Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስኪ እንጠያየቅ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ በቀደም እየደጋገመ ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› እያለ ይከተለኛል። ብግን ብዬ አጉል ነገር ልለው ስዞር ደግሞ በኋላ ሁከት የተነሳ እንደሆን ብዬ እንደ ሎጥ ሚስት ዞሬ ቀረሁ። ዘንድሮ ለነገሩ በጀርባም በፊትም ሐውልት የሚሆንም ሐውልት የሚሠራለትም ሰው ጠፍቷል። ሲጠፋ አንዴ፣ ሲሞላ አንዴ ነዋ የእኛ ነገር። በኋላ ‹‹አንተ ሰውዬ ከእኔ ምን አለህ?›› ስለው እጁን ዘርግቶ ያራግበው ጀመር። ልመና መሆኑ ነዋ። ወይ ‹ጥቅምትና አጥንት?› ደግሞ ብለው ብለው በአባባሉ መጡ ብዬ ከማንጠግቦሽ ጋር ሳወራ፣ ‹‹ገና የቤተሰብህን ታሪክ አጥንተው በአያትህ ሙት ዓመት ይመጣሉ፤›› አለችኝ። አሰብኩት። ቁጭ ብዬ ሳስበው የአያቴ አሟሟት ትዝ አለኝ። የአሟሟቷን ሁኔታ እያሰብኩ የሚታየኝ የእኔ አኗኗር ነው።

አንድ ቀን ማልዳ ተነስታ እንደለመደችው አፏን ሳታሟሽ ቤተ ክርስቲያን ተሳልማ ስትመጣ መንገድ ላይ፣ ‹‹እእ. . . ወጋኝ፤›› አለች በቃ በዚያው ቀረች። ምን የለ ምን የለ። ጣር የለ ሕመም የለ። የባሻዬ ልጅ የአያቴን አሟሟት ባስታወሰ ቁጥር፣ ‹‹እግዜር አንዳንዴ ልክ እኛ ቴሌቪዥን ሲሰለቸን በሪሞት ኮንትሮል ድርግም እንደምናደርገው በቅጽበት እልም ሲያደርግህ ምንኛ መታደል ነው?›› እያለ የአሟሟቷ ጉዳይ ያስጨንቀዋል። እኔ አሁን ይኼን ሁሉ የማወራው ለምንድነው? በየየቀኑ መሞት ሰልችቶኝ ነዋ። ቆይ ግን እኔ ብቻ ነኝ ወይስ እናንተም አላችሁበት? ድሮ ድሮ ናፍቆትና ብርድ ይመስሉኝ ነበር በቁም የሚቀብሩት። ያኔ እንዳሁኑ ኑሮ ጣራ አልነካማ። ዛሬ ይኼውላችሁ በቀኝ በግራ ወጪ እያንዣበብኝ እኖራለሁ። ጭራሽ አሁንማ (መቼም እኔ ላይ የማይበረታ የለም) ‹በመድኃኔዓለም› ማለቱን ትቶ ‹በጥቅምት አንድ አጥንት› ብሎ እንደለመነኝ ዓይነት በአባባልና በምሳሌ የሚፈልጡኝም መተዋል። እኔስ ያለማውጣት አዋጅ ናፈቀኝ ጎበዝ!

ዛሬ መቼም ካነሳሁት አይቀር ስለገንዘብና አያያዙ ብዙ እንድንጫወት ፈልጌያለሁ። እኛና ገንዘብ እንዲሁ አሁን አሁን አይጥና ድመት ከመሆናችን በፊት፣ እንዲያው ማን ይሙት የሠራነው ግፍ አይቆጠርም። በአጭሩ ‹ጢባ ጢቤ ተጫወትንበት› በተባለው ብንይዘው ይቀላል። ሌላ ገላጭ የለውም። ዛሬ እሱ በተራው ይኼው ያንቀረቅበናል። እኛም አያያዙን አንችልበት እሱም ማንጠባጠቡን አብዝቶት አዳሜ አግኝቶ በማጣት ተውኔት ሰማይ ነክቶ ሲፈርጥ የአልፎ ሂያጅ መሳቂያ ሆኗል። ከአወዳደቅ መማር ለእኛ አልተፈጠረምና የሳቅንም በዓመቱ ሊሳቅብን ተራ እንይዛለን። ኧረ አጀብ ነው። ታዲያ ምን ሆነ መሰላችሁ? ከዚህ በፊት አጫውቻችሁ እንደሆነ አላውቅም ከአባት ሆላንድ አገር ወደ እናት ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የመጡ ደቾች ጋር ተወዳጅቻለሁ።

ጠላት ደስ አይበለውና ይኼው እኔም ወጉ ደርሶኝ ቀበሌውና ክፍለ ከተማውን በማያውቁት ሥፍራ ፎቶ እየተነሳሁ ፌስቡክ ላይ ለመልቅቅ ተዘጋጅቻለሁ። መቼም ፌስቡክ አንደኛውን ከተዘጋ የሚጎዳው እኔን ነው ዘንድሮ ስል አንድ ፎቶ አንሺ ወዳጄ ሰምቶኝ ‹‹አይዞህ ግፋ ቢል ተነስተህ ፊልሙን ትልክልኛለህ፣ እኔ ፎቶ ቤት ውስጥ በትልቁ አጥቤ እሰቅለዋለሁ። ወዳጆችህ መደሰታቸውን፣ ጠላቶችህ መቃጠላቸውን እንደሆነ አያቆሙም. . .›› ብሎ ተስፋ ሲሰጠኝ እረጋጋለሁ። እና ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ እነዚህ ደች እንግዶቼ አንድ ቀን ላይ ታች ሲያለፉኝ ውለው እስኪ ጥሩ ምግብ ቤት ውሰደን የአገራችሁን ምግብ እንቅመስ ይሉኛል። እኔ ደግሞ እንደ ሌላው ፈረንጅ መስለውኝ አብዛኛው ጎብኝዎች ሲያደንቃቸው ወደምሰማቸው ቤቶች አንዱን መርጨ መውሰድ። ተበላ፣ ተጠጣ፣ ተሳቀ (ወሬን ቋንቋና ኔትወርክ አይገድቡትም እንዲሉ) ኋላ ሒሳብ ሲባል እኔ ባልሰማ ዘና ብዬ ተቀምጫለሁ። አቤት አቀማመጤን ብታዩት!

አራቱም ደንበኞቼ ሥሌት ላይ ናቸው። እኔ የዓመት ጥርቅም አድርጌ በልቼ አልሰማቸው።  በኋላ አንዱ ነካ አደረገኝና ሞባይሉን ሰጠኝ። ምንድነው? ብዬ ሳይ ሦስት ቁጥሮች አሉ። 300፣ 80 እና 10 ይታዮኛል። አንደኛው እንዳልገባኝ አውቆ፣ ‹‹ሦስት መቶ የበላኸው ምግብ፣ 80 የመጠጥህ፣ 10 ቲፕ የምንሰጠው ነው። ሁላችንም አሥር አሥር እንስጥ ተባብልን ስለተስማማን ነው፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ወዲያውኑ የባለሁት መላወስ ጀመረ።  መቼም ማስመሰል አንደኞች ነንና እኔ ወንድማችሁ አላሰፈርኳችሁም፡፡ እንዴ ይችማ ምን አላት ምናምን ብዬ ቀባጥሬ ማንጠግቦሽ ዘይት ግዛበት ብላ የሰጠችኝን የአደራ ገንዘብ አውጥቼ ክፍል። ምናለበት በዚህ ቢያልቅ? ደግሞ ሁለቱ ዋና ዋና ኢንቨስተሮች በሳንቲም ተጣሉልኛ። ይኼን ያህል ያወጣሁት እኔ ነኝ፣ ይኼ የእኔ መልስ ነው እየተባባሉ ሲካረሩ ሳይ እነዚህ ሰዎች የእውነት እዚህ አገር ሥራ ሊሠሩ ነው የመጡት ወይስ ለቀልድ ነው? እያልኩ ፈዝዤ ቀረሁ።

እንግዲህ እንደነገሩኝ ከሆነ ሦስቱም የሚተዋወቁት ከ‹ሃይስኩል› ጀምሮ ነው። አብረው ተምረው አብረው የጎለመሱ ወዳጆች ናቸው። እንዲያውም አንደኛው ያገባት የዚያን የወዳጁን እህት ነው። ገርሞኝ ገርሞኝ ኋላ ቀን አልፎ እኔም ከኃፍረቴ አገግሜ ለባሻዬ ልጅ ስነግረው፣ ‹‹እንግዲህ እርስ በርስ ቲፕ በሰጡት ሳንቲም ድርሻ ከተጣሉ፣ ካልሸጎጣችሁ አታልፉም የተባሉ ቀን ምን ሊውጣቸው ነው?›› ሲለኝ ነበር። እሱ ደግሞ በማይሆን ሰዓት የማይሆን ነገር ማውራት ይወዳል። ‹‹እኔ እኮ የጠቅኩህ ዕውን የእኛ ባህል ነው ጥሩ ወይስ የነሱ? ዕውን የእኛ የገንዘብ አያያዝ በዚህ በተወደደ ኑሮ ያዛልቀናል ትላለህ?›› ስለው፣ ‹‹የፊት የፊቱን ኑር። ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል፣ ነገ ስለራሱ ይጨነቃል፤›› አይአለኝ መሰላችሁ? ራሱ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ! ከተማረው ትምህርት እንዲህ የባሻዬ ሃይማኖታዊ አስትምህሮ አዕምሮው ውስጥ ሰርፆ ይግባ? ሳይንስና ሃይማኖት አጓጉል አንድ ሊሆኑ ሲሞክሩ ሳይ ስለሚገርመኝ እኮ ነው!

እዚያም እዚህም ተፍ ተፍ ብዬ ደግሞ የልማዴን ላደርስ ባሻዬ ዘንዳ ጎራ ማለቴ አይቀርም። እሳቸው ደግሞ ሰሞኑን ጭንቅ ላይ ናቸው። ከገጠር አንዲት ዘመዳቸው ያለፈቃዷ ተደፍራ ፌስቱላ ልትታከም መጥታ እሳቸው ቤት አርፋለች። በዚያ ላይ እርጉዝ ናት አሉ። ባሻዬ ተጨንቀው ተጠበው ሊሞቱ ነው። በቀደም ‹‹እባክህ አንበርብር አንድ አምስት ሺሕ ብር አበድረኝማ። የዚህች ልጅ ነገር ትቼ የማልተወው ነው። ቶሎ አሳክሜ አገሯ ልስደዳት እንጂ?›› ሲሉኝ አንጀቴ ተንቦጫቡጮ ጨመር አድርጌ ሰጠኋቸው። ማሳከማቸውና የሚያስፈልጋትን መድኃኒት መግዛታቸው ሳያንስ ደግሞ፣ እርጉዝ ናት ምን ያምራት ይሆን አሁን እያሉ ሦስት አራት ዓይነት ወጥ ያሠሩላታል። እኔ ይኼን እያየሁ መፈላሰፍ ያምረኛል። የዚያን ሕገወጥ ሰው ሸክም ባሻዬ በምን ዕዳቸው ይሸከማሉ? ሕይወት ግን የምትጫወተው ቁማር ምን ዓይነት ነው? እያልኩ ሳወጣ ሳወርድ እውላለሁ። እኔ መስመር ስስት ኢሉአባቦር የሚኖር ምስኪን አባወራ ለምን ጎብጦ ይኖራል? የአንዱ የጥጋብ ግሳት ለምድነው ለሌላው እንደ ጦር ነጋሪት ድምፅ ሆኖ የሚሰማው? እያልኩ ጭልጥ እላለሁ። ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ሆኖ ነገሩ አንዱን ሳነሳው አንዱን ስጥለው ያለሁበትን ረስቼ፣ ሥራ ፈትቼ የማታ ራቴ ለቁርስ ተሸጋግሮ አገኘዋለሁ። ታዲያ ባሻዬን ጠጋ ብዬ ‹‹ለመሆኑ የደፈራት ማን እንደሆነ ይታወቃል? ነግራዎታለች? ሕግ ፊት ቀርቧል?›› ስላቸው፣ ‹‹ምን ብዬ እጠይቃታለሁ ደግሞ ይኼንን?›› ካሉ በኋላ፣ ዝም በል ብለው አፍ አፌን እያሉ በይ በይ አይዞሽ ሲሏት ይውላሉ። እም ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል?!

በሉ እንሰነባበት። ማለቱን እንላለን እንጂ መኖሩን ከተውን ቆይተናል። ንግግር የበዛው ለምን መሰላችሁ ታዲያ? እውነቴን ነው። ሰሞኑን ታዲያ እኔና የባሻዬ ልጅ በጊዜ ተገናኝተን በጊዜ ተጎንጭተን በጊዜ ወደ ቤታችን መሯሯጥ ይዘናል። የባሻዬ ልጅ  በችኮላ ወጥተን በችኮላ ስንገባ እያየ፣ ‹‹አወይ ኃላፊነትን መዘንጋት?›› ይላል። ‹‹የምን ኃላፊነት?›› ስለው፣ ‹‹አታይም እንዴ እያንዳንዳችን የገዛ ኃላፊነታችንን እየረሳን በሰላማችንና በህልውናችን ላይ የመጣውን ችግር። ሳይቃጠል በቅጠሉን ረስተን ይኼው እንደ ፖንፔ ሕዝብ ገሞራው ከፈነዳ በኋላ የሞት የሽረት ጨዋታ ስንጫወት. . .›› ሲለኝ ግራ ገብቶኝ ዝም አልኩ። ‹‹እኔ እምልህ?›› አልኩት ቀስ ብዬ። ‹‹እ. . . . ?›› አለኝ። ‹‹ፖንፔ ማንናት?›› ስለው ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹አይ አንበርብር አረጀህ እኮ. . .›› ብሎ ይስቅብኛል። እሱ የዓለምን ታሪክ ጠጥቶታልና እኔ ማስታወስ ሲያቅተኝ አረጀህ እባላለሁ። ‹‹ወይ ዘንድሮ?›› አለ ዘፋኙ። እናላችሁ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በትንሹ ያጫወተኝ የፖንፔ ታሪክ መሰጠኝ። የፖንፔ ሕዝብ በአሁኒቷ ጣሊያን ግዛት የዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመት በፊት ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው። ማሲቩየስ የሚባል ታላቅ ተተራ አጠገቡ አለ። ይኼ ተራራ ያልበረደ የእሳት ውኃ ውስጡ እያራገበ ከቀን ቀን ቅራኔው ሲጨምር የፖንፔ ሕዝብ ይበላ ይጠጣ ይዘፍን ይዳራ ነበር። አንድ ቀን አገር አማን ብሎ ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሲያከናውን ያ እሳተ ጎሞራ ወጥቶ ፈሰሰባቸው። የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ከሆነ ዛሬ በቁፋሮ የተገኘችው የዛኔዋ እፁብ ድንቅ ፖንፔ ዛሬ የቱሪስት መዳረሻ በመሆን፣ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመት በአምስት መቶ ዲግሪሴንቲ ግራድ የፈላ እሳት ያጠባቸውን ዜጎች አስከሬን እንዳለ እያስጎበኘች ትኖራለች። ዛሬም ግና የሰው ልጅ ከታሪክ የተማረ አይመስል። በእሳት የሚጫወተው በዝቷል። ቆይ ግን እስከ መቼ በእሳት እንጫወታለን? እስኪ እንጠያየቅ! ተጠያየቁ እስኪ። መልካም ሰንበት!

   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት