Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በነዳጅ ፍለጋ ልማትና ንግድ ለመሰማራት እየተንቀሳቀሰ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል ይፈልጋል

መንግሥት በነዳጅ ፍለጋ፣ ልማትና ንግድ፣ በማዕድን ፍለጋና ልማት እንዲሁም በባዮፊዩል ልማት ለመሰማራት የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን የተሰኘ የመንግሥት የልማት ድርጅት በ15 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በማቋቋም በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በተለያየ ጊዜያት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የሚደረጉ የነዳጅ ፍለጋና ልማት ውሎች ውጤታማ ሊሆኑ ባለመቻላቸው መንግሥት የአገርን ጥቅም የሚያስከብር ብሔራዊ ኩባንያ ለመመሥረት በማቀድ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ድርጅት የተሰኘ የመንግሥት የልማት ድርጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 2004 ዓ.ም. ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ የቢሮ ማደራጀትና የጥናት ሥራዎችን ሲያካሂድ ቆይቶ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ድርጅቱን በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. እንደ አዲስ የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን በማለት አቋቁሞታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ባካሄዳቸው ተግባራትና በነደፈው የልማት መርሐ ግብር ዙሪያ ከመስኩ ባለድርሻ አካላት ጋር ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን በፍልውኃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደው የምክክር መድረክ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ ሰይድ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ በአደረጃጀት ሥራ ተጠምዶ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሦስት ዘርፎችን ማለትም የፔትሮሊየም፣ የማዕድንና የባዮፊዩል ሥራዎችን አካቶ የያዘ በመሆኑ ባለሙያዎችን ከየዘርፉ የማሰባሰብ ሥራ፣ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ያሉ ክፍሎችን ወደ አንድ ማምጣት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር አንድ ዙር ውይይት ተካሂዶ የፍኖተ ካርታ የማዘጋጀት ሥራ፣ የመርሐ ግብር ቀረፃና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን በታንታለም ምርት የሚታወቀውን የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የጠቀለለ ሲሆን፣ በማዕድን ዘርፉ እሴት የተጨመረበት ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ወርቅ፣ የከበሩ ድንጋዮች የኢንዱስትሪ ማዕድናት በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱን፣ በኮርፖሬሽኑ የማዕድን ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ዘሪሁን ደስታ ገልጸዋል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ፍጥነት ማደግና የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ለኢንዱስትሪ ማዕድናት ሰፊ ገበያ የፈጠረ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ፊልድ ስፖር፣ ዶሎማይት፣ ኳርትዝና ለሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ከማዕድናት ምርት በተጨማሪ የጂኦሳይንስ መረጃ የመሰብሰብ፣ የቁፋሮና የማዕድናት ላቦራቶሪ አገልግሎት በስፋት በመሥራት በአጠቃላይ ከማዕድኑ ዘርፍ 1.7 ቢሊዮን ብር፣ በውጭ ምንዛሪ 77 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኑ ለአገራችን ዕድገት ሽግግር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና በማዳን ከፍተኛ የኢኮኖሚ አጋር ሆኖ መንቀሳቀስ አለበት፤›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ ኮርፖሬሽኑ እንደ ናይጄሪያ፣ ጋናና ብራዚል ካሉ አገሮች ልምድ በመውሰድ በ2017 ዓ.ም. በዓለም ተመራጭነት ያላቸው የማዕድን፣ የነዳጅና የባዮፊዩል ምርቶችና አገልግሎቶች ለማቅረብ መርሐ ግብር ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም. ኮርፖሬሽኑ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት ያቀደ ሲሆን፣ 300 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምርትና አገልግሎት በመተካት 200 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ገቢ ለማስገባትና ለ2,000 ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአገር ውስጥ ግንባር ቀደም ግዙፍ ኮርፖሬሽን እንደሚሆን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ በ15 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታልና በአራት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ በእጅ ያለው 400 ሚሊዮን ብር ካፒታል ብቻ እንደሆነና አራት ቢሊዮን ብር ካፒታሉ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከጅምሩ ውስብስብ ችግሮች የተጋረጡበት ሲሆን፣ የካፒታል እጥረት ዋነኛው ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሊሠራቸው ያሰባቸው ሰፊና ውስብስብ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ በመሆናቸው የሚያስፈልገው አራት ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዲሟላለት፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ጥያቄውን ማቅረቡን አቶ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የካፒታል ጥያቄውን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹የጠየቅነው የካፒታል ጥያቄ ካልተሟላልን የተሰጠንን ግዙፉ ኃላፊነት ለመወጣት ችግር ይገጥመናል፤›› ብለዋል፡፡

በፔትሮሊየም ዘርፉ ኮርፖሬሽኑ ልምድ ካካበቱ የውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክናና በራስ አቅም የነዳጅ ፍለጋና ልማት ለመሰማራት ማቀዱን የፔትሮሊየም ዳይሬክቶሬት የቴክኒክ አማካሪ አቶ ዓባይነህ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በነዳጅ ሥራዎች በቀጥታ መሳተፍ ኢንቨስት ማድረግ፣ በነዳጅ ሥራዎች ውስጥ አገልግሎት (የጂኦሳይንስ መረጃ መሰብሰብ ቁፋሮና ላቦራቶሪ) መስጠት፣ በነዳጅና ማዕድን ልማት ፕሮጀክቶች የመንግሥት ተሳትፎ ድርሻ መወከልና ማስተዳደር ኃላፊነቶች እንደሚኖሩት አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡ ድፍድፍ ነዳጅ ማጣራት፣ የነዳጅ ውጤቶች ማከፋፈል፣ የማለስለሻ ቅባቶችና ዘይቶች ማምረትና ማከፋፈል ሥራዎች በዘርፉ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ወይም በራስ አቅም ሊሠራ እንደሚችሉ አቶ ዓባይነህ ተናግረዋል፡፡

በነዳጅ ምርት የረዥም ጊዜ ልምድ ካካበቱ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ መወሰዱን የገለጹት አቶ ዓባይነህ፣ እንደ ብራዚል ፔትሮባስና የማሌዥያው ፔትሮናስ ያሉ ግዙፍ የመንግሥት የነዳጅ ኩባንያዎች ከነዳጅ ፍለጋና ምርት ጀምሮ እስከ ማከፋፈል የነዳጅ ማደያዎችን ጭምር እንደሚያስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

በባዮፊዩል ዘርፉ ለባዮዲዝል ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ የባዮፊዩል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናደው ታደለ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በባዮዲዝል ልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ ገልጸው፣ ኮርፖሬሽኑ የባዮዲዝል ልማት የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ ወደ ልማት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ባዮዲዝል እንደ ጃትሮፋ ካሉ ተክሎች ለማምረት መታቀዱን፣ ኮርፖሬሽኑ በመጪው አራት ዓመት በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ ሁለት የባዮዲዝል ማምረቻ ማዕከላት ገንብቶ ወደ ምርት እንደሚሸጋገር ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ስድስት የባዮዲዝል ማምረቻዎች በማቋቋም በዓመት 212 ሚሊዮን ሊትር ባዮዲዝል ለማምረት ዕቅድ ተይዟል፡፡ አገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የነዳጅ ፍጆታ እየጨመረ መጥቶ በዓመት 2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የነዳጅ ውጤቶች ከ38 ቢሊዮን ብር በላይ (ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ) ገዝታ በማስገባት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም የአገሪቱን 80 በመቶ የውጭ ምንዛሪ በመውሰድ ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያትና አገሪቱ ከምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አንፃር የባዮፊውል ልማት በአማራጭ የኃይል ምንጭነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ውይይት የተለያዩ ባለሙያዎች ስለፋይናንስ ምንጭ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ልማት፣ የአካባቢና ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ጥናት አስፈላጊነት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የተሰነዘሩት አስተያየቶች ኮርፖሬሽኑ በሚቀርፀው የቢዝነስ መርሐ ግብር በግብዓትነት እንደሚጠቀምባቸው አቶ ሙሉጌታ በመዝጊያ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች