Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአፍሪካ የእርስ በርስ ንግድ የሚጠበቀው የአፍሪካ ነፃ ገበያ ቀጣና ስምምነት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በድንበር ተጋሪ አገሮች መካከልም ቢሆን የንግድ ልውውጡ ትርጉም ያለው ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የንግድ ለውውጡ አለ እንኳ ቢባል አብዛኛውን እጅ የሚይዘው ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገሮች ጋር የሚደረገው ግብይት ነው፡፡ የንግድ ሚዛኑ ሲታይም አፍሪካውያን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡት ይልቅ የሚገዙት ገዝፎ ይታያል፡፡ ሚዛኑ የሚያደላውም ከአፍሪካ ውጭ ላሉት የንግድ ሸሪኮቻቸው ነው፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ አፍሪካ ለምግብ ፍጆታ ብቻ በዓመት ከ300 ቢሊዮን ዶላር በላይ እያወጣች እንደምትገኝ የሚያመላክት ነው፡፡ ምግብ ነክ ምርቶችን ሳይቀር አፍሪካ ከውጭ ለመሸመት ከተገደደችባቸው ምክንያቶች አንዱ በአኅጉሪቱ የሚካሔደው የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ደካማ መሆን ነው፡፡ ይህንን ለመለወጥ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የደረሱበት ስምምነት ተስፋ ቢጣልበትም፣ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቀሪ ሒደቶች አሉ፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣናውን መመሥረቱ አስፈላጊና ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ከአፍሪካ ውጭ ያለው ግብይት ለእርስ በርስ ግብይት ቦታውን እየለቀቀ በአንፃሩ የእርስ በርስ ግብይቱ እንዲጧጧፍ ለማድረግ በርካታ የቤት ሥራዎች ገና ባለመጠናቀቃቸው ሒደቱን አዝጋሚነት እንደሚታይበት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አፍሪካውያኑ ዕድሉን በመጠቀም የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት የሚችሉበት በርካታ አማራጮች መኖራቸውንም የሚጠቁሙ አሉ፡፡ ይሁንና እንዲህ በተስፋ የሚጠበቀውን የነፃ ገበያ ቀጣና ስምምነትን ኢትዮጵያ ገና ለመፈረም ዳር ዳር እያለች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ ማኔጅንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚጠቅሱት፣ ለአኅጉሪቱ የእርስ በርስ ግብይት ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት አንዱን አገር ከሌላኛው የሚያገናኝ ደረጃውን የጠበቀ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት አለመኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የአኅጉሪቱ አንድ አካል እንደመሆኗ የንግድ ልውውጧ አፍሪካን መሠረት ያደረገ ሳይሆን፣ ከአፍሪካ ውጭ ያሉ አገሮችን የሚማትር ነው፡፡ በጥቅሉ የአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት እንከንና ተስፋዎች እንዲሁም የኢትዮጵያን ዕቅድ በተመለከተ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ከዳዊት ታዬ ጋር ያደረጉት አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ ትልቅ የገበያ መዳረሻ አኅጉር ነች እየተባለ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን አፍሪካ ውስጥ ያሉ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ልውውጣቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? አሁን ላይ ያለው የእርስ በርስ ግብይቱ መጠን ምን ያህል ደርሷል?

አቶ ዘመዴነህ፡- የኢንትራ አፍሪካ ትሬድ ወይም የአፍሪካ አገሮች የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አጠቃላይ ንግድ ውስጥ አፍሪካውያን አገሮች እርስ በርስ የሚነግዱበት አግባብ ወይም የእርስ በርስ የንግድ መጠናቸው 12 በመቶ ብቻ ነው፡፡ 88 በመቶ የሚሆነው የንግድ ልውውጥ ከአፍሪካ ውጭ ካሉ አገሮች ጋር የሚደረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ጋር 300 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ ከአሜሪካ ጋር 75 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የንግድ ልውውጥ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአፍሪካውያን የእርስ በርስ ግንኙነት በሌሎች አኅጉሮች ውስጥ ያሉ አገሮች እርስ በርስ ከሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ጋር ሲነፃፀር የአፍሪካውያን የእርስ በርስ ንግድ አነስተኛ ስለመሆኑ አኃዙ ያሳየናል፡፡ ለምሳሌ አውሮፓውያን ከጠቅላላ የንግድ ልውውጣቸው ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው እዛው በአውሮፓ ውስጥ ባሉ አገሮች ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚነጋገዱበት ነው፡፡ የተቀረው 40 በመቶ ግን ከሌሎች አገሮች ጋር የሚገበያዩት ይሆናል ማለት ነው፡፡ የአፍሪካውያን የእርስ በርስ ግብይት 12 በመቶ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዕድገቱም ቢሆን አዝጋሚ  ነው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2000 አንደኛው አፍሪካዊ አገር ከሌላኛው አገር ጋር የፈጸመው ግብይት ከጠቅላላው የአኅጉሪቱ የንግድ ልውውጥ አኳያ ሲታይ ይዞ የነበረው ድርሻ አሥር በመቶ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 12 በመቶ ላይ ብቻ መድረሱ ዕድገቱ እጅግ አዝጋሚ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካውያን የንግድ ልውውጣቸው የዚህን ያህል ዝቅተኛ የሆነበት ዋናው ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዘመዴነህ፡- ይህ ለምን ሆነ ብለን ስናይ በዋናነት እንደምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው የመሠረተ ልማት ካለመሟላት ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ አንዱን የአፍሪካ አገር ከሌላው የአፍሪካ አገር የሚያገናኙ መንገዶች የሉም፡፡ ያሉትም ቢሆኑ ለንግድ የሚያመቹ አይደሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ የቢዝነስ ሰው ከአንድ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላ የአፍሪካ አገር በአውሮፕላን ለመጓዝ ቢፈልግ በጣም ይቸገራል፡፡ ከተወሰኑ አገሮች በቀር የአየር ትራንስፖርት ሳይቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ካሉ አገሮች በስተቀር ብዙዎቹ የራሳቸው አየር መንገድ የላቸውም፡፡ እንደውም ወደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተነስተው መብረር ቢፈልጉ በመጀመሪያ ወደ አውሮፓ ተጉዘው እንደገና ወደ አፍሪካ የሚበር አውሮፕላን ፈልገው ነው የሚጓጓዙት፡፡ ስለዚህ ለአፍሪካውያን የእርስ በርስ ንግድ የመሠረተ ልማት ያለመሟላት አንዱ ችግር ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሌላው ችግር ድንበር አቋርጦ ለመጓዝ የሚስችል የተመቻቸ ነገር ያለመኖሩ ነው፡፡ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ለመጓዝ ሲፈለግ ሁሉ ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ከባድ ነው፡፡ ድንበር ላይ ያለው ቢሮክራሲ ውስብስብና አስቸጋሪ ነው፡፡ ድንበሩን ለመሻገር ድንበር ላይ የሚጠየቀው የወረቀትና የሰነድ ሥራ በርካታ ነው፡፡ ለእርስ በርስ የንግድ ልውውጡ እንደ እንቅፋት የሚቆጠረውና ሊጠቀስ የሚችለው ሌላው ጉዳይ በአኅጉሪቱ ውስጥ ያሉት የኢኮኖሚ ወይም የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ በርካታ ተቋማት በርካታ ሆነው መገኘት ነው፡፡ እርግጥ ቁጥራቸው እየቀነሰ ቢመጣም ብዛታቸው ግን አንዱ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪካ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች የጋራ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) አለ፡፡ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ስትወጣ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (ኢስት አፍሪካን ኮሚውኒቲ) የሚባል ተቋም አለ፡፡ በደቡብ አፍሪካም እንደዚያው ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በየቦታው ስትሄድ የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በቀጣና ገድበው የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ አውሮፓን ስታይ ግን አንድ የንግድና የኢኮኖሚ ቀጣና ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ስለዚህ በአፍሪካ ያለው ሁኔታ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ እርግጥ የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ለእርስ በርስ የንግድ ልውውጡ ዝቅተኛ መሆን ሌላው እንደ ምክንያት የሚታየው ነገር፣ አፍሪካውያን  ለገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች በአብዛኛው ጥሬ ዕቃዎች መሆናቸው ነው፡፡ ጥሬ ዕቃ ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላላቸው አገሮች የሚላክ ነው፡፡ አፍሪካ በአንፃሩ የማኑፋክቸሪንግ መሠረት የላትም፡፡ ቢኖሩም የተወሰኑ ናቸው፡፡ እስከዛሬ በብዛት ወደ ውጭ ሲልኩ የነበረው ኮፐርና ወርቅ፣ ተቆፍሮ እየወጣ የሚላከው በጥሬው ነው፡፡ ስለዚህ የብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የወጪ ንግድ በጥሬ ዕቃ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህንን ጥሬ ዕቃ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ቢሆኑ የሚገበዩት አይደለም፡፡ ጥሬ ዕቃውን የሚጠቀሙበት ፋብሪካም ያን ያህል የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ለአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት የተለያዩ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ለማካሃድ ምን ያህል ፍላጎት አላቸው? የአፍሪካ አገሮች የሚከተሏቸው  ሕጎችና ፖሊሲዎች ምቹ አለመሆንም ይጠቀሳልና ስለዚህ ምን ይላሉ?

አቶ ዘመዴነህ፡- ዛሬ የአፍሪካ አገሮች ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን ያለታሪፍና ያለ ኮታ መላክ ይችላሉ፡፡ የከኮታና ከታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድል (አጎዋ) አለ፡፡ የንግድ ቀጠናዎቹ ብዛት አነስተኛ ቢሆንና ሁሉም አገሮች በአንድ የንግድ ቀጣና ውስጥ ተካተው የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ኮታዎቹና ታሪፎቹ ለአኅጉሪቱ አንድ ወጥ ሆነው የሚሠራባቸው ቢሆኑ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ያሉት የንግድ ቀጣናዎች አምስትና ስድስት አገሮችን ብቻ የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ ከዚያ ውጭ ከሆንክ የነፃ ገበያ ዕድልና ተጠቃሚነትን አታገኝም ማለት ነው፡፡ ወደፊት ግን እነዚህ እየቀነሱ ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የነፃ ገበያ ቀጣናው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የተሻለ ለውጥ ይኖራል፡፡ ምናልባት ግን ከታሪፍ የበለጠ የመሠረተ ልማት አለመኖርና የቢሮክራሲው ጉዳይ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ከሌለህ ከፍተኛ እሴት የሚያመጣልህን ነገር አፍሪካ ውስጥ አምርተር መሸጥ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ቡና የሚላከው ወደ አውሮፓ ነው፡፡ ቡና ጀርመን ተልኮ ፕሮሰስ ተደርጎ ተመልሶ ለሌሎች አገሮች ገበያ ይቀርባል፡፡ ኢትዮጵያን ብትወስድ ቡናዋን ወደ ኬንያ ልትልክ አትችልም፡፡ ምክንያቱም ኬንያም ቡና አላት፡፡ ኬንያ ለመላክ ከፈለግህ ቡናህ ላይ እሴት ጨምረህ መላክ አለብህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወዲያው መሥራት ያለባቸው ሥራዎች እሴት የሚጨምሩ ምርቶችን በማምረቱ ላይ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ እንደጀመረችው አካሄድ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ካነሳን አይቀር በተለይ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ረገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ዕቅድ እንዳላት አስታውቃለች፡፡ ይህ ሲታሰብ የአፍሪካ ገበያ ታስቧል?

አቶ ዘመዴነህ፡- ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ጥራት ያለው ጫማ አሜሪካ ሄዶ  ተወዳዳሪ ሆኖ መሸጥ እንደቻለው ሁሉ ኬንያና ናይጄሪያ ወይም ታንዛኒያ ሄዶ መሸጥ የማይችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካውያን የመግዛት አቅም እየጨመረ ሲሄድ፣ ከሩቅ አገር ገዝተህ ከምታመጣ እዚሁ ጎረቤት ካለው መግዛት ስለሚቀልህ ያንን ትችላለህ፡፡  ዋናው ግን ለገበያው የሚሆን ምርት ማቅረብ መቻልህ ነው፡፡ በሐዋሳ የተገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲህ ያለውንም የአፍሪካ ገበያ ያየ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ በፓርኩ የሚመረቱ ምርቶች በዓለም ደረጃ መወዳደር የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሊሸጥ ይችላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት እንዴት ይታያል? ወደፊትስ ምን ይጠበቃል?

አቶ ዘመዴነህ፡- የንግድ ግንኙነቷ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ካለው ዕምቅ አቅም ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ወደፊት ግን የቻይና ፋብሪካዎች በብዛት እየመጡ ስለሆነ ከቻይና ዕቃ ለመላክ ይልቅ በኢትዮጵያ ካላቸው ፋብሪካቸው ወደ ሌላ የአፍሪካ አገሮች መላክ ስለሚቀላቸው ይህንን ሊያደርጉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት እያሰፋው ይሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ ይህንን ያህል የቻይና ፋብሪካዎች ወደ ኢትዮጵያ ወይም ወደ ሌላ የአፍሪካ አገር ነቅለው ይመጣሉ የሚለው ምልከታ አሁንም አለ?

አቶ ዘመዴነህ፡- አዎ፡፡ ይህ በመሆኑም በተወሰነ ደረጃ የእርስ በርስ ግብይቱን እንጨምራለን እንጂ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ወይም ወደ አፍሪካ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ ግን ዕድሉ አለ፡፡ ጎረቤቶቻችንን ተመልከት፡፡ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ወደፊት ደግሞ የሶማሊያ ኢኮኖሚ መረጋጋት ሲያሳይ፣ ከሩቅ አገር እየገዙ ከሚያመጡ ይልቅ እዚሁ ትልቅ የማኑፋክቸሪንግ እንብርት ኢትዮጵያ ስለምትሆን፣ እዚህ ሐዋሳ ኢንዱስሪ ፓርክ  ውስጥ የሚመረተው ምርት ለሶማሊያ በአንድ ቀን ተጓጉዞ ይደርሳታል ማለት ነው፡፡ ከቻይና ተገዝቶ አንድ ወር ፈጅቶ ከሚመጣ ይልቅ ከኢትዮጵያ የሚገዛው ምርት በሦስት ቀን ቢበዛ በሳምንት ይደርሳታል፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት እንዲጎለብት ምን መደረግ አለበት? ይህንን የገበያ ትስስር ለማምጣት ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ማነው? እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ተቋማት ሚናስ ምንድን ነው?

አቶ ዘመዴነህ፡- በአፍሪካ ደረጃ የሚዘረጋው የነፃ ገበያ ቀጣና አመሠራረትና አተገባበርን  የሚመለከተውን ዝርዝር ነጥብ የአፍሪካ ኅብረት በፖሊሲ ደረጃ ይዘውታል፡፡ በፖሊሲ ደረጃ ከላይ ሊመራ ይገባዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አገሮች  ቢሮክራሲውን ሊቀንሱበት የሚያስችላቸው ከአንድ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላ የአፍሪካ አገር ድንበር ስታቋርጥ ተግባራዊ የሚደረግበት መነሻ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ አንድ ዕቃ ኤክስፖርት ለማድረግ ያለው ሒደት ከ37 ቀናት በላይ ይወስዳል፡፡ እንደ አውሮፓ ባሉ አኅጉሮች ግን ከአሥር ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሒደቱ ያልቃል፡፡ እንዲህ ያለውን የረዘመ ጊዜ ሊቀንስ የሚችል አስፈጻሚ አካል ያስፈልጋል፡፡ መሠረተ ልማቱንም ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ የመሠረተ ልማት አስፈላጊነትን ለመጥቀስ በቅርቡ የተመረቀው የአዲስ አበባ-ጂቡቲ ምድር ባቡር መስመር በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ለአፍሪካ የንግድ ትስስር ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ከጂቡቲ አዲስ አበባ ለመምጣት 10 ሰዓት ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ለንግድ ልውውጡ ቅልጥፍና ይሰጠዋል፡፡ እንዲህ ያለውን መሠረተ ልማት ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኬንያ፣ ከኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ከኬንያ ግብፅ ወዘተ. እየተባለ መሠረተ ልማቱ ከተሠራ፣ ለእርስ በርስ የንግድ ልውውጡ ዕድገት መምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ስለዚህ የእርስ በርስ የንግድ ልውውጡን ለማቀላጠፍ ከላይ የአፍሪካ ኅብረት ከዚያም እንያንዳንዱ መንግሥት ሥራውን መሥራት አለበት፡፡ አሁን ላይ ግን ከባድ ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት አፍሪካ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ በቀደም አሊኮ ዳንጎቴ ቃለ ምልለስ ሲያደርግ፣ ወደ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ለመመላለስ 35 ቪዛ ያስፈልገኛል ብሏል፡፡ ትልቁ አፍሪካዊ ኢንቨስተር እንግዲህ ዳንጎቴ ነው፡፡ ዳንጎቴን የሚያህል ኢንቨስተር ይህንን ያህል ቪዛ ካስፈለገው፣ ትንንሾቹ የቢዝነስ ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ቢሮክራሲ ማሰብ ትችላለህ፡፡ ይህ እንደተጠቀ ሆኖ የአኅጉሪቱን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ የሚያሳድገው እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን የሚያመርቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች መሠረት ካለህ ብቻ ነው፡፡ ያው ጥሬ ዕቃ በመላክ የሚቀጠል ከሆነ ግን ግብይቱ ባለበት ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች