ለሙዚቃው ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ምቱን እየተከተለ ወዲያና ወዲህ እያለ በነፃነት ይጨፍራል፡፡ የመድረክ አያያዙም ደስ ያሰኛል፡፡ ከታዳሚው ጋር አብሮ ሲጫወት ሲታይ ደግሞ በሙያው ዓመታት የቆየ ይመስላል፡፡በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውቅናን ያተረፈበት ዲንዳሾ የተሰኘው ነጠላ ዜማው ቅጽል ስሙ እስከመሆን በቅቷል፡፡
ድምጻዊ አስገኘው አሽኮ ተወልዶ ያደገው አርባ ምንጭ ከተማ፡፡ ለሥነ ጽሑፍ፣ ለውዝዋዜና ዳንስ ፍቅር ያደረበት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ጋዜጣ አዟሪም ነበር፡፡ ወደ ኪነ ጥበቡ ከገባ በኋላም ትኩረቱ የሙዚቃ ግጥም መጻፍ እንዲሁም ውዝዋዜና ዳንስ ላይ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግን ድምጻዊ የመሆን አጋጣሚ አገኘ፡፡ በዘመናዊ የሙዚቃ ስልት አንድ ሙዚቃን ሠራ፡፡ ያቀናብር የነበረው ጓደኛውም ሥራውን ወደደለት፡፡
በወቅቱ ግጥም ጽፎ ለድምጻውያን ከመስጠት ያለፈ ህልም አልነበረውም፡፡ ይሁንና ጓደኛው ድምፃዊ እንዲሆን አደፋፈረው፡፡ አስገኘውም እያመነታ የመጀመሪያ ሥራው የሆነውን ዲንዳሾን ሠራ፡፡ 40,000 ብር አውጥቶም ጥሩ የሚባል የሙዚቃ ክሊፕ አሠርቷል፡፡ ይህንን ያደረገውም በቂ ገንዘብ ኖሮት ሳይሆን ታዋቂነትን ለማትረፍ ነበር፡፡ ሥራው ከሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ ሙዚቃዎችን በዩቲዩብ ድረገጽ ላይ ለሚያወጣለት አንድ ዌብሳይት ሰጠ፡፡ ነገር ግን አልተሳካለትም ሥራው ቀደም ብሎ በሌላ ዌብሳይት ላይ ተለቋል በሚል እንደማይቀበሉት ገልጸው አሰናበቱት፡፡
‹‹ለሌላ ዌብሳይት አልሰጠሁም ነበር፡፡ አይሆንም ሲሉኝ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ፍላጎቴ ሙዚቃዬ አድማጭ ጋር እንዲደርስ እንጂ ገንዘብ ማግኘትም አልነበረም›› የሚለው አስገኘው የመጀመሪያ ሙከራው ባይሳካም ሙዚቃው ባልተጠበቀ ሁኔታ በሌሎች ዌብሳይቶች ተለቆ ተወዳጅነትን እንዳተረፈለትና ታዋቂ እንዳደረገው ይናገራል፡፡
ከዚያ በኋላ አራት ነጠላ ዜማዎችን ለሕዝብ ጆሮ አብቅቷል፡፡ ለእያንዳንዱ ሙዚቃዎች ክሊፕ ለማሠራትም ከ30 እስከ 40 ሺሕ ብር አውጥቷል፡፡ ሙዚቃዎቹን የሚያሳትም የሚገዛው ሌላ ድርጅት ባለመኖሩ በሥራዎቹ የሚያገኘው ይህ ነው የሚባል ገቢ የለም፡፡ በመሆኑም ሌሎች ሥራዎችን ለሕዝብ ጆሮ ለማድረስ አቅም የለውም፡፡ ስለዚህም የተለያዩ ድርጅቶችን ድጎማ መጠየቅ ግድ ይለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዕድገት ታሪክ ባለፉት ዘመናት ድምፃዊነት እንደ ሙያ አያታይም ነበር፡፡ ለሙያው ልዩ ፍቅር ያላቸው ወጣቶች ዘፋኝ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ከባድ ፈተናዎች ይገጥማቸውም ነበር፡፡ አዝማሪ የሚል ቅጽል ስም ይሰጣቸዋልም፡፡ ዘፋኝ በመሆናቸው ከቤተሰብ እስከመገለል ይደርሱ ነበር፡፡
ከማህበረሰቡ በሚደርስባቸው ተፅእኖ ሙያውን ወደጎን ብለው በሌላ ሥራ የተሰማሩ መኖራቸውም እርግጥ ነው፡፡ ይሁንና እጃቸውን ያልሰጡ ጥቂት የማይባሉ ለዛሬው የአገሪቱ ሙዚቃ እድገት መሠረት መጣል የቻሉ ድምጻውያንን ማፍራት ተችሏል፡፡ እንደ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ሒሩት በቀለ፣ ዓለማየሁ እሸቴ ያሉ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ተጠቃሽ የሆኑ የአገሪቱን ሙዚቃ አንድ ዕርምጃ ማስኬድ የቻሉ ድምጻውያን የዛ ዘመን ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ለሙዚቀኞች የነበረው አመለካከት እንዲለወጥ በማድረግ ረገድም ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ እንደ ብርቅ ይታዩም ነበረ፡፡ ሳይደመጥ የሚቀር ካሴትም አልነበረም ሊባል ይችላል፡፡ ገዝቶ ለማድመጥ ያልቻሉ ቢኖሩ እንኳ ተቀባብለው ያደምጡበት ትውስታ የቅርብ ጊዜ ነው፡፡
ሙዚቀኞች እንደ አሸን በፈሉበት በአሁኑ ወቅት ግን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቱ ውስጥ እየተለቀቁ ያሉት የሙዚቃ አልበሞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በተለይም ደግሞ አዲስ የሚለቀቁ ነጠላ ዜማዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በየሁለት ቀኑ አንድ ነጠላ ዜማ ከነክሊፑ ይለቀቃል፡፡ ለሙዚቃዎቹ ክሊፕ ለማዘጋጀትም የካሜራ ኪራይ፣ የአልባሳት፣ የተወዛዋዥ፣ የቦታ ኪራይና ሌሎችን ጨምሮ ከ25 እስከ 40 ሺሕ ብር ያስፈልጋል፡፡ 25 ሺሕ ብር የሚጠይቁት ከተማ ውስጥ የሚቀረጹ ዘመናዊ የሙዚቃ ክሊፖች ሲሆኑ፣ 40 ሺሕ ብር የሚፈጁት ደግሞ የባህላዊ ሙዚቃ ክሊፖች ናቸው፡፡
አብዛኛዎቹ ክሊፖች ከደረጃ በታች እንደሆኑ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች እንደሚጎድሏቸው፣ የምስል ጥራት ችግርና ሌሎችም እንከኖች በስፋት እንደሚስተዋሉባቸው አሰልቺ እንደሆኑም አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወራት ፈጅተው በጥሩ ሁኔታ የሚሰሩ ብዙ ናቸው፡፡
ይህንን ያህል ዋጋ ተከፍሎባቸው የሚዘጋጁት እነዚህ የሙዚቃ ክሊፖችን ለአድማጭ ጆሮ ለማድረስ ያለው ፈተና ከባድ ነው፡፡ ድምጻዊ ማኅደር አሥራት ወደ ሙዚቃው ዓለም ከገባ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሥራውን የጀመረው በናይት ክለቦች ተቀጥሮ በመሥራት ሲሆን፣ እስካሁን አንድ አልበምና ሁለት ነጠላ ዜማዎች ሠርቷል፡፡ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማው በ1997 ዓ.ም. ያወጣው አስየው ቤሌማ የተሰኘው የቡሄ ዜማ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሲያምረኝ ተሾመ ጋር በሂፕሆፕ የሙዚቃ ስልት የሠራው ‹‹መጨነቅ›› የተሰኘው ሥራው ነው፡፡ ከፋ አገር ሄዶ የሠራውም ‹‹የሻሞን›› የሚለው የሕዝብ ዘፈኑ ነጠላ ዜማ የነበረ በኋላ ግን በአልበሙ ያካተተውን ሙዚቃ ክሊፕ ለማሠራት 30 ሺሕ ብር አውጥቷል፡፡ ይህ በወቅቱ ከፍተኛ ወጪ እንደነበር ይናገራል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ወደ ክልል ከተሞች ተሂዶ ከሚሠሩ ክሊፖች ውጪ ያሉት አስምት ሺሕ ባልሞላ ብር ይጠናቀቁ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ክሊፕ እስከ 150,000 ብር ይፈጃል፡፡ አንድ ክሊፕ ለመሥራት የሚወጣው ወጪ እንደሚሠሩት ክሊፕ ዓይነት ይወሰናል፡፡ እስከ 150,000 ብር የሚያስወጡት ክሊፕች ወራት ፈጅተው ከከተማ ውጪ የሚሠሩ ናቸው፡፡
‹‹ድምፃውያኑ ከ150,000 ብር በ25,000 ብር ክሊፕ ቢያሠሩም ክሊፑ አይሸጥም፡፡ ምናልባትም ሕዝቡ አይቶ ከወደዳቸው በተለያዩ መድረኮች እየተጋበዙ ሥራቸውን በማቅረብ ገንዘብ ቢከፈላቸው ነው›› ይላል፡፡
የሙዚቃ ሥራ እንደሸቀጥ ተመን አይወጣለትም የሚለው ማኅደር የአንድን ሙዚቃ ክሊፕ ለማዘጋጀት ከሚወጣው ገንዘብ ውጪ ለቅንብር፣ ኦዲዎውን ለማዘጋጀት ለግጥምና ዜማ የሚከፈለው ገንዘብ ቀላል እንዳለሆነ፣ ክፍያውም ሆነ የስራው ጥራት ከእስቱዲዮ ስቱዲዮ፣ ከአቀናባሪ አቀናባሪ እንደሚለያይ ገልጿል፡፡
በዚህ መልኩ የተሠሩ የሙዚቃ ክሊፖች በቴሌቪዥን አልያም በተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ለአድማጮች ከተጋበዙ የድምጽዊው ዕድል ሊሰምር ይችላል፡፡ አንዳንድ ድምጻውያን እንደሚሉት፣ አዲስ የሚለቀቁ የሙዚቃ ክሊፖች በመገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁት ሥራው የታዋቂ ድምጻዊ ሲሆን አልያም በመገናኛ ብዙኃን የሚሠራ የሚያውቁት ሰው ሲኖር ነው፡፡ ካልሆነ ግን ምንም እንኳን ሥራው ጥሩ የሚባል ቢሆንም ከሰው ጆሮ ሳይደርስ የሚቀርባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ይህም ጥቂት የማይባሉ ወጣት ድምጻውያንን ተስፋ እያስቆረጠ ይገኛል፡፡
የድምጻዊነት ሙያውን የተቀላቀለችው ምነው ወዳጄ በሚል የአምባሰል ስልት ያለው የነጠላ ዜማዋ ነበር፡፡ የሙዚቃ ክሊፑን የሠራችው ከሦስት ዓመታት በፊት ከልጅ ሚካሄል ጋር ነበር፡፡ ሥራዋ ጥሩ የሚባልና በቀላሉ የሕዝብ ጆሮ ሊገዛ የሚችል ቢሆንም እንደጠበቀችው አልሆነላትም፡፡ ሥራው በመገናኛ ብዙኃን በኩል ለሕዝብ ጆሮ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ሥራዋ እንዲደመጥላት ብዙ እንደጣረች የምትናገረው ድምፃዊቷ ተስፋ ባለመቁረጥ ከዚያ በኋላ ሌሎች አዳዲስ ሥራዎች ማውጣቷን፣ ነገር ግን ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው ትናገራለች፡፡
ክሊፖቹን አሳትሞ በተገቢው መንገድ ለአድማጭ ጆሮ የሚያደርስ ራሱን የቻለ ተቋም አለመኖሩ ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ድምጻውያኑ ይስማማሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉት ግን ሌሎች መንገዶችን ማለትም ሥራቸውን ከዩትዩብ ጋር አብረው ከሚሠሩ እንደ ድሬ ትዩብ፣ ሆፕ ሚውዚክ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮ ዋንላቭ በተሰኙ ዌብ ሳይቶች ላይ በመልቀቅ መጠነኛ ክፍያ ለማግኘት ይጥራሉ፡፡
እሹሩሩ በሚል ከወራት በፊት ባወጣው ነጠላ ዜማ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምጻዊ ብዙአየሁ ክፍሌ ከድሬ ትዩብና ሆፕ ሚውዚክ ኢትዮጵያ ጋር አብሮ ይሠራል፡፡
በቅርቡ ግን ከድሬ ትዩብ ጋር የነበረውን ውል አቋርጦ ከሆፕ ጋር እየሠራ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እስካሁን አምስት ነጠላ ዜማዎችን ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል፡፡ እሹሩሩ የተባለውን የሙዚቃ ክሊፑን ለማሠራት 30,000 ብር እንደፈጀበት ይናገራል፡፡ ሙዚቃውን የለቀቀው በሆፕ ሚውዚክ ኢትዮጽያ ድረ ገጽ ላይ ሲሆን የሚከፈለው ሙዚቃው ተመልካች ባገኘ መጠን እንደሆነ ይናገራል፡፡ ክሊፑ እስካሁን 224,017 ጊዜ ተመልካች አግኝቷል፡፡
በዚህ የሚያገኘው ክፍያ ክሊፑን ለመሥራት ካወጣው ገንዘብ በጣም የሚያንስ ቢሆንም ‹‹ሙዚቃዎቹን ለማስተዋወቅ የራስ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ እኔ ራሴንና ሥራዎቼን በተለያዩ መንገዶች ለማስተዋወቅ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ይህም በየመድረኩ እየተጋበዝኩ ሥራዎቼን እንዳቀርብ ረድቶኛል፡፡ ያወጣሁትን በመድረክ ሥራዎች አገኛለሁ›› ይላል፡፡
አቶ ብሩክ ተከስተ የሆፕ ሚውዚክ ፕሮሞሽን ኤንድ ኤቨንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመው ከስድስት ዓመታት በፊት ቢሆንም ሥራ የጀመረው ግን የዛሬ ዓመት ገደማ ነበር፡፡
አቶ ብሩክ እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች ጥሩ ክሊፕ እንዲሠሩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የሙዚቃ ክሊፑን ለማሠራት የሚያወጡትን የተወሰነ ወጪም ያግዛቸዋል፡፡ ሥራውን የሚሠሩት ከዩትዩብ ጋር በመተባበር ሲሆን ከሚገኘው ገቢ እኩል ይከፍሉታል፡፡ ክፍያው የሚፈጸመውም በየስድስት ወሩ ነው፡፡ 60 በመቶውን ዩትዩብ ይወስዳል፣ 40 በመቶው ደግሞ ድርጅቱና ድምጻዊው፡፡ አንድ የሙዚቃ ክሊፕ 1,000,000 ጊዜ ቢታይ 100,000 ብር ይገኝበታል፡፡ ከብሩ ላይ 60,000 ለዩትዩብ ገቢ ይሆናል፡፡ 40,000 ደግሞ ሆፕ ሚውዚክና ድምጻዊው 20,000 20,000 ብር ይከፋፈላሉ፡፡ በሆፕ ድረገጽ ላይ የሚገኙት የቴዲ አፍሮ ሰባ ደረጃ የተሰኘው የሙዚቃ ክሊፕና የእመቤት ነጋሲ ሠንዳበል ከስምንት ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታዩና ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን በድረገጽ የሚገኙት አብዛኞቹ ክሊፖች የታዩት በ100,000ዎች ብቻ በመሆኑ የሚከፈላቸው ገንዘብ ከ20,000 ብር ያነሰ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
የድሬ ትዩብ ባለቤት አቶ ቢኒያም ነገሱ እንደሚሉት ደግሞ፣ በድረ ገጹ ላይ ለሚወጡ ክሊፖች ክፍያ የሚፈጸመው ገጹ ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎች በታዩ መጠን ነው፡፡ ለአንድ እይታ (ቪው) የሚከፈለው ገንዘብም እንደየሁኔታው ተለዋዋጭ ይሆናል፡፡ በፈረንጆቹ ገና ወቅት የማስታወቂያዎች ቁጥርና የማስታወቂያ ዋጋ በከፍተኛ መጠን የሚጨምርበት በመሆኑ ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ወቅት ነው፡፡
‹‹እኛ የአገሪቱን ሕግ ተከትለን ነው የምንሠራው›› የሚሉት አቶ ቢኒያም ሙሉ አልበም የሚያሳትሙ ድምጻውያን የራሳቸው የዩትዩብ ዌብሳይት እንዲከፍቱ እንደሚደረግ፣ ድርጅቱ የሚከፈለው የማኔጅመንት ብቻ እንደሆነ ሙዚቃው ተመልካች እስካገኘ ድረስ ለድምጻዊው ዩትዩብ እንደሚከፍለው ይህም ድምፃዊው ተገቢውን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኝ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ የድምጻዊት ፍቅረአዲስ ነቀአጥበብ ምስክር የተሰኘው የሙዚቃ ሥራ የድሬትዩብ የዕይታ ሠንጠረዥን በአንደኝነት እየመራ እንደሚገኝ የታምራት ደስታ ሠሊናና የዳዊት ነጋ ወዛማይ ሁለተኛና ሦስተኛ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ድምጻውያኑም በ100,000ዎች እንደሚከፈላቸው አቶ ቢኒያም ተናግረዋል፡፡
እንደ አሸን ለፈሉት ነጠላ ዜማዎች መድረክ የፈጠረው ዩትዩብ በመጠኑም ቢሆን አለኝታ የሆናቸው ይመስላል፡፡ ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ሙዚቃውን በድረገጾቹ ከመጫን ባለፈ ጠንካራ የማስታወቂያ ሥራ መስራት ግድ ይላል፡፡ ይህም የሙዚቀኛውን የግል ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡