግ፣ ሰኞና ማክሰኞ መልስ፣ እንሾሽላ ስለምሠራ እረፍት አልነበረኝም፡፡ ይህ ዓመት ከገባ ግን ሦስት ሠርግ ብቻ ነው የሠራሁት፤” ይላል፡፡

ለሠርግ ፎቶና ቪዲዮ ወይም ለጫጉላ ሽርሽር ከኢትዮጵያ የሚወጡ ጥንዶች፣ በየቤታቸው የሚጋቡ ሙሽሮችም ለሠርጋቸው የተለያየ አገልግሎት ሰጪዎችን መቅጠራቸው አይቀርምና ሠርግ መቀዝቀዙ ብዙ ቢዝነሶችን ይጎዳል፡፡ አሁን ያለው ድባብ ከወራት በኃላ የሚጋቡ ሙሽሮች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ከመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ ጋር ይስማማል፡፡

“ለፎቶ ከ50,000 ብር ጀምሮና ለቪዲዮ እስከ 80,000 ብር የሚያወጡ አሉ፡፡ ለባንድ ወይም ለዲጄ ከ25,000 ብር ጀምሮ፣ ለሜካፕ እስከ 40,000 ብር የሚከፍሉም አሉ፡፡ የሙሽራ መኪና እንደ ዓይነቱ ለመርሴዲ ወይም ሊሞዚን እስከ 120,000 ብር ይወጣል፡፡ ምግብና መጠጥ፣ መስተንግዶ፣ ዲኮሬሽንና ሌላም አገልግሎት ሰጪዎችም አሉ፡፡ ሠርግ በጣም ከፍተኛ በጀት የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ነውና ሲቀዘቅዝ ተጎጂው ብዙ ነው፤” ሲል ይገልጻል፡፡

የዲቫ ዲኮር ሥራ አስኪያጅ ዲጄ ዳኒ ኮሞሮስ የተለየ ሐሳብ አለው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የሠርግ ቁጥር የቀነሰው በወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ ነው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ “ሠርግ የሚታቀደው ቢያንስ ከስድስት ወር በፊት ነው፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ አስቀድሞ ለማወቅ ስለማይቻል ሰዎች ሠርግ ከማቀድ ወደኋላ አላሉም፡፡ እንዲያውም የሠርግ ቁጥር መቀነስ ከሰዎች ኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው፤” ይላል፡፡ ብዙዎች የሠርግ መጠንን ማሳነስ ቢጀምሩም፣ ዲጄ ወይም ዲኮሬሽን ፈልገው ወደሱ የሚያመሩ ጥንዶች ቁጥር ከመስከረም ይልቅ ጥርና ሚያዚያ ላይ እንደሚጨምርም ይገልጻል፡፡

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የአበባ እርሻዎች እየተቃጠሉ ነው፡፡ ስለዚህም ለዲኮሬሽን የሚያስፈልገውን የተፈጥሮ አበባ ግብዓት ለማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ አሁን የተፈጥሮ አበባ የሚመስሉ ሰው ሠራሽ አበቦችን ከቻይና በማምጣት ለመጠቀም ተገዷል፡፡ ዲጄ ዳኒ ኮሞሮስ እንደሚለው፣ ሁሉም ሰው የአገሪቱን ሁኔታ ስለሚያውቅ ማግኘት በቻለው ግብዓት ዲኮር ሲያደርግ ቅሬታ አልገጠመውም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሠርግ እስከ እኩለ ለሊት የሚቆይበት አጋጣሚ ስላለ ሥጋት እንደሚያድርባቸው የሚናገረው ዲጄው፣ ፍርኃታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ያምናል፡፡ “ሠርግ ማካሄድ ላይ ተፅዕኖ የሚያርግ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ብዙዎች ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለመረዳትም፣ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ሠርግ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ሰምቻለው፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፤” ይላል፡፡  

የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ፣ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአዳራሽ እንዲሁም መኪና ኪራይ መቀዛቀዝ እንደታየ ይናገራሉ፡፡ “ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ተደናግጠው ቡክ ያደረጉትን የሰረዙ አሉ፡፡ መንግሥት አገሪቱን ለማረጋጋት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ስለሆነ ለወደፊት ለውጥ ይኖራል ብለን እናምናለን፤” ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ድርጅታቸው ለዘጠኝ ዓመታት ለሙሽሮች ሊሞዚን በማከራየት ቢዝነስ ውስጥ ነው፡፡ በሆቴላቸው አዳራሽ የሚከራዩ ጥንዶች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አሁን ባለው የመንግሥት አካሄድ የሠርግ ቢዝነስ በሚጧጧፍበት ወቅት የአገሪቱ ሁኔታ እንደሚስተካከል ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን ቪድዮግራፈር፣ “በ2009 ሠርግ ጋብ ብሏል፡፡ አንደኛው ምክንያት ጥንዶች ሳይ ሠርጉ እንዲሁ አብሮ መኖርን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው ነው፡፡ ጉዳዩን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ብቻ ለማያያዝ ግን ያስቸግራል፤”ይላል፡፡ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተፅዕኖ የሚያርግባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ቢገልፅም፣ ዘንድሮ ለመጋባት ያሰቡ ሙሽሮች ባጠቃላይ ሁኔታው ያጠላባቸዋል ብሎ አይገምትም፡፡

በእርግጥ ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት እሱጋ ለቪዲዮግራፊ ቡክ ያረጉትን ቦታ የሠረዙ ጥንዶች እንዳሉ ሳይጠቀስ አላለፈም፡፡ እነዚህ ጥንዶች የከፈሉትን ቀብድ ትተው ሠርጋቸውን ቢሰርዙም፣ በዕቅዳቸው መሠረት የሠረጉም አሉ፡፡ በሠርግ ቢዝነስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሠርግ ውጪ ያሉ ክንውኖችን በማዘጋጀት የሚደረስባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መቀነስ ይችላሉም ይላል፡፡ ብዙዎቹ ተቋሞች በጾም ወቅት ከሠርግ ውጪ ያሉ ሥራዎችን ስለሚሠሩ በነዚህ ሥራዎች መግፋት እንደሚችሉ ያክላል፡፡

ለአሥር ዓመታት በሠርግ ፕሮቶኮልነት የሠራችው ወ/ሮ ወይንሸት ይላቅ እንደምትናገረው፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ መስከረም እንደ ሌሎች የሠርግ ወራት ሙሽሮች እየተበራከቱበት ነው፡፡ “ጥር የአፍሪካ መሪዎች ስብስባ ስለሚኖር ሆቴልና አዳራሽ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ መንገድም ይዘጋጋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ሠርጋቸውን ወደ መስከረም እያዞሩ ነው፡፡ ዘንድሮ መስከረም ላይ ለሚካሄድ ሠርግ ከወራት በፊት ቡክ ካደረጉኝ ሰዎች አብዛኞቹ ሰርዘዋል፤” ትላለች፡፡

ወ/ሮ ወይንሸት የሙሽሮች ሜክአፕ፣ የመኪና ዲኮር፣ ሙዚቃና ሌሎችም የሠርጉን ዕለት ክንውኖች ትከታተላለች፡፡ ሙሽሮችና ሚዜዎቻቸውን ከሠርጉ አስቀድሞ ማዘጋጀትም የሷ ኃላፊነት ነው፡፡ ንግዷ ሙሉ በሙሉ ሠርግ ላይ የተመረኮዘ ከመሆኑ አንፃር፣ ሠርግ መቀነስ እንዳሳሰቡት ትናገራለች፡፡ እንደሷው ቢዝነሳቸው ሠርግ ተኮር የሆኑ ቬሎና ሱፍ አከራዮችና የሙሽራ ሜክአፕ የሚሠሩም ተመሳሳይ ሥጋት አላቸው፡፡

“ከወራት በፊት ቡክ ያደረጉ ሰዎች እየሰረዙ ነው፡፡ አጉል ከምናደርግሽ አስቀድመን መሰረዛችንን እንንገርሽ ብለዋል፡፡ ከውጪ መጥተው የሚጋቡ ሙሽሮችም እኛ ብንመጣ እንኳን ወዳጆቻችን መምጣት ስለማይችሉ ሰርዘናል ያሉኝም አሉ፤” ትላለች  ለወደፊት የሚሆነውን መገመት ባይቻልም ነገሮች ካልተረጋጉ የዘርፉ ህልውና አሳሳቢ መሆኑንም ታክላለች፡፡

ያነጋገርናት የውበት ሳሎን ባለቤት መስከረም ውስጥ ሜካፓቸውን የሠራችላቸው ሙሽሮች ቁጥር ከቀደመው ጊዜያት ባይቀንስም፣ ለወደፊቱ ሥጋት እንዳላት ትናገራለች፡፡ የውበት ሳሎኑ ከሙሽሮች ውጪ ለሌሎች ሰዎችም አገልግሎት መስጠቱ ተስፋ ቢሰጣትም፣ “በአንድ ሠርግ የሚገባው ገቢ እየተንጠባጠበ ከሚመጣ የመደበኛ ቀን ገቢ ጋር አይደራረስም፤” ትላለች፡፡

የኦፒያ የሠርግ ካርድ ባለቤት ቢኒያም ብርሃኑ በበኩሉ፣ በሠርግ ካርዶችና የሠርግ ካርዶች ኅትመት ላይ ለውጥ አለማየቱን ይናገራል፡፡ “ጥንዶች ብዙ ወጪ ያወጡበትን ሠርግ ይሰርዛሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ ሠው የሞተበት ሠው እንኳን ቢሆን ‘ሠርግና ሞት አንድ ነው’ እንደሚባለው ያቀደውን ሠርግ ከማከናወን ወደ ኃላ አይልም፤” ሲል ይገልጻል፡፡

የወቅቱን የሠርጎች ሁኔታ በተመለከተ በአንድ በኩል ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚያያዙ በተቃራኒው ደግሞ ከአገሪቱ ሁኔታ ነጥለው የሚያዩትም አሉ፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በግለሰቦች ሕይወትም ማጥላቱ አይቀርም፡፡ ከአስተያያት ሰጪዎቻችን መካከል ለወደፊት ነገሮች እንደሚሻሻሉ ተስፋ የሚያደርጉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከአሁኑ በበለጠ የእንጀራ ገመዳቸው አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ የሠጉም አሉ፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...