Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈልፈያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈልፈያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ

ቀን:

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ተቃውሞ ምክንያት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካታ ንብረት ወድሟል፡፡ በዚህም አገሪቱና ሕዝቦቿ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን የገለጸው መንግሥት፣ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፡፡ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር መመርያዎች እንደሚወጡ፣ ይህንን ለማስፈጸም ኮማንድ ፖስት መቋቋሙንም አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ኮማንድ ፖስት የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንም ሥራ ጀምሯል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲተገበር፣ ኮማንድ ፖስቱ የፀጥታ ሁኔታን ይቆጣጠራል፣ ለተቋማት መሠረተ ልማቶች ጥበቃ ያደርጋል እንዲሁም ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ይቆጣጠራል ሲል መንግሥት ነግሮናል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት እንደሚወሰዱ ከተጠቀሱት ዕርምጃዎች ውስጥ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ በማደፍረስ ተግባር ላይ ተሳትፏል ብሎ የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያጣራ ወይም እያስተማረ ለመልቀቅ፣ አዋጁ ተፈጻሚ መሆን እስካለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ይችላል ተብሏል፡፡

ወንጀል የተፈጸመባቸውን ወይም ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውም ቤት፣ ቦታና ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፡፡ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ ዕቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት የማቅረብ፣ አጣርቶ ለባለመብቱ የመመለስ ሚናዎቹም ከተደነገጉት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ መንግሥት እነዚህን ዕርምጃዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ አለበት እላለሁ፡፡

መንግሥት ‹‹የፍትሕ አካላትን ጨምሮ በኪራይ ሰብሳቢነት እየተዘፈቁ ተቸግሬያለሁ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት አለ፣ ሙስናም ይታያል፡፡ እነዚህ የሕዝብ ብሶት መፈልፈያ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩን እቀርፋለሁ፤›› ብሏል፡፡ መንቀሳቀስም ጀምሯል፡፡ ሆኖም ችግሮቹን ገና አላስታገሰም፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲተገበር፣ በእውነትም ይሁን በሐሰት በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው፣ በብርበራ ስም ንብረታቸው እንዳይዘረፍ፣ በየሰፈሩ በተፈጠሩ ቁርሾዎች ምክንያት በሚደረጉ ጥቆማዎች ንፁኃን ሰዎች የቂም መወጫ እንዳይሆኑ መንግሥት አብዝቶ መጠንቀቅ አለበት፡፡

ይህን ለማለት ያነሳሳኝ በደርግ ዘመን በየቤቱ ብርበራ በሚደረግበት ወቅት ተከስተው የነበሩ ዘረፋዎችና ብዙዎችን ለእልቂት የዳረጉ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱ በማሰብ ነው፡፡

የአገርን ሰላም ለማስከበር፣ ሕዝብንም ከውጥረት ለማውጣት ሲባል ቤት መበርበር መፍትሔ ከሆነ፣ መንግሥት በግልጽና በፍትኃዊነት ሥራውን ሊያከናውን ይገባዋል፡፡ ቤት ለመበርበር ወደ ግለሰቦች ቤት የሚላኩ የደኅንነት አካላት ሊይዙ ከሚገባቸው የተለየ መለያ በተጨማሪ መንግሥት የሚልከው ሰነድ በሁለት ኮፒ ሊዘጋጅ፣ በቤት ብርበራው ወቅት ከግለሰቡ የተገኙ የደኅንነት ሥጋት ናቸው የተባሉ ቁሶች ሁሉ የሚመዘገቡበት፣ በኋላም በፈታሹ አካልና በተፈታሹ በጋራ ተፈርመው አንዱ ሰነድ ለተፈታሹ የሚሰጥበት ሥርዓት ሊዘጋጅ ይገባል፡፡

ይህ ሲሆን ሰዎችን ከአላስፈላጊ ዘረፋ መታደግ ይቻላል፡፡ ከየቤቱ የሚወሰዱ ዕቃዎች በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች የማይወረሱ ከሆነ፣ ለባለንብረቱ በአግባቡ ለመመለስ ያስችላል፡፡ እንዲህ ሲደረግም ተዓማኒነትን ያሰፍናል፡፡

በርባሪ አካላት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተጠርጣሪዎች ቤት ገብተው መበርበር ይችላሉ ተብሏል፡፡ እዚህ ላይ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ቢኖር፣ በየቤቱ ለፍተሻ የሚገባው ሁሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መብት የተሰጠው አካል ነው ወይ? የሚለውን የሚያስገነዝብ  ግልጽ መግለጫ ለሕዝቡ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ በመጣ ቁጥር ግለሰቦች በራቸውን መክፈት አለባቸው? ወይስ በርባሪዎች በማንም አካል በሐሰት ተመሳስሎ የማይሠራ (ፎርጅ የማይደረግ)፣ ተመሳሳይና ሕዝቡ በግልጽ እንዲያውቀው የሚደረግ መለያ ይሰጣቸዋል ወይ? የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ጠቋሚዎችን በተመለከተም መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ መውሰድ አለበት፡፡ መንግሥት በራሱ የደኅንነት አካላት ከሚደርስበት ጉዳይ ወይም ተጠርጣሪ በተጨማሪ፣ በግለሰቦች የሚደረግ ጥቆማ የየግል ቂም መወጣጫ እንዳይሆን፣ በጠቋሚና በተጠቋሚ መካከል ቀድሞ ቁርሾ ስለመኖር አለመኖሩ የሚያጣራበትን አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት በጥልቅ ታድሼ ሕዝቤን አገለግላለሁ ብሎ የገባውን ቃል የሚንድ አሠራር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ሀብት ያላቸው ሰዎች ለሙስና እንዲጋለጡ፣ ሕዝቡም በፍርኃት እንዲርድ፣ በፍርኃቱ ሳቢያ መንግሥትን ራሱን ፈተና ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ሊረዳው ይገባል፡፡

የአዋጁ መንፈስ ሕዝቡ ከገባበት ከፍተኛ ውጥረት ለማላቀቅና የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እስከሆነ ድረስ፣ ለዚህ ሥራ የሚሰማሩ በሙሉ ሕዝቡን መጠቀሚያ እንዳያደርጉት ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ቆሜያለሁ ካለም፣ በደርግ ዘመን ብዙኃኑ ንብረቱን፣ ገንዘቡን፣ ሕይወቱን በብርበራ ሰበብ ማጣቱን በማስታወስ (ይህ ለቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ ታጋዮች በግልጽ ይገባቸዋል) በጣሙን ይጠንቀቅ እላለሁ፡፡

(ፍስሐ ገብረኪዳን፤ ከአዲስ አበባ)

* * *

የንግድ ባንክ ማሽኖች ገንዘባችንን

‹‹ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ!›› የሚለው የባንኩ ማስታወቂያ መልዕክት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በአዕምሯችን ይከስታል፡፡ ባንኩ ከዘመኑ ጋር በመራመድ የተለያዩ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ በማዘጋጀት ተደራሽነቱን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ከሚሰጣቸው የባንኪንግ አገልግሎቶች ውስጥም የኤቲኤም ባንኪንግ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ አገልግሎቱን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ የሚውሉ የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣት ባንኩ ይበልጥ ለደንበኞች ተደራሽ ይሆን ዘንድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱለት ይገኛሉ፡፡

በቅርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች ባንኮች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በአንድ ኤቲኤም ካርድ አማካይነት ከሌሎች ኤቲኤም ማሽኖች ገንዘብ ውጭ ማድረግ ያስችል ዘንድ አዲስ አሠራር ተዘርግቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሽኖች ከበፊትም ያለባቸው ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ በአዲሱ አሠራርም ደንበኞች ይበልጥ እየተስተጓጐሉ ይገኛሉ፡፡

 ለዚህ ማስረጃ ይሆነን ዘንድ ሰሞኑን የሆነውን በምሳሌ ላስረዳ፡፡ አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤም ተጠቃሚ አገልግሎት ለማግኘት በአቅራቢያ ወደሚገኘው የአዋሽ ባንክ ኤቲኤም ማሽን ይሄዳል፡፡ ካርዱን ካስገባ በኋላም የሚፈልገውን የገንዘብ መጠን ይጠይቃል፡፡ ማሽኑ ትዕዛዙን ከተቀበለ በኋላ የተጠየቀውን የገንዘብ መጠን መስጠት ሲገባው ምንም ሳይሰጥ አገልግሎቱን ያቋርጣል፡፡ ይህ ሁኔታ በርካታ ደንበኞችን ለችግር እየዳረገ ይገኛል፡፡ ማሽኑ የተጠየቀውን ብር አለመስጠቱ ሳያንስ ደንበኛው የጠየቀው ገንዘብ ከተቀማጭ ሒሳቡ ላይ ተቀናሽ እንደተደረገ የሚገለጽ የአጭር መልዕክት ይልካል፡፡ ይህ ደንበኛ እዚሁ ማሽን ላይ ሁለቴ ሞክሮ ባይሳካለትም ባንኩ ግን ሁለት ጊዜ የጠየቀው ገንዘብ ተቀናሽ መደረጉን የሚገልጽ መልዕክት ልኮለታል፡፡

ይሁንና ደንበኛው በአዋሽ ባንክ ኤቲኤም ማሽን አገልግሎት ማግኘት ስላልቻለ ወደ ሌላ ኤቲኤም ማሽን መሄድ ግድ ስለሆነበት አቅራቢያው ከሚገኝ የዳሸን ባንክ በማቅናት ለመጠቀም ተገዷል፡፡ ሆኖም የዳሸን ባንክ ማሽንም ሆነ ከዚያው በመቀጠል የጎበኘው የወጋገን ባንክ የኤቲኤም የሰጡት ምላሽ ከአዋሽ ባንኩ ማሽን ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡

 በዚህ ሒደት የኤቲኤም ማሽኖች ትዕዛዝ ከተቀበሉ በኋላ በምላሹ ገንዘብ የማይሰጡ ከሆነና ደንበኛው ምላሽ አጥቶ ከሄደ በኋላ ምላሽ የሚሰጡበት ሁኔታ ካለ፣ ተጠያቂው ማን ሊሆን ይችላል? እነዚህ ማሽኖች በሚፈጥሩት የደንበኞች መስተጓጐልስ ባንኩ ኃላፊነቱን ይወስዳል?

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህን አዲስ አሠራር ሳይጀምር በፊት በኤቲኤም ማሽኖች ላይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች አልፎ አልፎ ይከሰቱ ነበር፡፡ ባንኩም እነዚህን ችግሮች በ24 ሰዓት ውስጥ ለመፍታት ሲሞክር ይስተዋል ነበር፡፡ አሁን ከሌሎች ባንኮች ጋር በጀመረው የኤቲኤም ባንኪንግ አገልግሎት ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ካጋጠመ ችግሩን ለማስተካከል ቢያንስ አሥራ አምስት ቀን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ባንኩ በ951 ነፃ የስልክ መስመር ለሚደውሉ ደንበኞች ያሳውቃል፡፡ ባንኩ ይህን ይበል እንጂ ብዙ ወረፋ አለ በሚል ሰበብ ችግሩ ሳይስተካከል፣ ያለ አግባብ ከደንበኞች ተቀማጭ ሒሳብ ላይ የተቀነሰ ገንዘብ ሳይመለስ ለወራት ሊቆይ ይችላል፡፡

ስለሆነም በሚፈጠረው ችግር ምክንያት ደንበኛው የሚፈልገውን ገንዘብ ከባንኩ ማሽኖች በማውጣት በተገቢው ጊዜና ቦታ እንዳይጠቀም ከመገደዱም በላይ ለበርካታ መጉላላቶች እየተዳረገ ይገኛል፡፡

ንግድ ባንክ የኤቲኤም አገልግሎት ለ24 ሰዓታት ይሰጣል ይበል እንጂ አገልግሎቱን የሚሰጡት ማሽኖች መሸት ካለ አብዛኞቹ አይሠሩም፤ አልያም ትዕዛዝ ተቀብለው ምላሽ የላቸውም፡፡ በተለይ በሳምንቱ የዕረፍት ቀናት በእነዚህ ማሽኖች ገንዘብ ከማሽኖች አውጥቼ እገለገላለሁ ማለት ከባድም ዘበትም እየሆነ ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚተማመኑበት ባንክ ሆኖ ለመዝለቅ፣ በአገልግሎቶቹ ዙሪያ ለሚፈጠሩት ተግዳሮቶች አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠትና የደንበኞቹን ማጉላላት በመቀነስ መጓዝ መቻል አለበት፡፡     

(ሚካኤል ብርሃኑ፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

ኢትዮ ቴሌኮም ገበታችንን ይመልስ!

የኢንተርኔት አገልግሎት ዓለማችን በጊዜ ሒደት ከተጎናፀፈቻቸው የፈጠራ ውጤቶች ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ዓለምን አንድ ከማድረጉም በላይ የተለያዩ አድካሚና ጊዜ የሚጨርሱ የተግባቦት ሁኔታዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማከናወን በአንድ አገር ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም አለው፡፡

ይህ አገልግሎት የታዳጊ አገሮችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከሕዝቡ ጋር በማስተሳሰርና በቀላሉ የመረጃ ፍሰትን በመጨመር ካሉበት የድህነት አረንቋ በፍጥነት ሊያስመልጣቸው ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ይህን አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ እየተጠቀሙበት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትን በበላይነትና በሞኖፖል የሚቆጣጠረው ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም ከደረሰበት የኢንተርኔት አጠቃቀም አንፃር ሲታይ እንደ ኤሊ ከመንቀራፈፉም በላይ ለሕዝቦች ተደራሽ ከመሆን አንፃር ብዙ የሚቀረው ይመስላል፡፡ በመንግሥት ደረጃ ‹‹የምትታለብ ላም›› በመባል የሚጠራው ቴሌ፣ ዜጎቹን በትንሽ ክፍያ ብዙ አስጠቅማለሁ ይበል እንጂ ‹‹ውስጡን ለቄስ እንዲሉ…›› ያለ ምንም አገልግሎት ዜጎችን እየበዘበዘ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያው ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ለደንበኞቹ ያቀረበውን የሞባይል ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎት ወይም ኢትዮ ገበታ ነው፡፡ የዚህን ጥቅል አገልግሎት ለመግዛት *999# መደወል ዕለታዊ፣ ሳምንታዊና ወርኃዊ የክፍያ አማራጮችን በመምረጥ በእያንዳንዱ አማራጭ ሥር የተቀመጠውን የገንዘብ ልክ በመክፈል የኢንተርኔት አገልግሎቱን እስከተባለው ቀነ ገደብ ድረስ መጠቀም ይቻላል፡፡ ነገር ግን የደንበኛው የአጠቃቀም ሁኔታ ኢንተርኔቱ የሚቆይበትን የጊዜ ገደብ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ሳምንታዊ የጥቅል አገልግሎትን የገዛ ደንበኛ ሳምንት ሳይቆይ በብዛት የሚጠቀም ከሆነ በአንድ ቀን ሊጨርሰው ይችላል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል የተለያዩ ፖለቲካዊ ክስተቶችን ምክንያት በማድረግ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ኢንተርኔት ሲቋረጥ ደንበኞች የገዙትን የጥቅል አገልግሎት ሳይጠቀሙ የአገልግሎት ጊዜ ገደብ ያልፋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ደንበኞች ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያደረጉት ስምምነት በመንግሥት ጣልቃ ገብነትም ይሁን በሌላ ምክንያት ያለ ደንበኞች ፍላጎት ስምምነቱ ሲጣስ ይስተዋላል፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ቀርፋፋነት በተጨማሪ እነዚህን አዳዲስ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ካቀረበ በኋላ በፈለገው ጊዜ የሚያቋርጣቸው ከሆነ፣ ደንበኞች ለሚደርስባቸው ኪሳራ ኃላፊነቱን ከመውሰድም በላይ ይቅርታ በመጠየቅ ያላግባብ ያጡትን አገልግሎት ማካካስ በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም እንዲህ ያለው ሥነ ምግባር የለመደበት ባለመሆኑ፣ ከዚህ በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች ኢንተርኔት ሲያቋርጥም ሆነ ሰሞኑን በፖለቲካ ምክንያት ኢንተርኔት ሲያቋርጥ ደንበኞች ላይ ለደረሰው መስተጓጎል ምንም ያለው ነገር የለም፡፡

ያደረገው ነገር ቢኖር የሞባይል ኢንተርኔት ጥቅል አገልግሎትን ከኢትዮ ገበታ ውጭ ማድረግ ነበር፡፡ አገልግሎቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደተቋረጠ ሳይገለጽ ድርግም ያለው የሞባይልና የሲዴኤምኤ ኢንተርኔት፣ አገልግሎቱ ባልተሰጠበት ወቅት የቆረጠውን ገንዘብ ማካካስ፣ ያቋረጠውንም የገበታ አገልግሎት እንዲመለስ እንጠይቃለን፡፡

(መላኩ ገድፍ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...