Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የዚህ ገጠመኝ ጸሐፊ መኖሪያዬ ኮተቤ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ እዚህ ሠፈር ተከራይቼ ከገባሁ አንድ ዓመት አልፎኛል፡፡ የምኖርበት ግቢ የባለንብረቶቹን ጨምሮ ሰባት ቤቶች ይገኙበታል፡፡ የአባወራው ተለቅ ያለ ቪላ ቤትና መደዳውን የተሠሩ ስድስት ባለ ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች ማለት ነው፡፡ ከእኔ በስተቀር ሁሉም ተከራዮች ባለትዳሮች ናቸው፡፡ የእኔ ወንደላጤ መሆን የማይመቻቸው አባወራው ባገኙኝ ቁጥር ማግባት እንዳለብኝ ያስገነዝቡኛል፡፡ እሳቸው ለረጂም ዓመታት በውትድርና ተሰማርተው በየበረሃው ሲንከራተቱ በመኖራቸው፣ ትዳር የመሠረቱት ዘግይተው በመሆኑና ልጆቻቸው በለጋ የወጣትነት ዕድሜ ላይ ስለሚገኙ እንደሚቆጩም ይነግሩኛል፡፡ ለዚህ ነው መሰል በጣም ያቀርቡኛል፡፡

አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ፣ እኔ ደግሞ ወደ መሀል ከተማ ለመሄድ ጉዞ ስጀምር የግቢው በራፍ ላይ ተገናኘን፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ‹‹ልጄ በጠዋት ወዴት ነው?›› አሉኝ፡፡ ከጓደኛዬ ጋር መቀጣጠሬንና ወደ እሱ እየሄደኩ መሆኑን ስነግራቸው፣ ‹‹ጥሩ ነው፡፡ ግን ቀጠሮህ ከሴት ጓደኛህ ጋር ሆኖ ስለትዳር ምሥረታ ብትነጋገር ጥሩ ነበር፡፡ የዘንድሮ ጓደኛ የሚመራው ወደ ጫት፣ መጠጥ፣ አልባሌ ቦታና ዝሙት ነው፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ መያዣ መጨበጫ የሌለው ትርጉም አልባ ወሬ ውስጥ ይዘፍቅህና የሐሜትና የአሉባልታ መደብር ያደርግሃል፡፡ ይልቁንስ አስተዋይ የሆነች ቢጤህን በአስቸኳይ አፈላልገህ ወደ ቁም ነገር ግባ፡፡ ቁም ነገር የሌላቸው ናቸው የትም ባክነው የሚቀሩት፤›› ብለው ከመከሩኝ በኋላ ተሰነባብተን ተለያየን፡፡

ከእሳቸው ከተለየሁ በኋላ ዋናው መንገድ ደርሼ ታክሲ ተሳፈርኩ፡፡ የተቀመጥኩት እናቴ ከሚሆኑ ሴት ጋር ነበር፡፡ ሴትዮዋ ወያላውን፣ ‹‹ምናለበት በነፃ ብትወስደኝ? እናትህ አልሆንም? የዘንድሮ ልጆች ልባችሁ ገንዘብ ላይ ስለሆነ እናት አታውቁ አባት …›› ሲሉ ወያላው ደግሞ፣ ‹‹አይ ማዘር ቀልደኛ ነዎት፡፡ እንደ እርስዎ ዓይነት ስንትና ስንት ማዘሮች ስጭን እየዋልኩ በነፃ ብል ምግብ የለ፣ ልብስ የለ፣ በርጫ የለ፣ …›› እያለ ሳቀ፡፡ ይኼኔ ሴትዮዋ፣ ‹‹በል ተወው፡፡ የእኔ ምርቃት ከምትለው በላይ ነበር…›› ብለው ዝም አሉ፡፡ ይኼኔ የእኔንና የእሳቸውን ጨምሬ ሒሳብ ስከፍል ሴትዮዋ፣ ‹‹ልጄ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ ለእኔ እንደከፈልክ እግዚአብሔር ይክፈልህ፡፡ ዕድሜ ይስጥህ፡፡ ካላገባህ ደግሞ እንደ እናት የምትሆን ሚስት ይስጥህ፤›› ካሉኝ በኋላ ማግባትና አለማግባቴን ጠየቁኝ፡፡ ‹‹አላገባሁም›› ስላቸው፣ ‹‹በል ልጄ ቶሎ ብለህ አግባ፡፡ የትም የባከነ ዕድሜ ትርፉ ኪሳራ ነው …›› እያሉ ስለትዳር መልካምነት ሲዘረዝሩልኝ የአከራዬና የሴትዮዋ አጋጣሚ ገረመኝ፡፡ አንዳንድ ቀናት ይገርማሉ፡፡

እኔና አከራዬ የትዳር ምሥረታ አጀንዳ ሁሌም የምንነጋገርበት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሌሎች ጉዳዮችም ያነጋግሩናል፡፡ እሳቸው በረሃ ለበረሃ ሲያንከራትታቸው የኖረው ረጂሙ የውትድርና ሕይወታቸው ብዙ አስተምሯቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱን ነገር የሚያጤኑት በልዩ ጥንቃቄ ነው፡፡ አንድ ቀን አንደኛው ተከራይ ጎረቤታችን ከሚስቱ ጋር ዱላ ቀረሽ ጠብ ይጨቃጨቃል፡፡ እሱ ጥቅም የሚያገኝበት የትርፍ ሥራ አግኝቶ ለሁለት ቀናት ከአዲስ አበባ ወጣ ማለት ፈልጓል፡፡ እሷ ደግሞ ጊዜው አስተማማኝ ባለመሆኑ ከከተማ መውጣት የለብህም ትለዋለች፡፡ እሱ የአሁኑን አጋጣሚ ካበላሸ ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ዕድሎች እንደሚያመልጡት ይናገራል፡፡ በዚህ የተነሳ ሁለቱ ጥንዶች ኃይለ ቃል ይለዋወጣሉ፡፡ አዛውንቱ ፀብ ለማብረድ ይሄዳሉ፡፡ ሁለቱንም በፅሞና ካዳመጡ በኋላ፣ ከመጨቃጨቅ ይልቅ ዛሬም ሆነ ነገ የሚገኘው ጥቅም በሕይወታቸው ላይ የሚያመጣውን ለውጥ መመዘን እንጂ፣ ጩኸት ፋይዳ እንደሌለው አስረድተው ሰላም አሰፈኑ፡፡ የሚገኘው ጥቅም ፋይዳ ያን ያህል ባለመሆኑ በመግባባት ጉዞው ተሰረዘ፡፡

ይህንን ጉዳይ አስመልክተው ሲያስረዱኝ፣ ‹‹ልጄ በትዳር መሀል ጭቅጭቅ ይኖራል፡፡ ተገቢም ነው፡፡ ጭቅጭቁ ግን ብልኃት ከታከለበት ይረግባል፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሳይሆን የጋራ ድል የሚገኝበት ነው፡፡ ትዳርን በአገር ብትመስለው የጋራ የሆነ መግባባት ከሌለ ጥሩ አይሆንም፡፡ ባል ጉልበተኛ፣ ጠጪ፣ አመንዝራ፣ አባካኝና ግዴለሽ ከሆነ ለሚስት በጣም ከባድ ይሆናል፡፡ ሚስትም በተመሳሳይ አጥፊ ከሆነች ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ አገርም የሚያስተዳድሯት ሥርዓት ከሌላቸው፣ አንዱን ከሌላው ካበላለጡ፣ ፍትሕ ካዛቡ፣ ሕዝብ ካንገላቱና ችግር ከፈጠሩ አገር ትበላሻለች፡፡ ልጄ ትዳርን ስታስብ በመከባበርና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ተቋም መሆኑን ተገንዘብ፡፡ ትዳርንም አገርንም እንዲህ ካላሰቡ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም…›› ሲሉኝ ዕድሜ እንዴት የሰውን ልጅ በሳል እንደሚያደርግ ተገነዘብኩ፡፡

እኚህ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ አዛውንት ማንኛውንም ወሬ ሲሰሙ ማጣራት ይወዳሉ፡፡ መቼ? የት? ለምን? እንዴት? ወዘተ. ካላሉ በስተቀር የሚነገራቸውን ማዳመጥ አይፈልጉም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ በመማር ላይ የሚገኙት አራቱ በላይ በላይ የተወለዱ ልጆቻቸው ከአባታቸው ጋር ሐሳብ የሚለዋወጡት ለሚቀርቡላቸው የአፀፋ ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆቹ በጣም ጎበዝ ተማሪዎች ከመሆናቸውም በላይ፣ አስተሳሰባቸው ከዕድሜያቸው በላይ ነው፡፡ በጣም አንባቢና ጠያቂ በመሆናቸውም ዕውቀታቸው የደረሰበት ደረጃ አስደናቂ ነው፡፡ በፌስቡክም ሆነ በተለያዩ መንገዶች የሚሰሙዋቸውን መረጃዎች ከሥር መሠረታቸው ሳያጣሩ አይቀበሉም፡፡ አባትየው እንደነገሩኝ ከሆነ፣ ያልተጣራ መረጃ በራስ ሕይወት ላይ የተሳሳተ ውሳኔ ለማስተላለፍ መንስዔ ስለሚሆን ማጣራት ተገቢ ነው፡፡ የሰሙትን ወሬ እንደ ወረደ ለሌላው ማስተላለፍ ዋሾ ያደርጋልም ይላሉ፡፡ ‹‹ዘጠኝ ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ›› የሚሉት አባባልም አላቸው፡፡

በቀደም ዕለት በየቦታው የሚሰሙት ወሬ የሆነ ጥርጣሬ ፈጥሮባቸዋል መሰል ስልካቸውን ያወጡና የሆነ ቦታ ይደውላሉ፡፡ ተነጋግረው ይጨርሱና ከዚያም እየደጋገሙ እስኪበቃቸው ደውለው ከተለያዩ ሰዎች ጋር ካወሩ በኋላ ይጠሩኛል፡፡ ‹‹ልጄ አገር እኮ ባልተጣራ ወሬ ሊፈርስ ነው፡፡ ሁሉም እየተቀባበለ የሚያወራው ያልተጣራ ወሬ ስለሆነ ሰው ይሞታል፣ ንብረት ይወድማል፡፡ ፖለቲካ ያልገባቸው ለጋ ልጆች ሳያውቁት የጥፋት መሣሪያ ይሆናሉ፡፡ ዘመነ ቀይ ሽብርንና ነጭ ሽብርን ያላየ ትውልድ የዚያ ቂመኛ ትውልድ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ ያንገበግበኛል፡፡ አዲሱ ትውልድ በሠለጠነ መንገድ ሁሉም ነገር ገብቶት ዓላማውን ማስፈጸም ሲችል፣ የጥፋት መሣሪያ ሆኖ አገሩን እንዳያወድማት እሠጋለሁ…›› እያሉ ተብሰለሰሉ፡፡ እየፈራሁ እየተባሁ፣ ‹‹ብሶት ይሆናል እኮ ትውልዱን ነውጠኛ ያደረገው?›› ስላቸው፣ ‹‹ማን ብሶት የለም አለ? መጠየቅና መሞገት በቅጡ የማያውቅ፣ የሚነገረውን ሳያጣራ እንደወረደ የሚቀበል ማኅበረሰብ ያፈራው ትውልድ ግብታዊ ሲሆን ነው አደጋው፤›› አሉኝ፡፡ ‹‹አዎን ግብታዊነትና ስሜታዊነት ባልተረጋገጡ ወሬዎች ሲታጀሉ ያስፈራሉ፡፡ አገርም ትዳርም የሚፈርሱት እንዲህ ነው፤›› ብለውኝ እኔም ከስሜታዊነት እንድርቅ ጠየቁኝ፡፡ ወገኖቼ መካሪ አያሳጣችሁ፡፡ (ቢንያም አስረስ፣ ከኮተቤ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...