Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በቀለበት መንገዱ ላይ ባሉ አደባባዮች በሙሉ ተላላፊ መንገዶች ይገነባሉ››

ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ

ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ የ39 ዓመት ጐልማሳ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጂነሪንግ አግኝተዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ በሥራው ዓለም ከ12 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው፡፡ በባለሥልጣኑ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ብዙ ፈተና አለበት የሚባለውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በዋና ሥራ አስኪያጅነት እንዲመሩ ከጥቂት ወራት በፊት ተሰይመዋል፡፡ ከዚህ ኃላፊነታቸው ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተገንጥሎ የወጣው የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ኮርፖሬሽኑን ውጤታማ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ ከዚያም የመንግሥት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችን በማጣመር የተመሠረተው የግዙፉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለወራት ሠርተዋል፡፡ እንዲህ ባሉ ትልልቅ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከመሥራታቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በኃላፊነት በመምራት አገልግለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት እንደሠሩና የተመደቡባቸው ፕሮጀክቶች ብዙ የተማርኩባቸው ናቸው ይላሉ፡፡ ሥራው ውጤታማ በሆነ መንገድ ቢያልቅም ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ በወጣትነት ዕድሜያቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መምራታቸው፣ ከዚያም አሁን እንዳሉበት የኃላፊነት ቦታዎች መቀመጥና ውጤታማ መሆን አይከብድም? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዲያውም ጥሩ የሚሠራው በዚህ ዕድሜ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው ጎልተው ወጡ እንጂ ዛሬ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየመሩ ያሉት ወጣት ባለሙያዎች መሆናቸውንም ያክላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን ችግር ለማቃለል እየሠሩ መሆኑን የሚገልጹት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ ባለሥልጣኑን በአዲስ የማዋቀር እንቅስቃሴም ጀምረዋል፡፡ ብዙ ችግሮች እየታዩበት ባለው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች፣ የከተማው ራስ ምታት በሆነው የትራፊክ መጨናነቅ፣ በተያያዥ ጉዳዮችና በእርሳቸው አመራር ሊወሰዱ ስለታሰቡ ዕርምጃዎች ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተሰይመዋል፡፡ አዲሱን ሥራ እንዴት አገኙት?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አዲሱ ሥራ ጥሩ ነው፡፡ ያው ፈተናዎች አሉት፡፡ ሥራው በባህሪው ትልቅ ነው፡፡ የሕዝቡ ፍላጎቶችም አሉ፡፡ ገና ያልተመለሱ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ተቋሙን የበለጠ ማጠናከር ይፈልጋል፡፡ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ አድርገን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እንደሚታየው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ብዙ ሥራዎች የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በተለይ የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተካከል አኳያ ብዙ የሚቀር ሥራ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ብዙ ጥያቄዎች ያሉበት በመሆኑ፣ ኃላፊነቱን ሲረከቡ የከተማዋን የመንገድ ዘርፍ እንዴት መዘኑት? ያሉትንስ ችግሮች እንዴት እቀርፋለሁ ብለው አስበዋል?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን በተመለከተ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ከመንገድ ሀብቱ ጋር ያለ ችግር ነው፡፡ መንገዶችን መንከባከብ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው፡፡ ተደራሽነቱም ያን ያህል ነው ሊባል አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላዊ ሆኖ ከዚሁ በውስን እንቅስቃሴ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ወደ ስድስት ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ አለ፡፡ ስድስት ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ አለ ስንል በአስፋልት፣ በጠጠርና በኮብልስቶን የተሠሩትን መንገዶች ጨምሮ ነው፡፡ 44 በመቶ የሚሆነው በአስፋልት የተሠራ መንገድ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ መንገድ ማዕከላዊ በሆነ መንገድ ማስተዳደር ያስቸግራል፡፡ ጥገናዎች ወቅቱን የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ የግል ዘርፉ ጥገና ውስጥ መግባት አለበት፡፡ አስፈላጊ ሲሆን የኮንትራት አሰጣጡን ወይም የኮንትራት ዓይነቱንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ለረዥም ጊዜ አፈጻጸምን መሠረት ያደረጉ ኮንትራቶች ጭምር መሰጠት አለባቸው፡፡ እኛ የምንመራበት መንገድም ቢሆን ችግር ያለበት በመሆኑ መለወጥ አለበት፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶችን በሚመለከት ያለው አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ ሌላው ኮንስትራክሽኑን የሚመለከት ነው፡፡ እሱም የራሱ የሆነ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች አሉበት፡፡ ከውስጣዊ ችግሮች ውስጥ የተቋሙ የአቅም ችግር አንዱ ነው፡፡ ከተማ ስለሆነ የወሰን ማስከበር ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ የኮንትራክተሮችና የአማካሪዎች የአቅም ጉዳይ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከሥርዓት ጋር ችግሮች ናቸው፡፡ እንደ አገር እንደ መንግሥት በሒደት የሚፈቱ ናቸው፡፡ ተቋሙን በተመለከተ ግን በዋናነት በመንገድ ሀብቱ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት አሁን ያልተማከለ ለማድረግ እየሄድን ነው፡፡ አመቺ በሆነ ሁኔታ ለማስተዳደር አዲስ አበባ ከተማን በአምስት ሪጅኖች ከፋፍሎ በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ደረጃ እንዲሠሩ ለማድረግ የሚያስችለው መዋቅር ተዘጋጅቷል፡፡ ቦርዱ በአጭር ጊዜ ይወስናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ መዋቅሩ ሲወሰን ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህም አሁን ባለው የከተማው የመንገድ ጥገናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የትራፊክ ፍሰቱንና ጥገናውን ጭምር የሚመራ አካል እንዲፈጠረና እንዲሠራ ያስችላል፡፡ አሁን እዚህ ሆነን ጠቅላላ ከተማውን መምራት ከባድ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በጣም እየተወሳሰበ ይመጣል፡፡ ብዙ ማሳለጫዎች የመሬት ሥር ሥራዎችና የላይ መተላለፊያዎችን ወደ መገንባት ይገባል፡፡ መሬት ላይ ያለው ሥራ በብዛት ስለተሠራ ከዚህ በኋላ ወደተላላፊ መንገድ ሥራዎች ነው የሚኬደው፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚመጥኑ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ የመንገድ ዘርፍ እስካሁን ሲመራባቸው የነበሩ አሠራሮች ይለወጣሉ ማለት ነው? ይህን ከሆነ የምታደርጉት ለውጥ ምንድነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ምንድነው የምታደርጉት ብትለኝ የተለየ ሊፈጠር የሚችል ነገር አይኖርም፡፡ አንደኛው ተቋሙን እንደገና ማዋቀር ነው፡፡ ይህንን ካደረግን በኋላ በተቻለ መጠን አቅም በፈቀደና መንግሥት ከፈቀደ ተወዳዳሪ የሆነ ባለሙያ ማምጣት ነው፡፡ ከዚያ የመጣውን ባለሙያ ማልማት ነው፡፡ ተወዳዳሪ የሆነ ባለሙያ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በበለጠ ደግሞ መለወጥ ያለባቸው በርካታ የአሠራር ሥርዓቶች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ሊለወጡ ይገባቸዋል የተባሉት የአሠራር ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? የተወሰኑትን ቢጠቅሱልኝ?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ለምሳሌ የፕሮኪውመንት ሲስተማችን አንዱ ነው፡፡ በዋናነት ሁለት ትልልቅ ነገሮች ናቸው ያሉት፡፡ ቁጥጥሩን በተመለከተ አንዱ የፕሮኪውመንት ሲስተም ነው፡፡ የኮንትራት ማኔጅመንት ሥርዓታችንም መታየት አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮች እንደገና መታየትና መጠናት አለባቸው፡፡ ኦፕሬሽኑም ላይ ያለውን አሠራር ለመቀየር የምንወስደው ዕርምጃ አለ፡፡ ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ ወጪን የሚቆጥብና የሥራ ሒደቱ እየፈተሸ የሚሄድ መሆን ይገባዋል፡፡ መንገድ ግንባታ ጥራቱን የተጠበቀ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ የአይቲ ቴክኖሎጂን መጠቀም አለብን፡፡ እንዲህ ያሉ ዋና ዋና ሥርዓቶችን ስትቀየር በተግባር ተቋሙን ቀየርክ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ የትራፊክ ፍሰት በጣም እየተቀየረ ነው፡፡ አታካችና አስቸጋሪ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ እየታየ ነው፡፡ በተለይ ጠዋትና ማታ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መንቀሳቀስ እጅግ ፈታኝ እየሆነ ነው፡፡ ነዋሪዎች እየተማረሩ ነው፡፡ እንዲህ ለመሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ቢሆንም የእናንተም የአሠራር ድክመት አለ፡፡ በእናንተ ዘንድ የችግሩ ምንጭ ምንድነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- መጨናነቁ በእርግጥ በዓለም ላይ እንዳሉት ትልልቅ ከተሞች ያን ያህል ብዙ መኪና ላይኖር ይችላል፡፡ በመሠረቱ የትራፊክ መጨናነቁን ለመቀነስና ለሁሉም የተጠቃሚነት መብት ለመስጠት የፐብሊክ ትራንስፖርቱን አገልግሎት ማስፋፋት ነው የሚሻለው፡፡ ምክንያቱም 60 ሰዎች 60 መኪኖች ከሚይዙ በአውቶቢስ ቢሄዱ የተሻለ ይሆናል፡፡ መጨናነቁም ይቀራል፡፡ ሞዳሊቲውም መቀየር አለበት፡፡ ለአውቶቡስ ብቻ የሚሆኑ ኮሪደሮች ለመመሥረት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የግል ትንንሽ መኪኖች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር መጨናነቁ ያጋጥማል፡፡ አሁን ያለው መሠረተ ልማት ደግሞ እሱን የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ ከዚህ በተረፈ መሻሻል ያለባቸው፣ መስፋፋት ያለባቸው ኮሪደሮችም አሉ፡፡ በተለይ በቀለበት መንገድ ላይ ያሉ ኮሪደሮች ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሻሻል ይኖርባቸዋል ስንል በአደባባዮች አካባቢ ያለውን ፍሰት የሚያስተናግድ በሚችል ደረጃ ማሻሻል ማለት ነው፡፡ ወደ መብራት ማዞር ያስፈልጋል፡፡ አደባባይ እንዳይጠቀሙ አመቺ መንገዶች ካሉ እነሱን መክፈት ያስፈልጋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የላይ መተላለፊያ የደረጃ ማሻሻል ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ይህ ጥናት ጨረታ ላይ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ይስተካከላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ጥገናውም ራሱ ችግሩን እንዲቀርፍ በሚያስችል ደረጃ መሠራት አለበት፡፡ አንዳንዴ መንገዱ በመበላሸቱ የተበላሸውን መንገድ ለመሸሽ የሚፈጠሩ መጨናነቆች አሉ፡፡ በተለይ በቀለበት መንገድ አካባቢ ችግሩ ጐልቶ ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለመቀነስ ግን አሁን ጥገና እየተሠራ ነው፡፡ በሦስት ምዕራፍ የተጀመረ የጥገና ሥራ አለ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ተላላፊ መንገዶቹ እስኪሠሩ ድረስ አሁን ለጊዜው አደባባዮችን በማፍረስ መብራት በመትከል ጊዜያዊ መፍትሔ መስጠት ነው፡፡ አንዳንዱን ለተወሰነ ጊዜ ዘግቶ ጥሩ ጥገና ማድረግ ግድ የሚልበትም ቦታ አለ፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማየት የነበረበት በጣም የለሙ መስመሮችም አሉ፡፡ ትራፊክ የተቀየረባቸው ማለት ነው፡፡ አዳዲስ የተከፈቱ የፍጥነት መንገዶችም አሉ፡፡ እነሱ በተለይ በምዕራብ የከተማው ክፍል በኩል እንደ ለቡ፣ ጀርመን አደባባይና በአጠቃላይ በምዕራብ በኩል ያሉ አደባባዮች በጣም መጨናነቅ በዝቶባቸዋል፡፡ አዲስ የተፈጠረ ነገር ባይኖርም የኤክስፕሬስ መንገዱ ሲከፈት ትራፊኩ በመቀየሩ ተጨማሪ መጨናነቅ ፈጥሯል፡፡ በመሠረቱ የመጣውን የትራፊክ መጨናነቅ የምናስተካክልበት አሠራር መኖር ነበረበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ የተወሰነ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ለማንኛውም ለአጭር፣ ለመካከለኛና ለዘለቄታ የሚሆኑ ነገሮችን ለመፍታት ያስችላሉ ያልናቸውን እየሠራን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እርስዎ በምዕራብ የከተማው ክፍል የበለጠ ጐልቶ ታይቷል ያሉትን መጨናነቅ ጠቀሱልኝ እንጂ፣ የትራፊክ መጨናነቅ በሁሉም የከተማው ክፍል የሚታይ ነው፡፡

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አዎ መጨናነቁ በሁሉም ቦታ አለ፡፡ በብዙ ቦታ መጨናነቁ አለ፡፡ እንዳልኩህ የተለየ ነገር አለ የሚያስብል የሚታየኝ ነገር የለም፡፡ ያን ያህል በአገሪቱ ውስጥ መኪና ሞልቶ ወይም በዝቶ ነው ለማለትም ያስቸግራል፡፡ ምናልባትም ትራፊኩን ለማሳለጥ የምንወስዳቸው የትራፊክ ማኔጅመንት ሥርዓቶቻችን፣ የመብራት አጠቃቀሙ ማኔጅመንታችንም የተወሰነ ችግር ሊኖርባቸው ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ በተረፈ በተለይ አደባባዮች አካባቢ ነው በብዛት መጨናነቅ እየተፈጠረ ያለው፡፡ መሀል ከተማ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በከተማዋ የሚካሄዱ የተለያዩ ግንባታዎች አሉና ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚሆኑ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በተለይ ችግሩ ጐልቶ የሚታየው ጠዋት በሥራ መግቢያና ማታ መውጫ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና ከትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትም ጋር ተባብረን እየሠራን ነው፡፡ ከማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋርም እየሠራን ነው፡፡ አንዳንዶቹ እየተጠኑ መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ በላይ ቀለበት መንገዱ ላይ ግን አስቸኳይ ማሻሻያ ስለሚያስፈልግ እሱ ላይ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማው የትራፊክ መጨናነቅ ጐልቶ የሚታየው አደባባዮች አካባቢ ነው፡፡ አሁን እንደገለጹልኝ አደባባዮቹን አፍርሶ ለጊዜው በመብራት መጠቀም ያስፈልጋል ብላችኋል፡፡ ይህ እንዴት ነው ተግባራዊ የሚሆነው? እንዲህ ካለው ጊዜያዊ መፍትሔ ባሻገር ለዘለቄታው ምን ታስቧል?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በመሠረቱ የቀለበት መንገድ ፈጣን ትራንስፖርት ሥርዓት የሚስተናገድበት ነው፡፡ በቀለበቱ መንገድ በፍጥነት ነድተህ ስትመጣ አደባባዮች ላይ ስትደርስ ትቆማለህ፡፡ አንዳንዶቹ አደባባዮች በጣም ጠባብ ናቸው፡፡ ስለዚህ ትቆማለህ፡፡ አደባባዮቹ አካባቢ ትራፊክ ፖሊስ ካለ ብዙ ሳትቆይ በተራ ልትስተናገድ ትችላለህ፡፡ ትራፊክ ፖሊሱ ዞር ካለ ሁሉም ሰው ቀድሞ ለማለፍ የሚራኮትበት በመሆኑ መጨናነቁን ያብሳል፡፡ ስለዚህ እዚህ አካባቢ ያለውን ችግር ለጊዜው ለመቅረፍ የተሻለ ይሆናል ብለን የደረስንበት አደባባዮቹን በማፍረስ ትራፊኩን በመብራት እንዲስተናገድ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ጊዜያዊ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አደባባዮች ላይ ተላላፊና ተሻጋሪ መንገዶች ያስፈልጋሉ፡፡ የደረጃ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንግዲህ ያኔም ቢሆን መገንባት የነበረበት ነው፡፡ አሁን ግን ሲታይ ትራፊኩ ከሚጠበቀው በላይ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በምዕራቡ ክፍል ያለውን ችግር በተሻጋሪ መንገድ ለመፍታት የሚያስችለውን ሥራ ለመሥራት ሒደቱ ጨረታ ላይ ነው፡፡ ሌሎች መስመሮችን ለመክፈትም እየተጠና የሚመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተላላፊ መንገዶች ይሠሩባቸዋል፣ ይፈርሳሉ የተባሉት የአደባባዮች የትኞቹ ናቸው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በአጠቃላይ በቀለበት መንገዱ ላይ ባሉ አደባባዮች በሙሉ ተላላፊ መንገዶች ይገነባሉ፡፡ ለምሳሌ ኢምፔሪያል ሆቴል፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ቃሊቲ አደባባይ፣ ለቡ፣ አስራ ስምንት ማዞሪያ አደባባዮችና የመሳሰሉት ሁሉ ተላላፊና የማሻሻያ መንገዶች የሚገነቡባቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በየአደባባዮቹ ይሠራሉ የተባሉ ተላላፊ መንገዶች ግንባታ ቀላል አይሆንም? ለዚህ የሚሆን በጀት አለ?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ጥናቱና ዲዛይኑ እንዳለቀ በበጀት ዓመቱ ወደ ግንባታ ለመግባት በጀቱን ማስፈቀድ ይቻላል፡፡ ካልደረሰልን ግን ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል፡፡ እስከዚያው ግን ጊዜያዊ መፍትሔዎቹ ይተገበራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የትራፊክ መጨናነቅና የመንገድ ጥገናዎች ሲታሰቡ የከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ችግሮች ይነሳሉ፡፡ የከተማ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ በተለይ በቀለበት መንገድ በተለያዩ አካባቢዎች ዝናብ በዘነበ ቁጥር መንገዱ ላይ የሚተኛው ውኃ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ያቆማል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዴት ይፈታሉ? ለምንስ መፍትሔ አይኖራቸውም? እርስዎስ ምን አሳስበዋል?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በመሠረቱ ለመንገድ ሀብታችን ማኔጅመንት የተሰጠው ትኩረት እውነት ለመናገር ከከተማው ፍላጐት ጋር የተጣጣመ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ተደራሽም አይደለም፡፡ አሥር ክፍላተ ከተሞች የያዘ ከተማ ኖሮህ ሌላው ቀርቶ በዋናው መሥሪያ ቤት እንኳን የተጠናከረ የሀብት ማኔጅመንት በሌለበት ለማስተናገድ ያስቸግራል፡፡ በእርግጥ የበጀት እጥረትም አለ፡፡ እየጠገንን ያለነው በትንሽ በጀት ነው፡፡ አሁን ግን ለጥገና ሥራ ተጨማሪ የጥገና በጀት እየተመደበ ነው፡፡ ስለዚህ ለምሳሌ አንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ ሁለት ክፍለ ከተሞችን የሚመራበት አሠራር ቢኖር የመንገድ ጥገናዎችን በባለቤትነት ማስተዳደር ይቻላል፡፡ ጥገናውን እየተከታተለ ይሠራል፡፡ ችግር ሲደርስ ደግሞ ወዲያው ዕርምጃ የሚወስድ፣ ሕገወጥ ሁኔታዎች ሲኖሩ እዚያው ወዲያው ዕርምጃ የሚወስድ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ አለመኖርና ትኩረት ያለመስጠት ነው እንጂ ችግሩ ሌላ ነገር የለም፡፡

ከዚህ በተረፈ በአብዛኛው የመንገድ ጥገና በራስ ኃይል (በባለሥልጣኑ ሥር ያለ የግንባታ ክፍል) የሚሠራ ነው፡፡ ወደፊት የግል ዘርፉ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የቀለበት መንገዱ ጥገና ሥራን ለኮንትራክተሮች ለመስጠት በጨረታ ሒደት ላይ ነን፡፡ ትልልቅ የምንላቸውና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው መንገዶችን ለማስጠገን ሥራው ለኮንትራክተር ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የጥገና ሥራዎች በራስ ኃይል ነበር የሚሠሩት?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አዎ በአብዛኛው በራስ ኃይል ነበር የሚሠሩት፡፡ በነገራችን ላይ ወደፊት የኮንትራት ሥራዎች ይቀየራሉ፡፡ የግንባታ ኮንትራት ውሉ ከግንባታ መጠናቀቅ በኋላ የጥገና ሥራውንም እንዲያጠቃልል፣ የግንባታ ሥራው እንዳለቀ ለ10 እና ለ15 ዓመታት የጥገና ሥራውንም ደርቦ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ ለኮንትራቱ የሰጠነውን ያህል ለጥገና የሰጠነው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ችግር ካወቃችሁ አሁንስ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አሁን በዚህ ክረምት ውስጥ ስድስት ቡድኖች አቋቁመን በአጠቃላይ በከተማ ውስጥ ያለውን ችግር በዘመቻ ሠርተን፣ ምን ያህል በጀት ለጥገና ያስፈልገናል የሚለውን አውቀናል፡፡ 270 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለጥገናው ሥራ ማለት ነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አዎ፡፡ ስለዚህ ከሚያስፈልገን ውስጥ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት 63 ሚሊዮን ብር ይመድባል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለውን ደግሞ ከመስተዳድሩ በጀት ጠይቀን ለመሥራት ነው፡፡ ስለዚህ በተሻለ ጥራት እየሠራን ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ቁጥር አንድ ጉዳይ ነው፡፡ የጥገና ሥራውን ሌሊት ነው የምንሠራው፡፡ ከተማ ስለሆነ ቀን ላይ መሥራት አመቺ አልሆነም፡፡ ነገር ግን ከትራፊክ ፖሊስ ጋር ተነጋግረን ቀን ላይ የሚሠራበት አግባብ ከሌለ ሥራው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ጥራቱ ላይም ችግር ሊኖረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥገና ሥራዎችን ከጀመራችሁ እስካሁን ያከናወናችሁትን ሊገልጹልኝ ይችላሉ? አሁንም ጥገና የሚሹ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በመጀመሪያው ምዕራፍ ዋና ዋና በምንላቸው ቦታዎች ላይ ጥገና ጀምረናል፡፡ ሣር ቤት አደባባይ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ በአራት ኪሎ አድርጐ ወደ ሽሮ ሜዳ፣ ፍልውኃ እየተጠገነ ነው፣ ተጀምሯል፡፡ በቀለበት መንገድም ከመገናኛ ጀምሮ እየተጠገነ ነው፡፡ ከአዲሱ ገበያ የባቡር መስመሩን ተከትሎ ወደ ቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የሚወስደው መንገድ ላይም ጥገና እየተሠራ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው፡፡ ወደ ሌሎችም እንሄዳለን፡፡ የጥገና ሥራውን ግን በራስ ያህል ብቻ መሥራት አይበቃም፡፡ የከፋው የከፋው ላይ ግን እየሠራን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የመንገድ ጥገና ጉዳይ መሠረታዊ እየሆነ ነው፡፡ መንገዶች እየተገነቡ ከመሆኑ አንፃር ከሥር ከሥር በቶሎ ጥገና የሚሹ መንገዶች እየበረከቱ ሄደዋል፡፡ ለመንገድ ጥገናው ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- አንደኛው ጉዳይ አዲስ መንገድ ከተረከብን በኋላ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች እንዲከታተሉ ማድረግ ነው፡፡ እንደ እኔ ቅድም እንደገለጽኩልህ የኮንትራት ባህሪዎችን እየቀየርን መሄድ አለብን፡፡ ‘ቢውልድ፣ ኦፕሬት ኤንድ ትራንስፈር’ ዓይነት ነገሮችን ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ግንባታውንና ጥገናውን የማስተዳደር ሥራውን ያጠቃለለ ኮንትራት መስጠቱ ጠቀሜታው ምንድነው?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮንትራክተሩ መንገዱን ሲገነባ ለረዥም ዓመት የጥገና ሥራውንም እንደሚሠራ ያስባል፡፡ ይህን ካወቀ የወደፊት ወጪውን ለመቀነስ ከመጀመሪያው ግንባታውን ተጠንቅቆ ይሠራል፡፡ ሌሎች ጠቀሜታዎችም አሉት፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመንገድ ማኔጅመንቱ የሰጠነው ትኩረት ብዙም አይደለም፡፡ አሁን ነው እየገፋ የመጣው፡፡ ምክንያቱም ብዙ መንገዶችን ሠርተን ሠርተን አሁን እየተጐዱ ስለሆነ ምርመራ ከሚደረገው ጊዜ አስቀድሞ ከፍተኛ የጥገና ወጪ እየጠየቀ ስለሆነ ጥገና ዓብይ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል የመጀመሪያው ዕርምጃችን ያልተማከለ ማድረግ ነው፡፡ የትራንስፖርት ችግርን የሚፈታ ነገር ማምጣት ነው፡፡ ከዚህ በኋላም መንግሥትም ለመንገድ ሀብት እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ ስለሆነ በቂ በጀት ይመደባል ብለን እናስባለን፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ከተፈቱና ጥገናው ላይ የግል ኮንትራክተሮች እንዲገቡ ከተደረገ ዘላቂው መፍትሔ ያን ያህል ያስቸግራል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አሉዋችሁ?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- በእጃችን ወደ 250 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችም ይኖሩናል፡፡ ለዘንድሮ ሥራችን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል፡፡ በተጨማሪ በጀትም ያስፈልገን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አቅም ካላነሰ እንሠራለን፡፡ ዘንድሮ ብዙ ኮንትራት ሰጥተን አሁን ባለው ሁኔታ ጥገናው ላይ ጊዜ ስለሚወስድ የራስ ኃይሉ በጥገናው ላይ እንዲያተኩር ነው፡፡ ምናልባት የራስ ኃይሉ የጀመረውን እንዲጨርስ እንጂ አዲስ ሥራ ግን ብዙ እንዳይወስድ ነው ያደረግነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ዓላማ ጥገና ላይ አተኩሮ መሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፍሳሽ ማስወገጃ ችግርን በተመለከተ በድጋሚ ማንሳት የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ በቀለበት መንገዱ የተለያዩ ቦታዎች ዝናብ ሲዘንብ ውኃ ይተኛል፡፡ ይህ የቀለበት መንገዱ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን እንቅስቃሴ ሲያውክ እየታየ እስካሁን መፍትሔ አልተበጀም፡፡ ለዚህ ችግር እርስዎ ምን አስበዋል?

ኢንጂነር ሀብታሙ፡- መንገድ ጥገና ስንል ፍሳሽ ማስወገጃውንም ይጨምራል፡፡ የመንገድ ምልክት፣ የእግረኛ መንገድና የመሳሰሉትንም ያካትታል፡፡ ፍሳሽ ማስወገጃን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ በጣም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ክረምት ላይ ውኃ አስፋልት ላይ ይፈሳል፣ ይተኛል፡፡ በመሠረቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የፍሳሽ ማስወገጃ ማስተር ፕላን በከተማው አስተዳደር እየተጠና ነው፡፡ ጥናቱ በዓለም ባንክ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል፡፡ አሁን ያሉትን የፍሳሽ ማስወገጃዎች ችግር ስንመለከት አንዳንዶቹ ላይ በዲዛይኑ ያልታዩ ታሳቢ ያልተደረጉ በኋላ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡ ፍሳሽ ማስወገጃው ሊደፈን ይችላል፣ መቀበያዎቹ የመጥበብ ችግር ያለባቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ በቀለበት መንገድ ውኃ መቀበያዎቹ ጠባብ ናቸው፡፡ ያልፀዱም አለ፡፡ ለችግሩ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ከመንገድ ጥገናው ጋር እያየን እየሠራን ነው፡፡ መንገዶቹ ሲሠሩ የነበሩ ችግሮች ከሆኑ ይህ ፈተና ነው፡፡ ግን ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ስታየው በአጭር ጊዜ በጣም ብዙ ሥራዎች ናቸው የተሠሩት፡፡ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል ብዙ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ ቅድም እንዳልኩት ማኔጅመንቱን የተሻለ ለማድረግ የሚቻልባቸው አማራጮች አሉ፡፡ እሱን ማስተካከል አለብን፡፡ እንደኔ በጣም ብዙ ሥራ መሥራት ያለብን በመንገድ ሀብት ማኔጅመንቱ ላይ ነው፡፡ የተሠራው መንገድ በአግባቡ እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ሁልጊዜ የሕዝብ ፍላጐት ያድጋል፡፡ እሱን እየተከታተሉ መፍትሔ መስጠትና የሚሠሩ ሥራዎችን ምን ያህል ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ፕሮጀክት አድርጎ ማየት ነው፡፡ ዕድገት አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ በሌሎች አገሮችም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ አለ፡፡ ዋናው ነገር መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...