Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየሕዝብ ተወካዮች ከእንደራሴነታቸው በጥሪ የሚወርዱበትና የማሟያ ምርጫ የሚከናወንበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕግ

የሕዝብ ተወካዮች ከእንደራሴነታቸው በጥሪ የሚወርዱበትና የማሟያ ምርጫ የሚከናወንበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕግ

ቀን:

  በውብሸት ሙላት

የዴሞክራሲ ሥርዓት አንድም በቀጥታ ካልሆነም በውክልና ይተገበራል፡፡ ከተወሰኑ ጉዳዮችና ዝቅተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የአስተዳደር እርከኖች በስተቀር አገሮች የውክልና ዴሞክራሲን ይጠቀማሉ፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ እንደራሴውን ከመረጠ በኋላ ውክልናውን የተቀበለው ሰው የመረጠውን ሕዝቡ በመወከል የተለያዩ ተግባራትን እንደ ሕዝቡ በመሆን ይፈጽማል፡፡ እንደ ውክልናው ካልፈጸመ ወይንም መራጩ አመኔታ ካጣበት ደግሞ ሊነሳ የሚችልበት አሠራር አለ፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር ‘Recall’ ይባላል፡፡ ሊገልጸው የሚችል አቻ የአማርኛ ቃል ስላላገኘሁለት፣ በሕጎቻችንም ውስጥ ስለሌለ፣ ‹‹ከቦታው ወይንም ከወንበሩ ማንሳት›› ወይንም ‹‹ጥሪ ማድረግ›› የሚለውን እንጠቀማለን፡፡

ባለሥልጣንነት በሹመት ወይንም በምርጫ ሊገኝ ይችላል፡፡ ሕዝብ ራሱ አምኖ መርጦት ነገር ግን ከመረጠው በኋላ አመኔታ ካጣበት በኢትዮጵያ ሕግ ከያዘው ወንበር ሊያነሳው የሚችለው ተመራጭን እንጂ ሹመኛን አይደለም፡፡ ሹመኛን የሚያነሳው የሾመው አካል ነው፡፡ ለምሳሌ ፕሬዚዳንት፣ ሚኒስትሮች፣ የቢሮ ኃላፊዎች ሹመኞች ናቸው፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራሉ ድረስ በሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት ደግሞ ተመራጮች ስለሆኑ፣ የመረጣቸው ሕዝብ ከወንበራቸው ሊያነሳቸው ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ በአመኔታ እጦት የይውረድልኝ አቤቱታ አማካይነት ሊወርዱ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አሠራር የለም፡፡ የምርጫ ሥርዓታቸው የተመጣጣኝ ውክልና ከሆነ በእምነት ማጣት አማካይነት የሚወርደው ሙሉ ምክር ቤቱ ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ሥርዓት ዜጎች የሚመርጡት ግለሰቦችን ሳይሆን ፓርቲን ነው፡፡ ፓርቲው ባገኘው ድምፅ መጠን ሰዎችን ይመድባል፡፡ ስለሆነም፣ በዚህ ሁኔታ የተመረጠ ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት እንዲበተንና ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ሕዝብ አቤቱታ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ጥሪ ማድረግ (Recall) የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በአንዳንድ አገሮች ዜጎች አይበጀንም የሚሉት ሕግ እንዲሻርላቸው ወይንም በአዲስ እንዲተካላቸው የሚከተሉት ሒደትንም ያካትታል፡፡   

የክልል ምክር ቤት አባላትና ከዚያ በታች ያሉ እንደራሴዎች ብቻ የሚነሱባቸው አገሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብንወስድ የትምህርት ቤቶች የቦርድ አባላት ሳይቀሩ በዚህ ሒደት ይተካሉ፡፡ በተወሰኑ የአሜሪካ ግዛቶች ደግሞ ሕዝብ አመኔታ ያጣባቸውን ዳኞችም ጭምር እንዲወርዱ በማድረግ ነው በሕገ መንግሥታቸው የቀረጹት የኮንግረስ አባላቱ (የሁለቱም ምክር ቤቶች) ግን በዚህ አኳኋን አይወርዱም፡፡ ጥቂት አገሮች ደግሞ ተመራጮች ብቻ ሳይሆኑ ተሿሚዎችንም በጥሪ ያወርዳሉ፡፡ በቬንዙዌላ ፕሬዚዳንቱንም ጭምር ማውረድ ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅት ፕሬዚዳንት ሁጎ ሻቬዝን ለማውረድ ተሞክሮ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳን አብላጫ ድምፅ ማግኘት ባለመቻሉ በሥልጣን ቢቆዩም፣ ሌሎች ሚኒስትሮችንም በዚሁ ሁኔታ ማውረድ ይቻላል፡፡

በአገራችን በደርግ ጊዜ ወጥቶ በነበረውም ይሁን በአሁኑ ሕገ መንግሥት በአመኔታ ማጣት እንዲወርዱ አቤቱታ ሊቀርብባቸው የሚችሉት ብሎም በምርጫ ማውረድ የሚቻለው በሕዝብ የተመረጡ እንደራሴዎችን ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ውጭ ሥልጣን ያላቸውን ሹመኞች በዚህ ዘዴ ማውረድ የሚቻልበት የሕግ አሠራር የለንም፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12(3) መሠረት ሕዝብ በመረጠው እንደራሴው ላይ አመኔታ ካጣ ማውረድ እንደሚችል ለመራጩ ሕዝብ መብት ሰጥቷል፡፡ የክልሎች ሕገ መንግሥታትም በተመሳሳይ መልኩ ጥበቃ አድርገዋል፡፡ ስለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራረጥ የሚናገረው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በአንቀጽም 54(7) ላይ መራጩ ሕዝብ አመኔታ ያጣበትን ተመራጭ ማውረድ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ በክልሎችም እንዲሁ!

አቤቱታው እንዴትና ለማን እንደሚቀርብ፣ በወረደው ተወካይ ምትክ እንዴት ምርጫ እንደሚደረግ ዝርዝር ሕግ እንደሚወጣ የፌዴራሉም የክልሎችም ሕግጋት መንግሥታት ስለገለጹ ይህንኑ መብት ተግባራዊ ለማድረግ በወጡት ሕግጋት መሠረት ወኪሎች የሚወርዱበት ሒደት በማሳየት ቁንጽልነቱንም አታካችነቱም እንመለከታለን፡፡ ስለሆነም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ፣ በሕዝብ የተመረጡ እንደራሴዎች ወይንም ባለሥልጣናት የመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ ሲያጣባቸው እንዴት ከወንበራቸው ማንሳት እንደሚችል ማሳየት ነው፡፡ እግረ መንገዱን ግን በጥሪ ከወንበር የማንሳት ሥርዓት ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር ሊኖረው የሚችለውን ፋይዳ ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን አሠራሩ ካለመለመዱ በተጨማሪም የሕጉ ጎደሎነት በቀላሉ ሥራ ላይ ማዋል የሚቻል እንዳይሆን ስለሚያውክ መሻሻል እንዳለበትም ያመላክታል፡፡

ወኪልን በጥሪ ከወንበር የማንሳት ፋይዳዎች

በቅርቡ በወቅታዊው የአገራችን ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ንግግር ካደረጉት ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን፣ ሕዝቡ ያለውን ቅሬታ ለተለያዩ ምክር ቤቶች በመረጣቸው ወኪሎቹ አማካይነት ማቅረብ እንደሚችል ገልጸው፣ ወኪሎቼ አቤቱታዬን አላቀረቡልኝም ካለ ደግሞ ከወንበራቸው በማውረድ ሌላ የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን መጠቀም አለበት ማለታቸውን ሰምተናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕዝብ ያለውን ቅሬታ ቀድሞ በመረጠው ወኪሉ አማካይነት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ወኪሎችም የመረጣቸውን ሕዝብ በየጊዜው በማግኘት ያላቸውን ብሶትና ያጋጠማቸውን ችግር ይሰማሉ፣ ይወያያሉ፡፡ ሕዝቡ ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል ብለው የሚያስቧቸው ሕጎች ካሉ ከመጽድቃቸው በፊት የመረጣቸው ሕዝብ ስለሚወጣው ሕግ ያለው አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ የተለያየ ጥረት ይደርጋሉ፡፡ ካልሆነ የምርጫ ጊዜው ባይደርስም እንኳን እንደሚወርዱ ስለሚያውቁ! ለምሳሌ ከአሜሪካን ግዛቶች አንዷ በሆነችው ኮሎራዶ፣ በጦር መሣሪያ አያያዝ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ለሚፈቅድ ሕግ ድምፃቸውን የሰጡ ሦስት የዲሞክራቲክ ፓርቲው አባላት ከግዛቲቷ ምክር ቤት ያላቸውን ወንበር የመረጣቸው ሕዝብ እንዲለቁ አድርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመረጣቸው ሕዝብ የሕጉን መጽደቅ እንደማይደግፍ ማወቅና የሕዝቡን ፍልጎት ማንፀባረቅ ሲገባቸው የፓርቲውን አቋም በመከተላቸው ነው፡፡

ይህ አቶ በረከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀምበት ይገባል ያሉት፣ በፌዴራሉም ይሁን በክልሎች ሕግጋት መንግሥታት የተረጋገጠው ወኪልን ከወንበር በጥሪ የማንሳት የመራጭ ሕዝብ መብት፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚፈይደውን እንመልከት፡፡

በእምነት ማጣት አንድን እንደራሴ እንዲወርድ የሚደረግበት ሥርዓት በርካታ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም የተወሰኑትን ብቻ እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሲያስገድዱ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ አስቀድሞ ምርጫ ለማከናወን ይረዳል፡፡ ሌላው ደግሞ የዜጎችን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ እንዲጨምር ያግዛል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ተመራጮች ለሕዝብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ እንደራሴዎቹም ለወከላቸው ሕዝብ ምላሽ እንዲሰጡ የማድረጊያ አንዱ ሥልት ነው፡፡ እንዲሁም የውክልና ሥልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙበት የመግሪያ ሥልት ወይንም ልጓም በመሆን ያገለግላል፡፡ ስለሆነም መራጮች የመረጡትን ወኪል የመቆጣጠር መብታቸውን እንዳይነጠቁ ይታደጋቸዋል፡፡ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁመው ማውረድ እንዳይቸግራቸው ሲባል የተዘረጋ ሥልት ነው፡፡

የመንግሥትን ዕጣ ፈንታም በመራጮች እጅ እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ በምርጫ የተወከሉ ሰዎች የተገራ ዲስፕሊን እንዲኖራቸው ያበረታታል፣ ይጠይቃል፡፡ ታማኝነትን/አመኔታን ይጨምራል፡፡ ወኪሎች ከመራጮች ጋር ያላሰለሰ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ እውነተኛ መሪንም ይፈጥራል፡፡ የጠነከረ የፓርቲ ዲሲፕሊንን ወይንም ለፓርቲ ብቻ ታማኝ መሆንን እንዲላላ ያደርጋል፡፡ ቅድሚያ ለመራጭ እንዲሆን ይረዳል፡፡ ከላይ የቀረቡት ፋይዳዎች ወይንም ግቦች በሁለት ንድፈ ሐሳቦች ማጠቃለል ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ግብ የውክልና (Agency) ንድፈ ሐሳብ ይባላል፡፡ እንደዚህ ንድፈ ሐሳብ ከሆነ አንድ ተወካይ ወይንም እንደራሴ የወከለውን ሰው ወይንም ሕዝብ በከፍተኛ የቅንነት መንፈስ፣ በታማኝነት፣ በታታሪነት ማገልገል አለበት፡፡ ውክልናውም ጸንቶ የሚቆየው ወካዩ እስከፈለገ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ወካዩ ባሰኘው ጊዜ ውክልናውን የማንሳት መብት አለው፡፡ ስለሆነም ለወኪሉ ከሰጠው ወንበር ላይ ለማንሳት ምንም ዓይነት ምክንያት አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ ይህንን ንድፈ ሐሳብ በመከተል አንድ የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም፣ መራጩ ሕዝብ ወኪሉን የመሻር መብታቸውን በማረጋገጥ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንደ ምክንያት ያቀረበውም ሕዝብ አንድን የምክር ቤት አባል ሲመርጥ ምክንያት ካልተጠየቀ፣ ለማውረድ በሚፈልግበት ጊዜ ሊጠየቅ አይገባውም የሚል ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው ትንሽ ከነባራዊው ሁኔታ ያፈነገጠና ሐሳባዊ ነው የሚሉ አሉ፡፡ አንድ የሕዝብ እንደራሴ (ወኪል) ከመራጮች በዘለለ ለአገር ወይንም ለሌሎች መዋቅሮች ስለሚሠራ ወካዮች ባሻቸው ጊዜ ሳይሆን በታወቁ ምክንያቶች ለአብነት ሙስናን፣ ብቃት ማነስን፣ ስንፍናን ምክንያት በማድረግ የተወከለበትን የማይፈጽም ከሆነ ሊነሳ ይገባል ይላሉ፡፡ ማንም ባሰኘው ጊዜ ለማውረድ የሚደረግ ውክልና መኖር የለበትም ባይ ናቸው፡፡ ይህ የተጨባጫዊነት ንድፈ ሐሳብ ይባላል፡፡

የአመኔታ እጦት መለኪያዎች

ከላይ ያየናቸው ንድፈ ሐሳቦች ሕዝብ ወኪሎቹን በምን በምን ምክንያቶች ማንሳት እንዳለበት ተጻራሪ የሆኑ ሁለት አካሄዶችን ተከትለዋል፡፡ አንዱ ምክንያት አያስፈልግም ሲል፤ ሁለተኛው ግን ያለምክንያት ማውረድን ይቃወማል፡፡ የእኛ ሕገ መንግሥት መራጩ ሕዝብ አመኔታ ያጣበትን ወኪል ማውረድ እንደሚችል በጥቅሉ በመግለጽ ዝርዝሩን ለሌላ ሕግ በመተው አልፎታል፡፡ አንዳንድ አገሮች ግን የሚነሱበትን ምክንያቶች በሕገ መንግሥታቸው አካትተዋል፡፡ መራጮቻቸው አመኔታ ያጣባቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዴት እንደሚወርድ ሥርዓት ለማበጀት ሲባል በወጣው አዋጅ ቁጥር 88/1989 ላይም መራጩ ሕዝብ ወኪሉን ለማውረድ ምክንያት ማቅረብ እንዳለበት አላስቀመጠም፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ደንብ ላይ ወኪላቸው እንዲወርድ መራጮች ያቀረቡትን አቤቱታ ለይውረድልኝ ጥያቄው መነሻ አይሆንም ብሎ ካመነ ምርጫ ቦርድ አቤቱታውን ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጻል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ምን እንደሆኑም በደንቡ ላይ አልተገለጹም፡፡ በደፈናው ለሕዝቡ አቤቱታ መነሻ የሆነው ነገር በቂ ካልመሰለው ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል ብቻ ነው የሚገልጸው፡፡ ሕዝቡ ቀድሞ እንዲያውቀው ባልተደረገ ምክንያት የምርጫ ቦርድ ማንኛውንም አቤቱታን ሲያሻው በአወንታዊ አለበለዚያም በአሉታዊ እንዲወስን የሚያስችል እጅግ የተለጠጠ ሥልጣን ለራሱ መስጠቱ ተገቢ አይደለም፡፡

በተጨማሪም የአመኔታ እጦት የሚለካው በአቤቱታ አቅራቢዎች ብዛት እንደሆነ አዋጁ ስላስቀመጠ ደንቡ ያልታወቁ ምክንያቶችን መለኪያ ማድረጉ ከአዋጁ ጋር ተጻራሪ ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱና አዋጁ አመኔታ በማጣት ለሚነሳ ወኪል መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶችን ስላልመረጠ የውክልና ንድፈ ሐሳብን ይከተላል፡፡ ደንቡ ደግሞ ያልተጻፉ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ መነሻ ስለሚፈልግወደ ሌላኛው ንድፈ ሐሳብ ያጋድላል፡፡

በአዋጁ መሠረት አንድ ተወካይ አመኔታ ታጥቶበታል የሚባለው በምርጫ ወረዳው ከሚገኙ መራጮች ውስጥ 15,000 ወይንም በምርጫ ወረዳው ያለው የወረዳ ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ድጋሚ እንዲጠራ ከወሰነና 10,000 መራጮች ከደገፉት ነው፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎችና አቀራረቡ

በወኪል ላይ አመኔታ ሲጠፋ ከወንበሩ እንዲነሳ ወይንም ድጋሚ እንዲጠራ በሁለት መንገድ አቤቱታ ሊቀርብ ይችላል፡፡ አንዱ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አነሳሽነት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በግላቸው አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ነው፡፡ አቤቱታው በፓርቲ አነሳሽነት ሲቀርብ የአቤቱታ አቅራቢዎች ቁጥር ከፍ እንዲል፣ በፓርቲ በኩል ካልሆነ ግን ዝቅ የማድረግ አዝማሚያን ይከተላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን በፓርቲ በኩል አቤቱታ እንዴት እንደሚስተናገድ ወይንም ደግሞ አቤቱታ አቅራቢዎች የፓርቲ አባላት የመሆንም ወይንም አለመሆን ቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም፡፡ በመሆኑም በምርጫ ወረዳው ውስጥ ሁለት ዓመታት የኖሩ 100 ሰዎች አቤቱታ ለማቅረብ በቂ ናቸው፡፡ አቤቱታቸውን ለወረዳው ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ያስገባሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ደግሞ ለቦርዱ ያስተላልፋል፡፡

የአቤቱታው ይዘት ምን መሆን እንዳለበት የእኛ ሕግ እንደ ሌሎች አገሮች በግልጽ ባያስቀምጥም፣ ቦርዱ የተለያዩ ቅጾችን ስለሚያዘጋጅ ይዘቱን ቅጾቹ ላይ ሊወሰን ይችላል፡፡ በተጨማሪም በአንድ አቤቱታ ስንት ሰዎችን ለማውረድ እንደሚቻል ወይም እንደ ሌሎች አገሮች በአንድ አቤቱታ አማካይነት ከአንድ ወኪል በላይ ማውረድ አለመቻሉን አይገልጽም፡፡ እንዲሁም የአቤቱታውን ይዘት መቀያየር ወይንም መጨመር መቻል ወይንም አለመቻሉን አልተገለጸም፡፡

የምርጫ ቦርድ የቀረበለትን አቤቱታ ካመነበት በወረዳው የምርጫ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ደጋፊዎች ከመቼ እስከ መቼ መመዝገብ እንዳለባቸው ያሳውቃል፡፡ በምርጫ ወረዳው ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች 15,000 ወይንም የወረዳው ምክር ቤትም ወስኖ ከሆነ 10,000 ሰው ከተመዘገበ ተወካዩ ይወርዳል፡፡ ይህ የምዝገባ ሒደት እንደ ማንኛውም የምርጫ ምዝገባ በየቀበሌው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡ አቤቱታ የቀረበበት ሰው ታዛቢ የሚሆኑትን ወኪሎቹን በየምርጫ ጣቢያዎቹ የማስቀመጥ መብት አለው፡፡ ይህ አሠራር በርካታ ክፍተቶች አሉበት፡፡ አራቱን ብቻ ላቅርብ፡፡ የመጀመሪያው፣ አቤቱታው የቀረበበት ሰው ስለቀረበበት ጉዳይ እንዴት (በፖስታ፣ በስልክ ወዘተ.) መስማት እንዳለበት፣ በምን ያክል ጊዜም መስማት እንዳለበት፣ ማን አቤቱታውን ማድረስ እንዳለበትም ሕጋችን አይናገርም፡፡

ሌላው፣ አቤቱታውን 100 ነዋሪዎች ለማቅረብም ይሁን ተወካዩን ከወንበሩ ለማስነሳት እንደማንኛውም ምርጫ ቅስቀሳ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የተወሰኑ አንቀሳቃሽ ፈቃድ የሚገኙበትና ወጪዎችን የሚሸፈኑበት አሠራር ያስፈልጋል፡፡ በርካታ አገሮች፣ ማንም ሰው እንዲህ ዓይነት አቤቱታ ለማቅረብ በማሰብ መቀስቀስ ሲፈልግ ምርጫውን የሚያከናውነው መሥሪያ ቤት (በእኛ ሁኔታ የወረዳው የምርጫ ጽሕፈት ቤት) የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡ ፊርማ ለማሰባሰብም፣ ግለሰቦችን ወይንም ድርጅቶችን ቀጥሮ ማሰማራት ይቻላል፡፡ የማውረድ እንቅስቃሴውን ለማሳካትም ባለሀብቶች ወጪዎችን ቢሸፍኑ ከሚከፍሉት ግብር ላይ ተቀናሽ ይደረግላቸዋል፡፡ ስለፋይናንስ የሚደነግጉት የምርጫ መመርያዎችም ጠቅላላ ምርጫን እንጂ በጥሪ ማውረድና ማሟያ ምርጫን አያካትትም፡፡ ዋናው ነገር በምርጫ አስፈጻሚው አማካይነት ስለወጪው ትክክለኛነት በኦዲተር እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው፡፡ ወደ እኛ አገር ሕግ ስንመለስ፣ የሕዝብን ጉዳይ በማንሳት ኮሚቴ መሥርቶ መንቀሳቀስ ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ ውሎ አድሮም የግጭት መንስዔ ሲሆንም እያየን ነው፡፡ አንድ ተመራጭን ለማውረድ ብቻ ሳይሆን የማንነት ጥያቄዎችም ሲነሱ ተመሳሳይ ችግር ስለሚያጋጥሙ ምርጫ ቦርድ መፍትሔ መሻት አለበት፡፡ ከኮንሶ፣ ከወልቃይትና ከሌሎችም ጉዳዮች እንደታዘብነው የኮሚቴ አባላት ዕጣ ፋንታቸው ሕዝብን በማነሳሳት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በመሞከር አንዳንዴም በሽብርና በመሳሰሉት ወንጀሎች መከሰስ ነው፡፡

ሌላው ችግር ደግሞ ተወካይን ለማውረድ መደገፍ ያለበት የመራጮች ብዛት ነው፡፡ ሁለት ዓይነት የማውረጃ መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሦስት እርከን ያለው ሲሆን፣ የተወሰነ ቁጥር/ፐርሰንት ያላቸው ሰዎች አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ከዚያ ይውረድ ወይንም አይውረድ የሚለው ላይ መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ ከወረደ ከእንደገና ለማሟያ ምርጫ ድምፅ ይሰጣል፡፡ ሌላው ደግሞ ሁለት እርከን ያለው የማውረጃ ሒደት ሲሆን፣ ከመራጮቹ የተወሰኑ ፐርሰንት ፊርማ ከተሰባሰበ እንደወረደ ይቆጠራል፡፡ ከዚያ ድጋሚ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለው ባለ ሁለት እርከኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች አገሮች አቤቱታ ከቀረበ በኋላ ምን ያህል ሰው አመኔታ አጥቶበታል የሚለው የሚለካው ቀድሞ በነበረው ምርጫ ላይ ከተሳተፉት ውስጥ የተወሰነ ፐርሰንቱን በመውሰድ ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች እስከ 15 ፐርሰንት ድረስ ዝቅ ሲል 40 ፐርሰንት እንዲፈርም የሚጠየቅበትም ሁኔታ አለ፡፡ ለምክር ቤቱ ድምፅ የሚሰጠውን የሕዝብ ብዛት መሠረት በማድረግ መራጩ አነስተኛ ከሆነ ፐርሰንቱ ከፍ እንዲልና መራጩ ከፍ በሚልበት ላይ ደግሞ የሚፈለገውን መጠን አነስተኛ ማድረግ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ለምሳሌ ለፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወረዳ ላይ 50,000 ይመርጣል ብንል፣ ለቀበሌ ምክር ቤት ደግሞ 1,500 ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ለመጀመሪያው 15 ፐርሰንት ቢሆን ለሁለተኛው 40 ፐርሰንት ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ግን በሎሎች ከተለመደው ባፈነገጠ መልኩ በፐርሰንት ሳይሆን ቁርጥ ያለ ቁጥር ተቀምጧል፡፡ በግዳጅ ምርጫ ሳይኖር እንደዚህ ቁጥር ማስቀመጥ ለዴሞክራሲ እንቅፋት ነው፡፡ በዋናውም ምርጫ በአንድ የምርጫ ወረዳ ይኼን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ድምፅ ላይሰጥ ይችላል፡፡

በመጨረሻው መነሳት ያለበት እንከን፣ የይውረድልኝ አቤቱታ የማይቀርብባቸውን ወኪሎችን የሚመለከት ነው፡፡ ዜጎች አመኔታ ያጡባቸውን ወኪሎች ይውረድልን በማለት አቤቱታ ለማቅረብ ከተመረጠ በኋላ የተወሰነ ጊዜ መቆየትን ይጠይቃል፡፡ ትንሽ ፋታ ሳያገኙ የይውረድልኝ ጥሪ መቅረብ የለበትም የሚሉ አሉ፡፡ በርካታ አገሮች ቢያንስ ለስድስት ወራት ያህል ያልተሞከረን ወይንም ዕድል ያልተሰጠውን እንዲወርድ ጥሪ ማቅረብን ከልክለዋል፡፡ እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ድረስ የሚዘልቅ የሙከራ ጊዜም የሚሰጡ አሉ፡፡ በዋሽንግተን ግዛት ምርጫ በተደረገ በማግሥቱ፣ በዚያና ደግሞ ከአምስት ቀናት በኋላ መጀመር ይቻላል፡፡ የእኛ ሕግ ግን ዝምታን መርጧል፡፡ ስለሆነም በማናቸውም ጊዜ ማቅረብ ይቻላል እንደማለት ነው፡፡ በእኛም ሕግ፣ የአገልግሎት ዘመኑ ሊያበቃ ከስድስት ወራት በታች ከቀረውም እንዲሁ አቤቱታ ማቅረብ አይቻልም፡፡ በዚህ መንገድ ማንኛውንም ተመራጭ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይሁን ሌሎች ባለሥልጣናትን፣ የፓርላማ አባላት እስከሆኑ ድረስ የመረጣቸው ሕዝብ በድጋሚ ሊጠራቸውና ከወንበራቸው ሊያነሳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ለማውረድ ግን ከላይ የተቀመጠው አሠራር ብዙም የሚረዳ አይደለም፡፡ በዋናነት እነዚህ የምክር ቤት አባላት የሚመረጡት ከክልሎች ምክር ቤት በመሆኑ ሕዝቡ የሚያወርድበት ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባት በቀጥታ የተመረጡ ካሉ ግን ማውረድ ይቻላል፡፡

የማሟያ ምርጫ

በይውረድልኝ ጥያቄ አንድ ወኪል ከተነሳ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ምርጫ ሊደረግ እንደሚደረግ ከላይ ያነሳነው አዋጅ ላይ ተገልጿል፡፡ በአመኔታ እጦት ምክንያት ከተነሳ በሥነ ምግባር ጉድለት ከምክር ቤት ከተባረረ፣ በወንጀል ተከስሶ የምክር ቤት ወንበሩን ካጣ፣ በሞት ወይንም በሌሎች ምክንያቶች ምክር ቤቶች አባላታቸው ሲጓደሉ የማሟያ ምርጫ ይደረጋል፡፡

በአገራችን በአመኔታ እጦት እንዲወርዱ የተደረጉ ወኪሎች ስለመኖራቸው በሰፊው የሚታወቀው በ1993ቱ የሕወሓት ክፍፍል ጊዜ የአንጃው ወገን የሆኑት የነስየ አብርሃ ቡድንን ነው፡፡ የማሟያ ምርጫ በሌሎች ጊዜያትም ተከናውኗል፡፡ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርት የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ስላልተረከበ የማሟያ ምርጫ ተደርጓል፡፡

በአመኔታ እጦት ምክንያት አንድ ወኪል ከወንበሩ በመነሳቱ ለሚኖረው የማሟያ ምርጫ ዕጩዎች እንዴት ሊቀርቡ እንደሚችሉ እንይ፡፡ በመጀመሪያ በየትኛውም አገር፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ የወረደው ወኪል በራሱ ጊዜ አልወዳደርም እስካላለ ድረስ የመወዳደር መብት አለው፡፡ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን ግን የይውረድልኝ ጥሪ ያቀረቡት አካላት ዕጩ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ማለትም በዜጎች አነሳሽነት ከሆነ የግል ተወዳዳሪ፣ በፓርቲ አነሳሽነት ከሆነ ደግሞ ፓርቲው ያቀርባል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት አንድን ተወካይ ካባረረ፣ ለዚህ ለጎደለው ወንበር የሚደረገው የማሟያ ምርጫ ላይ ይሄው በሥነ ምግባር የተባረረው ሰው መልሶ እንዲወዳደር ሕጉ መብት ይሰጣል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...