Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የድሮ ሰው ‘ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት’ የማለው አባባል ነበረው፡፡ ይህ አባባል ተራ ሳይሆን በእርግጥም ቁምነገር ያለው ነው፡፡ እኔ በልጅነቴ ያደግኩበት ሠፈር ውስጥ ዕድራችንን ይመሩ የነበሩ ሰዎች ምሥጉን መምህራን፣ በነገር አዋቂነታቸው የተመሠከረላቸው አዛውንቶችና ማኅበረሰቡ የሚያከብራቸው ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለብዙ ዓመታት እያገለገሉ ‘ደከመን፣ እንረፍ፣ ሌላ ደግሞ ገብቶ ይሥራ፣ ወዘተ’ ብለው ስማፀኑ እንኳ፣ የዕድር አባላቱ ‘ያለናንተ አይሆንልንም’ በማለት ሳይወዱ በግድ እንዲያገለግሉ ይጫኑዋቸዋል፡፡ እነሱም በይሉኝታም ሆነ በተሰጣቸው ከበሬታና ሙገሳ በመፅናናት አገልግሎታቸውን በክብር ያበረክቱ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በበርካታ ሥፍራዎች በገቢር እንደታየ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በአንድ ወቅት ዕድሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አጥፊዎችን ይቀጡ ነበር፡፡ ማኅበረሰቡን መበጥበጥ ወይም በግለሰቦች ላይ ጉዳት ማድረስ ከዕድር እስከመወገድ የሚያደርስ ከፍተኛ ቅጣት ስለነበር፣ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ችለዋል፡፡ በደርግ ዘመን ቀበሌ የሚባለው መዋቅር መጥቶ የዕድሮች ሚና እየቀነሰ ቢመጣም፣ በዚህች አገር ውስጥ የተጫወቱት ትልቅ ሚና መቼም ቢሆን አይዘነጋም፡፡ ይህንን በተመለከተ ለረጂም ጊዜ ከማውቀው ከሥራ ጓደኛዬ ጋር ስንወያይ፣ በቀበሌም ሆነ ወረዳ በሚባሉ መዋቅሮች ውስጥ ልክ እንደ ድሮ ዕድሮች ለምን በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች እንዲያገለግሉ አይደረግም? የሚል ሐሳብ ተነሳ፡፡ በትምህርት፣ በዕድሜ፣ በሥነ ምግባርና በመሳሰሉት በየአካባቢያችን የተመሠገኑ ሰዎች ቢፈለጉ እኮ የሕዝብ ቅሬታ በአግባቡ ተሰምቶ ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጥና ለግጭት የሚጋብዙ አላስፈላጊ ድርጊቶች እንደሚቆሙ ጓደኛዬ አንደ ነጥብ አነሳ፡፡

እሱ እንደሚለው፣ በስመ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም በአስመሳይነት የአካባቢያችንን መዋቅር ሥልጣን እየተቆጣጠሩ የሕዝብ መሬት ከሚሸጡ፣ የመንግሥት ቤቶችን ለግለሰቦች ከሚያስተላልፉ፣ የአገልግሎት አሰጣጦችን ከሚያበላሹና ሕዝብና መንግሥትን ቅራኔ ውስጥ ከሚከቱ ራስ ወዳዶች ይልቅ፣ በሕዝብ አመኔታና ከበሬታ ያፈሩ ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎችን መፈለግ የተሻለ ነው፡፡ ጓደኛዬ በአንድ ወቅት በኤችአይቪ ላይ የሚሠራ ግብረ ሠናይ ድርጅት ተቀጥሮ ሲያገለግል፣ መሥሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ የተወሰኑ ሠራተኞች በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ ከኃላፊዎቹ ጋር ዝምድና ወይም የጥቅም ግንኙነት የነበራቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በኤችአይቪ ለተጎዱ ሰዎች የሚመጡ ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶች ይመዘበሩ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ያሳዘናቸው ሁለት ምሥጉን ሰዎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ መሥሪያ ቤቱን በመታደግ መዝባሪዎች ለፍር ድ እንዲቀርቡ አደረጉ፡፡ በዚህ የተነሳ መሥሪያ ቤቱ ከሌብነት ተላቆ የተሰጠውን ኃላፊነት በሥርዓት ተወጣ ነው ያለኝ፡፡

እነዚህ የጠቀሳቸው ሁለት ግለሰቦች አንደኛው በውትድርና ያገለገሉ ጠንካራ መኮንን ሲሆኑ፣ ሌላኛው ደግሞ በቀድሞው የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን በኃላፊነት ደረጃ አገልግሎታቸውን ያበረከቱ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለት ብርቱ ዜጎች ሌሎች ጨዋ ሠራተኞችን ይዘው መሥሪያ ቤቱን ከመታደጋቸውም በላይ፣ በኤችአይቪ የተጎዱ ወገኖቻችን በአግባቡ እንዲረዱና እንዲያገግሙ ረድተዋል፡፡ ሁለቱ ብርቱ ሰዎች ከዘራፊዎቹና ከሌሎች የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ጋር ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ከፍተኛ ፈተና የገጠማቸው ከመሆኑም በላይ ፣ ከማስፈራሪያና ዛቻ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሠሩ ተደርገዋል፡፡ ሀቅን በመያዛቸውና ለወገኖቻቸው በነበራቸው ከፍተኛ ፍቅር መስዋዕትነት ከፍለው ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ከመላው ሠራተኞችና ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ምሥጋናና ዕውቅና ተችሮአቸዋል ሲለኝ በመገረም ነበር የሰማሁት፡፡

እኔ በበኩሌ አሁንም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ከራሳቸው ይልቅ ለአገራቸው የሚያስቡ ዜጎችን ችላ ባይሉ እመርጣለሁ፡፡ በእርግጥ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ወስዶ ሠርቶ የማሠራት ታሪካዊ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ በዕድሜም ሆነ በልምድ የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ወገኖቻችን ቢያግዙትና አጓጉል ድርጊት ውስጥ እንዳይገባ ቢያደርጉት እመርጣለሁ፡፡ በዕድሜ የበሰሉና በሥራ ልምድም የካበቱ ዜጎችን ወደ ጎን በማለት ያተረፍነው ኪሳራ ነው፡፡ የነበረውን እያፈረሱ እንደ አዲስ ከመገንባት ይልቅ፣ በነበረው መሠረት ላይ የተሻለ ነገር መሥራት ይጠቅማል፡፡ ለአገር ስንትና ስንት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ጭንቅላቶች ሥራ ፈተው በሌብነት የተካኑ ዘራፊዎች እንዲፈነጩ መፍቀድ ተገቢ አይደለም፡፡

በቅርቡ እጄ የገባ አንድ አገር ውስጥ በሚታተም የቢዝነስ መጽሔት (በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተም) አንድ ታዋቂ ሰው ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ እሳቸው በሥራቸው በጣም በርካታ የቢዝነስ ድርጅቶችን እንደሚመሩና አንዱን በማዕድን ዘርፍ የተሰማራ ድርጅት ለምን ለባለሙያ እንደማይለቁ ይጠየቃሉ፡፡ እሳቸውም ኮራ ብለው በአገሪቱ በዘርፉ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች የሉም ብለው ይናገራሉ፡፡ እኔ በጣም ነው የገረመኝ፡፡ አገሪቱ በማዕድናት ዘርፍ ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች አስተምራ የካበተ ልምድ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች እያሉዋት እንዴት እንዲህ ይባላል? በበርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች በሙያቸው አንቱ የተባሉ ዕውቅ ምሁራን ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ብቁ ባለሙያዎች የሉም ብሎ በአደባባይ መናገር ያሳፍራል፡፡ እኔ በበኩሌ ኅፍረት ነው የተሰማኝ፡፡ ጓደኛዬ ግን፣ ‹‹ይኼ ከኃፍረትም በላይ ነው፤›› አለኝ፡፡ እሱ እንደሚለው ሁላችንም በተለያዩ መስኮች የተሰማራን ዜጎችም ሆንን ራሱ መንግሥት አባባሉን እንደ ውርደት ነው ማየት ያለብን ያለው፡፡ አዎ! ሳታጣ እንዳጣች ያደረግናትን አገር ባናዋርድ ይሻላል፡፡ ለምን ቢባል በበርካታ መስኮች አገርን የከፍታው ማማ ላይ ማድረስ የሚችሉ ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ወገኖች አሉንና፡፡ የሉም ብሎ ከመኮፈስ ይልቅ ወጣ ብሎ መፈለግ ያስከብራል፡፡

(መስፍን ዋቅጅራ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...