Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና›› ሥርዓተ ቀብር ከፊል ገጽታ

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና›› የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ወታደራዊ ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡ ፎቶዎቹ ቤተሰቦቻቸውን፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ የቀድሞውን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ እንዲሁም የቀድሞዎቹ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ ደስታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ያሳያሉ፡፡ ፎቶ በሔኖክ ያሬድ

********

የተለያየን ቀን

ድንገት ሰማይ ተከፍቶ አለቀሰ

ደመና ቋጥሮ ምድርን አራሰ

ፀሐይም ብርሃን ጮራ ነፍጋ

ወራት ተቀየሩ ክረምት ሆነ በጋ

ወንዝና ተራራ ጋራው ሳር ቅጠሉ

በሐዘን ተኮራምተው ቀና ደፋ እያሉ

ካካላቸው ቁራጭ ቅጠል እየጣሉ

‹‹ፍቅር ተገነዘ ሊቀበር ነው›› አሉ

ውበት ፈገግታዋን ከላይዋ አውልቃ

ጠላሸት ተቀባች አዘነች ጨረቃ

በመረረ ስሜት እጅግ ስለባቡ

ምድር ማየት ጠሉ ክዋክብት አነቡ

የአዕዋፋት ዝማሬ ተረሳቸው ወጉ

የንጋትን ብስራት ዶሮዎች ዘነጉ

ኩርፊያና ፍቅራችን የእኔና የእሷ ሳለ

በፍጡራን ሁሉ ድብርት ተጣለ

ታሪኩ ከበደ ‹‹ምክረ ሰይጣን›› (2008 ዓ.ም.)

*********

 ‹‹የጨረቃ ጥላ›› ቅዳሜ ይመረቃል፡፡

‹‹የጨረቃ ጥላ›› በሚል ርእስ በደራሲ አሥራት ከበደ የተጻፈው ወጥ ረዥም ልቦለድ አዲስ መጽሐፍ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ቅዳሜ፣ ከቀኑ 7፡30 ሰዓት በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኛነትና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ተሻገር ሽፈራውና የኮምዩኒኬሽንና የሥነ ጽሑፍ ባለሞያው አቶ ነጻነት ተስፋዬ አበበ፣ ስለ መጽሐፉ ዳሰሳዊ ግምገማ ያቀርባሉ፡፡ ደራሲው አሥራት ከበደ ከዚህ ቀደም ‹‹የምሽት እንግዳ›› የተሰኘ ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወቃል፡፡

***********

68 ቀናት በመፆሟ ለሞተችው ልጅ ቤተሰቦቿ ላይ ምርመራ ተጀመረ

ባለፈው ሳምንት የሞተችው የ13 ዓመቷ ህንዳዊት ለሞቷ ምክንያት የሆነው 68 ቀናት መፆሟ በመሆኑ፣ ፖሊስ በቤተሰቦቿ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ፖሊስ የታዳጊዋ አራድሃና ሳማዳሪያ ቤተሰቦች፣ ፆሙን እንድትፈፅም አስገድደዋት ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ላይ ደርሷዋል፡፡

ቤተሰቦቿ ግን ልጃቸው ፆሙን የጀመረቸው የጃኒዝም እምነት በሚያዘው መሠረት በበጎ ፈቃደኝነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ሰዎች ያለምግብ እስከ ሁለት ወራት ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ታዳጊዋ ከሁለት ወራት በላይ መቆየቷ ለሞት ዳርጓታል፡፡

አባቷ ሳማድሪያ እንደሚሉት፣ ልጃቸው 51 ቀናትን እንደፆመች ፆሙን እንድታቆም መክረዋታል፡፡ ሆኖም ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ የማኅበራዊ ድረ ገጽ አቀንቃኞች ግን የቤተሰቦቿን ቃል አልተቀበሉትም፡፡

እንደ ዘገባውም፣ የአባቷ ሃይማኖታዊ አባት የ13 ዓመቷ ታዳጊ ለ68 ቀናት ብትፆም የአባቷ ንግድ እንደሚሳካለት ነግረዋት ነበር፡፡

********

ቻይናውያኑ የነገሡበት ውድድር

ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው ወርልድ ብላይንድ ቴስት ውድድር ላይ ቻይናውያን ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ሆኑ፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ወይን የመቅመስና ሥለቀመሱት ወይን ዝርዝር መረጃ የመናገር ውድድር ላይ የስፔን፣ የቤልጄም፣ የፈረንሣይና የአሜሪካ ተወዳዳሪዎች የውድድሩ ተካፋይ ነበሩ፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ተወዳዳሪዎቹ በብርጭቆ ተቀድቶ የሚቀርብላቸውን ወይን የምን አገር ምርት እንደሆነ፣ መጠጡን ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ የዋሉት የወይን ፍሬዎች ዓይነት፣ የወይን ፍሬው የተመረበት ምልክዓምድራዊ አቀማመጥ እንዲሁም መቼ እንደተመረቱ በትክክል መግለጽ አለባቸው፡፡ 50 በመቶ በዕድል 50 በመቶ ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ በተነገረለት ውድድሩ አሸናፊ የሆኑት የቻይና የወይን ቀማሽ ቡድኖች፣ በውድድሩ ላይ ባሳዩት መልካም ባህሪ ተመሥጋኝም ሆነዋል፡፡ የአሜሪካና የፈረንሣይ ቡድኖች ውድድሩን ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ሲሆኑ፣ የቀድሞ የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው ስፔን ደግሞ አሥረኛ ሆናለች፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች