በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሃና ማርያም አካባቢ በሚገኘውና ‹‹ቀርሳ ኮንቶማ›› በመባል በሚታወቀው ሥፍራ፣ የወረዳውን ሥራ አስፈጻሚና ሁለት የፖሊስ መኮንኖችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ግብረ አበር ነበሩ የተባሉ 33 ግለሰቦች ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ከሰነድ አልባ (ጨረቃ) ቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በነዋሪዎቹና ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት፣ የወረዳ አንድ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ታሪክ ፍቅሬና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ የለቡ ፖሊስ ጣቢያ ሽፍት ኃላፊዎች የነበሩት ኢንስፔክተር ሚካኤል ሽፈራውና ረዳት ኢንስፔክተር ተስፋዬ ባህሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ተከሳሾቹ ግብረ አበሮች እንደነበሩ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ግብረ አበሮች በመሆን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539ን በመተላለፍ የሰው ሕይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ክሱን ለተከሳሾቹ በመስጠት በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመስማት ለጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡