Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአደጋ የተከበበው የአዲስ አበባ ‹‹ሳንባ››

በአደጋ የተከበበው የአዲስ አበባ ‹‹ሳንባ››

ቀን:

የባህል አልባሳት፣ ጌጣጌጥና መገልገያዎች የሚሸጡበትን ሽሮ ሜዳ ስናልፍ የመኖሪያ ቤቶች ቁጥር እየቀነሰ፣ የዕፀዋት ብዛት እየጨመረ ሄደ፡፡ ታሪካዊውን የእንጦጦ ተራራ ጠመዝመዛ መንገድ ተከትለን ወደ ላይ አቀናን፡፡ ከተራራው ወደ ታች ሲቃኝ፣ በአገር በቀል ዕፀዋት የተሸፈነው እንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ ይገኛል፡፡

ከተራራው ጫፍ የአዲስ አበባን ገፅታ መመልከት ይቻላል፡፡ በታሪክ ወደ ኋላ መልሶ ከተማዋ ስለተቆረቆረችበት ወቅትም ያሳስባል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተበራከተው ግንባታ መዲናዋን ምን ያህል እንደለወጣት መገንዘብም ይቻላል፡፡

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአንኮበር ወደ አዲስ አበባ ከወጡ በኋላ ለቤተ መንግሥትነት የመረጡት እንጦጦን ነበረ፡፡ ከአካባቢው ተራራማ አቀማመጥና የተፈጥሮ ሀብቱ አንፃር በአካባቢው መስፈር ጥሩ አማራጭ ነበር፡፡ በከተማዋ ለማገዶና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚውል እንጨት ሲያጥር፣ ንጉሡ በአጭር ጊዜ አድገው ጥቅም የሚሰጡ ዕፀዋት ዘር ፍለጋ ወደተቀረው ዓለም አማተሩ፡፡

- Advertisement -

የአውስትራሊያው ዩካሊፕተስ በጥቂት ዓመታት እንደሚያድግ የሰሙት ንጉሡ፣ ወደ ኢትዮጵያ ዘሩን በማስመጣት እንዲተከል አደረጉ፡፡ ባህር ተሻግሮ የመጣው ዩካሊፕተስ፣ ባህር ዛፍ የሚል አገርኛ ስም ተሰጠው፡፡ እንደተፈለገው በአጭር ጊዜ አድጎ ግልጋሎት መስጠቱንም ቀጠለ፡፡

ባህር ዛፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን የዕፀዋት ዝርያ መሆኑ የታወቀው ብዙም ሳይቆይ ነበር፡፡ በረዣዥም ሥሮቹ የአካባቢውን የውኃ ሀብት ጠራርጎ ስለሚጠቀም በዙሪያው ሌሎች ዕፀዋት መብቀል አይችሉም፡፡ በደቦ የተተከለው ባህር ዛፍ በደቦ ይነቀልም ጀመር፡፡ ቢሆንም ከበርካታ አሠርታት በኋላ ዛሬም ዝርያው በአገሪቱ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡

ባህር ዛፍ በብዛት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ የእንጦጦ ተራራ ነው፡፡ አካባቢውን በጎበኘንበት ወቅት፣ ከመንገዱ በስተግራ በኩል የባህር ዛፍ ደን ተመልክተናል፡፡ ደኑ በአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚጠበቅ ነው፡፡ በስተቀኝ በኩል ያለው የተራራው ክፍል የተለየ ገፅታ አለው፡፡ መጤው ባህር ዛፍ መክኖ በአገር በቀል ዕፀዋት ተተክቷል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ባህር ዛፍን የእንጀራ ገመዳቸው ያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ቅጠሉን በመሸጥ ቤተሰብ የሚያስተዳደሩ እንስቶች በርካታ ናቸው፡፡ በመንገዳችን ላይ የተሸከሙት የባህር ዛፍ ቅጠል ጀርባቸውን አጉብጧቸው ቁልቁለቱን የሚወርዱ ሴቶች ገጥመውናል፡፡ ለነዚህ ሴቶች ባህር ዛፍ የሚተዳደሩበት፣ የሚኖሩበትን ቤት የሚገነቡበትና የዕለት ጉርሳቸውን የሚያበስሉበትም ነው፡፡

በሌላ በኩል ባህር ዛፍ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባትም የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር እንቅስቃሴ ከጀመረ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባህር ዛፍን በማምከን በአገር በቀል ዕፀዋት የመተካት ሥራውም ዓመታት ወስዷል፡፡

አሁን ከ1,300 ሔክታር የእንጦጦ ተፈጥሯዊ ፓርክ መካከል በ500 ሔክታሩ የሚታየው ኮሶ፣ የሐበሻ ጽድ፣ ዝግባ፣ የሐበሻ ግራር፣ ጥቁር እንጨት፣ ኮርች፣ ብርብራ፣ ውልክፋ፣ እንብልባይ እና ሌሎችም አገር በቀል ዕፀዋት ናቸው፡፡ ፓርኩን ያስጎበኙን የኢትዮጵያ ቅርሰ ባለአደራ ማኅበር የቅርስ ልማት ጥበቃና ክትትል ዋና ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሂርጳ ነበሩ፡፡

ቀይ በር በሚል የሚጠራውን የፓርኩን ክፍል ከከፍታ ቦታ ስንመለከት፣ የተለያዩ አገር በቀል ዕፀዋት በስብጥር አስተውለናል፡፡ ‹‹ሰውን ጨምሮ፣ የተለያዩ እንስሳት በሰንሰለት የሚኖሩበት ተፈጥሯዊ ዑደት ስብጥር ሕይወት ነው፤›› ይላሉ አቶ ሙሉጌታ፡፡

ተፈጥሯዊ ዑደቱ መጠበቅ እንዳለበት በአጽንኦት ገልጸው፣ ‹‹እንጦጦ የአዲስ አበባ ሳንባ ነው!›› ይላሉ፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 3,200 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው እንጦጦ፣ በዕፀዋትና በእንስሳት ስብጥሩ ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባን በአንድ ወገን የሸፈነው ፓርኩ የከተማዋ ህልውና መሠረት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየአቅጣጫው በግዙፍ ፎቆች ለተሞላችው ከተማዋ መተንፈሻ የሚሰጥ ተፈጥሯዊ ክልል ሆኖ ያገለግላል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ዙሪያ አገር በቀል ዛፍ በመትከል፣ ሰው ንፁህ አየር እንዲተነፍስ እንሠራለን፡፡ አፈሩ እንዲጠበቅ የእርከን ሥራም ሠርተናል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ማኅበሩ የእንጦጦ ተራራን በአገር በቀል ዕፀዋት ለመሸፈን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  አካባቢውን ለ100 ዓመታት በ1988 ዓ.ም. ከተረከበ በኋላ፣ አካባቢው እንዲያገግም የተለያዩ ሥራዎች አከናውነዋል፡፡

ባህር ዛፍን የማምከን ሥራ ቀዳሚው ነበር፡፡ ባህር ዛፉን በመቁረጥና ዳግም ሲበቅልም በማክሰም ከአካባቢው አስወግደዋል፡፡ ቀድሞ በአካባቢው ከባህር ዛፍ ውጪ ሌሎች ዕፀዋት አይበቅሉም ነበር፡፡ አዕዋፋትና የዱር እንስሳትም ከአካባቢው ሸሽተው ነበር፡፡ አፈሩ ተሸርሽሮ አካባቢው ለጎርፍ ተጋልጦ እንደነበር አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡

አካባቢው እንዲያገግም ከተደረገ በኋላ፣ የዕፀዋት ስብጥሩ እንደጨመረና እንስሳትም ለመጠለያነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሒደት አፈሩ ከመሸርሸር ከመዳኑ በተጨማሪ፣ ጠፍተው የነበሩ የውኃ ምንጮችም መመለስ ችለዋል፡፡ በእንጦጦ በሚገኙት ማርያም መስክ፣ ታጀብ፣ እንቁርቁሪትና ሌሎችም ኬላዎች 13 ምንጮች ይገኛሉ፡፡ ባህር ዛፍ የመወገዱ ውጤት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በአካባቢው ያለው የከርሰ ምድር ውኃ እንደሚጠራቀምና ጎርፍ እንዳይሆን እርከኑ እንደሚከላከል ያክላሉ፡፡

የምኒልክ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ከርከሮ፣ አነር፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛና ሌሎችም እንስሳት ይገኛሉ፡፡ እንደ ገደል አሙቅ ያሉ የአበባ ዝርያዎችም በአካባቢው ይበቅላሉ፡፡ ‹‹የእንስሳትና ዕፀዋቱ ሕይወት ከደን ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ደኑ ሲመናመን ጠፍተው የነበሩ እንስሳት ተመልሰው እየመጡ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አካባቢው በባህር ዛፍ ተሸፍኖ በነበረበት ወቅት ሳርና ቁጥቋጦ ሳይቀር ለመብቀል እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡ አካባቢው በተደጋጋሚ በጎርፍ ይጠቃም ነበር፡፡ ይህንን ለመግታት ክትር ከተሠራ በኋላ አገር በቀል ዕፀዋት ተተክለዋል፡፡ በፓርኩ ውስጥ ስንዘዋወር ካስተዋልነው ሳርና አበባ በተጨማሪ ከመሬት ውስጥ በራሳቸው ጊዜ ወጥተው ያፈሩ ዕፀዋት ተመልክተናል፡፡ የዕፀዋቱ የዘር ቅሪት (የዘር ባንክ የሚባለው) መሬት ውስጥ ለዓመታት የኖረ ሲሆን፣ አካባቢው የተመቻቸ ሲሆን በተፈጥሮ ኃይል ይበቅላሉ፡፡

የእንጦጦ ተፈጥሯዊ ፓርክ ከንክኪ ነፃ እንዲሆን በመደረጉ ለዓመታት አፈር ውስጥ የነበሩ የዕፀዋት ዝርያዎች በድጋሚ መብቀል መቻላቸውን አቶ ሙሉጌታ ይገልጻሉ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ምንጮች ለአካባቢው ማኅበረሰብ የውኃ ምንጭ ናቸው፡፡ ውኃ በጄሪካን የሚቀዱ ነዋሪዎች አስተውለናል፡፡ በቀጣይ ቦታውን ለአዲስ አበባ ውኃ ማጠራቀሚያነት ለማዋል ከአዲስ አበባ ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር መስማማታቸውን ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር አባላት፣ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋሞች ሠራተኞችና ተማሪዎች ጋር በመሆን በክረምት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ዕፀዋት ይተክላሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተከላው በጎ ፈቃደኞች፣ ባንኮችና ሌሎችም አካላት ተሳትፈዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በዋነኛነት አገር በቀል ዕፀዋት የተተከለው በእንጦጦ ሲሆን፣ በቅርብ ርቀት ያለው ፈረንሣይ አካባቢም ይጠቀሳል፡፡

የኢትዮጵያ የደን ይዞታ ከ80 በመቶ ወደ ሦስትና አራት በመቶ ማሽቆልቆሉ አሳሳቢ እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ የዛፍ ተከላ እንዲሁም የአፈርና ውኃ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ እንጦጦ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ በአሁን ወቅት የደን ሽፋኑ ወደ 13 በመቶ እያደገ መምጣቱንም ያክላሉ፡፡

ፓርኩ እንደ ተፈጥሮ መስህብነቱ የጎብኚዎች መዳረሻም ነው፡፡ ሆኖም በብዛት የሚጠቀሙበት የውጪ አገር ዜጎች መሆናቸውን በጉብኝታችን ወቅት አስተውለናል፡፡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው እንጦጦ፣ ጠቀሜታቸውን የሚገዳደሩ እንቅፋቶች የሸበቡት መሆኑንም ተመልክተናል፡፡

በጉብኝታችን እኩሌታ አንድ ወጣት በጎች ፓርኩ ውስጥ አስገብቶ እንዲመገቡ ሲያደርግ ገጥሞናል፡፡ አስጎብኚያችን እንስሳቱን እንዲያስወጣ ሲጠይቁትም ቀና ምላሽ አልሰጠም፡፡ በጎችን ከማብላቱ በዘለለ በጥብቅ አካባቢው እያዳረሰ ስላለው ጉዳት አለመገንዘቡም ግልጽ ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ተመሳሳይ እሰጣ ገባ የዘወትር ገጠመኛቸው ነው፡፡ አካባቢው መሣሪያ በታጠቁ ግለሰቦች እንዲጠበቅ የተደረገውም ለዚሁ ነው፡፡

ከምንጭ ውኃ ለመቅዳት፣ ለመናፈስ ወይም በተለያየ ምክንያት ወደ አካባቢው የሚገቡ ሰዎች ላስቲክ፣ የውኃ መያዣ ኮዳና ሌሎችም ቁሰቀሶች ጥለው ይወጣሉ፡፡ በአካባቢው ተፈጥሯዊ ሀብት የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ የእንጦጦ ፓርክ ከገጠሙት ፈተናዎች በአጠቃላይ የከፋው ከኦሮሚያ ክልል የተነሳው የድንበር ወሰን ጥያቄ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ሥራ አመራር ቦርድ ፕሬዚዳንት ሊቀ ካህናት አባይነህ አበበ ይናገራሉ፡፡

ማኅበሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተረከበው 1,300 ሔክታር መካከል አዲስ አበባና ኦሮሚያን በሚያዋስነው አካባቢ ባለው የፓርኩ ክልል መሥራት እንደማይችሉ የተገለጸላቸው ዓምና መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤትና የችግኝ ጣቢያ ከሚገኝበት መውጣታቸውንም ያክላሉ፡፡ ማኅበሩ ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎችም ክልሎች አገር በቀል ዛፎች በመትከል የሚንቀሳቀስ መሆኑን በመግለጽ፣ በቦታው የጀመሩበትን ሥራ መቀጠል እንዲችሉ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ይናገራሉ፡፡

‹‹በኦሮሚያ በኩል ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቶንና ፈቃድ አግኝተን እንድንሠራ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ እንቅስቃሴው የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ በአጠቃላይ ነው፤›› ይላሉ ሊቀ ካህናት አባይነህ፡፡ ለሚመለከታቸው አካሎች ጥያቄ ያቀረቡት ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ቢሆንም አስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ውሳኔው እስኪታወቅ ያለሥራ ብንቀመጥ የበጎ አድራጎትና የማኅበራት ኤጀንሲ ፈቃዳችንን አያድሰውም፤›› በማለት፣ ውሳኔ እስኪያገኙ አዲስ የችግኝ ጣቢያ እንደሚያቋቁሙ አያይዘው ተነግረዋል፡፡ በአካባቢው የድንበር ጥያቄ ሲቀርብ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ቤተክርስቲያኖችና ለዓመታት የኖሩ ግለሰቦችም የይገባኛል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

በጋምቤላ የመምህራን ኮሌጅ በቃልኪዳን ኢሳያስና አፈወርቅ በቀለ Species Composition Relative Abundance and Distribution of the Avian Fauna of Entoto Natural Park and Escarpment በሚል የተሠራው ጥናት፣ በእንጦጦ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት የሚዳስስ ነው፡፡ በአዕዋፋት ስብጥር ከሚጠቀሱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው እንጦጦ አምስት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አዕዋፋት እንደሚኖሩ ተመልክቷል፡፡ 11 አዕዋፋት ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ ይኖራሉ፡፡ በአካባቢው በአጠቃላይ 124 የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ዕፀዋት ስብጥር ለአዕዋፋቱ ህልውና መሠረት እንደሆነ በጥናቱ ተገልጾ፣ የሰዎች ሠፈራ፣ የደን ጭፍጨፋ፣ የአፈር መሸርሸርና የባህር ዛፍ ተፅዕኖ አካባቢውን እንደሚፈታተኑት ተጠቁሟል፡፡ አካባቢው ከሰዎች ንክኪ ውጪ መሆን እንዳለበትና ሕይወታቸውን የዛፍ ቅጠል በመሸጥ ያደረጉት ሰዎች ቀስ በቀስ አማራጭ ሥራ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የዛፍ ጭፍጨፋው ለአፈር መሸርሸር ምክንያት እንደሆነ በመግለጽ፣ ለአዕዋፋትና እንስሳት ጥበቃ ደኑን መንከባከብ የግድ መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ብዙም ተፈጥሯዊ ፓርኮች በሌሏት አዲስ አበባ፣ ያሉትንም መንከባከብ ካልተቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ ሐምሌ 19 ፓርክ፣ የካ ፓርክና ቦሌ ፓርክን የመሳሰሉትን ፓርኮች ጨምሮ ለተፈጥሯዊ ሀብቱ ጥበቃ ማድረግ ያሻል፡፡

የዓለም ሙቀት መጠን መጨመር (ግሎባል ዋርሚንግ) የዓለም ራስ ምታት በሆነበት ዘመን፣ የተፈጥሮ ሀብትን ቸል ማለት አያስኬድም፡፡ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ሲሉ የተፈጥሮ ሀብትን ገሸሽ ማድረጋቸው፣ ዛሬ ሕዝባቸው በአየር ብክለት ሳቢያ ጭንብል ለበሶ እንዲንቀሳቀስ አስገድዷል፡፡ በከተሞቻቸው በየቅርብ ርቀቱ ዛፍ በመትከል አገራቸውን ለመታደግ ቢጣጣሩም፣ ተፈጥሮ  እስኪያገግም አደጋ ላይ እየወደቁ ያሉ ዜጎቻቸው የትየለሌ ናቸው፡፡

በእንጦጦ የተፈጥሮ ፓርክ ያለው ድባብ ፍፁም መንፈስ የሚያድስ ነው፡፡ ለከተማዋ እንዲሁም ለአገሪቱ ህልውናም የጀርባ አጥንት መሆኑም አይካድም፡፡ ከተጋረጡበት ፈተናዎች መታደግ ካልተቻለ ኢትዮጵያም እንደ ሌሎች አገሮች መሆኗ አይቀርም፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ለዓመታት በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ድንበር በማስፋፋት፣ የቤት እንስሳት በማርባት፣ ከብቶች ወደ ፓርኩ በመልቀቅና በሌላም መንገድ ጫና ያሳድራሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ተገቢው የመኖሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ከፓርኩ ውጪ እንዲኖሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ይናገራሉ፡፡

‹‹ታሪክና ተፈጥሮ›› በተሰኘ ዘጋቢ ፊልም አስተያየታቸውን የሰጡት የሥነ ሕይወት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ፣ የአገሪቱ ዕድገት ዛፍ በመትከል ባህል ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አዲስ አበባን የሚያዋስናት የእንጦጦ ተራራ የንፁህ አየርና ውኃ ምንጭ በመሆን ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት፣ ጥበቃው እንዲጠናከር ያሳስባሉ፡፡

ባህር ዛፍ ለሕዝቡ እየሰጠ ባለው አገልግሎትና በተፈጥሮ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ተቃርኖ ሲገልጹ ‹‹ባህር ዛፍ ወይ አይዋጥ ወይ አይተፋ፣ በጉሮሮ እንደተሰነቀረ አጥንት ነው፤›› በማለት ነበር፡፡ ለሕዝቡ ቤት መሥሪያ ግብአትና መተዳደሪያ አማራጭ በመፍጠር ቀስ በቀስ ወደ አገር በቀል ዛፎች መሸጋገር እንደሚያስፈልግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከአፈር መሸርሸርና ከጎርፍ ለመዳን እንዲሁም በአካባቢው የውኃ ሀብት በስፋት ለመጠቀም እንዲቻልም ዘላቂነት ያለው ሥራ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ፡፡

እንጦጦ የአዲስ አበባ ‹‹ሳንባ›› የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በአካባቢው የሚነሱ የድንበርና የይገባኛል ጥያቄዎችና የነዋሪዎችና የቤት እንስሳዎቻቸው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ለነዚህ ውዝግቦች መፍትሔ ለመሰጠት የሚወሰደው ጊዜ፣ የተፈጥሮ ሀብቱ የሚጠፋበት መሆኑም ጉዳዩን አሳሰቢ አድርጎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...