Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየተደራራቢ አካል ጉዳተኞች የዝምታ ዓለም

የተደራራቢ አካል ጉዳተኞች የዝምታ ዓለም

ቀን:

ከባንዱ የሚወጣው የሙዚቃ ድምፅ አያዝናናውም አይረብሸውምም፡፡ በዙሪያው የተሰባሰቡት ሰዎች እነማንና ምኑ እንደሆኑም፣ በአጠቃላይ በአዳራሹ ውስጥ ሲከናወን ስለነበረው ጉዳይ የሚያውቀው ጉዳይ የለም፡፡ ዝም ባለው የብቻው ዓለም ውስጥ ምን እንደሚያስብና ምን እንደሚፈልግ ከሱ በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ እንዲህ ነው ብሎ ሐሳቡን መግለጽም አይችለም፡፡ የ13 ዓመቱ ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) መናገር፣ መስማትም ሆነ ማየት አይችልም፡፡ ራሱን ችሎ መቆምም ይከብደዋል፡፡

ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸውን ዜጎች ለመርዳት በካፒታል ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ የተገኘው ዩኒፎርሙን እንደለበሰ ከአስተማሪው ጋር ነበር፡፡ አስተማሪው የሱን ያህል ተደራራቢ ጉዳት ባይኖርባትም መናገር ግን አትችልም፡፡ ከሙሉ ቀን ጋር የምትግባባውም በታክታይል (የጣት እንቅስቃሴን በመከተል) ቋንቋ ነው፡፡

ዝግ የሆነውን የሙሉ ቀንን ዓለም ጭላንጭል ብርሃን የፈነጠቀችበት፣ ፀጥታ የነገሰበት ሕይወቱን ድምፅ የፈጠረችበት ይህችው መምህሩ ናት፡፡ ከጎኑ ለአፍታ ያህል እንድትርቅ አይፈልግም፡፡ ተደግፏት ይቀመጣል፣ ተደግፏት ይቆማል፡፡ ከጎኑ ያለችው እሷ መሆኗን ለማረጋገጥ ትንንሽ እጆቹን ወደ አናቷ ከዚያም ወደ መነፅሯ ሰዶ ያረጋግጣል፡፡ ብቻውን በሚኖርበት ሰፊ ዓለም ውስጥ ያለችው ብቸኛ ፍጥረት መምህሩ ናትና ደጋግሞ ቢያፈላልጋት አይገርምም፡፡

- Advertisement -

ከእናቱ ወ/ሮ ሸዋዬ ለገሠ ይልቅ መምህሩ ትቀርበዋለች፡፡ እሳቸው ለሙሉቀን ከመምህሩ ቀጥሎ ያሉ ሦስተኛ ሰው ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሸዋዬ እንግዳ በሆኑበት የሙሉቀን ዓለም፣ ልጃቸውን ለመርዳት ብዙ ጥረዋል፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ መማር ከጀመረ ወዲህ ግን እያሳየ ባለው ለውጥ በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡

ወይዘሮዋ መናገር ከማትችለው የሙሉቀን መምህር ጋር በቋንቋ መግባባት አይችሉም፡፡ ይህም ልጃቸው ምን እንደሚፈልግ፣ ምን እንደሚያሰኘው በመምህሩ በኩል ለማወቅ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ለነገሩ የሁለቱ መግባባት ለ37 ዓመቷ ወ/ሮ ትንግርት ነው፡፡ ሁለቱ በሆነ ጉዳይ ተግባብተው ፈገግ ሲሉ ምን እንዳስፈገጋቸው ለማወቅ ያላቸው ከፍተኛ ጉጉት እንደማይሳካ ቢያውቁም የልጃቸውን ለውጥ እያዩ አብረው ፈገግ ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ሸዋዬ ከወለዷቸው ሦስት ልጆች መካከል የሙሉቀንን እንዲህ መሆን አምኖ ለመቀበል ብዙ ተቸግረዋል፡፡ ሁኔታው ከድህነታቸው ጋር ተዳምሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል፡፡ የሚኖሩት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በ600 ብር በተከራዩት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ባለቤታቸው የቀን ሠራተኛ እሳቸው ደግሞ ተመላላሽ የቤት ሠራተኛ ነበሩ፡፡

ይሁንና በወር የሚያገኙት ገንዘብ የቤት ኪራይ ችሎ ለቀለብ የሚተርፋቸው አልነበረም፡፡ ስለዚህም የባልትና ውጤቶችን እያዘጋጁ መሸጥን መርጠዋል፡፡ ምን ያህል ትርፋማ እንደሆኑ በውል ባያውቁትም ቢያንስ አይራቡም፡፡ ልዩ ትኩረታቸውን ለሚሻው ሙሉቀንም ጊዜ እንዲሰጡ ዕድል የሚሰጣቸው በመሆኑ ደስተኛ ናቸው፡፡

የሙሉቀን ጉዳት ከጊዜ በኋላ የመጣ አይደለም አብሮት የተወለደ እንጂ፡፡ እናቱ ወ/ሮ ሸዋዬ ግን የልጃቸው ችግር ተደራራቢ መሆኑን አያውቁም ነበርና ችግሩ ያለው የዓይኑ ብርሃን ላይ ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡ መናገር እንደማይችል የተረዱት ከሁለት አመቱ በኋላ ነው፡፡ ‹‹ዓይኑ ብቻ ነበር የመሰለኝ ለካ አፉም ተይዞ ኖሯል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሸዋዬ፣ በሕክምና ለማዳን በደሃ አቅማቸው ያላደረጉት ጥረት እንዳልነበረ ያስታውሳሉ፡፡ በየቤተ ክርስቲያኑ፣ በየገዳማቱ ዞረው ጠበል ሞክረዋል፡፡ ልጃቸውን በጀርባቸው አዝለው በየሕክምና ተቋማቱም ተንከራተዋል፡፡

ይህንን የተመለከቱ ጎረቤቶቻቸውና ሌሎች በቅርበት የሚያውቋቸው ስለሙሉቀን ይሰጡት የነበረው አስተያየት ደግሞ ሞራላቸውን ይነካ ነበር፡፡ ‹‹በምን አቅምሽ ታሳድጊዋለሽ ለሰው ስጪው ይሉኝ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሸዋዬ፣ የሚያሽሟጥጧቸው እንደነበሩም ይናገራሉ፡፡

በየጤና ተቋማቱ ሲንከራተቱ ቆይተው አንድ ቀን እውነታው ተነገራቸው፡፡ ‹‹ይኼ ልጅ እኮ ማየት ብቻ ሳይሆን መናገርም አይችልም፡፡ እጅና እግሩም አይንቀሳቀስም፡፡ መፍትሔ የለውም ይዘሽው አትንከራተቺ፣ ለመንግስት ስጪው አሉኝ፡፡ ይህንን ስሰማ ቤት ገብቼ ተንሰቅስቄ አለቀስኩ›› በማለት ነበር ከባዱን ጊዜ ያስታወሱት፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ያለበት ጉዳት ምን ድረስ እንደሆነ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ መናገር አለመቻሉን እንጂ ጆሮው ይስማ አይስማ እርግጠኛ አይደሉም፡፡

ሙሉቀን እስከ ስድስት ዓመቱ ድረስ ውሎና አዳሩ አልጋ ላይ ነበር፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ እንደ አራስ ልጅ ይጠበቅ ነበር፡፡ አይንቀሳቀስም፣ አይናገርም፣ ሲያለቅስም አይሰማም ምግብ መብላት ስለማይችልም በጡጦ ኃይል ነበር ያደገው፡፡ በአንድ ወቅት ግን መሰል ችግር ያለባቸው ልጆች የሚማሩበትና የሚለወጡበት አጋጣሚ መኖሩን ሰሙ፡፡

ሙሉቀንም በ‹‹ኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር›› ውስጥ ከሚገኙ 215 ሰዎች ጋር ተቀላቅሎ መማር ቻለ፡፡ አጋጣሚው ከስድስት ዓመታት በኋላ ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ፣ ምግብ መብላት እንዲችል ዕድል ሰጠው፡፡ ‹‹በፊት እጁ እንኳን መጨበጥም ሆነ ጨርቅ መያዝ አይችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ቢያንስ ካልሲ ማድረግ ችሏል፤›› ይላሉ ወ/ሮ ሸዋዬ ለሙሉቀን ትልቅ እመርታ የሆነውን የትምህርት ሒደት ሲገልጹ፡፡

በትምህርት ላይ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ በዙሪያው ስላሉ ነገሮች፣ ስለ አካባቢው መረዳት ባይችልም ለውጡ ግን በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ችግር ላለባቸው ልዩ ትኩረት በተሰጠበት ማኅበረሰብ ውስጥ ቢያድግ ደግሞ የሙሉቀን ለውጥ ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ከሌላው የማኅበረሰብ ክፍል ጋር እኩል ዕድል መስጠት፣ በተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እኩል ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ በልማት ጉዳዮችም እንዲካተቱ ማድረግን በተመለከተ ትልቅ ክፍተት መኖሩ ይታወቃል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ዓመት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ፡፡፡ የጉዳታቸው መጠንና ዓይነት የተለያየ ሲሆን፣ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ በሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍል ላይ ይበዛል፡፡ በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ሴቶች፣ ሕፃናትና በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በተለየ ተጋላጭ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች ለጤና አገልግሎት፣ ለትምሀርት፣ ስራ የማግኘት ዕድል ከሌላው በተለየ ጠባብ ነው፡፡ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ለድህነት እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ ይህ ችግር ለዘመናት የቆየና እስካሁንም አበረታች ውጤት ያልታየበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ከ15 ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች በተለያዩ የልማት ሥራዎች ማካተት ከባድ ሆኗል፡፡ በተለይም እንደ ሙሉቀን ያሉ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች ከሌሎቹ በባሰ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ፕሮግራም ኦፊሰሩ አቶ መሠረት ያኔት እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ውስጥ ምን ያህል ተደራራቢ የአካል ጉዳት ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ እንኳ መረጃው የለም፡፡ የማኅበሩ አባላትም 216 ብቻ ናቸው፡፡ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ችግር ስላለባቸው ዜጎች ያለው ግንዛቤም እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...