Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየአገራችን የፖለቲካ ቀውስ መንስዔና መፍትሔ - በምክንያታዊ ዓይን

የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ መንስዔና መፍትሔ – በምክንያታዊ ዓይን

ቀን:

ክፍል አንድ

  • በልደቱ አያሌው

በአሁን ወቅት በአገራችን የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ለብዙዎች ድንገተኛና አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ በእርግጥ ለአንዳንዶቻችን ክስተቱ አሳዛኝ ቢሆንም ድንገተኛና አስደንጋጭ ግን አልሆነም፡፡ እኔም ሆንኩ አባል የሆንኩበት ኢዴፓ በአንድ በኩል በተገቢው ወቅትና ሁኔታ ራሱን ማደስ ወይም መለወጥ የማይችል ማንኛውም መንግሥት የመጨረሻ ዕጣ ፋንታው በዚህ ዓይነት አስቀያሚ ሁኔታ ማለትም በአብዮትና በጠመንጃ ከሥልጣን መውረድ መሆኑን ስለምንገነዘብ፣ በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነቱ አስቀያሚ የለውጥ ሒደት በአገራችን እንዳይከሰት በማሰብ የጽንፈኝነት ፖለቲካ ተወግዶ ምክንያታዊ የፖለቲካ ባህል በአገራችን እንዲፈጠር ለብዙ ዓመታት ያለ አድማጭ ስንጮህ ስለኖርን፣ ለእኛ የወቅቱ ክስተት የሚጠበቅ አሳዛኝ ክስተት እንጂ ድንገተኛና አስደንጋጭ አልሆነም፡፡

የሆነ ሆኖ በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ፣ የሚመጣው ለውጥ ግን የአገርን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የማያስገባና እንዳለፉት የአገራችን የመንግሥታት ለውጦች አንድን ገዥ በሌላ ገዥ የሚተካ ሳይሆን፣ እውነተኛ የሥርዓትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲሆን ለምንፈልግ ኃይሎች የወቅቱ ክስተት አስቸጋሪ አጣብቂኝ (Dilemma) ውስጥ የከተተን መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገባነው ያለምክንያት ሳይሆን በአንድ በኩል በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት በእውነተኛ የሕዝብ ምርጫ ሥልጣኑን ለማጋራትም ሆነ ለመልቀቅ ፈቃደኛ የማይሆን አምባገነናዊ መንግሥት መሆኑን  ከተግባራዊ ልምዳችን ጠንቅቀን ስለምናውቅ በሰላማዊ የሕዝብ ትግል ተገዶ ለውጥን እንዲቀበል እንፈልጋለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በድርጅትና በመርህ ሳይሆን በስሜት፣ በምሬትና በጥላቻ እየተመራ ያለው ያልተቀናጀ የሕዝብ ትግል መንግሥትን ከሥልጣን ከማውረድ አልፎ ጭራሹንም መንግሥትና አገር አልባ ሊያደርገን ይችላል የሚል ከተጨባጭ ምክንያት የመነጨ ሥጋት ስላለን፣ የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶናል፡፡

መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካና በድርጅታው ጥንካሬ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተዳከመበት ወቅት ቢሆንም፣ ከፀጥታ ኃይሉ አንፃር ግን ገና ያልተዳከመ ጉልበት ስላለው  የወቅቱን ቀውስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ቢሆን ለጊዜው ሊቆጣጠረው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ችግሩን ከምንጩ የሚያደርቅ አስተማማኝ መፍትሔ እስካልመጣ ድረስ ችግሩ ጊዜ እየጠበቀ በማመርቀዝ በአንድ ወቅት (ምናልባት በጥቂት ዓመታት ውስጥ) ከቁጥጥር ውጪ መውጣቱ አይቀርም፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት የተከሰተውን ቀውስ አስመልክቶ እያራመደው ያለውን አቋም በጥልቀት ካየነው  የችግሩን መሠረታዊ ምንጭ በአግባቡ ሊረዳው አልቻለም፣ ወይም አልፈለገም፡፡ በዚህም ምክንያት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምንጩ የሚያደርቅ የመፍትሔ አቅጣጫ መያዝ አልቻለም፡፡ በመንግሥት በኩል የችግሩ መንስዔ ተደርጎ እየተወሰደ ያለው በዋናነት በመንግሥት አመራር ዙሪያ የሚታይ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዘ የአፈጻጸም ድክመትና የኢኮኖሚ ዕድገቱ የፈጠረው የሕዝብ የበለጠ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ሲሆን፣ በመፍትሔነት የተቀመጠው አቅጣጫ ደግሞ (ገና በዝርዝር የቀረበ ባይሆንም) በጥቅሉ ሲታይ ጥልቅ ተሃድሶ በማካሄድ ኢሕአዴግን እንደገና ጠንካራ ድርጅት ማድረግና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚል ነው፡፡

ከዚህ የኢሕአዴግ አመለካከት የሚመነጨውን ዝርዝር ጉዳይ ገና የምናየው ቢሆንም፣ በችግሩ ምንነትም ሆነ መፍትሔነት ከተቀመጠው ከዚህ አጠቃላይ ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ግን ኢሕአዴግ ያተኮረው ችግሩን ለጊዜው ማስታገስ በሚያስችሉና ጊዜ በሚገዙ መለስተኛ ጉዳዮች ላይ እንጂ፣ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈቱ በሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በችግሩ ምንጭነት በዋናነት የሚጠቅሰው ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ቢሆንም በእኔ አመለካከት ግን መሠረታዊ የችግሩ ምንጭ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ለወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ ያበቁን ዋናዎቹ ምክንያቶች የፖሊሲ ስህተት፣ ከፍተኛ የመፈጸም ብቃት ማነስ፣ ሥር የሰደደ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትና ትምክህተኛነት ናቸው፡፡

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝ የሚችለውም ኢሕአዴግ እንደሚለው ኢሕአዴግን በጥልቀት በማደስ ብቻ ሳይሆን፣ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነውን ሕዝብና የሕዝቡን አስተሳሰብ  በየደረጃው ሊወክሉ የሚችሉ ሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የለውጥ ሒደቱ ሙሉ ተሳታፊና ባለቤት በማድረግ ጭምር ነው፡፡ የአገሪቱን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በእኔና በእኔ አስተሳሰብ ብቻ ነው የሚለው የኢሕአዴግ የትምክህት አመለካከት ጊዜው ያለፈበት ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት መሆኑን የወቅቱ የሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በግልጽ አሳይቷል፡፡ ኢሕአዴግ እስካሁን በለመደው መንገድ ሕዝብን እየገዛ ሊቀጥል እንደማይችል፣ ይህንን ተገንዝቦ ወደ እውነተኛ የለውጥ መንገድ  በአስቸኳይ መግባት ካልቻለ ራሱንም ሆነ አገሪቱን ወደ ከፍተኛ አደጋ ይዞ በመግባት ያለፉትን ሥርዓቶች ታሪክ ለመድገም እንደተዘጋጀ የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ስለዚህ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ አገሪቱ ወደ እዚህ ዓይነት የተካረረ ቅራኔ ውስጥ የገባችበትን ምክንያት በዝርዝር ለማሳየትና በአሁኑ ወቅት ከፊታችን ከተጋረጠብን አደጋ አሻግሮ ወደ ዘላቂና አስተማማኝ የለውጥ ሒደት ውስጥ ሊያስገባን የሚችለው የመፍትሔ አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት እንደ አንድ የፖለቲካ ተሳታፊ የሆነ ዜጋ በግሌ ያለኝን አመለካከት ለማጋራት ነው፡፡

የችግሩ መሠረታዊ ምንጭ ምንድን ነው? የመፍት አቅጣጫውስ?

ለወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ በዋናነት የዳረገን ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ የመነጨ ድክመት ቢሆንም፣ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብቸኛ የችግሩ ምንጮች ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ በእኔ አመለካከት መጠኑ ቢያንስም በተቃዋሚው የፖለቲካ ጎራና በሕዝባችን ውስጥ ያሉ ከፖለቲካ ባህል ጋር የተያያዙ ድክመቶችም የችግሩ ምንጭ አካል ናቸው፡፡ ስለዚህ በቅድሚያ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ፣ ቀጥሎ በተቃዋሚው ጎራና በሕዝባችን ዙሪያ የሚታዩትን ችግሮች ከነየመፍትሔ አቅጣጫቸው በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ለማየት እንሞክር፡፡

 የአሸናፊዎች ሕገ መንግሥት

ከአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ጋር በተያያዘ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን መሠረታዊ የአገራችንን የፖለቲካ ቅራኔዎች ለመገንዘብ ከሞከርን፣ መሠረታዊው ቅራኔ የአገሪቱን ማዕከላዊ የፖለቲካ ሥልጣን በተቆጣጠረው ኃይል (Center) እና ከፖለቲካ ሥልጣን ርቆ በሚገኘው ተቀናቃኝ ኃይል (Perfery) መካከል ያለ ቅራኔ ነው፡፡ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ለሥልጣን የበቁበትን የ1983 ዓ.ም. ፖለቲካዊ ሁኔታም ካየን ከመቶ ዓመት በላይ ከሥልጣን ርቆ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የነበረው የዳሩ ኃይል በማዕከላዊው የፖለቲካ ኃይል ላይ ያገኘው ድል ነው ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ የኃይል ሚዛን ውስጥ የ1983 ዓ.ም. ለውጥ በዋናነት የመራው ሕወሓት ከማዕከልና ከዳር (Center-Perfery) የኃይል አሰላለፍ ረገድ ጣምራ ሚና ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ሕወሓት የመነጨበት የትግራይ አካባቢ ላለፉት መቶ ዓመታት ከፖለቲካ ሥልጣን ርቆ የዳር አገርነት የተቀናቃኝ ሚና የነበረው ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከሌሎች የዳር አገር ተቀናቃኝ ኃይሎች በተሻለ የፖለቲካ ሥልጣን ማዕከልነት ሚና የነበረው አካባቢ ስለሆነ በሕገ መንግሥቱና በፌደራል አደረጃጀቱ አማካይነት ኢትዮጵያዊነትን በራሱና በአጋሮቹ ምልከታ እንደገና ሊተረጉመውና ሊቀርፀው ቢሞክርም ሙሉ በሙሉ ሊያፈርሰው ግን አልፈለገም፡፡

ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ኢትዮጵያ ኤርትራንና የባህር በሯን ቀይ ባህርን ያጣች፣ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት የበለጠ ትኩረት የምትሰጥ ግዛትዋ ያነሳና ውስጣዊ አንድነቷ የላላ አገር ብትሆንም፣ ቢያንስ ግን በአካባቢው የተሻለ ጠንካራ መንግሥትና አንፃራዊ ሰላም ያላት አገር ሆና መቀጠል ችላለች፡፡ በ1983 ዓ.ም. ለውጥ የሕወሓትን ሚና የያዙት ሌሎች የማዕከሉን ሥልጣን ተጋሪ ሆነው የማያውቁ የዳር አገር ተቀናቃኞች ቢሆኑ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የበለጠ ከመዳከም አልፋ አጠቃላይ ሕልውናዋን ልታጣ የምትችልበት አደጋ ሊፈጠር ይችል ነበር፡፡

ነገር ግን ሕወሓት ከመጀመርያው ጀምሮ ኢትዮጵያን አንድ አድርጌ ለመግዛት እችላለሁ የሚል የተሟላ በራስ መተማመን ስላልነበረው በውስጡ የነበረውን ጥርጣሬና ሥጋት የሚያንፀባርቁ ሕግጋቶችና አሠራሮች በሕገ መንግሥቱና በፌደራል አደረጃጀቱ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ አገሪቱን የዜጎች  ሳይሆን የቡድኖች (ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) አገር ያደረገው ድንጋጌ፣ ቋንቋንና ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት ያደረገው የፌደራል አደረጃጃትና ለእነዚህ የአገሪቱ ባለቤቶች እንዲሆኑ ለተደረጉ ቡድኖች የተሰጠው የመገንጠል መብት የሕወሓትና የአጋሮቹ ጥርጣሬና ሥጋት መገለጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከእንግዲህ ያሸነፍነው ማዕከላዊ የፖለቲካ ኃይል ወደ ሥልጣን ተመልሶ  መምጣት የለበትም  ብቻ ሳይሆን፣ ተመልሶ መጥቶ ሊገዛን ከሞከረም የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ መፈረካከሰ እናደርገዋለን በሚል የጠባብነት አመለካከት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የአገራዊ መግባባት መገለጫ ሳይሆን የአሸናፊነት መገለጫ ሰነድ አድርገውታል፡፡ በዚህ ምክንያት በሥልጣን ላይ የነበረው ማዕከላዊ የፖለቲካ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ የዚህ ኃይል ማኅበራዊ መሠረት የነበረው አካባቢ ሕዝብ ከፍተኛ የተሸናፊነት ስሜት እንዲሰማውና ሕገ መንግሥቱንና የፌደራል አደረጃጀቱን አገሪቱን የማዳከሚያና የማፍረሻ ሥልት አድርጎ በጥርጣሬ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በተለይም የራሱን ማንነት ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አንድና አንድ አድርጎ የማየት ሥነ ልቦና ያለው የአማራው ሕዝብና ከተለያዩ ብሔረሰቦች ተቀይጠው የተፈጠሩ የከተማ ነዋሪዎች ሥርዓቱን ከመጀመርያው በሙሉ ልባቸው የጋራችን ሥርዓት ነው ብለው እንዳይቀበሉት አድርጓቸዋል፡፡ በእኔ እምነት ቀደም ሲል በአገሪቱ አንዳንድ ከተሞች፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአማራው ክልል የተከሰተው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተለያዩ ወቅታዊና አካባቢያዊ ብሶቶች ሲቀባባ ቢታይም፣ በዋናነት ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት የኔ ሥርዓት ነው ብሎ ካለመቀበል የመነጨ ነው፡፡ የዚህ ሕዝብ የተቃውሞ ሥረ መሠረት በዋናነት ከሕገ መንግሥቱና ከፌደራል አደራጃጀቱ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ በሒደት የተከሰቱ የሥርዓቱ ግፍና በደሎች አባብሰውት ዛሬ  የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

ኢሕአዴግ በሕገ መንግሥቱና በፌደራል አደረጃጀቱ አማካይነት የማንነት ጥያቄን መልሻለሁ ቢልም መመለስ የቻለው በራሱ መነጽር ብቻ ማየት የቻለውን የራሱን የማንነት ጥያቄ ብቻ ነው እንጂ፣ ማንነቱን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አንድና አንድ አድርጎ የሚያየውን በብዙ ሚሊዩኖች የሚቆጠረውን ሕዝብ ስሜትና ፍላጎት  ግን በጥቅሉ በትምክህተኛነት አመለካከት በመፈረጅ ጨፍልቆት አልፏል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ በብቸኝነት ሲራመድ የኖረው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ሥልትም ለዚህ የኢትዮጵያዊ ማንነት ቦታ የነፈገም ብቻ ሳይሆን፣ ማንነታቸውን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አያይዘው የሚያዩ ዜጎችን የሚያንቋሽሽና የሚያወግዝ ነበር፡፡

የማንነት ጥያቄን ከኢሕአዴግ ቁንጽል ትንታኔ ወጣ ብለን ለማየት ከሞከርን ግን፣ ማንነት እንደያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን እንደያንዳንዱ የአገር ዜጋ የግል ስሜትና ፍላጎት ሊተረጎም የሚችል ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ነገር ግን ላለፉት 40 ወይም 50 ዓመታት በአገራችን ከነበረው የፖለቲካ ውዝግብ (Discourse) አኳያ ማንነትን በሚመለከት ያሉት መገለጫዎች በዋናነት ሁለት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት መገለጫዎች ከፍ ሲል ልገልጸው ከሞከርኩት የማዕከልና የዳር (Center-Perfery) የፖለቲካ ተቀናቃኝነት ጋር ተዛምደው ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ላለፉት መቶ ዓመታት ማዕከላዊውን የፖለቲካ ሥልጣን ተቆጣጥሮ የኖረው የፖለቲካ ኃይልና በእሱ የማንነት ትንታኔ ተቀርፆ ያደገው የኅብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያዊ ማነንትን ከሁሉም በላይ ገዥ አስተሳሰብ አድርጎ የሚያይና ከዚያ ውጪ ያሉ ከብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎችን ግን አሳንሶ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሉና የማይጠቅሙ አድርጎ የሚያይ  ነው፡፡ ይህ ኃይል እስካሁን ድረስ ተገዶ ካልሆነ በስተቀር በመታወቂያ ካርዱ ላይ ብሔረሰባዊ ማንነቱ እንዲጻፉ ፍላጎት የሌለው መሆኑን እየገለጸ ያለ ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት ከሥልጣን ተገልሎ የኖረው የዳሩ ኃይል ከብሔር ወይም ከብሔረሰብ ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎችን ቀዳሚ የማንነት ጥያቄ በማድረግ፣ ኢትዮጵያዊነትን ግን በሌሎች ተፅዕኖና ሚና የተሸከመው ዕዳ አድርጎ የሚያይ ነው፡፡ ይህ ኃይል ብሔረሰባዊ ማንነቱን ከኢትዮጵያዊነት አስቀድሞ ስለሚያይ፣ ኢትዮጵያዊነትን በድርድር የሚያዝ አገራዊ ስያሜ እንጂ ከነጭራሹም ማንነት አድርጎ አያየውም፡፡ በአጭሩ የማዕከሉ ኃይል የዳሩን ኃይል አስተሳሰብ ‹‹ጠባብነት›› አድርጎ የሚፈርጀው ሲሆን፣ የዳሩ ኃይል ደግሞ የማዕከሉን ኃይል አስተሳሰብ ‹‹ትምክህተኛነት›› አድርጎ ይፈርጀዋል፡፡ ይህንን ዓይነት የማንነት ትንታኔ ተከትሎ የሚመጣ ፍረጃ ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት በአገራችን ዋና የፖለቲካ ቅራኔ መገለጫ ሆኖ ኖሯል፡፡

ጠባብነትና ትምክህተኛነት አሉታዊ ትርጓሜ ያላቸው የትችት መሰናዘሪያ ቃላት ሆነው ጥቅም ላይ ቢውሉም፣ ዞሮ ዞሮ ከማንነነት ጥያቄ ጋር የተያያዘው የአገራችን የፖለቲካ ቅራኔ በሁለቱ ጽንፍ ውስጥ ያለ ነው፡፡ የሁላችንም አመለካከት በተወሰነ ደረጃ ሊከርና ሊላላ፣ ወይም ሊጠብና ሊሰፋ ቢችልም የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ከእነዚህ ሁለት (የጠባብነትና የትምክህተኛነት) ፍረጃ ሊወጣ የሚችል አይደለም፡፡ ራሳችንን በዚህ መልክ ዓይተን ላናውቅ ብንችልም በወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ አስተሳሰብ አሰላለፍ አንዳችን ለሌላችን ‹‹ጠባብ›› ወይም ‹‹ትምክህተኛ›› ነን፡፡ አሉታዊ ትርጓሜውን ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን ጠባብነትና ትምክህተኛነት በአገራችን ያለውን ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ቅራኔ የሚያሳዩ መገለጫዎች አድርገን ብናያቸው፣ የወቅቱ የአገራችን ሕገ መንግሥትና የፌደራል አደረጃጀት ጠባብነት በትምክህተኛነት ላይ ድል ማግኘቱ የተረጋገጠበት ሒደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑ በ1983 ዓ.ም. የመጣው የሥርዓት ለውጥ ቅራኔውን የአሸናፊነትንና የተሸናፊነትን ቦታ አቀያይሮ አስቀጠለው እንጂ ከቶውንም አላስቀረውም፡፡ ቅራኔው ሊታረቅ ይችል የነበረው ኢሕአዴግ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ የአንዱ ጎራ አስተሳሰብ ከሌላው ጎራ አስተሳሰብ ያነሰ ወይም የበለጠ፣ ትክክል ወይም ስህተት እንዳልሆነ ተገንዝቦ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና የፌደራል አደረጃጀት የጠባብነትና የትምክህተኛነት አመለካከት ሚዛን በጠበቀ አግባብ ተቻችለው እንዲስተናገዱ ቢያደርግ ነበር፡፡

በኢሕአዴግ ብቻም ሳይሆን በሁለቱም ጎራዎች ያለው መሠረታዊ ስህተት አንዱ የሌላውን የማንነት አመለካከት ስህተት አድርጎ በማየት የራሱን አስተሳሰብ በሌላው ላይ ለመጫን መሞከሩ ነው፡፡ ነገር ግን ማንነታችንን የምንገልጽበት አመለካከት እንደዚሁ ስለፈለግነው በውሳኔ የያዝነው አመለካከት ሳይሆን ከቤተሰባችን፣ ከአካካቢያችን፣ በአጠቃላይም ከኖርንበት ማኅበረሰብና ሥርዓት ጋር በተያያዘ ተቀርፀን ካደግንበት እውነታ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በማሸነፍና በመሸነፍ ወይም በማሳመንና በማመን ሊቀየር የሚችል አይደለም፡፡ አንድ ወለጋ ውስጥ ያደገ ኦሮሞ ከአንድ ጎንደር ውስጥ ካደገ አማራ፣ አንድ ሐመር ውስጥ ያደገ ዜጋ አንድ አዲስ አበባ ውስጥ ካደገ ዜጋ፣ አንድ ኦጋዴን ውስጥ ያደገ ሶማሌ ከአንድ ዓድዋ ውስጥ ካደገ ትግሬ ጋር የማንነት ጥያቄን በተመለከተ አንድ ዓይነት ወጥ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ መፍትሔው ይህንን እውነት ባለበት ተቀብለን በእኩልነትና በአንድነት አብሮ ሊያስኖረን የሚያስችል የጋራ ቀመር (Common Ground) መፈለግ ነው እንጂ፣ በአሸናፊነትና በተሸናፊነት መንገድ ችግሩን ልንፈታው አንችልም፡፡

በሕገ መንግሥቱና በፌደራል አደረጃጀታችን ውስጥ ያለውን ይህንን መሠረታዊ ጉድለት ሳንፈታ ሕገ መንግሥቱን እንደ ምሉዕ ሰነድ ወስደን ማባሪያ በሌለው የሰላምና የዴሞክራሲ ኮንፈረንስ፣ ወይም የምሁራን ትንታኔ የአንዳችንን ማንነት በሌላው ላይ ለማስረጽ መሞከር የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን የማንነቱ ዋና መገለጫ አድርጎ የሚያየውን ሕዝብ ማሳመን የሚቻለው በሕገ መንግሥቱና በፌደራል አደረጃጀታችን ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ጉዳይ ዋስትና እንዳገኘው ሁሉ፣ ለኢትዮጵያዊ ማንነትም አስተማማኝ ዋስትና በመስጠት ነው እንጂ በማስረጽ ዘመቻ አይደለም፡፡ ፌደራላዊ አደረጃጀት ለአገራችን አስፈላጊ መሆኑና የብሔር ብሔረሰቦች መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ቀጣይነትና ኢትዮጵያዊ ማንነትም በዚያው መጠን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘት አለበት፡፡ ይህ መሠረታዊ የአገሪቱ ከፊል ሕዝብ ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መልስ ሳያገኝ የአገራችን የፖለቲካ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ብሎ ማሰብም ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱ ያለበት ችግር የአፈጻጸም ችግር ነው ከሚለው ጠባብ የአሰተሳሰብ ሳጥን ወጣ ብሎ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም የማድረግ መፍትሔም ማሰብ አለበት፡፡

እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎቹ በአሁኑ ወቅት ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን እንዲያሻሽለው ለምን ይጠየቃል? ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጉዳይ ለምን ወደፊት በሕዝብ ምርጫ ኢሕአዴግን ለሚተካው መንግሥት አይተውም የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ በአንድ በኩል ኢሕአዴግ የማላምንበትን ሕገ መንግሥት ለምን አሻሽለዋለሁ ብሎ ሊያስብ ስለሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚው ጎራ ቀዳሚው ጥያቄ የኢሕአዴግ ከሥልጣን መውረድ እንጂ የሕገ መንግሥቱ መሻሻል አይደለም ብሎ ከማሰቡ ሊነሳ ይችላል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸው መስለው ቢታዩም፣ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጥያቄ መነሳትም ሆነ መልስ ማግኘት ያለበት በኢሕአዴግ ዘመን እንዲሆን የሚመረጥበት አንድ እውነት መኖሩን ግን ማወቅ አለብን፡፡

የወቅቱ የአገራችን ሕገ መንግሥት የተቀረፀው ኢሕአዴግን በምርጫ የሚተካው መንግሥት እንዳያሻሽለው ተደርጎ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል የሚችለው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የጋራ ይሁንታ ብቻ ስለሆነ ሁሉንም ክልሎች ከኢሕአዴግና ከአጋር ድርጅቶቹ ቁጥጥር ውጪ የሚያደርግ የምርጫ ውጤት እስካልተገኘ ድረስ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል አይችልም፡፡ የሁሉንም ክልሎች ይሁንታ ሳያገኝ ለመንግሥትነት የሚበቃ ፓርቲ ከሕገ መንግሥታዊው አካሄድ ውጪ ሕገ መንግሥቱን በተፅዕኖ ወይም በኃይል ለማሻሻል ከሞከረም ሊከተል የሚችለው ውጤት የአገር መፈራረስ ይሆናል፡፡ ይህንን እውነታ ግምት ውስጥ በማስገባት ራሱንና አጋር ድርጅቶቹን አሳምኖ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ታሪካዊ ኃላፊነት በኢሕአዴግ እጅ ያለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሆን ብሎ እንዳይሻሻል አድርጎ የቀረፀውን ሕገ መንግሥት ራሱ እንዲሻሻል የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢሕአዴግ ባለፉት 25 ዓመታት የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታም ሆነ የኃይል አሰላለፍ በይዘትም ሆነ በቅርፅ እየተቀየረ መምጣቱን አውቆ የሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ይዘት ከወቅታዊ ሁኔታዎቻችን ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እየተፈጠረ ያለው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ በግልጽ እየታየ የመጣና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዛሬ 25 ዓመት ከነበርንበት ሁኔታ በተለየ ጠባብነትና ትምክህተኛነት ቦታ ተቀያይረዋል፡፡ የጠባብነት አጀንዳ ይዞ ለሥልጣን የበቃው ኢሕኢዴግ የዛሬ ቁንጮ ትምክህተኛ፤ በትምክህተኛነት አመለካካት ሲከሰስና ሲወገዝ የኖረው ተቃዋሚው ጎራ ደግሞ የጠባብነትን አጀንዳ የራሱ አድርጎ በመውረስ ሥርዓቱን የማፈራረሻ መሣሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት እያየን ነው፡፡ የጠባብነትና የትምክህተኛነት አመለካከት ቦታ እየተቀያየሩና አሸናፊና ተሸናፊ እየሆኑ አገር የሚያፈራርሱበትን ሒደት የሚያስቆም የሕገ መንግሥት ማሻሻያን አሰፈላጊና ወቅታዊ የሚያደርገውም ይኸው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡

ሌላው ከሕገ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ የመወያያ ነጥብ መሆን ያለበት ጉዳይ የፓርቲዎች የብሔር አደረጃጀት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአገሩን ባለቤቶች ዜጎች ሳይሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሆኑና የአገሪቱ ፌደራላዊ አደረጃጀት መሥፈርት በዋናነት ቋንቋ እንዲሆን ያስገደደው፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የተደራጁት አገራዊ አስተሳሰብን መሠረት አድርገው ሳይሆን ብሔረሰባዊ ማንነትን መሠረት አድርገው በመሆኑ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ይዘትም ሆነ የፌደራል አደረጃጀቱ መሥፈርት በዋናነት እንዲጣጣም ተደርጎ የተቀረፀው ከአገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ጋር ሳይሆን ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብሔረሰባዊ አደረጃጀት ጋር ነው፡፡ ይህ በአሸናፊው ኃይል የተመረጠ አደረጃጀት አገራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ከሥርዓቱ ልዩ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ ከዚህ በተፃራሪ የመሀል አገሩ ሕዝብ ምርጫ የሆነው ኅብረ ብሔራዊ የፓርቲ አደረጃጀት ግን እንደ ትምክህተኛነት መገለጫ ተቆጥሮ የትችትና የጥቃት ዒላማ ሆኖ ኖሯል፡፡ ኢሕዴንም ከኢትዮጵያዊ ድርጅትነት ወደ አንድ ብሔር ድርጅትነት ተቀይሮ የአማራ ሕዝብ ወኪል እንዲሆን የተደረገው፣ የአማራው ሕዝብ የብሔር አደረጃጀትን ስለመረጠ ሳይሆን ወደደም ጠላም የግድ ከሕገ መንግሥቱና ከፌደራል አደረጃጀቱ ጋር ተጣጥሞ እንዲደራጅ ስለተፈለገ ነው፡፡

በእኔ አመለካከት ሕዝቡ ከአካባቢያዊ ጉዳዮች ባለፈ በወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታው ላይ እንዳያተኩርና አገሪቱም ወደ አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ እንዳትሸጋገር ያደረጋት ብሔረሰባዊ አደረጃጀት የሥርዓቱ ተመራጭ አስተሳሰብ መሆኑ ነው፡፡ በብሔር ወይም በብሔረሰብ ማንነት መደራጀት አንዳንድ አገሮች እንደሚያደርጉት ሕጋዊ ዕገዳ ሊጣልበት ይገባል ብዬ ባላምንም፣ ከብሔር አደረጃጀት ይልቅ አገራዊ አጀንዳን መሠረት ያደረገ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት በአገራችን የበለጠ ትኩረትና ቦታ ቢያገኝ  አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ የመፍጠር ፍላጎታችንን በተሻለ ፍጥነትና ሁኔታ ሊያሳካው ይችላል፡፡

አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ በመፍጠር የኢትዮጵያን ህዳሴ አሳካለሁ የሚለን ኢሕአዴግ በቅድሚያ ራሱን ወደ አንድ ውህድ የአስተሳሰብ ፓርቲ ሳይቀይር፣ ኢትዮጵያን ወደዚያ የላቀ ደረጃ ሊወስዳት የሚችልበት ዕድል የለውም፡፡ የብሔር አደረጃጀት ገዥ አስተሳሰብ ሆኖ አስከቀጠለ ድረስ የበለጠ ልዩነታችን እየሰፋ እንጂ አንድነታችን እየጠነከረ ሊመጣ አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን እንደሚታየው መቼም ቢሆን ይቆማል ተብሎ በማይታሰብ ሁኔታ ቀበሌዎች ወረዳ፣ ወረዳዎች ዞን፣ ዞኖች ክልል፣ አንዳንድ ክልሎችም አገር ለመሆን እያቀረቡት የሚገኘው አታካች ጥያቄ እያሳየን ያለው በአገራችን የሕዝቦች አንድነት ሳይሆን ልዩነት የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን ነው፡፡ 

ሕገ መንግሥት እንጂ ሕገ መንግሥታዊነት የሌለው ሥርዓት

ከፍ ሲል ለመግለጽ  እንደሞከርኩት ማዕከላዊው ኃይል ሕገ መንግሥቱን ከጅምሩ የኔ ነው ብሎ ያልተቀበለው ቢሆንም፣ አሸናፊው የዳር አገሩ ኃይል ግን ሕገ መንግሥቱን ከጅምሩ የራሱ አድርጎ ተቀብሎት ነበር፡፡ ይህ ኃይል ከእንግዲህ በኋላ የመብት ጥያቄዬ በሌሎች ኃይሎች እንዳይሸራረፍና እንዳይታፈን ሕገ መንግሥቱ ዋስትና  ሰጥቶኛል ብሎ በማመን ራሱን የሕገ መንግሥቱ ጠባቂና ባለቤት አድርጎ ማየት ጀምሮ ነበር፡፡ የዳር አገሩ ኃይል ብቻ ሳይሆን ማዕከላዊው ኃይልም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አንቀጾችን አምርሮ ቢጠላም፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች በአግባቡ ከተከበሩ መብቴን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ታግዬ ለመቀየር መሣሪያ ሆነው ሊያገለግሉኝ ይችላሉ የሚል ተስፋ ነበረው፡፡

ነገር ግን በሒደት እንደታየው ሥርዓቱ ሕገ መንግሥት ከማውጣት ባለፈ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሆን ስለተሳነው የማዕከሉንም ሆነ የዳር አገሩን ኃይል፣ ማለትም የአሸናፊውንም ሆነ የተሸናፊውን ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ የፌደራል አደረጃጃቱን እንደራሳቸው አጀንዳ የተቀበሉትን ኃይሎች መብት በፓርቲ ማዕከላዊነትና በሞግዚት አስተዳደር ጠልፎ በመውሰድ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ትርጉም አልባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ዕውቅና እንዲያገኙ ከማድረግም አልፎ ለብሔር ብሔረሰቦች ከአገር እስከመገንጠል የሚደርስ መብት በመስጠት በዓለም ለጋሱ ሕገ መንግሥት ተብሎ የተሞካሽ ቢሆንም፣ በተግባር መሬት ላይ ያለው እውነት ሲታይ ግን ሥርዓቱ ከንጉሡና ከደርግ ሥርዓትም በባሰ ሥልጣን በአንድ ፓርቲ፣ ከዚያም አልፎ በአንድ ግለሰብ ቁጥጥር ሥር የወደቀበት የተማከለ ሥርዓት ሆነ፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ደምቆ የተጻፈው የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እንኳንስ በወጉ ሊከበርና የፖለቲካ ድርጅቶች እየፈጠረ ለሕዝብ የሚያድለው፣ ማናቸውንም ዓይነት የፖሊሲ ውሳኔዎች እየደነገገ በካድሬዎቹ አማካይነት ቁልቁል ወደ ሕዝቡ የማስረጽ ሥራ የሚሠራው አራት ኪሎ የሚገኘው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሆነ፡፡ እንኳንስ ራስን በራስ የማስተዳደርና የመገንጠል መብት መሠረታዊ የሚባሉት የመደራጀትና ሐሳብን የመግለጽ መብቶችም ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉት የገዥውን ፓርቲ ፍላጎትና ጥቅም እስከ ደገፉ ድረስ ብቻ እንደሆነ በገሃድ ታየ፡፡

ለ17 ዓመታት በተካሄደ መራራ ጦርነት ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ታግያለሁ የሚለው ኢሕአዴግ ራሱን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ካቆናጠጠ በኋላ ግን አኒማል ፋርም (Animal Farm) በተሰኘው የጆርጅ ኦርዌል መጽሐፍ ላይ በመሪ ተዋናይነት የሚተውነውን ዓሳማ ዓይነት ሚና መጫወት ጀመረ፡፡ እንኳንስ ሕገ መንግሥቱን ከጅምሩ ያልተቀበሉትን ኃይሎች የሕገ መንግሥቱ ዋና ባለቤትና ተጠቃሚ ናቸው የተባሉትን ኃይሎችም መብት ሳያከብር ቀረ፡፡ በተለያዩ ወቅታዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች እየተቀባባ የሚቀርብ ቢሆንም፣ ላለፉት ዓመታት በዋናነት በኦሮሚያ ክልልና በተለያዩ የአገራችን የዳር አገር አካባቢዎች በመንግሥት ላይ እየቀረበ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በዋናነት የሚመነጨው ሕገ መንግሥቱን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መኖር ካለመቻሉ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ መንግሥትን ከሌሎች ጥቃት ለመከላከልና ሌሎችን ለማጥቃት በመሣሪያነት ጥቅም ላይ የዋለ የፖለቲካ መሣሪያ ከመሆን አልፎ ለሕዝቡ ጥቅምና መብት መከበር ዋስትና ሊሆን አልቻለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ የአገርንና የሕዝብን ዘለቄታዊ አንድነት በማስከበር ረገድ መሠረታዊ ጉድለቶች ያሉበት ሰነድ ቢሆንም፣ አብዛኛው የሕገ መንግሥቱ ክፍል ግን ለሕዝቡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ተገቢውን ዕውቅና የሰጠ ሰነድ በመሆኑ ቢያንስ ከነጉድለቶቹም በአግባቡ በተግባር የሚውልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፣ አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል በጎ ሚና በኖረው ነበር፡፡ ነገር ግን በወረቀት ላይ አምሮና ደምቆ ከመታየት አልፎ ትርጉም ባለው ሁኔታ በተግባር ላይ ሊውል ባለመቻሉ የቡድኖችንም ሆነ የዜጎችን ፍላጎት ማርካት አልቻለም፡፡

በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለሚታየው ብጥብጥና የሰላም ዕጦት ዓይነተኛ መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግሥት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ በምክንያትነት የሚጠቅሳቸው የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም ሕገ መንግሥቱ በይዘት ደረጃ ያለበትን ጉድለትም ሆነ የሕገ መንግሥቱን በአግባቡ ተግባር ላይ አለመዋል በዋና  ምክንያትነት ሊቀበለው አይፈልግም፡፡ በእኔ አመለካከት ግን በሕገ መንግሥቱ ይዞታና ትግበራ ዙሪያ የሚታዩት ችግሮች ራሱ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው አግባብ በሒደት ሊሻሻሉ የማይችሉ ከሆነ፣ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የማዕከሉና የዳሩ የፖለቲካ ኃይሎች ቅራኔዎችም ሆኑ በመንግሥትና በዜጎች መካከል የሚታየው ቅራኔ በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦት

ገዥው ፓርቲ መልካም አስተዳደርን የሚተረጉመው በራሱ መንገድ በቁንጽል ቢሆንም፣ ለወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ችግር ዋናው ምክንያት እንደሆነ አምኖ ይቀበላል፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለመከበር ጉዳይ በአገራችን ዋናውና መሠረታዊው የመልካም አስተዳደር ችግር ቢሆንም ገዥው ፓርቲ በአገራችን የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚተረጉመው በዋናነት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ድክመትና ከሙስና ጋር አያይዞ ነው፡፡ ስለሙስናም ሲያወራ ስለኢኮኖሚያዊ ሙስና እንጂ ለኢኮኖሚያዊ ሙስና መስፋፋት መሠረቱ የፖለቲካ ሙስና መኖር መሆኑን አምኖ መቀበል አይፈልግም፡፡ ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ የተከሰተውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የሚሞክረውና የሚፈልገው መሠረታዊ ምንጩን ማለትም የፖለቲካ ሙስናን  እንደ ዋና ምክንያት ሳይቀበልና ቅንጭብጫቢ አስተዳዳራዊ ችግሮችን በመፍታት ስለሆነ ችግሩን እስካሁን ሊፈታው ይቅርና ሊያቃልለውም አልቻለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ሁልጊዜም ተመሳሳይ  ነገር እያሰበና እየሠራ የተለየ ውጤት ላይ መድረስ የሚፈልግ ግብዝ ኃይል ስለሆነ ከፍተኛ የአገር ገንዘብ በማፍሰስ ለብዙ ዓመታት ያካሄዳቸው ተከታታይ የመዋቅር ማሻሻያዎች በሙሉ ትርጉም ያለው ለውጥ ሳያመጡ ከሽፈዋል፡፡ 

በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሙስና ብዙ መገለጫዎች ያሉት ነው፡፡ ምርጫን ማጭበርበር፣ ሕዝብ ያላመነበትንና ያልመከረበትን ሕግና ፖሊሲ በላዩ ላይ መጫን፣ የተቃውሞ አስተሳሰብ ባላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ የአፈና ድርጊት መፈጸም፣ ነፃና ገለልተኛ የሕዝብ ተቋማትን እያፈረሱ በጥገኛና አድሏዊ ተቋማት መተካት፣ የመንግሥትን ተቋማትና ሀብት ለፓርቲ ጥቅም ማዋል፣ ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመንግሥት የሚገኝን ሥራና ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የፓርቲ አባልና ደጋፊ እንዲሆኑ ማስገደድ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ራስን ለማወደስና ሌሎችን ያለ አግባብ ለማጥላላት መጠቀም፣ ከሕግ ውጪ የፓርቲ የንግድ ድርጅቶን እያቋቋሙ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ማዳከም፣ የገዥውን ፓርቲ ሕልውና እስካልተቀናቀኑ ድረስ የመንግሥት ሹማምንት በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በደል በዝምታ ማለፍ፣  ወዘተ. . .  እነዚህ ሁሉ ላለፉት 25 ዓመታት በዚህ አገር በጠራራ ፀሐይ ሲፈጸሙ የኖሩ የፖለቲካ ሙስናዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ፈርጀ ብዙ የፖለቲካ ሙስናዎች ሲፈጸሙ ዝም ብሎ ማየት ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የበላይነቱ ሲል በካድሬዎቹ አማካይነት እንዲፈጸሙ ሲፈቅድና ሲያዝ የኖረ መንግሥት፣ ዛሬ ካድሬዎቹ ከእሱ የፖለቲካ ሙስና ተምረው የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የኑሮ ሕልውና ለማስጠበቅ ሲሉ የኢኮኖሚ ሙስና ቢፈጽሙ ሊያስገርም አይችልም፡፡ እንደዚህ በፖለቲካ ሙስና የተዘፈቀ መንግሥትም የኢኮኖሚ ሙስናን ተዋግቶ ለማሸነፍ የሚያስችል ሀቀኛ ፍላጎት፣ አቅምና የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡

በዚህም ምክንያት የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለሕዝቡ ብሶትና ምሬት መባባስ አንዱ አንገብጋቢ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሕዝቡ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች አድማጭና ፈጻሚ የመሆን እንጂ ትርጉም ያለው የተሳትፎ መብት የለውም፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ የመንግሥት ሹማምንትን የመምረጥና ሰብዓዊ መብቱን ከጥቃትና ከአፈና የመከላከል መብቱን በካድሬዎች ተነጥቋል፡፡ ለዓመታት ደጅ ሳይጠና ወይም ጉቦ ሳይሰጥ ጉዳይ ማስፈጸምም ሆነ ፍትሕ ማግኘት ተስኖታል፡፡ የገዥው ፓርቲ አባልና ደጋፊ ካልሆነ በስተቀር በዜግነቱ የሥራ ዕድል ማግኘትም ሆነ በነፃነትና በእኩልነት ነግዶ የመኖር ዕድል ተነፍጎታል፡፡

በአገራችን የተከሰተው የመልካም አስተዳደር ዕጦት እጅግ ጥልቅና ውስብስብ ሲሆን፣ ይህንን ችግር እየፈጠረ ያለው ማንም ውጫዊ ኃይል ሳይሆን ገዥው ፓርቲ ታማኝ አባሎቼና ደጋፊዎቼ ናቸው ብሎ በዙሪያው ባሰባሰባቸው ሰዎች ነው፡፡ ከእነዚህ የአገሪቱን ቢሮክራሲ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ መዋቅር ከተቆጣጠሩት የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ውስጥ የችግሩ ተባባሪ ያልሆኑት ሰዎች ቁጥር ከአራት ወይም ከአምስት በመቶ ሊበልጥ ይችላል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ቁልፍ ጥያቄ እነዚህ ከአራትና ከአምስት በመቶ የማይበልጡ ጨዋ ሰዎች እንዴት አድርገው ከ96 በመቶ በላይ የሆነውን የችግሩ ፈጻሚ ኃይል ታግለው ሊያሸንፉት ይችላሉ? የሚል ይሆናል፡፡ ይህ ኃይል በቁጥር ብዙ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱ በጥቅም የተሳሰረ፣ የመንግሥትን የመዋቅር ማሻሻያ ጥረቶች ሁሉ እያመከነ የማስቀረት ልምድ የተካነና መንግሥትን መፍራትና መታዘዝ ያቆመ ኃይል ስለሆነ በቀላሉ ሊሸነፍ የሚችል አይደለም፡፡ ይህንን ኃይል ማሸነፍ የሚቻለው በግምገማ፣ በማስፈራራትና በመቅጣት ሳይሆን የሥርዓቱ መዋቅራዊ በሽታ የሆነውን የፖለቲካ ሙስና ከሰንኮፉ ነቅሎ በመጣል ነው፡፡

እርግጥ ነው የፖለቲካ ሙስና ሰንኮፍ ከአገራችን ከተነቀለ ኢሕአዴግም ከሥልጣን የመነቀሉ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ ሙስና እስካለ ድረስ ከሥልጣን የመነቀሉ ጉዳይ በሌላ መንገድም የማይቀር በመሆኑ፣ በየትኛው መንገድ መነቀል እንደሚፈልግ ምርጫው የኢሕአዴግ ይሆናል፡፡ የሕዝብን አደራ ከመወጣት፣ በታሪክ ተመስጋኝ ከመሆንና እንደገናም ተመልሶ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚኖርን ዕድል ከማስፋት አኳያ ግን በየትኛው መንገድ ሥልጣን ማጣት እንደሚበጅ ማወቅ ለማንም ሰው ግልጽ ይመስለኛል፡፡

ኢሕአዴግ ይህንን ችግር ከሥረ መሠረቱ ለመፍታት ከፈለገ በዙሪያዬ ያሰባሰብኩት ኃይል ለምን በዚህ መጠን ሕዝብን የሚያንገላታና ሙሰኛ ሆነ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት ከደፈረ የችግሩን ትክክለኛ መፍትሔ ለማግኘትም አይቸገርም፡፡ በእኔ አመለካከት በኢሕአዴግ ዙሪያ የተሰባሰበው ኃይል የዚህ ችግር ሰለባ የሆነው በሌላ ምክንያት ሳይሆን ለመንግሥት ሥራ የሚመለመለውና የሚቀጠረው በችሎታ፣ በዕውቀት፣ በልምድና በሥነ ምግባር መመዘኛ ሳይሆን ለሥርዓቱ ባለው የፖለቲካ ታማኝነት በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ከቀበሌ እስከ ክልል ባለው መዋቅር የመንግሥት ሠራተኛ እየሆነ ያለው ሰው ለኢሕአዴግ ዓላማና ፕሮግራም ፍቅር ኖሮት፣ ወይም ኅብረተሰብን የማገልገል ፍላጎት ኖሮት፣ ወይም ለኑሮው በቂ ደመወዝና ጥቅም ስለሚያገኝ አይደለም፡፡ እውነቱን በግልጽ መነጋገር ካለብን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት ሠራተኛ እየሆነ ያለው አብዛኛው ሰው በደመወዙ ሳይሆን በሙስና ኑሮውን እየደጎመ ለመኖር የሚፈልግ፣ ወይም የተሻለ አማራጭ እስከሚያገኝ ለጊዜው መቆያ የሚሆን ሥራ የሚፈልግ፣ ወይም ከመንግሥት ሥራ ውጪ የመቀጠር ዕድል የሌለውና በትምህርት ደረጃውና በሥራ ብቃቱ ደካማ የሆነ ሰው ነው፡፡

በገጠር አካባቢም በአብዛኛው የኢሕአዴግ ካድሬ እየሆነ የሚገኘው ወጣት እርሻና ትምህርት ጠል የሆነው ሲሆን፣ አብዛኛውን የኢሕአዴግ የአመራርነት ቦታ የያዙት ደግሞ ኑሯቸውን ለማሻሻልና ለማደግ ሌላ የሕይወት መንጠላጠያ መሰላል ያጡ የገጠር መምህራን ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ከ97 ምርጫ በኋላ በሠልፍ የኢሕአዴግን መዋቅር የተቀላቀሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በቅንጅት ዙሪያ ሆነው ሥርዓቱን አምርረው ሲታገሉ የነበሩና ኋላ ላይ በተቃዋሚው ጎራ መፈረካከስ ተስፋ ቆርጠው የድርሻቸውን እየተቀራመቱ ለመኖር ያለ እምነታቸው ሥርዓቱን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡  እንግዲህ ኢሕአዴግ በዚህ መልክ በሰበሰበው አድርባይና ጥቅም ፈላጊ ካድሬ አማካይነት ነው የሕዝቡን ነባራዊ ሁኔታ የሚመለከት መረጃ ሰብስቦ፣ በተሰበሰበው መረጃ መሠረትም ፖሊሲና ሕግ አውጥቶ አገርን እያስተዳደረ የሚገኘው፡፡ ኢሕአዴግ ከፖለቲካ ሙስና ጋር በተያያዘ የገባበትን እንዲህ ዓይነቱን መጠነ ሰፊ ችግር ጠራርጎ የሚያስወግድ ደፋር ዕርምጃ ካልወሰደ ችግሩን ከምንጩ ሊያደርቅ አይችልም፡፡

በአጭሩ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ብዙ ፍልስፍናና ረቂቅ ምርምር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ዋናው መፍትሔ የፖለቲካ ሙስናን ጠራርጎ ማስወገድና መብቱን ተነጥቆ በካድሬዎች ጫማ ሥር የወደቀውን ሕዝብ መብት ማክበርና እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ሕዝብ እውነተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ሆኖ ሹማምንቱን ለሥልጣን የመምረጥና ከሥልጣን የማውረድ ጉልበት ካለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሠረታዊ ምንጭ በዘላቂነት ይደርቃል፡፡ ወሳኙና ዋናው መፍትሔ እንዲህ ዓይነት ቆራጥ የፖለቲካ ዕርምጃ መውሰድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ አገር የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው የሚቀጠሩ ሰዎች ለኑሯቸው የሚመጥን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅምም ሆነ ማኅበራዊ ክብር እንዲያገኙ የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድም የመፍትሔው አካል ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብና የአስተሳሰብ ብዙኃነት አለመከበር

ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ ከመምጣትም በላይ እየተዳፈነ መምጣቱ ቢያንስ ከምርጫ 97 በኋላ ሊያከራክር በማይችል ሁኔታ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ እንደሌሎቹ ትችቶች ሁሉ ኢሕአዴግ በዚህ ረገድ የሚቀርበውን ትችትም ተቀብሎ አያውቅም፡፡ ኢሕአዴግ በ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ፣ ይባስ ብሎ በ2007 ምርጫ 100 በመቶ ምርጫውን አሸነፍኩ ካለ በኋላም ከአፈርኩ አይመልሰኝ ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየሰፋ ነው በማለት መከራከሩን አላቆመም፡፡ ኢሕአዴግ በተለመደ ድርቅናው እንዲህ ዓይነቱን የምርጫ ውጤት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓታችን ወደ አውራ ፓርቲ ዴሞክራሲ መሸጋገሩን የሚያሳይ ነው በማለት በሚያሳፍር ሁኔታ ሊያሳምነን ሞክሯል፡፡

በእኔ በኩል ኢሕአዴግ ዘግይቶም ቢሆን በሒደት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሒደትን ሊቀበል ይችላል በሚል የነበረኝ ትንሽ ተስፋ ሙሉ በሙሉ የተሟጠጠው ምርጫውን 100 በመቶ በማሸነፉ ማፈር ሲገባው በድል አድራጊነት ስሜት ሲመጻደቅ በማየቴ ነበር፡፡ በእኔ በኩል የአገራችን የፖለቲካ ምኅዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተጣበበ በመምጣት የአስተሳሰብ ብዙኃነት ሊያስተናገድ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን ማረጋገጥ የቻልኩት ሰዎች ሲያወሩ ሰምቼ ወይም የተጻፈ አንብቤ አይደለም፡፡ ለ24 ዓመታት በሒደቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ችግሩን በተጨባጭ ለማየት በመቻሌ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ  ኢሕአዴግን ለመውቀስና ለመተቸት የምሞክረውም ርካሽ የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኘት ብዬ ሳይሆን ፈጽሞ ልጠራጠረው በማልችል ደረጃ እርግጠኛ ስለሆንኩ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሚሠራቸውን በጎ ነገሮች በድፍረት በመመስከሬና በኢትዮጵያ ምክንያታዊ የፖለቲካ ባህል እንዲፈጠር በመሞከሬ ምን ያህል ዋጋ የከፈልኩ ሰው መሆኔ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከእኔ ዓይነቱ ሰው የሚሰነዘርን ትችት ትንሽም ቢሆን ለማዳመጥ ካልተግደረደረ የማንን ትችት ለማዳመጥ እንደሚችል አይገባኝም፡፡ እንደ ገደል ማሚቱ የራሱን ጩኸት ብቻ እያዳመጠ እስከ መቼ እንደሚቀጥልም አላውቅም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግማሽ ዕድሜየን ባሳለፍኩበት  የፖለቲካ ተሳትፎ በእርግጠኛነት ለመረዳት እንደቻልኩት ኢሕአዴግ መሠረታዊ በሆነ ደረጃ (Fundamentally) አምባገነናዊና ፀረ ዴሞክራሲ ድርጅት ነው፡፡

ከወቅቱ የዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ አኳያ የማያዋጣ ስለሆነበት በድፍረት አይናገረው እንጂ፣ ኢሕአዴግ ከነጭራሹም በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲም ሆነ መድበለ ፓርቲ ያስፈልገዋል ብሎ ከልቡ አያምንም፡፡ ነገር ግን በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ያለነው ሰዎች ብቻ ሳንሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ኢሕአዴግ አምባገነናዊ ድርጅት መሆኑን በማያጠራጥር ሁኔታ ተገንዝቧል፡፡ ኢሕአዴግ በአንድ በኩል በግራ ፖለቲካ ባህል ተኮትኩቶ ያደገ የ1960ዎቹ ትውልድ አካል በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለ17 ዓመታት ሽምቅ ተዋጊ ሆኖ በመራራ የማሸነፍና የመሸነፍ ሒደት ማንነቱን የቀረፀ ድርጅት ስለሆነ ስህተትን አምኖ መቀበልና ማረም ሽንፈት መስሎ ታይቶታል፡፡ በእርግጥ የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ባህል የዚያ ትውልድ አካል የሆኑት የሻዕቢያ፣ የኦነግ፣ የኢሠፓና የኢሕአፓ. . . ወዘተ. ሁሉ መገለጫ ስለሆነ ኢሕአዴግ በሆነ ተአምር ዴሞክራት እንዲሆን መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኢሕአዴግን አሳዛኝ ትዝብት ላይ የሚጥለው አምባገነን መሆኑ ሳይሆን ጧት ማታ አታካች በሆነ መጠን በሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ዴሞክራት ነኝ ብሎ ሕዝብን ሊያሳምን መሞከሩ ነው፡፡

ኢሕአዴግ በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ለከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት አድናቆትና ክብር የሚገባው ድርጅት ቢሆንም፣ በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ ሰማዕታት ጓዶቹ ስም ጧት ማታ እየማለና እየተገዘተ በአፈናና በሸፍጥ ፖለቲካ ራሱን ዘለዓለማዊ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ መሞከሩ ግን ከጊዜያዊ ሥልጣን በላይ ለዘላቂ ሕልውናውና ታሪኩ የማይጨነቅ ግብዝ ድርጅት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ኢሕአዴግ አመነም አላመነም በገሃድ የሚታየው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የአስተሳሰብ ብዝኃነት ቦታ ማጣቱን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖትና የባህል ብዝኃነት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ታሪካዊና ወቅታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎች የተፈጠረ በርካታ የአስተሳሰብ ብዝኃነት ባለበት አገር ውስጥ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ፓርላማ ድረስ ባሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የሕዝብ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ውስጥ አንድም የሕግ አውጭነት ውክልና ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የለም፡፡ ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ በሚባልበት አገር ከቀበሌ ካቢኔ ጀምሮ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ድረስ አንድም የሕግ አስፈጻሚው አካል የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የለም፡፡ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ በሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ በፍትሕ አካሉ ውስጥ የተወከለ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የለም፡፡

ኢሕአዴግ እነዚህን ሦስት የመንግሥት ምሰሶዎች በብቸኛነት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ አልበቃው ብሎ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሕዝብ ማኅበራትንና የሃይማኖት ድርጅቶችን ሳይቀር በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡ ይኼም አልበቃው ብሎ በተቃዋሚነት የተደራጁ ፓርቲዎች ውስጥ ሳይቀር አባላቱን አስርጎ እያስገባ የማዳከምና የመበተን ተግባር ይፈጽማል፡፡ ኢሕአዴግ የአገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካ ሕይወት በዚህ መጠን ለመቆጣጠር ሲል በፖለቲካ ተቀናቃኞች ላይ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የመብት ረገጣ ይፈጽማል፡፡ ሆኖም ግን አንድም ቀን፣ በአገራችን አንድም የገዥው ፓርቲ አባል በፖለቲካ የመብት ጥሰት ተከሶ ወይም ተቀጥቶ አያውቅም፡፡

ሥርዓቱ ሕዝቡ በገሃድ የሚያውቀውን ይህንን እውነት ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ፣ አገሪቱ ዴሞክራሲና መድበለ ፓርቲ የሰፈነባት አገር እንደሆነች አድርጎ ሲናገር ስለሚውል በአሁኑ ወቅት መንግሥት በተጋነነና በተዛባ ሁኔታ የሚያቀርበውን መረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በሀቅም የሚናገራቸውን መረጃዎች ሕዝቡ አምኖ መቀበል የማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ይኼም በመሆኑ ነው ደሃው ሕዝብ ሳይቀር ሳተላይት ዲሽ በየደሳሳ ቤቱ ጣራ ላይ ሰቅሎ ስለአገሩ እውነታ መረጃ ለማግኘት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚተላለፉ መገናኛ ብዙኃንን ሲያዳምጥ የሚውለው፡፡ ለአንድ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ መሆን ከዚህ በላይ ማሳያ ያለ አይመስለኝም፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በሰማዕታቱ ስም እየማለና እየተገዘተ የምታገለው ለዴሞክራሲ ነው ቢልም እየገዛን ያለው ግን በግራ ፖለቲካና በሽምቅ ውጊያ አስተሳሰብ (Mindset) ነው፡፡ ስለማዳመጥና ስለማሳተፍ ሳይሆን የራሱን አመለካከት በተፅዕኖ ስለማስረጽ፣ ስለመደራደርና መቻቻል ሳይሆን ስለመቆጣጠርና ማሸነፍ እያሰበ የሚሠራ ዴሞክራሲያዊ ባህሪና ባህል የሌለው ድርጅት ነው፡፡ ኢሕአዴግ አንዳንድ ጊዜ ሲናገሩ እንደምንሰማውም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መኖር የሚፈልጉት ጥፋቱን እየተናገሩ ስህተቱን የማረም ዕድል እንዲሰጡት ነው እንጂ፣ እውነተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ተቀናቃኝ እንዲሆኑ አይደለም፡፡

የወቅቱ የሕዝብ አመጽ በአጋጣሚና በስሜት የተፈጠረ ሳይሆን ኢሕአዴግ ከሥረ መሠረቱ አምባገነናዊ ድርጅት መሆኑን ከመረዳትና እንዲህ ዓይነቱን ድርጅት በትግልና በመስዋዕትነት እንጂ፣ በጥያቄና በተማፅኖ መቀየር እንደማይቻል ሕዝቡ ከልቡ ስለተረዳ ነው፡፡ በተገቢው ጊዜና መንገድ ራሱን ማደስ የማይችል ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት በመጨረሻ ሊያስተናግድ የሚችለው አብዮትና የትጥቅ ትግልን ስለሆነ፣ ኢሕአዴግም ዛሬ ላይ የገጠመው ችግር ዕድለ ቢስ ስለሆነ ወይም ሕዝቡ ውለታ-ቢስና ክፉ ስለሆነ ሳይሆን የዘሩትን ማጨድ አይቀሬ ስለሆነ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ከማንም በላይ ስለሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነት ሲሰብክ የኖረ ድርጅት ቢሆንም፣ በተግባር ግን ከሕዝብ ልብ ውስጥ ሰላምን የሚያርቅና የሚያጠፋ ድርጊት ሲፈጽም የሚውል ድርጅት ነው፡፡ ሥልጣን ላይ በወጣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ራሱ ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት የተገደደበትንም ሆነ ለሥልጣን የበቃበትን ምክንያት ረስቶ ያሸነፈውን መንግሥት ታሪክ እየደገመ ያለ ድርጅት ነው፡፡

በአጠቃላይ ሕዝቡ በፓርቲዎች ዙሪያ በአግባቡ ተደራጅቶ በመታገል ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ባይችልም እንኳ ብሶቱ፣ ምሬቱና ተቃውሞው የሚደመጥበት መድረክ እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ከ2002 ምርጫ በኋላ ግን የሕዝቡን አመለካከት የሚወክሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሕዝባዊ ማኅበራት በሥርዓቱ የአፋኝነት ድርጊት ከሒደቱ ተጠራርገው እንዲወጡ በመደረጋቸው ሕዝቡ በአመጽና በነውጥ የታፈነ ስሜቱን ለመግለጽ ተገዷል፡፡ ሥርዓቱ በሚፈጽመው የአፈና ተግባር ምክንያት በሰላማዊና ሕጋዊ ትግል አዋጭነት ላይ ሕዝቡ ያለው ተስፋ ተሟጦ በመጥፋቱም፣ የወቅቱን የሕዝብ ትግል የመምራቱን ዕድል በስደት የሚገኙ አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች ወስደውታል፡፡

የአገሪቱን የፖለቲካ ዕውነታ በገለልተኝነትና በድፍረት የሚያወራ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዳይኖር በመደረጉም የሕዝቡን ጆሮና ቀልብ የሚስቡት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚሰራጩት አመጽና ጦርነት ቀስቃሽ ሚዲያዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ዕውነታ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ የወቅቱ የሕዝብ ትግል የሚመራው አገር ውስጥ ከሕዝቡ ጋር አብረው እየኖሩ ባሉ ሕጋዊና ሰላማዊ ፓርቲዎች እንዲሆን ካልተደረገና በሕዝቡ የሚደመጡትና የሚታመኑት እዚሁ አገር ውስጥ የሚገኙት መገናኛ ብዙኃን እንዲሆኑ ካልተደረገ በስተቀር፣ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ መቼውንም ጊዜ ቢሆን ጤናማና ሰላማዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ሊቋቋመው ባልቻለ የፖለቲካ ነውጥ እየታመሰ የሚገኘው እንዲሁ ዕድለ ቢስ ድርጅት ስለሆነ ሳይሆን፣ አገር ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች እንዲዳከሙ ሆን ብሎ በሰራው ስህተት ምክንያት ነው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ምኅዳር አሁን ከሚገኝበት እንደሌለ ከሚያስቆጥር ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እንዲሰፋ ካልተደረገና የአስተሳሰብ ብዝኃነት የሚስተናገድበት ተጨባጭ ለውጥ በፍጥነት ካልመጣ፣ የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ እየተባባሰ እንጂ ከቶውንም እየረገበ ሊመጣ አይችልም፡፡

የሕወሓት የበላይነት

ኢሕአዴግ ለሥልጣን ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ የሕወሓት የበላይነት ጉዳይ ሕዝቡ ሥርዓቱን ለሁሉም ሕዝብ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት የቆመ ፍትሐዊ ሥርዓት አድርጎ እንዳያየው በማድረግ ረገድ በቁጥር አንድ ሊጠቀስ የሚችል ችግር ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ከኢሕአዴግ ታሪካዊ አመጣጥ ለመረዳት እንደምንችለው በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል  ሕወሓት የትጥቅ ትግሉን ቀድሞ በመጀመር ፣ በርካታ ተዋጊ ኃይል በዙሪያው በማሰባሰብና ከፍተኛውን የመስዋዕትነት ዋጋ በመክፈል ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ ድርጅት ነው፡፡ ከደርግ ጋር የተካሄደውን የትጥቅ ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት የሚያስችል ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሐሳቦችን በማፍለቅና ድርጅታዊ አመራር በመስጠት ረገድም ቁልፍ ሚና የተጫወተ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ሚናው ምክንያት ሕወሓት በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የኃይል አሠላለፍ ውስጥ የበላይነት ያለው ድርጅት ብቻ ሳይሆን፣ የአባል ድርጅቶቹ ፈጣሪም ለመሆን በቅቷል፡፡

የቀድሞ ኢሕዴን አፈጣጠር አከራካሪ ቢሆንም ቀደም ሲል ኢሕዴን የኢሕአዴግ መሥራች አባል እንዲሆን በማድረግና በኋላም ላይ ኢሕዴን ወደ ብአዴንነት ተቀይሮ የአማራው ሕዝብ ገዥ እንዲሆን በማድረግ፣ ኦሕዴድንና ደኢሕዴንንም በመልክ በመልክ አደራጅቶ በመፍጠር ለኦሮሚያና ለደቡብ ሕዝቦች ገዥ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ሕወሓት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ሕወሓት በትጥቅ ትግሉ ወቅትና በኢሕአዴግ የመንግሥት ምሥረታ ወቅት የነበረው ሁለንተናዊ የበላይነት በሒደት መለስተኛ ለውጥ እየታየበት የመጣ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡

የሕወሓት የበላይነት ጉዳይ በአንድ በኩል ሕዝቡ ሥርዓቱን ከጅምሩ ፍትሐዊ የሆነ የጋራ ሥርዓት አድርጎ እንዳያየው የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ግን ጽንፈኛ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በሥርዓቱ ላይ አንድ ጠንካራ ተቃውሞ የመቀስቀሻና የማነሳሻ አጀንዳ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ በዚህ የሕወሓት የበላይነት ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ሥርዓቱን የወያኔ፣ ከዚያም አለፍ ሲል የትግሬ ሥርዓት አድርጎ እንዲመለተከው፣ ከዚህ በተቃራኒም ከሕወሓት ውጪ ያሉትን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ አሻንጉሊት በመቁጠር በንቀት እንዲመለከታቸውና ተገቢ ዕውቅና (Legitimacy) እንዳይሰጣቸው አድርጓል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ይህ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለ የሕወሓት የበላይነት አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች ከሚያካሂዱት ቅስቀሳ ጋር ተደምሮ ሕዝቡ ያላግባብ ሕወሓትንና የትግራይን ሕዝብ ነጣጥሎ ማየት እንዳይችልና በትግራይ ሕዝብ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተዛባና ጤናማ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታም በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ቅራኔ የአስተሳሰብ ቅራኔ ከመሆን አልፎ ወደ ዘረኝነት የተጠጋ ቅራኔ እንዲሆን በማድረግ አስቀያሚ ገጽታ እንዲላበስ አድርጎታል፡፡

የሕወሓትን የበላይነት በሦስት መልክ ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛ ቀደም ሲል በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ስላሉ አንዳንድ ድንጋጌዎች ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ራሱን የበላይ አድርጎ ምን ያህል እንደሚቀጥል እርግጠኛ ባለመሆን በውስጡ የነበረውን ሥጋትና ጥርጣሬ ለመግለጽ የሞከረው ለራሱ የሚጠቅሙ ሕጎችን በመደንገግ ብቻ ሳይሆን፣ ከሥልጣን የበላይነት ጋር ወሳኝ ቁርኝት ያላቸውን የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች በመቆጣጠር ጭምር ነበር፡፡ በአገሪቱ የመንግሥት መዋቅር በቅደም ተከተል ወሳኝ የሚባሉትን አራት ቦታዎች ማለትም የጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የኤታማጆር ሹምነት፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊነትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሯቸው ኖሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ቁልፍ የመንግሥት የሥልጣን ቦታዎች ያለ ይሉኝታና የብሔረሰብ ተዋጽኦ ኮታ ሳይመለከታቸው በሕወሓት ብቸኛ ቁጥጥር ሥር ሆነው የኖሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቁልፍ ኃላፊነቶች በተጨማሪም ለአንድ መንግሥት የሥልጣን የበላይነትና ደኅንነት ወሳኝነት ባላቸው መከላከያን፣ ደኅንነትን፣ ኢሚግሬሽንን፣ ስደተኞች ጉዳይን፣ ፌዴራል ፖሊስን፣ ማረሚያ ቤቶችን፣ ጉምሩክን፣ አቪዬሽንንና አየር መንገድን በመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ወሳኝ የሚባሉትን ኃላፊነቶች በጎላ ሁኔታ ተቆጣጥረው የኖሩትና አሁንም የሚኖሩት የሕወሓት አባላት ወይም ሕወሓት ታማኝነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጪ ባሉ የፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሚስጥር ነክ መረጃ ያላቸውና ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚሠጉ ኃላፊነቶች በጥንቃቄ ተመርጠው በሕወሓት ሰዎች እንዲያዙ ይደረጋሉ፡፡

ይህንን እውነታ ሕዝቡ የሚያስፈጽመው ጉዳይ ኖሮት ወደ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ሲሄድ በሚያየው ሁኔታና ከአክራሪ የፖለቲካ ኃይሎች በሚሰማው ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ለቃለ መጠየቅ የሚቀርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችን ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሲመለከት በስማቸውና በድምፅ ቅላፄያቸው በቀላሉ ለይቶ እየቆጠረ እውነታውን ይረዳዋል፡፡ ከሕዝቡም በላይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ደፍረው በመድረክ ባይናገሩትም እውነታውን በቅርበት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ከድርጅታቸው ተነጥለው ሲወጡ የሕወሓትን የባላይነት በዋና የተቃውሞና የብሶት መግለጫነት ሲጠቀሙበት ዓይተናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ይህ ጉዳይ አንዳንድ የኦሕዴድና የብአዴን ካድሬዎች ከሕወሓት ዕይታ ተሰውረው ሕዝቡን በመንግሥት ላይ የሚያነሳሱበት አጀንዳ እንደሆነና በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የውስጥ ግምገማ ላይም የመወያያ ርዕስ እየሆነ እንደመጣ እየሰማን ነው፡፡

ሁለተኛው የሕወሓት  የበላይነት መገለጫ ሥነ ልቦናዊ የበላይነት ነው፡፡ ከማንም በላይ የሕወሓት አባላት ራሳቸውን የሥርዓቱ ባለቤትና ጠባቂ አድርገው ስለሚያስቡ ተጨባጭ የሥልጣን ቦታ ኖራቸውም አልኖራቸውም በየ መሥሪያ ቤቱ የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ መስለው የሚታዩት እነሱ ናቸው፡፡ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ያላቸው የሥራ ድርሻ ተላላኪነት፣ ጥበቃ ወይም ፅዳት ሠራተኝነት ቢሆንም እንኳ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለሥርዓቱ ተቆርቋሪነት የሚያሳዩትም ሆነ ተበድያለሁ ለሚል ባለጉዳይ አማላጅ ሆነው ለመቅረብ የሚሞክሩት የሕወሓት ሰዎች ናቸው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ የሥነ ልቦና የበላይነት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሕዝቡ ማኅበራዊ ኑሮዎች ጭምር የሚታይ ነው፡፡ በየታክሲው ውስጥ፣ በየመጠጥ ቤቱ፣ በየዕድሩ፣ በየቀበሌው. . . ወዘተ. ከማንም በላይ ራሳቸውን የሥርዓቱ ባለቤትና ጠበቃ አድርገው በማየት ስለሰላምና ልማት አስፈላጊነት ኅብረተሰቡን ለማስተማር ሲሞክሩ የሚታዩት እነሱ ናቸው፡፡ የልማት መዋጮ ሲሰባሰብ ቀድመው የሰው ቤት የሚያንኳኩት፣ ሕገወጥ ግንባታ ተካሄደ ሲባል ቀድመው ለቀበሌ ጠቋሚ የሚሆኑት፣ በየቀበሌው በሚካሄዱ ሕዝባዊ ስብሰባዎች በአስተናጋጅነት ቀድመው ሽር ጉድ የሚሉትና በስብሰባው ላይ የሁሉም ነገር ተንታኝ ሆነው የሚቀርቡት የሕወሓት አባላት ናቸው፡፡ ይህ ሥነ ልቦናዊ የበላይነት ቀስ በቀስ ከማንም በላይ አገር ወዳዶች፣ ጀግኖችና አዋቂዎች እኛ ነን ወደሚል የትምክህተኝነት ባህሪ እየተቀየረ  መጥቷል፡፡ ይህ በአብዛኛው በመሀል አገር በሚገኙ ጥቂት የሕወሓት አባላት የሚንፀባረቀው የትምክህት ባህሪ በሚሊዮን የሚቆጠረውን ትሁትና ጨዋ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ በቅርበት ማየት ዕድል ላላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተዛባ ዕይታ (Pereception) በመፍጠር በአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ ላይ አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሦስተኛው የሕወሓት የበላይነት ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ያለ ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ራሱን ችሎ ሊቆም እንደማይችል ሕወሓት ጠንቅቆ የሚያውቅ ድርጅት ነው፡፡ ሕወሓት ከዚህ ዕምነቱ በመነጨ ከአገሪቱ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሒደት በተቃራኒ ራሱን የበርካታ በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት የሚያንቀሳቅሱ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት አድርጓል፡፡  ተመሳሳይ የንግድ ተቋማት በማቋቋም ረገድ ለይስሙላ ያህል ሌሎቹም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንዲሳተፉ የተደረገ ቢሆንም፣ በሕወሓትና በሌሎቹ ድርጅቶች የንግድ ተቋማት መካከል ያለው የአቅም ልዩነት ግን ፈጽሞ ሊነፃፀር የሚችል አይደለም፡፡ ሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እንወክለዋለን በሚሉት የሕዝብ መጠን ከአሥር እጥፍ በላይ ከሕወሓት የሚበልጡ ቢሆኑም የሦስቱ ድርጅቶች የንግድ ተቋማት አቅም ተደምሮ የሕወሓትን አንድ ሦስተኛ አያክልም፡፡

እነዚህ የሕወሓት የንግድ ድርጅቶች የአገሪቱን ሕግ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥሰው የተቋቋሙት የትግራይ ክልልን ለማልማትና የሕወሓትን የፖለቲካ የበላይነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ታስቦ ነው ቢባልም፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መፈልፈያ በመሆን ሥርዓቱን ለአደጋ አጋለጡት እንጂ እንደታሰበው ለትግራይ ክልልም ሆነ ለራሱ ለሕወሓት የሚጠቅሙ አልሆኑም፡፡ በአንድ አገር ፓርቲና የንግድ ሥራ ሲደባለቁ ምን ዓይነት አደጋ እንደሚያስከትል በሰሞኑ የአገራችን የፖለቲካ ብጥብጥ በሰላም ባስ፣ በዳሸን ቢራና በዓባይ ባንክ ላይ ከደረሰው ጉዳት በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን፡፡

ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነቱ መዋቅራዊ ሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ጠቃሚ እንዳልሆነ ተረድቶ ችግሩን ማረም ሲገባው ይባስ ብሎ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት ወደ መጠነ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በማስገባት ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በአብዛኛው ቁልፍ የኃላፊነት ድርሻ ያላቸው የቀድሞ የሕወሓት አባላት ስለሆኑ፣ ከሠራዊቱ አመራሮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው የሕወሓት አባላትና ደጋፊዎች የኪራይ ሰብሳቢነት ሰለባ መሆናቸውን ይበልጥ አባብሶታል፡፡

ከሕወሓት የኢኮኖሚ የበላይነት ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ችግር አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች እንደማንኛውም ዜጋ በሀቅ ጥረው ግረው ሀብት ለማካባት የበቁ ቢሆንም፣ ከሥርዓቱ ጋር ባላቸው ጥብቅ ግንኙነትና ትስስር ያላግባብ ተጠቃሚ በመሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጎምቱ ባለሀብት ለመሆን የበቁ በቁጥር አናሳ፣ ነገር ግን የዕይታ ትኩረትን የሚስቡ የትግራይ ተወላጆች የመኖራቸው ጉዳይ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የከባድ መኪና ሾፌር፣ የመከላከያ ሠራዊት አባል ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ሰዎች የገንዘብ ምንጫቸው በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር በጀት የሚያንቀሳቅስ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ ይታያል፡፡ እነዚህ በኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሰዎች ለወታደራዊና ሲቪል ባለሥልጣናት የተመሩ መሬቶችን በመግዛት፣ ለሊዝ ጨረታ የወጡ ቁልፍ ቁልፍ መሬቶችን ተሻምቶ በመግዛት በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የነሱ ቋንቋ ጎልቶ የሚነገርበት መንደርና ጎዳና እስከመፍጠር ደርሰዋል፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ለመክበር የበቁ ሰዎች ከሁሉም ብሔረሰብ ሊገኙ ቢችሉም፣ ከፍ ሲል ከዘረዘርኳቸው የፖለቲካ  ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የበለጠ ጎልተው የሚታዩትና ትኩረት የሚስቡት ግን ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ሆነዋል፡፡

እነዚህ ያላግባብ ለመክበር የበቁ ሰዎች ከአጠቃላዩ የትግራይ ሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፃሩ በቁጥር ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ቢሆኑም፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ልዩ ተጠቃሚ ሆኗል›› በማለት ለሚቀሰቅሱ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ግን ጥሩ አጀንዳ ሆኖ አገልግሏቸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ የተጠቀመው ነገር ባይኖርም፣ በእነዚህ በባህሪም ሆነ በኑሮ ደረጃቸው የትግራይን ሕዝብ በማይመስሉ ጥቂት ባለሀብቶች ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጋልጧል፡፡

በቅርቡ በአገራችን በታየው የፖለቲካ ቀውስም የትግራይ ተወላጆች የፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን የቀጥተኛ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደዚህ አስቀያሚ ደረጃ የደረሰው በአንድ በኩል የትግራይ ሕዝብንና ሕወሓትን፣ በሀቅ ለፍቶና ደክሞ ባለሀብት የሆነውን የትግራይ ተወላጅና ከሥርዓቱ ጋር ተመሳጥሮ በአቋራጭ የከበረውን የትግራይ ባለሀብት አንድና አንድ አድርገው በሚያዩ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ቅስቀሳ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከሕወሓት የበላይነት ጋር በተያያዘ በአግባቡ ከሕዝብ እየተነሱ ላሉ ቅሬታዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ነው፡፡  ወደፊትም ይህ ከሕወሓት የበላይነት ጋር በተያያዘ የሚቀርበው የሕዝብ ቅሬታ በአግባቡ ዕውቅና አግኝቶ ካልታረመ በስተቀር የተገቢ ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን፣ የአክራሪነት የመቀስቀሻ መሣሪያ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የወቅቱን የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርም የበለጠ ያባብሰዋል፡፡ እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት አንድ ቁም ነገር ከሕወሓት የበላይነት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ከማንም በላይ ጉዳት እየደረሰበት የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ፣ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የሕወሓት የበላይነት የትግራይ ሕዝብ ከማንም ባላነሰ መቃወምና መታገል ይኖርበታል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከእንግዲህ ያለፈው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣብሃል በሚል ማስፈራሪያና በ17 ዓመቱ የትጥቅ ትግል ሰማዕታት ስም እየተገዘተ የሕወሓት የአስተሳሰብ እስረኛ መሆን የለበትም፡፡ አግባብ ባለው መልኩ የሕዝቡን ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በመቀላቀል የአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ምንጭ ተደርጎ ከመታየት ወደ የአገሪቱ የፖለቲካ የመፍትሔ አካልነት መሸጋገር አለበት፡፡ በተለይም አዲሱ የትግራይ ትውልድ ሕወሓትን ብቸኛ የትግራይ ሕዝብ ወኪል አድርጎ የማምለክን አስተሳሰብ ሰብሮ በመውጣት ከራሱና ከጊዜው ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚመጥን የፖለቲካ መስመር መያዝ አለበት፡፡ (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  
 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...