በአንድ ሙያዊ ሥልጠና ላይ ለመካፈል ከአንድ ጓደኛው ጋር ወደ ህንድ ያቀናው ከወራት በፊት ነበር፡፡ እንግዳ በሆኑባት ኒውዴል ከተማ እንደ ደረሱ ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸውና ወደተያዘላቸው ሆቴል የሚያደርሳቸው ሰው መመደቡ የተነገራቸው ከአዲስ አበባ ሳይነሱ በኢሜይል መልዕክት ነበር፡፡ ሲደርሱ ግን ያጋጠማቸው ከዚህ የተለየ ነበር፡፡
እንደደረሱ ‹‹ኢትዮጵያዊ ናችሁ?›› ሞቅ ባለ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላ ሰላምታ የተቀበለቻቸውን ወጣት ተከትለው ወደ አንደኛው የትኬት ወኪል ቢሮ አመሩ፡፡ የሁለቱንም ፓስፖርት ተቀብላም ፎቶ ኮፒ አደረገች፡፡ ሁኔታው ያላማረው ሰለሞን ስዩም የምታደርገውን ነገር በዓይነ ቁራኛ ይከታተላት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ፓስፖርታቸውን መልሳ አንድ መኪና አስመጣችና ሂዱ ብላ ከመኪናው ሹፌር ጋር አገናኘቻቸው፡፡
ሰለሞንም የት ነው የምትወስደን ብሎ ቋንቋ የሚቸግረውን ሹፌር ጠየቀ፡፡ በቋንቋ መግባባት ስላልቻሉ ነገሩ ወደ ጭቅጭቅ አመራ፡፡ ከዚያም ወጣቷ ተመልሳ በመምጣት ችግሩ ምን እንደሆነ ጠየቀቻቸው፡፡ ሰለሞንም የት እንደሚሄዱ ማወቅ እንደሚፈልግ ነገራት፡፡ የሚጠብቃቸውን ሰው አለማግኘታቸውን የተረዱት ‹‹አፖሎ ሆስፒታል›› ስትላቸው ነበር፡፡
አጋጣሚው የነሰለሞንን ፕሮግራም ከማጣረስ ባለፈ ህንድ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ያሳያል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ በህንድ ከተገኘ ወደ ሰው አዕምሮ የሚመጣው ነገር ለሕክምና መምጣቱ ብቻ እስኪሆን ድረስ ህንድ የሕክምና መዳረሻ ሆናለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የህንድ የሜዲካል ቱሪዝም እንዱስትሪ 3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2020 ከ7 እስከ 8 ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ሰዎች ለተሻለ ሕክምና ወደ ሌላ አገሮች የሚያደርጉት ጉዞ በብዛት በኮስሞቲክስ ሠርጀሪ፣ በጥርስ፣ በካንሰር፣ በተዋልዶ ጤና፣ በክብደት መቀነስና በልብ ቀዶ ሕክምና ምክንያት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሜዲካል ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከ45.5 እስከ 72 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ አብዛኛዎቹ የሜዲካል ቱሪዝም ተጠቃሚዎች ኮስታሪካ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ማሌዥያ፣ ታይዋን፣ ታይላንድን የመሳሰሉት አገሮችን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡
በሕክምናው ዘርፍ ብዙ የሚቀራቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችም የእነዚህ አገሮች ደንበኞች ናቸው፡፡ በተለይም እንደ ህንድ፣ ታይላንድ ያሉት በአብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን የሕክምና ዕርዳታ ፈላጊዎች ዘንድ ተመራጭ ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መሰል የሕክምና ጉዞዎች እስከ 6000 ዶላር ይፈጃሉ፡፡ ወደተለያዩ አገሮች የሚሄድ ኢትዮያዊያን የሚያወጡት ወጪ ደግሞ ከዚህ እንደሚበልጥ የማኅበረሰብ ተኮር ቢዝነሶች አማካሪው አቶ ታዲዮስ አበበ ይናገራሉ፡፡ አቶ ታዲዮስ እዚሁ ጎረቤት አገር ኬንያ ሄዶ ለመታከም እስከ 35,000 ዶላር እንደሚያወጡ ይናገራሉ፡፡ በህንድና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚሰጡ ሕክምናዎችም በተመሳሳይ ውድ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
700 ዶላር የማይደርስ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባላት አገር ውስጥ ለሚኖር ማኅበረሰብ እንኳንስ 35,000 ዶላር ከፍሎ መታከም 100 ዶላርም ከባድ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ለዚህም ለሕክምናቸው የሚያስፈልጋቸውን በ100 ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ክፈሉ የተባሉ ምስኪኖችን ጭንቀት መመልከት በቂ ነው፡፡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቤት ንብረትቸውን ሸጠው የሚንከራተቱ ብዙ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት የሞላ ኑሮ የነበራቸው ኩሩዎችን ሳይቀሩ የውጭ አገር የሕክምና ወጪን ለመሸፈን ለልማና እጃቸውን ሲዘረጉ ይታያል፡፡
የውጭ አገር ሕክምና ላላቸው ፈውስ ለሌላቸው ደግሞ የመሞቻ ቀናቸውን ቁጭ ብሎ የመጠበቅ ያህል ከባድ ነው፡፡ የተጠየቁትን ገንዘብ እስኪያሟሉ ድረስ በሽታቸው ሥር ሰዶ ለሞት የሚዳረጉ እንደሚኖሩም ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ባህር ማዶ መታከሙ ብቻ ለመዳናቸው ዋስትና አይሆንምና የተባለበት አገር ሄደው ተገቢውን ሕክምና ያገኛሉ አያገኙም የሚለው ጉዳይም ሌላው አጠያያቂ ነገር ነው፡፡
በርካቶችን ለዕንግልትና ለስቃይ የሚዳርጉት በውጭ አገር የሚሰጡ ሕክምናዎች በአገር ውስጥ መሰጠት የሚችሉበትን አቅም መገንባት ለበርካቶች ዕፎይታ ነው፡፡ የዚህ ጅማሮ ከሰሞኑ በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል ታይቷል፡፡ ‹‹ለሕክምና ወደ ውጭ አገር በመሄድ የሚያወጡትን ወጪ ያስቀሩ›› በሚል መርህ ከታኅሣሥ 2 እስከ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የተዘጋጀው ይህ የሕክምና አገልግሎት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዕፎይታን ሰጥቷል፡፡ የነርቭና የኅብለሰረሰር፣ አጠቃላይ ቀዶ ሕክምና፣ የአጥንት እንዲሁም የመካንነትና የማሕፀን ሕክምና ላይ ትኩረቱን ያደረገው ሕክምና የሰጡት ከህንድ የመጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
አገልግሎቱን ለማግኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሆስፒታሉን አጨናንቀው ነበር የሰነበቱት፡፡ ሪፖርተር ታኅሣሥ 5 ቀን ረፋዱ ላይ ሆስፒታሉን በጎበኘበት ወቅት ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ፈልገው በመጡ ታካሚዎች ሠልፍ ተናንቆ እንደነበር ታዝቧል፡፡ የሕክምና ክፍሎቹን ካጨናነቁ ታካሚዎች መካከል ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ውጪ አገር ድረስ ሄደው የታከሙ ነገር ግን መዳን ያልቻሉ፣ በሽታቸው በአገር ውስጥ ባለሙያና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች መታከም የማይችልና ውጭ ሄደው እንዲታከሙ የተነገራቸው እንዲሁም በአገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች ለዓመታት የታከሙ ነገር ግን መዳን ያልቻሉ ይገኙበታል፡፡
ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ካሉ ታካሚዎች መካከል በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘውና ከሦስተኛ ፎቅ ላይ ወድቃ በደረሰባት ከባድ ከባድ ጉዳት የምትሰቃየው ወጣት አንዷ ነበረች፡፡ ወጣቷ በደረሰባት አደጋ የዳሌ አጥንቷ የተጎዳ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የተደረገላት ሕክምና ጤናዋን ሊመልስላት አለመቻሉን ደግፏት የሚንቀሳቀሰው ወንድሟ ይነገራል፡፡
የምትሸናበትን ካቲተር በቀኝ እጇ ከያዘችው ብትር ጋር አጣብቃ ይዛዋለች፡፡ አደጋው ከደረሰባት ወራት የተቆጠረ ቢሆንም ስቃይዋ እስካሁን አብሯት እንዳለ ነው፡፡ ራሷን ችላ መንቀሳቀስ ስለሚቸግራት በአንዱ ጎኗ የያዘችው ብትር በሌላው ደግሞ ወንድሟ ይደግፋታለ፡፡ ሌሎች በተለያየ የዕድሜና የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ጋር ተራዋን ስትጠባበቅ የራቃትን ጤንነት መልሳ እንደምታገኝ በተስፋ ነው፡፡ እንዲህ ባለ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር በራሷ ወጪ ህንድ ድረስ ሄዳ መታከም እንደማትችል ድህነትና ህመም ተፈራርቆ ያጎሳቆለው ገጽታዋ ይናገራል፡፡
ለነገሩ የውጭ ሕክምና እንኳንስ እንደሷ ላለ ምስኪን የተሻሉ ለሚባሉትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ለዚህም አጋጣሚውን እንደ ገቢ ማስገኛ የሚጠቀሙበት ደላሎች መብዛት አንዱ ፈተና ነው፡፡ ከሆስፒታሉ መሥራቾች መካከል አንዱ አቶ ሲሳይ ሽመልስ የውጭ ሕክምና ጉዞዎች በደላሎች የተያዙ መሆናቸውን ‹‹ደላሎች ልክ እንደ መኪና ሽያጭ ተደራድረው ይልኩሻል፤›› በማለት ሕክምናን ወደ ቢዝነስ የቀየሩ ደላሎች የያዙትን ቁማር ይናገራሉ፡፡ ደላሎቹ ለታካሚዎቹ የሚነግሯቸው አጠቃላይ ዋጋም ተገቢውን ሕክምና ማግኘት የሚችሉበትን ሳይሆን ዝቅተኛውን ነው፡፡ ይህም ታካሚዎች መዳረሻቸው አገር ከገቡ በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚጠየቁ ይናገራሉ፡፡
በዚህም አብዛኞች ቤት ንብረታቸውን ሸጠው የሄዱ ያሰቡትን ሕክምና ሳያገኙ ለመመለስ ይገደዳሉ፡፡ ታክመው የሚመለሱም ቢሆኑ አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ማግኘት የሚችሉበት አሠራር ባለመኖሩ በአገር ውስጥ አልያም ከአገር ውጪ ሕክምና የሰጣቸው ተቋም ዘንድ ተመላልሰው የሕክምና ክትትል ማድረግ ባለመቻላቸው ለተጨማሪ እንግልት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
ፈውስን ለማግኘት ጥሪትን አሟጥጦ በሚደረገው የውጭ አገር የሕክምና ጉዞ እንደ ሸቀጥ በደላሎች እጅ መግባቱ በግለሰቦች ላይ ከሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ በአገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በግል ሆስፒታል የሚሠሩ አንዳንድ እንግዳ አስተናጋጆች ሳይቀሩ ዜጎች የውጭ አገር ሕክምና እንዲመርጡ ግፊት እንደሚያደርጉባቸው ይናገራሉ፡፡
ታካሚዎች በአገር ውስጥ ሕክምና የሚያገኙበትን አማራጭ በማሳየት ፈንታ ሕመምተኞችን ወደ ውጭ የሚልኩ ወኪሎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቶ ወደ 12 ደርሷል፡፡ አቶ ታዲዮስ እንደሚሉት፣ እነዚህ ወኪሎች በነፍስ ወከፍ ከ1,500 እስከ 2000 ሰዎችን ይልካሉ፡፡
በመሠረቱ ለሕክምና ወደ ውጭ የሚደረግ ጉዞ ተፈላጊው ሕክምና አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎችና የሕክምና መሣሪያዎች መስጠት ካልተቻለ የሚሰጥና የሚፈቀድ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ታካሚዎች ውጭ ሄደው እንዲታከሙ በደላሎች የሚደረግ ግፊት ምን ፋይዳ አለው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዶ/ር ይበልጣል መኰንን፣ አንድ ታካሚ ወደ ውጭ አገር ሄዶ እንዲታከም የሚወሰነው ሕክምናው በአገር ውስጥ መሰጠት እንደማይቻል በሐኪሞች ቦርድ ሲታመንና የምስክር ወረቀት ሲሰጡ መሆኑን ይናገራሉ ነገር ግን እነሱ የሚያስተላልፉት ውሳኔ የመጨረሻ አይደለም፡፡ በመንግሥትና በግል የጤና ተቋማት የሚሰጡ የሕክምና ዝርዝሮችን ከያዘው ናሽናል ሠርቪስ ዳይሬክቶሪ ላይ ዳይሬክቶሬቱ የተባለው ሕክምና መሰጠት አለመሰጠቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህ ሒደት አልፈው ፈቃድ የሚያገኙ ወደ ባህር ማዶ በሚደረጉ የሕክምና ጉዞዎች ከታካሚው ጋር አንድ አስታማሚ አብሮ ይሄዳል፡፡
‹‹ብዙዎቹ ወደ ህንድ፣ ታይላንድ መሄድን ይመርጣሉ፡፡ አሜሪካ ሄደው የሚታከሙም አሉ፤›› የሚሉት ዶ/ር ይበልጣል፣ በሚኒስቴሩ ፈቃድ የሚሄዱ ታካሚዎች የሚኒስቴሩን ፈቃድ የሚፈልጉት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብቻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከኅዳር ወር ጀምሮ እስካሁን 63 ታካሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሄደዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥም በአጠቃላይ 224 ታካሚዎች የሕክምና ጉዞ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ የሚሰጣቸው የጉዞ ፈቃድ ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሲሆን፣ አስፈላጊውን ገንዘብ ከጥቁር ገበያ ማግኘት የሚመርጡ ደግሞ የዳይሬክቶሬቱ ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው መጓዝ ይችላሉ፡፡
አብዛኛው ጉዞ የሚደረገውም ከዳይሬክቶሬቱ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ይበልጣል፣ የዳይሬክቶሬቱን ፈቃድ አግኝተው የሚጓዙ በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ ይናገራሉ፡፡ ከፍተኛውን ድርሻ በሚይዘው በግል በሚደረገው ጉዞ ደግሞ በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚወጣ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ታዲዮስ እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጽያ በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር በውጭ አገር ሕክምና ጉዞ ታጣለች፡፡
አጋጣሚው ሕመምተኞች በአገር ውስጥ ያለውን የሕክምና አማራጭ በጥልቀት ሳይመለከቱ የውጭ ሕክምናን እንደ ብቸኛ አማራጭ እንዲጠቀሙበት እያደረገ ይገኛል፡፡ በአገር ውስጥ የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ጥራት ላይ ችግር መኖሩ ቢነገርም የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መኖራቸውም ይወሳል፡፡
እነዚህን አማራጮች ሳይጠቀሙ የውጭ አገር ሕክምናን እንደ ብቸኛ መንገድ የመጠቀሙ ሁኔታ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ እያደረጋት ይገኛል፡፡ ብቻ ይህንን አማራጭ መጠቀሙም ምን የሚሉት አካሄድ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት ‹‹ሰዎች ለምርመራ ብቻ ወደ ባንኮክና ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ ከተሞች ይሄዳሉ፡፡ ለአንድ ምርመራ እስከ 600 ዶላር ድረስ ይከፍላሉ፤›› የሚሉት አቶ ታዲዮስ፣ ዜጎች ምክንያታዊ ያልሆነ የሕክምና ወጪ እያወጡና አገሪቱንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያሳጡ እንደሚገኙ ቁጭታቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹በእኛ በኩል የሚሄዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ በራሳቸው የሚወጡ ሲሆን፣ እነሱን መቆጣጠር አንችልም፤›› ያሉት ዶ/ር ይበልጣል፣ ለሕክምና የሚደረግ የውጭ አገር ጉዞ አጠቃላይ ገፅታን የሚያሳይ ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በተለይም የግሎቹ አብረው የሚሠሩበት ሥርዓት አለመኖር ለተፈጠረው ክፍተት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የጤና ተቋማትት ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችና ብቁ ባለሙያዎችን አጣምረው የያዙ ቢሆንም አብረው መሥራት ላይ ክፍተት በመኖሩ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ወደሚችለው ሪፈር የማድረግ ልምዱ ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ሲሳይ ይናገራሉ፡፡
እንደሳቸው አገላለጽ፣ በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል የተጀመረው የውጭ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ሕክምና እንዲሰጡ የማድረግ ጅምር በየወሩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህ ሒደት በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት ሁሉ በኔትወርክ ተሳስረው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ኔትወርኩ የሚሰጠው የሕክምና ዓይነት አንደኛው ተቋም ጋር ባለው መሣሪያ መሠራት የማይችል ከሆነ ተገቢው መሣሪያ ያለው ጋር ሄዶ መሠራት እንዲችል የሚያደርግ ነው፡፡
አገር ውስጥ ባለው በየትኛውም መሣሪያ ሕክምናውን መስጠት የማይቻል ከሆነ ደግሞ በውጭ አገር ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር መሥራት የሚቻልበትን አማራጭ የያዘ ነው፡፡ ወደ ውጭ ሪፈር የሚደረገውም በአገር ውስጥ ባለ ኃይል ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ከተጠናቀቁ በኋላ ይሆናል፡፡ የሕመምተኛውን አጠቃላይ ሁኔታም ሕክምናውን እንዲሰጥ ከተዘጋጀ የውጭ ባለሙያ ጋር በሚደረግ የቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲወያዩ ይደረጋል፡፡ ይህም ለሕክምና የሚወጣውን ወጪና እንግልት በከፍተኛ መጠን የሚቀንስ፣ ደላሎች የሚገቡበትን ክፍተትም የሚሞላ እንደሆነ አቶ ሲሳይ ይናገራሉ፡፡
‹‹በሌላ አገር የሚሠሩ የእኛ ሐኪሞች ብዙ ናቸው፣ የሙያ ችግር የለብንም፡፡ ዋናው ነገር አስፈላጊውን መሣሪያዎች ማሟላቱ ላይ ነው፤›› የሚሉት አቶ ታዲዮስ ደግሞ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት አድርጎ ቢሠራ አገሪቱ ከቡናና ሰሊጥ በተጨማሪ የሕክምና አገልግሎትን ኤክስፖርት ማድረግ የምትችልበትን አቅም የምትገነባበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡