Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፕሬዚዳንቱ መንግሥት በፍጥነት ሊመልሳቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ለፓርላማው አቀረቡ

ፕሬዚዳንቱ መንግሥት በፍጥነት ሊመልሳቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ለፓርላማው አቀረቡ

ቀን:

    – ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን አሳሰቡ

    – ተመጣጣኝ የሕዝብ ውክልና በአዲስ የምርጫ ሕግ ሊከበር ይገባል አሉ

    – ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ መከበር አለበት አሉ

- Advertisement -

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አገሪቱ ከገባችበት ሁከትና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለመውጣት መንግሥት በዚህ ዓመት በፍጥነት ሊመልሳቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦች፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባዔ አቀረቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓታችን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሁለቱን ምክር ቤቶች በምንከፍትበት በዛሬው ዕለት በብዙ መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከር እንደሚገባን ከማንም የተሰወረ አይደለም፤›› በማለት የመክፈቻ ንግግራቸውን ማሰማት የጀመሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ችግሮቻችንን መላ የአገራችንን ሕዝቦች በሚያረካ ደረጃ ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ በዝርዝር ልንመክርባቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ሙላቱ መንግሥት ትኩረት አድርጐ ሊመልስ ይገባል ካሏቸው ነጥቦች መካከል ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት የአገሪቱ ወጣቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህ እውነታ ወጣቶች የሚገኙበትን ሁኔታ በትክክል መገንዘብና ለችግራቸውም ሆነ ለጥያቄዎቻቸው የሚመጥን መሠረታዊ መፍትሔ ማቅረብ አጣዳፊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ በገጠር አካባቢ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን አብዛኛው ወጣት ኃይልም በዚሁ አካባቢ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ይህ ወጣት ኃይል መሬት አልባ በመሆኑ ከገጠር ጋር ተጣብቆ የሚቆይበት ምክንያት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ገጠርን እየለቀቀ ወደ ከተሞች እንዲንቀሳቀስ ግድ የሚልበት  ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለወጣቶች ታስበው የተቀረፁ ፕሮግራሞች በአድሎዓዊና በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ሲደነቃቀፉ የወጣቱ ትውልድ ቅሬታ እንደሚባባስ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

ስለዚህም የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መፍታት እንደሚገባ የገለጹት ዶ/ር ሙላቱ፣ በዚህ ረገድ መንግሥት በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚሁ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንደሚያቋቋም ገልጸዋል፡፡ ለዚሁ ሲባል ለፈንዱ ማቋቋሚያ አሥር ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሩ የተቻለውን ያህል መሬቱን ከፍተኛ ጥቅም ሊያገኝ በሚችልበት ሁኔታ እንዲያለማው ከማድረግ ጀምሮ ለላቀ አገራዊ ጥቅም በሚፈለግበት ጊዜ ደግሞ፣ ይህንኑ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ዘላቂ፣ ቀጣይና ታዳጊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መንገድ ሊፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሀቁ ይህ ቢሆንም በከተሞች አቅራቢያ የሚካሄደው ወይም በሌሎች አካባቢዎች የአርሶ አደርና የአርብቶ አደሮች መፈናቀል ከተመጣጣኝ ካሳና የማቋቋም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ጉድለቶች የሚታዩበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ ለከተሞች በቀረቡ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ለልዩ ልዩ ቅሬታዎች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በ2009 ዓ.ም. ይህንን ችግር መቅረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ያላግባብ መጠቀም የተጠናወታቸው ጥቂት ማኅበራዊ ኃይሎች ለአገራዊ ዕድገት ካበረከቱት አስተዋጽኦ በላይ ሲጠቀሙ የሚታይ በመሆኑ፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ በጥብቅ መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የፐብሊክ ሰርቪሱን የኑሮ ሁኔታ፣ እንዲሁም የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊቶችን ኑሮ የሚያሻሽልና ግሽበትን ታሳቢ ያደረገ የኑሮ ማስተካከያ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ትኩረት የሰጡት ከፖለቲካዊ መብቶች መሸራረፍ ጋር በተያያዘ አገሪቱ ስለገባችበት አጣብቂኝ ነው፡፡ ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከማስተናገድ አኳያ፣ በመንግሥትም ሆነ በኅብረተሰብ ደረጃ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ለሕዝብ ቅሬታ መከሰት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በፍጥነት ካለማረም ጀምሮ ሕዝብ የተጠማውን ቅሬታ በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ይገልጽ ዘንድ በበቂ ሁኔታ ያለማስተናገድ ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች በመንግሥትም ሆነ በኅብረተሰብ ደረጃ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን በማበልጸግ ተጨማሪ ዕርምጃዎች መራመድ እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ላለፉት ሁለት ምርጫዎች እንደተከሰተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ያለበት ሁኔታ ተስተውሏል፡፡

ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሙላቱ፣ ተቃዋሚዎችን የመረጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ አለመወከሉ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ተረጋግቶ ከመቀጠል አኳያ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመጠቆም የምርጫ ሕጉ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልናን የሚያጣምር የምርጫ ሕግ እንዲቀረጽ አሳስበዋል፡፡

ከማንነት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች እልባት መስጠት እንደሚገባው የገለጹት ዶ/ር ሙላቱ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በዚህ ዓመት በሕግ መከበር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...