Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹የመንግሥት የዓመቱ አቅጣጫ›› ከተሃድሶው አንፃር

‹‹የመንግሥት የዓመቱ አቅጣጫ›› ከተሃድሶው አንፃር

ቀን:

  በፀሐዬ መንበር

የመስከረም 2009 ዓ.ም. የመጨረሻዋ ሰኞ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሸን ምክር ቤቶች ስብሰባ በጋራ የተከፈተበት ዕለት ነው፡፡ በዚሁ ቀንም የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ከአንድ ሰዓት በላይ ይፈጀ ንግግር ተንፀባርቋል፡፡ መንግሥት (ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው) ከዚህ መነሻ ተነስተው የራሳቸውን ዝርዝር ዕቅድና ተግባሮች በማውጣት ወደ ሥራ እንደሚገቡም ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጸሐፊ እምነት ግን በንግግሩ የቀረቡ ዕቅዶች አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የሚገጥማቸው ፈተና አለ፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ብሎ ከጀመረው ሥራ አኳያም ሽግግራዊ ተሃድሶ ማስመዝገብ ካልቻለ፣ ንግግሩ መና ላለመቅረቱ ዋስትና የለም በሚል ለመሞገት እወዳለሁ፡፡ በዚሁ አቅጣጫ ወይም በሌላ ዕይታ የሚመለከተው ካለም ልንወያይበት እንችላለን፡፡ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ዋና ዋና ትኩረቶች አንድ በአንድ በመምዘዝ በራሴ አመንክዮ ለመሞገት እሞክራለሁ፡፡

ወጣቶችን ከነውጥ ወደ ለውጥ ለማውጣት እንዴት?

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በሚያወጣው መረጃ መሠረት ከ65 ሚሊዮን በላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች በአገሪቱ ይኖራሉ፡፡ ከወጣትነት ዕድሜ በታች ያሉ ሕፃናትን ጨምሮም እስከ 27 ሚሊዮን ዜጎችም ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ድኅረ ምረቃ ትምህርት ተሰማርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የቅርብ ጊዜ መረጃ መሠረትም በአገሪቱ ከድህነት ወለል በታች ከሆኑ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መሀል 17 ሚሊዮን የሚደርሱ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ይታወቃሉ፡፡

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ወጣት ሥራ አጥ ሆኖ የሚገኝበት የገጠሩ ክፍል መሆኑ ደግሞ ገጽታውን ሌላ መልክ ያስይዘዋል፡፡ የአርሶ/አርብቶ አደሩ ልጆች በገጠር መሬት የላቸውም፡፡ የሚቀጠሩበትም ሆነ የሚሰማሩበት በቂ የሥራ ዕድልም የላቸውም፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ስበሰባ ላይ ‹‹ወጣቱ ኃይል እንደ ማዕበል እየመጣ ያለ የአኅጉሩ ፈተና›› የሚል አጀንዳ ተነስቶ የተመከረበት ለኢትዮጵያ ይሠራል፡፡

ይህንን ማዕበል ቀድሞ የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ወጣት ተኮር ፓኬጆችን›› በመንደፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረጉ ይታወቃል፡፡ የተባለለትን ያህል ውጤታማ ባይሆንም ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት በተባለው መርሐ ግብር በተለይ በአንዳንድ ክልሎች (አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ትግራይ) የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ትንሽ አይደሉም፡፡ በሌላ አካባቢ ጥረቱ ቢኖርም ያሳተፋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የተመናመኑና በአስፈጻሚው የውሸት ሪፖርት ሲሰለቅ የከረመ ነው፡፡

በዘንድሮው የፕሬዚዳንቱ ንግግር በዓመቱ ‹‹የወጣች ፈንድ›› የሚባል መሥሪያ ቤት በሁሉም ወረዳዎች ይከፈታል፡፡ ለዚህም የአሥር ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል ብሏል፡፡ ፈንዱ ምን? እንዴትና የት ይሠራል? የሚለው ገና በዝርዝር ዕቅድ የሚመለስ ነው፡፡ ነግር ግን ፈንዱን አደራጅቶ፣ አሠራር ዘርግቶ፣ ሀብት አደላድሎ ወደ ተግባር መግባት በራሱ ረዥም ጊዜና ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የተባለው በጀት በአገሪቱ ለሚገኙ 900 ወረዳዎች በአማካይ 10.5 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ነው የሚችለው፡፡ ይህ ገንዘብ ሥርዓት ባለው መንገድ ካልተመራ ደግሞ ከጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ የሚያልፍ አይደለም፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ በወጣቶች ላይ የሚሠራው ሥራ የገጠመው ፈተና የፍትሐዊነት ችግር ነው፡፡ በብዙዎቹ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ‹‹ተደራጅተው ውጤታማ ሆኑ›› የተባሉ ወጣቶች ለመንግሥት ፖለቲካ ቅርብ የሆኑ፣ ለባለሥልጣናትና (በታችኛው ደረጃ) ጭምር የዝምድና፣ የብሔርና የሃይማኖት ቅርበት ያላቸው ናቸው፡፡ በበርካታ ወጣቶች ስም ተደራጅተው (በተለይ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ) የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በነፃ አግኝተው፣ ብድርና ሥልጠና ተሰጥቷቸው፣ ገበያ ተመቻችቶላቸው በጥቂት ቤተሰቦች የተያዙ ‹‹ማኅበራትን›› ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ በአዲስ አበባ ከመኪና እጥበት ጀምሮ፣ በግንባታ ምርት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍና በደረቅ ምግብ ምርት መሰክ የተሰማሩ ወጣቶች ተወላጆች ሳይሆኑ ከሌላ አካባቢ መጥተው የተመቻቸላቸው ናቸው፡፡ ሌላው ይቅርና ባለፈው ዓመት የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ያለበትን ደረጃ የሚመረምርና ቆጠራ የሚያካሂድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ያገኘው ውጤት እጅግ የሚያሳፍርና የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ ታዲያ ይህን የተዝረከረከና ፖለቲካዊ ጩኸቱ የበዛ ሥልት ወደምን ቀየሮ ይሆን ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚቻለው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡

ሌላው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ስለወጣቶች ተጠቃሚነት ያወሳው ጉዳይ በሜካናይዝድ እርሻና በመካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወጣቶችን የማሰማራቱ ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ዕቅድ በፍትሐዊነትና በግልጽነት ከተሠራበት የነቻይና፣ ኮሪያና ጃፓንም መንገድ ነው፡፡ እዚህም ላይ ያለው ፈተና ግን ሀብቱ (Resource) ያለበት ቦታና ሥራ አጡና አማራጩ ኃይል በብዛት የሚገኝበት ክልል የተጣጣመ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህን አቀራርቦ ለላቀ ውጤት ለመብቃት ደግሞ ቋንቋና ብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ዜጎችን ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ከመሄድ ይልቅ በረሃ ቆርጠው፣ ባህር ተሻግረው ቢሰደዱ እንዲመርጡ አድርጓቸዋል፡፡ ሁሉም ከፈለሰ ወደ ዋና ከተማዋ ብቻ ሆኗል፡፡ ይህ ከባድና አደገኛ ዝንባሌ በምን ይገታል?

በመንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ አሁን ከተደቀነው ልማትን ዋስትና የሚያሳጣ የሰላምና የመረጋጋት ጉዳይ ገና ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት አሁን በቀላሉ ወደ ‹‹ነውጥ›› እና ሁከት ወይም የሥርዓት ለውጥን ወደ ማማተር የገባውን ወጣት ኃይል ለመያዝ የሚጠብቀው ፈተና ከባድና ውስብስብ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል፡፡

የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት ቁርጠኝነት አለ?

      አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ዴሞክራሲያዊ አይደለም›› የሚሉ ወገኖች ሥር ነቀል ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ጥገናዊ ለውጥ ሊቀይረው አይችልም ይላሉ፡፡ ሥርዓቱ በተለይ ካወጣው ሕገ መንግሥት ጋር የሚጋጩ የተለያዩ ሕግጋትን

(የፀረ ሽብር ሕግ፣ የመረጃና መገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የሲቪክ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ) ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ማውጣቱ ክፉኛ ጎድቶታል የሚሉም አሉ፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎዳቱም ሆነ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበቡ በግልጽ ታይቷል፡፡ ምንም እንኳን ችግሩ በተለያዩ ወገኖች ሲነሳ መንግሥት ባይቀበለውም አሁን ግን በየአካባቢው ለተነሳው ቀውስና ሁከት ‹‹የሰላም በር መጥበቡ ያመጣው ጣጣ ነው›› የሚለው አመክንዮ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግርም ይህንኑ ያሳያል፡፡

ያም ሆኖ አሁንም የተነገረው ተስፋ ምን ያህል በመስኩ ሽግግራዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል አልታወቀም፡፡ በቀዳሚነት የተጠቀሰው ‹‹የምርጫ ሕጉን የማሻሻል›› ጉዳይ ነው፡፡ ያውም ከሦስት ዓመታት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ፡፡ ነገር ግን በምን ያህል መጠን ይሻሻል? የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ወሳኝ ጥያቄ እንዴት ይፈታል? የዜጎች የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ ፖለቲከኞች በሁሉም አካባቢ ያለሥጋት የመንቀሳቀስ ነገር. . . እንዴት ይሆናል? ብሎ በአንክሮ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ድርሻ ያለው የፕሬስ ነፃነትና የማኅበራዊ ድረ ገጽ ነፃነትና በሥርዓት የመመራት ጉዳይም በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ በተለይ መንግሥት በሞኖፖል የያዘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤትነት፣ የዴሞክራሲ ውይይትን የሚፈሩት የአገሪቱ የኤፍኤፍ ሬዲዮ ጣቢያዎች መነሾነት፣ ጭልጭል የሚለው የግል ፕሬሱ በሥርዓትና ማኅበራዊ ኃላፊነት ቅኝት የዴሞክራሲ ባህሉን ለመገንባት ካላገዙ ንግግሩ ዋጋ አይኖረውም፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ንግግር አንፃር ተስፋ የተጣለበት የዜጎች አማራጭ ሐሳብን የማዳመጥ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ መንግሥት ‹‹ብዝኃነት›› ሲነሳ የሚናገረው ስለብሔር፣ ሃይማኖትና ፆታ ብዝኃነቶች ብቻ ነበር፡፡ ትልቁ የልዩነት ምንጭ ግን የፖለቲካ አመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን እውነት እንደሌለ ቆጥሮ ሁሉንም ‹‹በአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ለማጥመቅ መቋመጥ ያለጥርጥር የሚጋብዘው ውድቀትን ብቻ ነበር፡፡

መንግሥት ይህን ችግር ዘግይቶም ቢሆን በመገንዘብ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የሚደመጡባቸው ምክር ቤቶችና መንግሥታዊ ፎረሞች ይፈጠራሉ ብሏል፡፡ በእውነት መተግበር ከተቻለ! ለዚህ ተግባር በርካታ አብነት ያላቸው የአፍሪካም ሆኑ የዓለም አገሮች በወሳኝ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ምሁራንን እስኪደክሙ ያወያያሉ፡፡

በዚህ አገር ከላይ የተጠቀሱትን አካላት እንደ ባለድርሻ ቆጥሮ ለማወያየት የሚሞከረው አንድም በምርጫ ወቅት ካልሆነም በቀውስ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ያኔም ቢሆን ‹‹እንዴት እናድርግ? ምን ትመክሩናላችሁ?›› በሚል ሳይሆን፣ ‹‹ይህን አድምጡና ተቀበሉ›› በሚል ከላይ ወደታች በሚለቀቅ አጀንዳ ላይ ለማጥመቅ እንደሆነ ዘንድሮ የመምህራንና የተማሪዎች ‹‹ውይይት›› ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ከእነዚህ ነባራዊ ሀቆች አንፃር በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የመንግሥት ቁርጠኝነት ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ከትምህርት ቤቶች አካዳሚክ ነፃነት አንስቶ፣ የሲቪል ሰርቪሱን ገለልተኝነት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና ልዩ ልዩ ማኅበራትን ነፃነት የመጀመር ሥራ መታየት አለበት፡፡ ሕዝቡ ‹‹የሰላም በር አልተዘጋም›› ሊል የሚችለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡

‹‹የዴሞክራሲ አንድነትን እንገነባለን›› በየትኛው ተግባር?

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ወቅታዊውን የአገሪቱ አሥጊ ሁኔታ በመዳሰስ በየአካባቢው ዜጎች ከጠባብነትና ‹‹ፀረ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ወጥተው አገራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንገነባለን ብለዋል፡፡ ሐሳቡ መልካምና ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡ ግን እንዴት ሊሳካ ይችላል?  የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ያሳስባል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት በጎሳና በማንነት ላይ ብቻ ያተኮረው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተለያዩ ብሔረሰቦች እንዲታወቁና መብታቸው እንዲከበር (ቢያንስ በማንነት) አድርጓል፡፡ ግን ያለጥርጥር አንድነትና አገራዊ ብሔርተኝነትን ማምጣት አልቻለም ብል ማጋነን አይመስለኝም፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት የሚጠየቅበት ስለልዩነት ድምቀት ያወራውን ያህል ስለአንድነትና ኅብረት፣ ስለኢትዮጵያዊነት ያልሠራ መሆኑ ነው፡፡ የጋራ ባንዲራ፣ የጋራ የሥራ ቋንቋ፣ በታሪክ አጋጣሚ የጋራ ባህልና ወግ፣ የጋራ ሃይማኖቶች. . . ያሏቸው የአገራችን ሕዝቦች ለመለያየትና ለመገፋፋት ቅርብ ሆነዋል፡፡ በተለይ ደግሞ አዲሱ ትውልድ በመንደርተኝነት እየተነዳ ከዚህ ውጣ፣ ያ የኔ ብቻ ነው. . . የሚል ጎጠኛ አጀንዳ እያራገበ ነው፡፡ ባሳለፍናቸው ወራት በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልልና በደቡብ (ዲላና ኮንሶ) እንደታየው የሕዝቦች አብሮ የመኖር ገመድ ክፉኛ ላልቷል፡፡ ዋስትናም ህሊናና የጋራ ማንነት ሳይሆን መሣሪያ መስሏል፡፡

መንግሥት ይህን አደገኛ ችግር ተረድቶ ከሆነ ‹‹የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንገነባለን!›› ያለው መልካም ነው፡፡ ይህ ግን ከራሱ ከገዥው ፓርቲ መጀመር እንዳለበት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ራሱ ለሁለት አሥርት ተኩል ዓመታት ከብሔር ፓርቲ ወጥቶ ኅብረ ብሔራዊ ድርጅት መሆን አልቻለም፡፡ በእሱ አምሳል የተፈጠሩት የተቃዋሚ ማኅበራትም ቢሆኑ ከመንደር አስተሳሰብ አልወጡም፡፡ ኅብረት በሌለው ፖለቲካ ምን ዓይነት የሕዝብ አንድነት ይጠበቃል ማለት የሚበጀውም ለዚህ ነው፡፡

በርዕሰ ብሔሩ ቃል ‹‹የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርትን በስፋት ማስረፅ›› ሲባል አንዱ የዜጎችን ሥነ ምግባር፣ ተነሳሽነትና አገራዊ ስሜት መገንባት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትምህርትና የእምነት ተቋማት፣ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና መገናኛ ብዙኃንም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሠረቱ ጠባብነትና መንደርተኝነት የኋላ ቀርነት ጥሩ መገለጫ ነው፡፡ ዓለም አንድ መንደር ሆኖ ሳለ እኛም ዜጎች ጭምር ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ‹‹በለው! አሳደው!›› ማለትን ካላራገፍን የትም ልንደርስ አንችልም፡፡

ከዚህ አንፃር በአገሪቱ አንዳች ዓይነት አብዮታዊ ኅብረ ብሔራዊነት እስኪፈጠር ሳንጠብቅ የኅብረትና የአንድነት መንገድን መጀመር አለብን፡፡ መንግሥት ‹‹አንድ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ፈጥረናል›› የሚለውን ምዕተ ዓመት የሚወስድ መላምት ትተን፣ ከተዛባው የታሪክ መጓተትና መፈላቀቅ ወጥተን የምንከባበርና የምንተማመን የአንዲት ኢትዮጵያ ሕዝቦች መሆናችን በገቢር ማሳየት አለብን፡፡ መንግሥት ሆይ እንደ ንግግርና ዕቅድ ይኼም ተግባር ቀላል አይደለምና አስብበት ማለት ይሻላል፡፡

መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማስተካከል መልካም አስተዳደር ማስፈን

ከሞላ ጎደል አንድ ዓመት ገደማ ያስቆጠረው በተለያየ መንገድ የተነሳ ሕዝብ ጥያቄ መነሻው የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፡፡ መንግሥትም ከቀደሙት ዓመታት ጀምሮ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሕዝቡን እንዳማረረ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህን ለመቅረፍ እንደሚሠራ በድርጅቱ ጉባዔና በጥናት ጭምር ተናግሮ በተግባር ግን ለውጥ ሲጀምር አልታይ አለ እንጂ፡፡

እንደ ኦሮሚያ ባሉት ክልሎች ከመሬት ካሳ፣ ከይዞታ ማስተላለፍ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ፣ በሌሎች ክልሎችም ከፍትሐዊ የሥራ ዕድል ፈጠራና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ብዙ ቅሬታ ተነሳ፡፡ በአዲስ አበባ አብዛኛው አገልግሎት በጉቦና በእጅ መንሻ ብቻ የሚፈጸም ሆነ፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው ተሿሚና ተቀጣሪ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እየሸሸ በሥልጣን የመጠቀምና ሀብት የማካበት ልድም ውስጥ ተነከረ፡፡ ይህ ለአሁኑ ተሃድሶም ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኗል፡፡

በሙስና ደረጃም በየጉልቱ ችርቸራ ከምትገባዋና ባጃጅና ታክሲ ነድቶ ከሚውለው ጀምሮ እስከ ቱባው ባለሀብት ደረጃ የዕለት ቋንቋ ሆነ፡፡ በእርግጥ ለሙስና መባባስ ራሱ ማኅበረሰቡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ተሸካሚ መሆኑ የፈጠረው ጫና ቢኖርም፣ መንግሥትም ችግሩን ለመታገል የፖለቲካ ቁርጠኝነትን አጣ፡፡

በተለይ የመንግሥትን ሥልጣን የያዙ ቱባ ባለሥልጣናትና ሕገወጥ ደላሎች  (ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶች) በፈጠሩት መስተጋብር ንፋስ አመጣሽ ሀብታሞች በየቦታው ተቀፈቀፉ፡፡ ግብር ከመደበቅ፣ የጉምሩክና የቀረጥ ነፃ አሻጥር (በብረታ ብረት ማስገባት ብቻ 112 ሕገወጦች ተከሰው ለዓመታት የሕዝብ ጥቅም ማጥፋታቸው እየታወቀ ዕርምጃ መወሰድ እንዳልተቻለ ይነገራል) ጥቂቶች ከልክ በላይ በለፀጉ፡፡ ይህን ሕገወጥ ውድድር መቋቋም ያልቻሉ ነባር ባለሀብቶችም ደቀቁ ወይም ተሰደዱ፡፡

የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን የአገሪቱን ሕዝቦች ‹‹ለምን?›› እያስባለ ያለው የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ልዩ ዞን ያለው የአገር ይዞታም በሙስና ተቸበቸበ፡፡  በየከተሞች የተመደቡ ‹‹ከንቲባዎች›› በሺዎች የሚቆጠሩ ካርታዎችን ከአሻጥረኞች ጋር ሆነው ሸጡ፡፡ ለዘመድና ወዳጆቻቸው አስተላለፉ፡፡ አርሶ አደሩም ላይቀርልኝ እያለ በጥቂት ገንዘብ እየሸጠ (ካሳ እየተቀበለ) ተፈናቀለ፡፡ ጊዜው ሲደርስም ድርጊቱ ተጠራቅሞ አገር የሚያፈርስ የሕዝብ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከትልልቅ ሀብቶች ጀርባ ስማቸው የሚነሳ ባለሥልጣናትና ሸሪኮቻቸው አሉ፡፡ በሥርዓቱም ስም ነግደው ባለሕንፃና ድርጅት የሆኑትም ትንሽ አይደሉም፡፡ አንዳንዱ የደኅንነትና የፀጥታ አካልም የግል ጥቅሙን እያስቀደመ ከብሯል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አብሮ ሲሰርቅ የነበረው ወይም በፍርኃትና በአድርባይነት ድምፁን አጥፍቶ የከረመው ቀሪው ደግሞ ‹‹የእዕገሌ ሀብት›› እያለ ጣቱን እየቀሰረ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ የገዘፈ ፈተና ባለበት ወቅት ነው የከረመ ቆሻሻ በረት ለመጥረግ ‹‹ሙስናን እታገላለሁ›› የሚል የመንግሥት ጩኸት የሚሰማው፡፡ ፈተናው ግን ‹‹ማን ማንን?›› ለመታገል ይችላል ሲባል ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት በእውነት የሕዝብን ድጋፍና አጋርነት ከፈለገ ግን የሚከፈለውን መስዕዋትነት ሁሉ ከፍሎ ዋና ዘራፊዎችን ማጋለጥ፣ ከዚህም በላይ የመልካም አስተዳደር መሠረት ለመገንባት የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን ነፃነትና ጥንካሬ መፍቀድ ያስፈልጋል፡፡ የሚዲያ ነፃነትም መጠናከር አለበት፡፡

አሁን ኢሕአዴግ ሥልጣን የግል ጥቅምን ማባረሪያ አይደለም እንደሚለው ሁሉ፣ በተግባርም የማይነቃነቅ መርህ ያስፈልጋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በመንደር ልጅነት፣ በኔትወርክና በታዛቢነት መሿሿም ሊቆም ግድ ይለዋል፡፡ ብቃት፣ ሥነ ምግባርና አገር ወዳድነት ቀዳሚ የሕዝብ ኃላፊነት መመልመያ መሆንም አለባቸው፡፡

ይህ መሆን ሲጀምር ደግሞ ሲቪል ሰርቪሱና ሕዝቡን በቀጥታ የሚያገለግለው ኃይልም የባለቤትነት ስሜት ይኖረዋል፡፡ ‹‹እነ እገሌ እየበሉ. . .›› እያለ ከመቆዘም ወጥቶም ለህሊናውና ለሕዝቡ መሥራትን ያስቀድማል፡፡ መርህ ሲከበርም ተደፋፍሮ ሌብነትን ያጋልጣል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትንም ‹‹እሺ!›› ብሎ ከመቀበል ይላቀቃል፡፡

በዚሁ እሳቤ መንግሥት ‹‹መዋቅሩን ላስተካክል›› ሲል ከመዲናዋ መጀመር አለበት፡፡ በሺዎች የሚቆጠር ሕገወጥ ገንቢ መሬት ወሮ መብራትና ውኃ እንዲገባለት እየተደረገ ለዓመታት ከተበዘበዘ በኋላ ‹‹ይፈረስ›› እያለ ሕዝብ የሚያስለቅስ ቡድን መራገፍ አለበት፡፡ በትልልቅ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችና የመንገድ ሥራዎች ያለ ጨረታና በድርድር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲፈቅድ የከረመ ተጠርጣሪ ሁሉ ሊፈተሽ ግድ ይለዋል፡፡ እንደ ወርቅ የተወደደውን የአገሪቱ መሬት የቸበቸበና ያስቸበቸበም እንዲሁ. . .

በአጠቃላይ የዶ/ር ሙላቱ ተሾመን የመራሔ መንግሥት ንግግር በተስፋ ማየት ጥሩ ሆኖ ከፊት ያለው ገደል ሲታይ ግን ትግበራው መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥትም ሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ተነስተው ለለውጥ መነቃነቅ አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን ንግግሩን ወደ ተግባር ለመውሰድ የሚገጥመው ተቃርኖ ከውቅያኖስም የሰፋ ነው ባይ ነኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...