Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአሜሪካና አውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን እንዳይጐዳ አሳሰቡ

አሜሪካና አውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቶችን እንዳይጐዳ አሳሰቡ

ቀን:

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና አውሮፓ ኅብረት በቃል አቀባዮቻቸው አማካይነት ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጐችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሳይጥስ እንዲፈጸም አሳሰቡ፡፡ ከየትኛውም ወገን ቢነሳ አመፅና ብጥብጥ ለአገር ስለማይጠቅም በሁሉን አቀፍ ድርድርና ውይይት ችግሮች እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ አማካይነት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተቀሰቀሰው ተቃውሞና አመፅ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሜሪካን እንዳስጨነቀ አመልክቷል፡፡ ‹‹ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር እንዲፈጸም መፍቀድና የኢንተርኔት አገልግሎት መዝጋትን ጨምሮ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን መገደብ፣ ሕዝባዊ ስብሰባን መከልከልና የሰዓት እላፊ ገደብ መጣልን ጨምሮ የመናገር መብት መገደብን የመሳሰሉ ተፅዕኖዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ይህ አዋጅ በዚህ ሁኔታ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነም በቅርቡ ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት አያስችልም፤›› ሲልም መግለጫው ያትታል፡፡

መግለጫው የዜጐችን መሠረታዊ መብቶች ማክበር የተቃውሞ ሠልፈኞችንና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ተገቢ የሆኑ ብሶቶች ምላሽ ለመስጠት አስፈላጊ እንደሆነም አስምሮበታል፡፡ ‹‹ለረጅም ጊዜያት ለኢትዮጵያ መንግሥት የምንገልጸውን የዜጐቹን መብት እንዲያከብር፣ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠላቸውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት እንዲያረጋግጥ፣ እንዲሁም መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በተግባር በማዋላቸው የታሰሩ ዜጐችን እንዲፈታ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ነፃና ትችት ያዘሉ ድምፆችን ማፈንና ማሰር በራስ ላይ ውድቀትን የሚጋብዝ ሲሆን፣ ልዩነቶችን ይበልጥ የሚያሰፋና በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይ የሆነ መፍትሔ ማግኘት አስቸጋሪ ያደርገዋል፤›› በማለትም መግለጫው የአሜሪካን ሥጋት መነሻዎች ያብራራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ወገኖች በአገሪቱ በቀጣይ የአመፅ ተግባራት ከመፈጸም እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ወደምትፈልገው ተሃድሶ የሚያደርሳት ጐዳና ሰላማዊ ውይይት ነው፤›› ሲልም የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቁሟል፡፡

መግለጫው መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግሥታቸው እንደ የመሬት መብት፣ የምርጫ ሕግን ማሻሻልና የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚያገኘው ጥቅም ዕውቅና መስጠትን ለመሳሰሉ የሕዝብ አቤቱታዎች ዕልባት እንደሚሰጥ ቃል መግባታቸውን አሜሪካ በመልካም ሁኔታ እንደተቀበለችው አመልክቷል፡፡ መንግሥት ቃል የገባባቸውን ጉዳዮች በአስቸኳይና በቁርጠኝነት በተግባር እንዲያውልና የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋትን ባለመ መንገድ ሁሉን አካታች ማሻሻያዎች በቀጠሮ እንዲያደርግ፣ አሜሪካ እንደምታበረታታም መግለጫው ገልጿል፡፡ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተረጋገጠውን ሰብዓዊ መብት እንደማይጥስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባውን ቃልም አጢነናል፤›› ሲል መግለጫው ይደመድማል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትም መግለጫ በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዳሉት፣ በማንኛውም ጊዜ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡ የፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መገደብ እንደሌለባቸውም በአጽንኦት ገልጿል፡፡

መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርላማው ሲከፈት ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግና ለሕዝቡ ቅሬታዎችና ብሶቶች ምላሽ ለመስጠት ቃል መገባቱንም መልካም አጋጣሚ ነው ብሎታል፡፡ ‹‹ይኼ ወደ አጠቃላይ የለውጥ ማዕቀፎች ሊመራ ይገባል፤›› ብሏል፡፡

በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ ደም አፋሳሽና አውዳሚ ግጭት ቦታ ሊኖረው እንደማይገባም አውሮፓ ኅብረት አሳስቧል፡፡ ‹‹አሁን በአገር ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ኃይሎች መረጋጋትን መመለስና ኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የልማት ጐዳና ላይ ሆና መቀጠሏን ለማረጋገጥ የሚተገብሩበት ጊዜ ነው፤›› ሲልም ደምድሟል፡፡

ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካወጀች በኋላ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዲፕሎማቶች የተለያዩ ጥያቄዎች እየቀረቡላት ይገኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከዲፕሎማቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በመድረኩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ዲፕሎማቶቹ ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረብን ነው በማለት ያቀረቡት ቅሬታ ተጠቃሽ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ለሥራ አስፈላጊ የሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ክፍት እንደሆኑና ግጭት ለመቀስቀስ ያስችላሉ የተባሉ ሚዲያዎች ላይ ብቻ ክልከላ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...