Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበዘፈቀደ የሚመራው የግንባታ አካባቢ ደኅንነት

በዘፈቀደ የሚመራው የግንባታ አካባቢ ደኅንነት

ቀን:

በግንባታው አካባቢ የሚታየው የደኅንነት አጠባበቅ እንዝህላልነት ለብዙዎች ሞትና አካል ጉዳት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉት የሥራ ላይ የደኅንነት ሕግ፣ የግንባታ ፖሊሲ እንዲሁም ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሥራ ላይ ደኅንነት ሕጎች ከወረቀት አለመዝለላቸውም፣ በግንባታው ዘርፍ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እመርታ እያስመዘገበች በምትገኘው አገር፣ ለብዙዎች ሞትና ጉዳት አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡

በመላ አገሪቱ በተለይም የግንባታ ሥራዎች በሚጎሉባት አዲስ አበባም ለሥራ ላይ ደኅንነት የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባም አይባልም፡፡ ይልቁንም በተፃራሪው በጅምር ሕንፃዎች ሥር አገልግሎት መስጠት፣ ያለምንም የደኅንነት ትጥቅ መሥራት፣ ደረጃውን የጠበቀ የግንባታ አጋዥ መሣሪያዎች አለመጠቀም፣ የግንባታዎችን ሥፍራ በግዴለሽነት ያለንም የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክት መተው፣ በግንባታ ወቅት በግንባታው አቅራቢያ የሚኖሩ ቤቶች ላይ የመደርመስ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል አውቆ ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረግና ሌሎችም በግንባታ አሠሪዎች በኩል የተዘነጉና ቦታ ያልተሰጣቸው ስለመሆናቸው በአዲስ አበባ ባሉ የግንባታ አካባቢዎች ያለው እውነታ ምስክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ኢንቨስትመንት ፎረም ታኅሳስ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው ውይይት የቀረበው  ‹‹በግንባታው ዘርፍ የደኅንነት ጉዳይ›› ጥናት ያረጋገጠውም፣ የተዘነጋና በዘፈቀደ የሚመራ የግንባታ አካባቢ ደኅንነት በተለይ በአዲስ አበባ መንሰራፋቱን ነው፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተሠራውና በወ/ሪት ሳራ በርነህ እና ወ/ሮ ራቢያ ሁሴን የቀረበው ‹‹የግንባታ ሥራ አካባቢ የደኅንነት የዳሰሳ ጥናት›› እንዳመለከተው፣ የኮንስትራከሽን ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም፣ በተደጋጋሚ በሚከሰተው አደጋና በሠራተኞች ላይ በሚፈጠረው የጤና እክል ምክንያት ኢንዱስትሪው አደገኛ እየሆነ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ 377 የሥራ ተቋራጮች፣ 65 አማካሪዎች፣ 34 የግንባታ ባለቤቶችና 812 የግንባታ ሠራተኞች በመጠይቅ በተሳተፉበትና በ2009 ዓ.ም. ተሠርቶ በዕለቱ ይፋ በሆነው ጥናት፣ የግንባታ አካባቢ ደኅንነትን በተመለከተ የተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ደንቦች ቢኖሩም፣ የተቀመጡትን ሕጎች በርካቶች ቢያውቋቸውም የወጣውን ሕግ ተከታትሎ የማስተግበርና የማስፈጸም ሥርዓቱ የላላ ነው፡፡ ተግባራዊ የማያደርጉትን ለማስተማርም ሆነ ለመቅጣት የተቀመጠ የቅጣት እርከንም የለም፡፡

አብዛኞቹ የሥራ ተቋራጮች የደኅንነት አልባሳት የማያሟሉት ወጪን በመፍራትና የተሻለ ትርፋማ ለመሆን በማሰብ ሲሆን፣ በቁጥር አናሳ የሆኑት ደግሞ ገንዘቡ ኖሯቸውም ስለደኅንነት ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነ በጥናቱ ታይቷል፡፡

የደኅንነት ዕቃዎችና መሣሪያዎችን በተመለከተም፣ ተቋራጭና ሠራተኛው ለግንባታ አካባቢ ደኅንነት በቂ ትኩረት አለመስጠት፣ ለሚሠሩት ሥራዎች የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክት አለማስቀመጥ፣ የቀን ሠራተኞች ስለሚሠሩት ሥራ ጠለቅ ያለ  ዕውቀት አለመኖር፣ የደኅንነት አልባሳትን መጠቀም ያለውን ጠቀሜታ ጠንቅቀው አለማወቅም እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡

የመስክ ምልክታ ከተደረገባቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ 3.18 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የደኅንነት ባለሙያ መድበው እያሠሩ እንደሚገኙ፣ ሆኖም ሥራውን ወደ ጎን በመተው በሌሎች ሙያዎች የመሳብ አዝማሚያ ስለሚያሳዩ ውጤቱ አመርቂ እንዳልሆነና በአጠቃላይም በአገሪቱ ያለው የኮንስትራክሽን ነባራዊ ሁኔታ የግንባታ ደኅንነት ቅድመ ጥንቃቄው በልምድና በዘፈቀደ እየተሠራና ትኩረት የተነፈገው ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በተደጋጋሚ ለሚደርሱ አደጋዎችና መንስዔዎቻቸውም በሕንፃ ግንባታ ወቅት ከላይ በመውደቅና ከላይ በሚወድቁ ዕቃዎች መመታት፣ በቁፋሮ ወቅት አፈር መደርመስ፣ በቁርጥራጭ ብረቶችና ሚስማሮች መመታት፣ በዊንች (የከባድ ዕቃ ማንሻ) መበጠስ፣ በኤሌክትሪክና በማሽነሪ ሥራ ጥገና ወቅት መጎዳት ናቸው፡፡ 

ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘም፣ ግብዓት ከአንድ አካባቢ ከተወሰደ በኋላ ጉድጓድ ስለማይደፈን ውስጥ መግባት፣ ለፍሳሽ ተብለው ወይም ክዳናቸው በጠፉ ጥልቅ ጉድጓዶች ውስጥ መግባት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ መግባት፣ የጎርፍ አደጋ፣ በማሽን ሥራ ላይና ጥገና ወቅት የሚደርሱ አደጋዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የደኅንነት አልባሳትና የቅድመ ጥንቃቄ ምልክቶች አለመሟላት፣ ከግንዛቤ እጥረት ባልተነሳነሰ ሁኔታ ለደኅንነት ትኩረት አለመስጠት፣ በመንገድ ግንባታ ላይ የምሽት ሥራና የዲዛይን ችግር መኖር፣ በእግረኞች መንገዶች ላይ የኤሌክትሪክ ፖል፣ የቆሻሻ ማስቀመጫና ሌሎች መቀመጫዎችና በመንገድ ግንባታ ወቅት የቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር ለአደጋ መከሰት ምክንያት ሆነዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ሥራ ምክንያት የደረሱ አደጋዎችን የመመዝገብ ልምድ መጓደልም በጥናቱ ከታዩ ችግሮች አንዱ ነው፡፡ ከግንባታ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. በሪፈራል ሆስፒታሎች፣ በአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከሪፈራል ሆስፒታሎች መረጃ እንዲሰጡ ከተጠየቁት ሰባት ሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ አምስቱ በግንባታ ሥራ ምክንያት የሚደርሱ አደጋዎችን የመመዝገብ ልምድ እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህም የትኞቹ ጉዳቶች በግንባታ አካባቢና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች እንደደረሱ ለማወቅ እክል ሆኗል፡፡ አንድ ሪፈራል ሆስፒታል ለአጥኚዎች ትብብር አድርጎ በ2009 ዓ.ም. በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ባደረገው ምዝገባ 125 አደጋዎች እንደተመዘገቡ፣ በሌላው ሆስፒታል ደግሞ በ2008 ዓ.ም. 531 በመውደቅ፣ 79 በኤሌክትሪክ፣ 27 በማሽን መቆረጥ፣ 122 በኬሚካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተመዝግቧል፡፡ በድምሩ በ2008 ዓ.ም. 759 እና በ2009 ዓ.ም. 967 አደጋዎች ተከስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኮንስትራክሽን ዙሪያ የተመዘገበና በ2008 ዓ.ም. የተከሰተ የሞት አደጋ ለካባ የተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በተጠራቀመ ውኃ  በመስመጥ ስድስት ሰው፣ ከሕንፃ በመውደቅ ሁለት ሰው፣ ያልተዘጉ ቱቦዎች ውስጥ በመግባት ሁለት ሰው፣ አፈር ተንዶ ሁለት ሰውና በኤሌክትሪክ ምክንያት ስድስት ሰው ሲሆኑ፣ ይህም ከወንጀል ጋር ተያያዥነት ያለው ብቻ ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በሚያስገነባቸው የመንገድ ግንባታ ቦታዎች አካባቢ በ2008 ዓ.ም. በተለያየ ምክንያት በሥራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸውና በሕክምና መስጫ ክሊኒክ ሕክምና ያገኙ ሠራተኞች 305 ወንዶችና 148 ሴቶች ሲሆኑ፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ፣ በ2007 ዓ.ም. በኮንስትራከሽን ሥራ ምክንያት የተፈጠሩ አደጋዎች ቁጥር በአዲስ አበባ ከተማ 1,021 እንደሆነ ያሳያል፡፡

የሠራተኛውንና የሌሎችንም ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የግንባታ ሥራ ደኅንነት መላላት፤ ሕጎች ተግባራዊ አለመሆናቸው፣ የሥራ ላይ ደኅንነትን በተመለከተ በጨረታ ሰነድና በኮንትራት ዶክመንቱ እንደ ማንኛውም የስምምነት አካል እንዲካተት አለመደረጉ፣ በተቋራጮች በኩል ወጪን በመፍራት የደኅንነት አልባሳትን ያለሟሟላት፣ የግንባታ ደኅንነትን በተመለከተ የተቀመጡ ሕጎችን ለመተግበር የሚያስችል አስገዳጅ  የሕግ ማዕቀፍ አለመኖርና በግንባታ ባለቤት፣ አማካሪና የሥራ ተቋራጭ በኩል ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠት በሰፊው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዋና ዳይሬክተር ተወካይ አርጋው አሻ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በግንባታው ዘርፍ የደኅንነት ጉዳዮችን ለመተግበር የተለያዩ ሕጎችና ፖሊሲዎች ቢኖሩም፣ ተፈጻሚ አልሆኑም፡፡ በመሆኑም የሕግ አስገዳጅነት እንዲኖር ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሥራ ላይ ደኅንነት መመርያ ምን መምሰል አለበት? ለሚለው በተጠናው ጥናት ላይ መሠረት አድርጎ ቀጣይ ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ በግርድፍ በጥናቱ ወቅት በተገኘው አማካይ መረጃ መሠረት፣ (ከእያንዳንዱ ተቋም የተገኘው የዓመቱ ሙሉ አይደለም) 3,500 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ቁጥር የተገኘው ከተበጣጠሱ መረጃዎች ነው፡፡ በግንባታ ዘርፍ እየደረሰ ስላለው አደጋና ሞት የተደራጀ መረጃም የለም፡፡ ሰው ግን እየሞተና እየተጎዳ ነው፡፡ በመሆኑም ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሁሉም አካላት ተባብረው መሥራት አለባቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...