ሰላም! ሰላም! የዘንድሮ ንፋስና ሰላም መላ ቅጡ ጠፍቶበታል። የወጉን ለማድረስ እኔና እናንተ ሰላም ብንባባል ግን አይከፋም። ሰላምታም ታክስ እስኪጣልበት ለማለት ፈልጌ ነው እንጂ ወጉንማ ማን ወግ ብሎት? አታዩንም እንዴ በየቦታው ተሰነጣጥቀን ስንዳማ። እኔና ማንጠግቦሽ ቢቸግረን ‘አባታችን ሆይን‘ ‘ኢኮኖሚያችን ሆይ‘ በሚለው ተክተነዋል። ልቀንጭብላችሁ? ምን ቆርጦኝ። አደራ ታዲያ እናንተም ስትነሱ ስትቀመጡ ይህን ፀሎት ደጋግሙት። ‹‹ኢኮኖሚያችን ሆይ በልማታዊ ባለሀብቶቻችን ጉያ የምትኖር በረከትህ ለእኛ ለአኗኗሪዎችም ትምጣ። መቀመጫህ ከላይ ከላይ እንደሆነ ሁሉ ወደ ታችም ይሁን። የዕለት ሸመታችንን ዋጋ ተቆጣጠርልን። ፈቃድህ በፀሐዩ መንግሥታችን እጅ እንዳለ ሁሉ በእኛም እጅ ይሁን . . . ›› እያለ ይቀጥላል። እና ማሳረጊያው፣ “እባክህ ብዙ ደም ሳትጠጣ ቶሎ ቶሎ አድገህ አረጋጋ። አንዴ ክፍፍሉ ለመላው አገር ከበቃ ቅሬታችን ይበርዳልና፤” ብሎ ያሳርጋል።
ምን እናድርግ ብላችሁ ነው? አንድ ያለን ተስፋ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ብቻ ሆኖ እኮ ነው። ሌላማ ተስፋ የምናደርግበት ሁሉ በኖ ጠፋ። እውነት አጋነንክ አትበሉኝና አንድ መቶ ሚሊዮን አንሞላም። ታዲያ ስንቶቻችን ነን ከዚህ ሁሉ ወገን አንድ ሰው አይጠፋም አላህ ወይ እግዜር ያዘጋጀው፣ ተስፋ የሚሆነን ብለን የምናስብ? እኔ ያለ አይመስለኝም። በእንቅርት ላይ እንቅርት፣ በደግፍ ላይ ደግፍ ሆኖብኛል ነገሩ። በየሄዳችሁበት በእሳት ላይ ቤንዚን ካልዘነበ ብሎ የሚጮህ በዝቷላ። ኧረ በልማቱ ይዤሃለሁ እንዳትሉት ‘ታርጌት‘ ልትሆኑ ነው። ‘ታርጌት‘ ለመሆን ደግሞ ጊዜው ቀላል ነው። አፍ ያድጠው ብቻ። አለቀ አከተመ። እና እኔ ምለው አንድ አገር ነው ያለን፡፡ የት አገር ሂዱ ነው ይኼ ሁሉ ትርምስ? ስትሉ ማን ይመልሳል። ማንም። ግን ይኼ ዝም ዝም ተቅዘምዝሞ፣ ተቅዘምዝሞ የወደቀ ዕለት . . . ተውት አንጨርሰው። ደግሞ በኋላ በኮድ ተጠቃቀሳችሁ ተብለን ሆሆ!
ኮድና መልዕክቱን ካነሳን አይቀር የዘንድሮ መልዕክትና መልዕክተኛ የማያስነብበን ጉድ የለም። በነገራችን ላይ አዲስ ‘ጌም‘ ፈልስፌያለሁ። ከዚህ በፊትም ደጋግሜ አጫውቻችሁ ነበር። ስለዚህ ስለቴሌ መልዕክት ነዋ። የፈጠርኩት ‘ጌም‘ ምን መሰላችሁ? የጽሑፍ መልዕክቶቹን አጠራቅሞ በሦስት ሰከንድ መደለት ነው። ታክሲ ስትጠብቁ፣ ወይም ባቡር፣ ወይም መብራት፣ ወይም ስኳር፣ ወይም ሁሉም ጠፍቶ ሲደብራችሁ ሞክሩት። የምሬን ነው። ‘ፓተንቱ‘ ግን የእኔ ነው አደራ። በቀደም አንድ ካሚዮን እያሻሻጥኩላችሁ መኪናውን የሚፈትሸው መካኒክ ስልኩን አጥፍቶ ራሱም ጠፋ። መቼም ስለአጥፍቶ ጠፊው ለእናንተ ማብራሪያ አያሻም። እምዬ ምኒልክ አገር ይግባባ፣ ይዘንጥ ብለው ስልክ እንዳላስተዋወቁን በዘመን ሒደት ይኼው መገናኛው ሽቦ አልባ ሆኖ በመዳፋችን ልክ ሲሆን፣ ዕድሜ ‹‹ለስዊድች ኦፍ›› ትርፋችን መደናቆርና ቋንቋ መደባለቀ ሆነ። ሆድ ይፍጀው ነው ብቻ።
እና ሌላ መካኒክ መፈለግ ነበረብኝ። ለአንድ ወዳጄ ደውዬ ፈጥኖ የሚደርስ መካኒክ ስልክ ካለው ‘ቴክስት‘ አድርግልኝ አልኩት። አፍጥጬ ስጠብቅ ጢን ብሎ መልዕክት ገባ። ስከፍተው ‘ወርቅ በወርቅ‘ ይሁኑ ይላል። ሌላ መጣ ‘ባጃጅ‘ ይላል። አሁንም ሌላ ‘ሲኖትራክ‘ ይላል። በዚህ በኩል ሠርታችሁ ቆጥቡ፣ ተለወጡ ይሉናል። በዚህ ደግሞ ምርቃና በፈጠረው ቢዝነስ በህልም ያፈዙናል። ኧረ እዚህ አገር ግን መቼ ነው ለሕዝብ አዕምሮ እረፍትና ሰላም የሚጨነቅ ፖሊሲ የሚወጣው? እያልኩ የባሻዬ ልጅ የተሳለቃት ነገር ትዝ ብላኝ ፈገግ አልኩ። ስለዘመኑ መልዕክትና መልዕክተኛ ስንጫወት ሳቅ ብሎ፣ ‹‹ሐሰተኛ መልዕክተኞችን ከሀቀኞች ለመለየት አንዱ ዘዴ ምን መሰለህ?›› አለኝ። ‹‹ደግሞ ምን ልትል ነው?›› ስለው፣ ‹‹መልዕክቱ የሚላክበት ቁጥር በስምንት መጀመሩንና አለመጀመሩን ማየት ነው። ስምንት ከሆነ ምናልባት ከስምንተኛው ሺሕ ፍካሬ ጋር የሚሰናኝ መልዕክት ሊሆን ስለሚችል ጠንቀቅ ብለህ ትንቢቱንም፣ መልዕክቱንም መመርመር አለብህ . . . ›› ሲለኝ ደንገጥ ብዬ፣ ‹‹ለህዳሴው ግድብ የዋጣነው እኮ 8101 ነው፡፡ ስለው፣ ‹‹ኦኦ! በል የተናገርኩትን ደምስሰው፤›› ብሎ ሳቀ። ሳቁ ትዝ ብሎኝ የአዲሱን መካኒክ ስልክ ቁጥር እስኪደርሰኝ እየጠበቁ ፍቅር፣ ርህራሔ፣ ደግነት፣ ወንድማማችነት ከችሮታና ከማኅበራዊ ኑሮ ወደ በራሪ ፖስት ካርድነት የመቀየራቸው ነገር እያጤንኩ ወይ ስምንተኛው ሺሕ አልኩኝ አምልጦኝ። እና በአጭሩ ሐሰተኛ መልዕክትና መልዕክተኞችን አጣሩ ለማለት ነው!
ያው ታዲያ ተፍ ተፉ እንዳለ ነው። “ሕይወታችን በምን ይመሰላል?›› ይባላል አሉ አንዱ፣ “በገብረ ጉንዳን” ብሎ መለሰ አሉ። “የትኛው ግብራችን ነው አንተ ካልጠፋ ነገር ከጉንዳን ያመሳሰለን?” ሲባል አሉ፣ “ሠልፋችን!” ብሎ አረፈው። ቴሌና ቴክስቱን አላልኩም አሁን። ይኼንን የትራንስፖርት ችግር ያማረረው ነው ያለው። ‹‹ቲሽ! በባቡር አይሄድም?›› ብዬ ነበር እኔም እንደ እናንተ። “ዘመኑ እኮ የ ‘ኮምፒቲሽን’ ነው፣ የ‘ፒቲሽን’ ማሰባሰቢያ አይደለም፤” አሉኝ የሰሙኝ። “እንዴት?” ብዬ ሳልጨርስ (በዚህ ሰብዕናዬን በዚህ እንዴቴን የሚያስቀማ ዘመን ላይ ልውደቅ?’ አይስብልም እሺ አሁን?) “አታየውም እንዴ ፍጥነቱን። በዚያ ላይ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑት ተመልሰው ሥራ ይጀምራሉ ብለው ይኼው በሙከራ ብዛት መልሰው ሊበላሹ ነው። እንኳን እኛ ዔሊም በአቅሟ ለዘመናት የተጫናት ድንጋይ እንዲቀልላት ከሆነም እንዲነሳላት የት ሄጄ ልለምን በምትልበት የጥንቸሎች ዘመን፣ የባቡራችን ፍጥነት ፊርማ ለማሰባሰብ ካልሆነ ‘ቻፓ’ ለመሰብሰብ መቼ ይሆናል?” ዓይሉኝ መሰላችሁ?
በልቤ ይኼኔ የጫት ሰዓትህ ደርሶ ይሆናል እያልኩ በልቤ፣ “የምን ፊርማ?” ብዬ ነገር መጠምዘዝ። “የብሶት!” መቀጠል እነሱ፡፡ “ማነው የባሰው?” እኔ፡፡ “የባሰው!” እሱ። ‘እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም . . . ‘ አለች ስትዘፍን ውላ ብታድር የማትሰለቸዋ። ውሎ ማደር ቀርቶ በቅፅበት ቅለቀፄና ዕይታ አንቅረን የምንተፋው ነገር በዝቷላ ዘንድሮ። አስቡት እስኪ እምዬ ምኒልክ ለጣይቱ ‘እንደ ቀልድ የቆረቆርሻት አዲስ አበባ እነሆ 131 ዓመት ሆናት‘ ሲሏቸው ጣይቱ ወደ እኛ እያዩ፣ ‘ከእናንተው ዘመንስ የእኔ እንቅልፍ ይሻላል’ ሲሉን። ባቡሩ ብቻ አይደለማ የሚጎተተው። መፍትሔው ሥራ ፈጠራው፣ ንቃታችን፣ ዓይናችን፣ እግራችንና ሁሉ ነገር ነዋ የሚንቀራፈፈው። ዋሸሁ? ለማንኛውም እንደ እኔ እንደ እኔ፣ “አልበር እንዳሞራ ሰው አርጎ ፈጥሮኝ . . . ” ማለቱን ትተን ከታሪክ ራስ ወረድ ብንል ጥሩ ነው። ‘በአንድ ራስ ሁለት ምላስ’ ያስተዛዝባል። በእዚያ ‘ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን፣ ንፋሱ ዕድገታችን እያላችሁ አስደፈጠጣችሁን’ ብለን ሳንጨርስ፣ በእዚህ ጉረኛዋን ጥንቸል ትሁቷ ኤሊ በሩጫ ውድድር ቀድማት መግባቷ ሲተረትለት እንዳላደገ ትውልድ፣ ‘ተኝታችሁ አስተኛችሁን’ ማለት ‘ፌር’ አይደለም። ደግሞስ እንነጋገር ከተባለ፣ ዝግታ ነው ፍጥነት እየጨረሰን ያለው? ለነገሩ ሁለቱም ሆኗል ዘንድሮስ!
የልብ የልባችንን እንጫወት ካልን ዘንድ የተፈታውን እያሰርን፣ ያሰርነውን እየፈታን መጫወት ደስ ይላል። ያን ካሚዮን እንደ ምንም መካኒክ ፈልጌ አስፈትሼ አሸጥኩት። እናም ጨዋታውን በማሰርና በመፍታት መቀጠሉ ግድ ነው። “ሲታሰር ወደ እኔ ሲፈታ ወደ እሷ” ሰሞኑን በማስታወቂያ ብዛት ልባቸው ባበደ ኤፍ ኤሞቻችን በኩል ስለምጋብዛችሁ አደራ ጆሯችሁን አንቅታችሁ የስፖንሰሮቼን ‘ቶርች‘ ችላችሁ አዳምጡት። “ደግሞ ልደት ደረሰ” አሉ ባሻዬ በቀደም። ታዲያ ቢደርስስ ስላቸው፣ ‹‹በስፖንሰር ብዛት ልናብድ ነዋ፤›› አሉኝ የምር ተክዘው። አሁንስ ቀረልን እንዴ? ከቁም ነገሩ እኮ ሸቀጡ ገደለን። ኧረ ኡኡኡ . . . ብንል እንኳን፣ ይህን ኡኡኡ ስፖንሰር ያረገው ብለው ጩኸታችንን ሊቀሙንም ያምራቸዋል። ቀልዴን እንዳይመስላችሁ። አስቡት እስቲ ስፖንሰሮቻችን በዝተው እኮ ነው በልዩነት ከማመን አልፈን ካልተጨፈላለቅን እያልን የምንንሸራተተው። ሸርተቴ የሚጫወት ብላቴና ማየት እንዴት እንደ ናፈቀኝ እግረ መንገዴን ስነግራችሁ ቅር እንዳይላችሁ። ማን አለኝ ያለ እናንተ?
የምናነጋግረው ሰው መስሎኝ ያጣነው። የሕዝብ ቁጥር መጨመር የሚያሳስበኝ እኮ ለዚህ ነው። በተባዛን ቁጥር የሚናገረን እንጂ የሚያነጋግረን ሰው ይመነምናል። በጥናት ያልተደገፈ ወሬ አታውራን ትሉኝ ይሆናል። ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ወሬ በጥናት መደገፍ የጀመረው? የሚለውን ተውትና ደጋገምከው ካላላችሁኝ ቅድም ያጫወትኳችሁን የ‘ሜሴጅ‘ አባዜ አስታውሱት። ደግሞስ እንኳን ወሬ እኛስ ብንሆን በጭፍን እንደግፋለን በሥልት እንገፋለን እንጂ፣ ተደግፈን እናውቃለን እንዴ? የተፈታውን ማሰር፣ የታሰረውን መፍታት ብዬ የጠበቀውን ማጥበቅ፣ የላላውን ማላላት ላይ ስገባ አሁን ገና ታወቀኝ እናንተ። የአፈጻጸም ችግር በሚለው ልታለፍ? በጥልቅ ታድሼ በጥልቅ እስኪብስብኝ አንድ ዕድል ብቻ ስጡኝ ብዬ ከመለመን ውጪ አሁንስ ምንም ቃል የለኝ።
በሉ እንሰነባበት። አንዱ በቀደም ደውሎ፣ “ሚዜ ሁነኝ” ሲለኝ፣ “እሺ” አልኩት። አክብሮኝ መስሎኝ። ቆየት ብሎ ደወለና “ሱፍ ራስህ ነህ የምትገዛው” አለኝ። “ይሁን” አልኩ። የምለብሰው እኔ። ከሰዓት መልሶ ደወለና “ለሚዜ የምከራየውን መርሰዲስ ከፋይ ያው አንተ ነህ፤” አይለኝ መሰላችሁ? “ለምን ዳረኝ?” አትለኝም አልኩት። አያችሁ የስፖንሰር ብዛት የት ድረስ እያጦዘን እንዳለ። ከዋሉ ካደሩ እኮ በዚህ ዓይነት ሥራዬን ሥራልኝም ሊመጣ ነው። አስባችሁታል? ደንቆኝና ገርሞኝ፣ “ዘንድሮስ የተገላገለ ያበደ ብቻ ነው፤” ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ “ለማበድም እኮ ፈቃድ ያስፈልጋል፤” ብላ አፈጠጠችብኝ። የተባልኩትን ስነግራት ምን ብትለኝ ጥሩ ነው፣ “እኔም ቬሎ ልግዛና በቃ ደግመን እንጋባ፤” ባይሆን ይኼ አይሻልም? ግን እንዲህ በጥቅማ ጥቅም ላይ የተመሠረቱ ጥቃቅንና አነስተኛ አስተሳሰቦች ማኅበራዊ ሕይወታችንን “ዲም ላይት” ሲያደርጉት ዝም ነው በቃ? ግራ ገባኝ። አሁንስ ኡኡ እያሉ መጮህ ነው ያማረኝ፡፡ ግን ስፖንሰሩ የት ይገኛል? መልካም ሰንበት!