Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሃይማኖት ተቋማቱ ሰላምን የመፈለግ ጥረት የት ላይ ነው?

የሃይማኖት ተቋማቱ ሰላምን የመፈለግ ጥረት የት ላይ ነው?

ቀን:

አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ መንበረ ሥልጣን ሲመጡ ‹‹ሥዩመ እግዚአብሔር›› ተብለው ከፖለቲካ በተጨማሪ ሃይማኖትን የሥልጣን የኃይል መሠረታቸው አድርገው ነበር፡፡ ይህም አሠርታትን ተቀባይነት አግኝተው እንዲዘልቁ አስችሏል፡፡ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ፍልስፍና ይመራ የነበረው የደርግ ሥርዓት ደግሞ ለሃይማኖት ዕውቅናና ቦታ አልሰጠም ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በመጨረሻዎቹ የደርግ ዘመናት በተደረጉ ለውጦች የየትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች የፓርቲ አባል እንዲሆኑ በሮች ክፍት ሆነው ነበር፡፡ በመጨረሻዎቹ የደርግ ቀናትም እልቂት እንዳይፈጠር መረጋጋት እንዲሰፍን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የካቶሊክና መካነ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም ድምፃቸውን አሰምተው እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ደግሞ የመንግሥትና የሃይማኖት የተለያዩ መሆን የሃይማኖት ነፃነትም በግልጽ በሕገ መንግሥቱ ታወጀ፡፡

መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ እንደማይገባ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11(3) በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፣ መንግሥትና የእምነት ተቋማትን በአንድ ላይ የሚመለከቱ፣ በአንድ ላይ እንዲሠሩም የግድ የሚሉ ጉዳዮች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያም የሚስተዋል እውነታ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ብቻም ሳይሆኑ በሥነ ምግባር፣ በትምህርት፣ አገርን አንድ በማድረግና በእርቅ፣ ድምፅ ለሌላቸው፣ ለተጨቆኑ ደካሞች ድምፅ በመሆን ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ የሃይማኖት መሪዎችም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖት ተቋማት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከቤተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን በመቃወምና የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ድምፅ በመሆን፣ ከዚያም የአገሪቱ እውነት አፈላላጊና እርቅ ኮሚሽን ሊቀ መንበር የነበሩት ዴዝሞን ቱትን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ማሳደር ከቻሉ ሃይማኖታዊ መሪዎች መካከል መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጣልያን ወረራ ወቅት ትልቅ ተሰሚነት የነበራቸውን አቡነ ጴጥሮስ ሕዝቡን እንዲገዝቱለት ጣልያን መጠየቁ የሃይማኖት መሪው የነበራቸውን ከፍተኛ ተፅዕኖ ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ ከዚህ አንፃር በተለይም በወቅታዊው የአገሪቱ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ምን ዓይነት ሚና እየተጫወቱ ነው?

ወቅታዊው ሁኔታና የሃይማኖት ተቋማት እንቅስቃሴ

የማንነትና ከፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ የወሰን ጥያቄዎች በሒደት ወደ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ በመሸጋገር ላይ መሆናቸው በተለያየ መንገድ ተንፀባርቋል፡፡ ጥያቄዎቹ በተለያየ መንገድ እየተነሱ አድማዎችን፣ ተቃውሞዎችን፣ የሰው ሕይወት መጥፋትን የግለሰብና የመሠረተ ልማት ውድመትን አስከትለዋል፡፡ እንደ ኢሬቻ ያሉ መንፈሳዊና ባህላዊ በዓላትም የተቃውሞ ድምፅ ማሰሚያ ሆነው አልፈዋል፡፡

አሁን ያለው ወቅታዊ ቀውስ መነሻ ማንነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ማንነትን ከሚገነቡት አንዱ ደግሞ የጋራ ልማድና ሃይማኖት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ሃይማኖት አንዱ የማንነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል፡፡ አሁን በአገሪቱ የተስፋፋው ተቃውሞ ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣ ከሆነ ሃይማኖትን መሠረት ወዳደረገ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡

ወቅታዊውን ሁኔታ ተከትሎ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት ያደረገ አስተምሮት ይሰበክ ዘንድ ማንዋል ተዘጋጅቶ ለሃይማኖት ተቋማት መሠራጨቱን፣ የአሠልጣኞች ሥልጠናም መካሄዱን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡ ከማስተማር በዘለለ የውይይት ባህል እንዲዳብር፣ መንግሥት አግባብ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎችን በአፋጣኝና ትርጉም ባለው መልኩ እንዲመልስ፣ በግጭቱ የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጉባኤው ማድረጉን የሚናገሩት መጋቢ ዘሪሁን፣ በወልቃይት ጉዳይ ነገሮች ከመስመር ከመውጣታቸው በፊት ጥያቄ ያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ለማደራደር መሞከሩን በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

ምንም እንኳ መንግሥት በሃይማኖት የሃይማኖት ተቋማትም በመንግሥት አሠራር ጣልቃ አይገቡም ቢባልም፣ በጋራ የሚሠሩባቸው አጀንዳዎች መኖራቸውን የሚያስረግጡት ጠቅላይ ጸሐፊው ‹‹መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡና በፍጥነት መመለስ እንዳለበት ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ ሐሳባችንን ተቀብለውናል፡፡ ሌሎች ጥያቄዎችንም አቅርበን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፡፡ መንግሥት በሐሳብ ከሚመሳሰሉት ጋር ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ከሚለዩት ጋርም የመነጋገር ልምድ እንዲኖረው እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡

ጉባኤው በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡ የጉባኤው መሥራቾች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን 97 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ እንደሚወክሉ ጠቅላይ ጸሐፊው ይገልጻሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ ማሳወቅና ማስገንዘብን በማስቀደም ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እያስተማረች ቢሆንም፣ ጥያቄ የሚያነሱና የመንግሥት አካላትን በራሷ ዐውድ በራሷ ስልት በማደራደርና በመሸምገልም ላይ መሆኗን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አባ ኃይለማርያም መለሰ ይገልጻሉ፡፡ የሕዝቦች ደኅንነት የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አባ ኃይለማርያም በቀጣይም ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ከፌዴራል ደረጃ እስከ ዞን ድረስ በመውረድ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ ዕርምጃዎችን የመውሰድ አካሄድ እንደሚኖር ይጠቁማሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በአገር አቀፍ ደረጃ መረጋጋት እንዲፈጠርና ሰላም እንዲሰፍን ከምትሠራው ሥራ ባሻገር በየቦታው ያሉ አህጉረ ስብከት፣ አባቶች የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሼህ ኡመር ኢማምም፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግጭቶች እንዳይፈጠሩ የማደራደር ሥራ እንደሚሠሩ በየዓመቱም ከ500 እስከ 600 ለሚሆኑ ስለሰላም የአሠልጣኞች ሥልጠና እንደሚሰጡ፣ ይህ ደግሞ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሚያደርጉት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ አባ ሐጐስ ሀይሽ በወቅታዊው የአገሪቱ ችግር ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው እንዲፀልዩ ከማድረግ በዘለለ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ተጎጂ ለሆኑ የተለያዩ ዕርዳታዎችን ማድረጋቸውን፣ መንግሥትም በሕዝብ ለተነሱ ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡

ሰላምና ልማት የመንግሥት አጀንዳ የመሆኑን ያህል የሃይማኖት ተቋማትም አጀንዳ እንደሆነ የሚገልጹት የሃይማኖት መሪዎችም ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ የባሕር ዳር የምዕራብ ጎጃም፣ የአዊና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም መንግሥት የሕዝብን ጩኸት ሰምቶ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ የተቃውሞ ድምፁ መሰማቱን እንደሚቀጥል፣ መንግሥትም ለኃይል ሳይሆን ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለማስፈን መጣር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ቄስ ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲናም በአሜሪካ አትላንታ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ሕዝቡ እንደ ጣዖት ከሆነበት የብሔር ፖለቲካ መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱና የሃይማኖት መሪዎቹ ድምፅ ይሰማል?

የሃይማኖት ተቋማቱና መሪዎቹ ጥረት ውጤታማነት

የሃይማኖት ተቋማት በገለልተኝነት፣ ምሳሌ መሆን በሚችል አመራር ለምድራዊ ኃያላን ሳይንበረከኩ የሰላም ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ መሪዎች ገለልተኝነትና ነፃነት በብዙ መልኩ ጥያቄ ውስጥ ሲወድቅ ይስተዋላል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ተከትሎ የሃይማኖት ተቋማት በተለያየ መንገድ ድምፃቸውን ቢያሰሙም የሚያደምጣቸው እንደማይኖር ስለዚህም ይህ ነው የሚባል አዎንታዊ ተፅዕኖ ያመጣሉ ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ የሚያስቀምጡት ምክንያት ደግሞ የሃይማኖት ተቋማቱ ተዓማኒነትና ተቀባይነትን ካጡ መቆየታቸውን ነው፡፡ ተመሳሳይ አስተያየታቸውን የሰጡን የሕግ ባለሙያም የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን የማሳመን አቅማቸውን ከተነጠቁ እንደቆየ፤ ተከታዮቻቸውም የኔ ወኪል ናቸው ብሎ ይቀበላቸዋል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ያላቸው አቅም እንጂ ኃይል አይደለም፡፡ ተቀባይነትና ተሰሚነትን ያጡት ደግሞ እንደ ሙስና ባሉ ለዓመታት በተስተዋሉ ተደራራቢ ክፍተቶች ነው፡፡

የአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ በምሳሌነት ቢነሳ ደግሞ ግጭቶች እዚህም እዚያም እንደተከሰቱ ለወራት ዘግይተው መንግሥትን ተከትለው መግለጫ መስጠታቸው ጥያቄ ያስነሳል ይላሉ አስተያየት ሰጪው፡፡ ‹‹ግጭት ይቁም ውጥረት ይርገብ›› ለማለት ለወራት መዘግየት ምን ይባላል? በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ መቼ ድምፃቸውን አስተላለፉ የሚለውንና የመልዕክታቸውን ይዘት በመመልከት፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ክፍተት እንዳለባቸው፣ ተቀባይነታቸውም እንደተሸረሸረ በመጠቆም የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ መሪዎቹ የወቅታዊው ችግር መፍትሔ አካል መሆን እንደማይችሉ ይደመድማሉ፡፡ ስለዚህም ለቀጣይ ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ቅቡልነታቸው መጀመሪያ መሥራት አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹የሃይማኖት መሪዎች ስለተናገሩ ነገሮች በአንድ ጊዜ ቀጥ ይላሉ አይባልም፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ሰፊ ነው፡፡ ቢሆንም ሕዝቡ ሰምቶናል ብለን እናምናለን፤›› የሚሉት መጋቢ ዘሪሁን፣ የሃይማኖት ተቋማት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡ ቢሆንም ግን ገለልተኝነት ላይ በተለያየ መልኩ ጥያቄ እንደሚነሳና የሃይማኖት ተቋማት ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ መውደቅ ተግዳሮት እየሆነባቸውም እንዳለ አልሸሸጉም፡፡

መጋቢ ዘሪሁን እንደሚሉት፣ የሃይማኖት ተቋማት ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳው የሃይማኖት መሪዎች (በግል) ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ስለሚነሳና ተቋማቱ ገለልተኛ እንዳልሆኑ አድርጎ የመሣል ፍላጎት ያላቸው አካላት በመኖራቸውም ጭምር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ተፅዕኖ እንደሌለባት የሚናገሩት ዶ/ር አባ ኃይለማርያምም በመርህ ደረጃም ቢሆን የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት በላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የአንድ ወቅት ተሰሚነት አይደለም ያላት፡፡ ለዘመናት ትደመጥ ነበር፡፡ አሁንም እየደመጠች ነው፤ ነገም መደመጧን ትቀጥላለች፡፡ ለአገርም ብዙ ነገር ያበረከተች ናትና፤›› ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ደግሞ የአገሪቱ ሕዝብ ሃይማኖተኛ በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በወቅታዊው ሁኔታም ተመሳሳይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንደሚችሉ ፅኑ እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በምሕረት አስቻለውና በሻሂዳ ሁሴን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...