Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የጥበብ ልጆች››

‹‹የጥበብ ልጆች››

ቀን:

የ12 ዓመቷ ሀና በሐዘን ተቆራምዳ ጓዳ ውስጥ ተቀምጣ ታለቅሳለች፡፡ ቤተሰቦቿ ቅጥር ግቢ ባለው ዘፈንና ጭፈራ አልተደሠተችም፡፡ ሀና ያለ ዕድሜዋ ለጋብቻ የታጨች ሲሆን፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤቶች ድግሱን እያሟሟቁ ነው፡፡ እሷ ግን በትምህርት መግፋትና ዕድሜዋ ለትዳር ሲደርስ በምርጫዋ ማግባት ትፈልጋለች፡፡ እናቷ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የአካባቢው ሴት በለጋ ዕድሜያቸው እንደሚያገቡ እሷም ትዳርን ቀስ በቀስ እንደምትለምደው በመግለጽ ሊያግቧቧት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡

የሀና ቤተሰቦች ቤት አቅራቢያ ሦስት ታዳጊዎች ገመድ እየዘለሉ ይጫወታሉ፡፡ ከታዳጊዎቹ አንዷ ገመድ ዝላዩን ታቆምና፤ የሀና ለቅሶ በቅርብ ርቀት እንደሚሰማትና እሷና ጓደኞቿ ሀና እንዳትዳር መርዳት እንዳለባቸው ተናገረች፡፡ ሦስቱ ሴቶች ከመቅፅበት ከመሬት ከፍ ብለው ተሽከረከሩ፡፡ ገመድ ሲዘሉ ለብሰውት የነበረው ልብስ ጥቁር፣ ቀይና አረንጓዴ ጥለት ወዳላቸው ጥበብ ቀሚሶች ተቀየረ፡፡ የታዳጊዎቹ ጥበብ ቀሚሶች ላይ ጥቁር፣ ቀይና አረንጓዴ ካባዎች ተደረቡና ፊታቸው  በጭንብል ተሸፈነ፡፡

 በሰማይ እየበረሩ ሀና ወዳለችበት ቤት አመሩና በድብቅ ይዘዋት ወጡ፡፡ የሀና እናት፣ አያትና የአካባቢው ነዋሪዎች የሦስቱን ታዳጊዎች መምጣት ይጠባበቁ ነበር፡፡ የሀና አያት ‹‹እነዚህ ጥበብ ለባሾች የአገራችንን ወግና ልማድ ለመሻር ስለሚፈልጉ ብዙ ሠርግ አውከዋል፤›› አሉ፡፡ ሦስቱ ታዳጊዎች ሀናን እንደያዙ የብረት አጥር ውስጥ አሰሯቸው፡፡ ከአጥሩ ለማምለጥ ሲፍጨረጨሩ፣ የአካባቢው ነዋሪ ይደሰት ጀመረ፡፡ ከታዳጊዎቹ አንዷ ግን መሬት ውስጥ ለውስጥ ቆፍራ እንዲያመልጡ አደረገች፡፡

- Advertisement -

ይህ ‹‹የጥበብ ልጆች›› ከተሰኘ ተከታታይ የልጆች አኒሜሽን ፊልም የተቀነጨበ ነው፡፡ የሀና ታሪክ የፊልሙ የመጀመሪያ ክፍል (ኤፕሶድ) ሲሆን፣ ያላቻ ጋብቻ ላይ ያተኩራል፡፡ ሦስት ጀግና ሴቶች (ሱፐር ሒሮይንስ) የፊልሙ ዋነኛ ገጸ ባህሪያት ናቸው፡፡ ሴቶቹ ፍቅር፣ ትዕግሥትና ፍትሕ ይባላሉ፡፡ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ የላቀ (ሱፐር ሒውማን) ኃይል አላቸው፡፡ ተከታታይ ፊልሙ በተለያዩ ክፍሎቹ ታዳጊ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች የሚያሳይ ሲሆን፣ በተያያዥ ኮሚክ ቡክ (ከሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ የላቀ ኃይል ስላላቸው ልቦለዳዊ ገጸ ባህሪዎች የሚያትቱ ተከታታይ መጻሕፍት) አለው፡፡ በዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ የተዘጋጀው ፊልምና መጽሐፍ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በጎተ ኢንስቲትዩት (የጀርመን ባህል ማዕከል) ተመርቋል፡፡

የዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ አጋር መሥራች ብሩክታዊት ጥጋቡ ‹‹የጥበብ ልጆች›› አዘጋጅ ናት፡፡ ዊዝ ኪድስ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ልጆች ላይ ያተኮሩ መርሐ ግብሮች የሚያዘጋጅ ድርጅት ሲሆን፣ በተለይም ‹‹ፀሐይ መማር ትወዳለ›› በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን የልጆች ፊልም ይታወቃል፡፡ ‹‹ትንሾቹ መርማሪዎች›› እና ‹‹አሳትፉኝ›› ሌሎቹ የዊዝ ኪድስ ውጤቶች ናቸው፡፡

ብሩክታዊት እንደምትገልጸው፣ ‹‹የጥበብ ልጆች›› የተጠነሰሰው ከሦስት ዓመታት በፊት ወላይታ በነበራት ቆይታ ነው፡፡ ‹‹አሳትፉኝ›› በልጆች የተሠሩ የአንድ ደቂቃ ፊልሞችን የሚያካትት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ወደ ወላይታ ያቀናችው ብሩክታዊት፣ ከአካባቢው ልጆች ጋር መሥራት ነበረባት፡፡ ከልጆቹ መካከል ሴቶቹ ላይ ያተኮረው መርሐ ግብር ነገሮችን በተለየ መንገድ እንድታጤን እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡

በፕሮጀክቱ ከተሳተፉት ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ከስድስተኛ ክፍል በላይ መማር ያልቻሉ ነበሩ፡፡ ያለዕድሜያቸው በመዳራቸው እንዲሁም በቤት ውስጥ የሥራ ጫና ምክንያት በትምህርት መግፋት አልቻሉም፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ ወይም አቅመ ደካማ ቤተሰብ ያላቸው እንስቶችም ይገኙበታል፡፡ በትምህርት የዘለቁት ሴቶችም ልዩ ልዩ ተፅዕኖ ስለሚደርስባቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ ሴቶቹ ለሚገጥሟቸው ችግሮች የመፍትሔ ሐሳቦችን ከባለሙያዎች ጋር እንዲመካከሩ ጥረት መደረጉን ታስታውሳለች፡፡

ሴቶቹ በራሳቸው ጥረት ሊፈቷቸው የሚችሉ ችግሮችን እንዲቀርፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡ እንደ ምሳሌ የምታነሳው የወር አበባ ማየትን የመሰሉና ከዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሰውነት ለውጦችን እንዴት መቀበል እንዳለባቸው ያደረጉትን ውይይት ነው፡፡ በተጨማሪም ያላቻ ጋብቻና ሌሎችም ሕይወታቸው ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ልማዶችን ለማስቆም የሴቶቹ ሚና ምን መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡

ለቀናት በዘለቀው ውይይታቸው ማብቂያ ላይ ሴቶቹ ለብሩክታዊት አንድ ጥያቄ አቀረቡላት፡፡ ጥያቄያቸው በአካባቢው ካሉ ታዳጊዎች ውጪ ላሉ ሴቶች በምን መልኩ ተመሳሳይ ሥልጠና ትሰጪያለሽ? የሚል ነበር፡፡ እንደ ‹‹አሳትፉኝ›› ያለ ፕሮጀክት በአንድ ዙር ሊደርስ የሚችለው ውስን ታዳጊዎችን መሆኑንም ገለጹላት፡፡ ታዳጊዎቹ ከሰነዘሩት ጥያቄ ባሻገር ብሩክታዊትም የታዳጊ ሴቶችን ችግሮች ለመቅረፍ ሙያዊ ምክክር ብቻውን ውጤታማ እንደማይሆን ታምናለች፡፡

‹‹የአካባቢው ሴቶች ከዕድሜያቸው ጋር  በተያያዘ ሰውነታቸው ላይ ለውጥ ሲኖር ቀርበው የሚያማክሩት ሰው ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ያለ ዕድሜያቸው ለጋብቻ ሲሰጡም የሚያስጥላቸው ላይኖር ይችላል፡፡ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚችሉበትን መንገድ የሚያሳያቸውም አያገኙም፡፡ ስለዚህ በልቦለዳዊ መንገድ ስለችግሮቹና መፍትሔዎቻቸው ማስተማር እንደሚቻል አሰብኩ፤›› ትላለች፡፡ ታዳጊዎቹ ከዕድሜያቸው በላይ ከሆኑ ሴት ተምሳሌቶች ይልቅ የዕድሜ እኩዩቻቸው አመለካከታቸውን ለመቀየር ቅርብ እንደሆኑ መገንዘቧንም ታክላለች፡፡

ሦስቱ ልቦለዳዊ ሴት ጀግና ገጸ ባህሪዎች ፍቅር፣ ትዕግሥትና ፍትሕ ሴቶች የለውጥ ኃይል እንዲሆኑ እንደሚያነሳሱ በማመን እንደተፈጠሩ ታስረዳለች፡፡ የመጀመሪያ የፊልሙ ክፍል ላይ ያለችው ሀና ያጋጠማት መሰናክል ያላቻ ጋብቻ ሲሆን፣ በሌሎች የፊልሙና መጽሐፍ ክፍሎች ደግሞ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዩች ይዳሰሳሉ፡፡ ብሩክታዊት እንደምትለው፣ ገጸ ባህሪዎቹ ታዳጊዎች ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትን መንገድ ማመላከት ይችላሉ፡፡ ‹‹ፊልሙ ሴት ልጆች ችግራቸውን መጋፈጥ የሚችሉበትን መንገድ ልቦለዳዊ በሆነ መንገድ ያቀርባል፡፡ ገጸ ባህሪዎቹ ለሴቶቹ ተምሳሌት መሆን ይችላሉ፤›› ትላለች፡፡

ፊልሙ ላይ እንደሚታየው፣ የሀና አያትና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ሦስቱን ሴቶች ‹‹ጥበብ ለባሾች›› ይሏቸዋል፡፡ የአካባቢውን ልማድ የሆነውን ያላቻ ጋብቻ ስለሚከላከሉ አይወዷቸውም፡፡ በአካባቢው ትክክል ነው ተብለው ከሚታመኑ ልማዶች በተቃራኒው ስለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ሴቶቹን ለመግታት ይሞክራሉ፡፡ የፊልሙ ገጸ ባህሪዎች ማኅበረሰቡን ለማሸነፍ ከሰው ተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ኃይሎችን ቢጠቀሙም፣ የቆሙለት ዓላማ ለልጆች ትምህርት ሰጪ እንደሆነ ታምናለች፡፡ ‹‹የጥበብ ልጆች›› የሚለው ስያሜ ለፊልሙ የተሰጠው ከሴቶች ተፈጥሯዊ ባህሪ በመነሳት እንደሆነም ትገልጻለች፡፡ የሴቶችን ብልህነትና ችግርን በጥበብ ፈቺነታቸውን ያመለክታል፡፡ ለአንዳች ችግር መፍትሔ ለመስጠት ሲተባበሩ የሚለብሱት ጥበብ ቀሚስ መሆኑም ለስያሜው መነሻ ሆኗል፡፡

ፍቅር የተባለችው ገጸ ባህሪ ሩህሩህ ስትሆን፣ የሰዎችን ዕጣ ፋንታ ከመፈጠሩ አስቀድሞ የማወቅ ኃይል አላት፡፡  ትዕግሥት እጅግ አዋቂ ስትሆን፣ ማንኛውንም ነገር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍጠር ትችላለች፡፡ ፍትሕ በጣም ጠንካራ ናት፡፡ ከሰው የተፈጥሮ ባህሪ ውጪ የመብረርና በጣም ከባድ ነገሮችን የማንሳት ችሎታ አላት፡፡ ሴቶቹ በተናጠል እንደማንኛውም ታዳጊ ሰዋዊ ባህሪ ያላቸው ሲሆኑ፣ ሲተባበሩ ግን ልዩ ኃይላቸው ይወጣል፡፡ ማንኛዋም ታዳጊ ችግር ሲገጥማት ከመርዳትም ወደ ኃላ አይሉም፡፡

እንደ ብሩክታዊት ገለጻ፣ ‹‹የጥበብ ልጆች›› ሴቶችን ችግር ፈቺ ከማድረግ ጎን ለጎን ወንዶች ስለ ሴቶች ያላቸውን አመለካከት ለማስተካከልም ያለመ ነው፡፡ ወንዶች ሴቶችን እንደ ደካማና ዕርዳታ ፈላጊ እንዳይመለከቱ ስለ ጠንካራ ሴቶች ማወቅ አለባቸው፡፡ ሴቶች ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ የወንዶች ተሳትፎም አስፈላጊ በመሆኑም ወንዶችን ማካተት የግድ ይላል ትላለች፡፡

የፊልሙና መጽሐፉን ተደራሽነት ለማስፋት በተለያዩ ክልል ከተሞች የሚገኙ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የመንግሥትና የግል ተቋሞች ጋር ግንኙነት እንደፈጠሩ ትናገራለች፡፡ ‹‹የጥበብ ልጆች›› የተሰኘ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ የልጆች መርሐ ግብር ይኖራል፡፡ በትምህርት ቤት ወይም መኖሪያ አካባቢ ‹‹የጥበብ ልጆች›› የተሰኘ የታዳጊዎች ክለብ ተቋቁሞ ሴቶች እርስ በርሳቸው የሚወያዩበትን መንገድ የማስፋት ዓላማም አንግቧል፡፡ ‹‹ይህ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ስላለው ችግር ግንዛቤ ያላቸውና ለለውጥ የተዘጋጁ ዜጎች ቀስ በቀስ ለመፍጠር ይረዳል፤›› ትላለች፡፡

‹‹የጥበብ ልጆች›› የመጀመሪያ ክፍል ቀረፃ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የአንድ ሲዝን ታሪክ ደግሞ ተጽፏል፡፡ በአገራችን የመሣሪያና የሰው ኃይል ውስንነት ሳቢያ አኒሜሽን ፊልም መሥራት ቀላል አይደለም፡፡ ብሩክዊትም ይህ ችግር እደተፈታተናት ትገልጻለች፡፡ የፊልሙ የመጀመሪያ ክፍል የተዘጋጀው በኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳና የህንድ አርቲስቶች ነው፡፡ ፊልሙና መጻሕፍቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ጠቃሚ ስለሚሆኑ በእንግሊዝኛ ተርጉሞ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለና በአገር ውስጥም ይሁን በውጪ ‹‹የጥበብ ልጆች››ን ማስተላለፍ የሚፈልጉ ተቋሞች መግዛት የሚችሉበት መንገድ ማመቻቸታቸውን ታክላለች፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...