Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአሥር ቢሊዮኑ ፈንድ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት ዓመቱን ሥራ ሲጀምር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ካደረጉት ንግግር ውስጥ ከወቅታዊ የአገሪቱ ትኩሳት ጋር በተገናኘ ይደረጋሉ ከተባሉት ለውጦች መካከል ወጣቶችን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንደሚቋቋም ይደረጋል የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለፈንዱ መነሻ እንዲሆን አሥር ቢሊዮን ብር መመደቡንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ፈንዱ የሚቋቋመው እንዴት እንደሆነ፣ የገንዘብ ምንጩ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን አልተጠቀሰም፡፡ ቢሆንም የተንቀሳቃሽ ፈንዱ ዋነኛ ዓላማ ወጣት ሥራ አጦችን ይታደጋሉ ተብለው ለሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች የሚውል ነው፡፡

በፈንዱ አጠቃቀም ላይ ከወጣቶች ጋር የሚመከርበት ስለመሆኑም በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ ተካቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ካለው የወጣት ሥራ አጦች ቁጥር አንፃር የተጠቀሰው ገንዘብ ምን ያህሉን ሊታደግ ይችላል? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህን ያህል ደረጃ ቦታ የተሰጠውን ይህ ጉዳይ በትክክል ወደ መሬት ለማውረድና እንደገንዘቡ መጠን ሁሉ ሥራውን ማከናወን ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህንን ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ምን ያህል ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ ዝርዝር መረጃ ባይኖርም፣ ለፈንዱ ይውላል ከተባለው የገንዘብ መጠን አንፃር ጥሩ ማኔጅመንትና ልቡንም ሐሳቡን የሚሰጥ ቆራጥ አመራር ያስፈልገዋል፡፡ ወጣም ወረደ ይህ ገንዘብ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ምናልባትም ፈንዱ አንድ የገንዘብ ምንጭ ኖሮት መጠኑ እያደገ ሊሄድ ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ ያለው  የሀብት አጠቃቀም ሥርዓቱ ምን ይመስላል? ወጣቶቹ ሲመለመሉስ በምን መስፈርት ይከናወናል? ለወጣቶች ጥቅም ይውላል ሲባልስ በምን መልኩ ሊውል ታስቧል የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ግድ ነው፡፡ መንግሥት ገንዘቡን በምን ዓይነት የኢንቨስትመንት መስክ አፍስሶ ሥራ አጡን ባለሥራ ያደርጋል የሚለውም ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው የፈንዱ ዓላማን የሚያመላክት ዝርዝር ይዘት ሲታወቅ ነው፡፡

እንዲህ ያሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው ገንዘቡን በትክክል ለሚፈለገው ዓላማ ለማዋል በአንድ ወገን ብቻ የሚሠራ ሥራ ውጤታማ እንደማያደርገው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ገንዘቡ አሁን ያለውን ትኩሳት በጊዜያዊነት ለመፍታት ብቻ የታለመ አለመሆኑንና ዘላቂ መፍትሔን ሰንቆ እንዲጓዝ ካስፈለገም የፀዳ አሠራር መቅረጽ ይገባል፡፡ መንግሥት አድርባይና ልባቸው ከሕዝቡ የሸፈቱ አመራሮቹን ወደ ጎን እያደረገ፣ በወጣቱ ላይ ያለውን እምነትም እያሳደገ ቢሄድ ለሚሠራቸው ሥራዎች በቀላሉ ተቀባይነትን ያተርፉለታል፡፡ ለወጣቶች አቋራጭ የገንዘብ ማካበቻ መንገዶችን የሚያመቻቹ፣ ቢዝነስ ሠርተው የሚሠሯቸውን ሳይሆን አገርን አሳይተው፣ ለአገር የሚሠሩ፣ ለአገር የሚኖሩ፣ ለቤታቸው የሚቀኑ፣ ለነጋቸው የሚተጉ እንዲሆኑ የሚያጸናቸው የአመራር ትውልድ ይሻሉ፡፡ የስደትን መንገድ ሳይሆን የአገር ማቅናትን ጎዳና የሚጠርግላቸው ባለፋና ካገኙ፣ በአሥር ቢሊዮኑ ላይ ብዙ ቢሊዮኖችን የሚጨምሩ የአገር ልጆች በርካታ ናቸውና ቦታውም፣ ጊዜውም ይሰጣቸው፡፡  

ይሁንና መንግሥት የገለጸው ገንዘብ አዋጭ የሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲውል ምክረ ሐሳብ መሰብሰብ ያለበት የገንዘቡ ተጠቃሚ ይሆናሉ ከተባሉት ወጣቶች ጋር ብቻም ሳይሆን በየእርከኑ ካሉ አካላት ጋር በመሆንና በመመካከር መሆን ይኖርበታል፡፡

እርግጥ ይህንን ያህል ገንዘብ አለና በምን ሥራ ላይ እናውለው ማለቱ ተገቢ ቢሆንም፣ ፈንዱን በአግባቡ ለመጠቀም ነፃና ገለልተኛ ተቋም አቋቁሞ አዋጭ የሆኑ ፕሮጀክቶች እንዲቀርጹ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን እንዲህ ያለው ትልቅ ዕቅድ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ነፃ በሆነ መንገድ ፈንዱን የሚያስተዳድር ተቋም ሲኖር ነው፡፡ በፈንዱ በሚቋቋሙ ፕሮጀክቶች ውስጥ ባለቤት የሚሆኑት ወጣቶች እንዲሆኑ ማድረግ፣ በባለቤትነት እንዲቋቋሙ የተደረጉት ፕሮጀክቶችም የፈሰሰባቸው ገንዘብ ትርፍ አፍርተው የሚመልሱ፣ ሌላ ብዙ ገንዘብ የሚወልዱና ሌሎች ብዙ ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሊሆን ይገባቸዋል፡፡ መንግሥት ፈንዱን እንዴት መጠቀም ይቻላል? የሚለውን የራሱን ሐሳብ ይዞ የባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ እንዲቀበልና ተግባራዊ እንዲያደርግ ይመከራል፡፡ ወደ ውስጥ ወደ ራስ ማየት ለእንዲህ ያለው ጊዜ መጥቀሙ እዚህ ላይ ነው፡፡  

አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ ፈንዱ የፖለቲካ መጠቀሚያና የጭልፊቶች ሲሳይ እንዳይሆን ሁሉንም በእኩልነት ሊያስተናገድ የሚችል አሠራር ሊቀረጽለት እስካልተቻለ ድረስ የሚፈለገውን ግብ መምታት ይቻለዋል፡፡

በቂ ጥናት ያልተደረገላቸው ፕሮጀክቶች  ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶባቸው እንዲሁ መባከናቸውን የሚሳዩ የቀደሙ ልምዶችና መረጃዎች ስላሉ፣ የቀደመው ግድፈት እንዳይደገደም እርግጠኛም ቁርጠኛም መሆን ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ቢሊዮኖች ይፈስባቸዋል ተብለው የተያዙ ፕሮጀክቶች ከግብ ያልደረሰቡት ምክንያት ተደርጎ ከሚጠቀሰው ውስጥ ብቁ ላልሆኑ አመራሮች ኃላፊነቱ ይሰጥ ስለነበር ነውና ፈንዱ ከእንዲህ ያለው ነገር የራቀ እንዲሆን ቀድሞ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት