Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የ850 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ የፋይናንስ ማግኘታቸውን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል

ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚውል የ850 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት መፍቀዱን የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ መንግሥት በመደበኛነት ከሚያገኛቸው የብድር ማዕቀፎች በተጓዳኝ ለሚገነባቸው የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ፋይናንስ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡

በባንኩ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ ከሚሰጣቸው የፋይናንስ ድጋፎች ውስጥ አገሩቱን ጨምሮ መላው አፍሪካ ተጠቃሚ ይሆንበታል የተባለውንና ለአሥር ዓመታት የሚውለውን የ25 ቢሊዮን ዶላር ወይም በየዓመቱም የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ገብርኤል ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነም፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ እንደ አባል አገር ከሚሰጣት ድርሻ ባሻገር ለግሉ ዘርፍ ተዋንያንም ብድር አመቻችቷል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ደርባ ሲሚንቶ ያሉት የግል ኩባንያዎች ከባንኩ ፋይናንስ ድጋፍ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሌሎች የግል ኩባንያዎች ከባንኩ ፈንድ ለማግኘት እየተጠባበቁ እንዲገኙና ብድር ሊለቀቅላቸው የመጨረሻውን ሒደት ላይ መሆናቸውን አቶ ገብርኤል ጠቅሰው፣ ኩባንያዎቹ እነማን እንደሆኑ ከመግለጽ መቆጠብን እንደሚመርጡ ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት በአማራ፣ በትግራይ፣ በአሮሚያና በደቡብ ክልሎች 30 ቢሊዮን ብር ወይም ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቁ አራት የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ይፋ ያደረገው ዕቅድ በውጭ ለጋሾች ተቀባይነት አግኝቶለታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለሁለት ቀናት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተካሄደው የመጀመርያው የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረምን በጋራ ያሰናዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ)ን ጨምሮ የጣልያንና የኔዘርላንድስ መንግሥት እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ለግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ አብተው፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት በፋይናንስ ረገድ የሚፈለገው ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከእነዚህ ተቋማትና መንግሥታት ቃል ከተገባለት ድጋፍ ቀደም ብሎ 300 ሚሊዮን ዶላር ለፓርኮቹ መሠረተ ልማት ግንባታ እንዲውል ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ አራቱን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ለመገንባት ከተመደበው ውስጥ ለግንባታ የሚጠይቀው ወጪ ከ660 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ መሆኑም ስለፓርኮቹ ግንባታ ይፋ የተደረገው ሰነድ ይጠቁማል፡፡

አቶ አሕመድ እንዳብራሩት፣ መንግሥት በክልሎች ባለቤትነት የሚገነቡትን የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያገኙት ተቀባይነትን መነሻ በማድረግ ሌሎች 13 ተጨማሪ ፓርኮችን ለመገንባት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚረዳውም አብራርተዋል፡፡ በአገሪቱ ዋና ዋና ምርት አምራች አካባቢዎች፣ በመቶ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ይገነባሉ የተባሉት እነዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብዓት እጥረት እንዳያጋጥማቸው ታስቦም ትርፍ አምራች የተባሉ ቦታዎች መለየታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም ወቅት የዩኒዶ ዋና ዳይሬክተር ሊ ዮንግን ተሰናባቹ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያና በአፍሪካ አገሮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተለይ ሎፔዝ ያደረጉት ቀስቃሽ ንግግር፣ አፍሪካ በኢንዱስትሪ መስክ ጀማሪ ስትሆን ወደ ኋላ የቀረች ቀደምት የኢንዱስትሪ ባለቤት ከሆኑት ተርታ የምትመደብ አኅጉር መሆኗን አብራርተዋል፡፡ በአፍሪካ አገሮች መካከል የእርስ በርስ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ ሲጠይቁም፣ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝቦችን ፍላጎት ለማሟላት ሰፊ ገበያ ስላለ አገሮች እርስ በርስ እንዲተባበሩና እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች