Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየንግድ ምክር ቤቱ ባለቤት ማን ነው?

የንግድ ምክር ቤቱ ባለቤት ማን ነው?

ቀን:

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ህልውናውን እንደ አዲስ ሲያረጋግጥ ለ54 ዓመታት የከተማውን የንግድ ኅብረተሰብ በማገልገል ነበር፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ28 ያላነሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔዎችን አካሂዶ እንደነበር ስለምክር ቤቱ የተጻፉ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ የቀድሞዎቹ ጠቅላላ ጉባዔዎች በንግድ ኅብረተሰቡ ዘንድ ጉልህ ተሳትፎ ሲንፀባረቅባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በውጤታቸውም የጉባዔዎቹ ባለቤት የሆነውን የአዲስ አበባ ንግድ ኅብረተሰብ ብቻም ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የንግድ ኅብረተሰብ በመወከል ላከናወናቸው ተጨባጭ ሥራዎች በመላው ኅብረተሰብ ዘንድ አድናቆት ይቸረው እንደነበር እስከ ዛሬ ይታወሳል፡፡

በእነዚህ ጠቅላላ ጉባዔዎች አማካይነት በየሁለት ዓመቱ በሚደረጉ የአመራር አባላት ምርጫዎች ወደ ኃላፊነቱ ቦታዎች የወጡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ለምክር ቤቱ ባበረከቱት ጥረት በነበረው የአመራር ብቃታቸው ምክር ቤቱን ከአገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃም ታዋቂና ዝነኛም እንዲሆን አብቅተውት ነበር፡፡

ምክር ቤቱን ለዚህ መሰል ጥንካሬና ብቃት ካበቁት ዓበይት ምክንያቶች መካከል በዘመኑ የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጥንካሬ ሲሆን፣ ይህም የሥራ ብቃትን ከጥሩ ሥነ ምግባር ጋር በማዋሃድ ሲያገለግሉ የነበሩ ዋና ጸሐፊዎች፣ የልዩ ልዩ ክፍል ኃላፊዎችና መላው ሠራተኞች የቀጠራቸውን ንግድ ኅብረተሰብ ጥቅም ከማስከበር ባሻገር የንግዱን ኅብረተሰብ አገራዊ የልማትና የማኅበራዊ ኃላፊነት ሚና ጐልቶ እንዲወጣ ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረት የንግድ ምክር ቤቱን መልካም ስምና ዝና በአያሌው ከማሳደጋቸውም በላይ ተወዳጅነትን እንዲያርፍ አብቅተውት ነበር፡፡

ዛሬ ወደ ምክር ቤቱ ማዕከል ጐራ ብሎ በዘመኑ ይከናወኑ የነበሩ ጠቅላላ ጉባዔዎችን፣ ይወጥኑና ይተገበሩ የነበሩ ሥራዎችን፣ ይዘጋጁና ይካሄዱ የነበሩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን፣ አመራር ይሰጡ የነበሩ ፕሬዚዳንቶችን፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችንና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን በየዓመቱ ወደ ውጭ አገሮች ለንግድ ጉብኝት የሚልኳቸው አባላቱንና የሚያስተናግዳቸውን የውጭ አገሮች የንግድ ልዑካን ብዛትን፣ ከንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊ ጋር በንግድ ግንኙነት ዙሪያ ለመነጋገር ቀጠሮ እያስያዙ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ይጐርፉ የነበሩ የየአገሩ ኤምባሲ ተወካዮችን ዝርዝር የሚያሳዩ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ ሪፖርቶች፣ ሳምንታዊ የውስጥ ዜናዎችን ወዘተ በመመልከት ስለ ንግድ ምክር ቤቱ የተባለው ሁሉ ማጋነን ያልታከለበት እውነት መሆኑን ሊገንዘብ ይችላል፡፡

ከሃምሳ አራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ምክር ቤቱ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሚል ስያሜ መንቀሳቀስ ጀምሮ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ ካደረገበት ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ቀደምት መገለጫ ባህርያቱ ትዝታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ቀድሞ ብቃት ያላቸው የንግድ ኅብረተሰብ መሪዎች ወደ ምክር ቤቱ አመራርነት ለማምጣት በዕጩዎች አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አማካይነት ከፍተኛ የማግባባትና የማሳመን ሥራ ይካሄድ ነበር፡፡ በዚህ እልህ አስጨራሽ ልመናና ውትወታ አማካይነት ወደ አመራሩ የሚመጡ ፕሬዚዳንቶችና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የተረከቡትን ኃላፊነት የሚቀበሉት ለሁለት ዓመት ብቻ ሲሆን ለዚህ ጊዜ ብቻ እንደሚያገለግሉ ቅድም ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ነበር የሚመጡት፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ልመናና ተጽእኖ ለሁለተኛ የአመራር ዘመን ከደረሱ ጥቂት ፕሬዚዳንቶች በስተቀር ሁሉም የምርጫ ዘመናቸውን እንደጨረሱ በሌሎች ይተኩ ነበር፡፡ ዛሬ እንዲህ ዓይነቱ ነገር የማይታሰብ ሲሆን፣ የአሁኖቹ ከጠቅላላ ጉባዔዎች ዋዜማ እስከ ፍጻሜ ድረስ በሴራ፣ በዱለታ በአምባጓሮና በግብግብ ታጅበው የሚመረጡ ሥልጣን የሚይዙ ሆነዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በጠቅላላ ጉባዔዎች ወቅት የሚታተሙ ጋዜጦች ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው፡፡

አዲሱ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ለምክር ቤቶች አደረጃጀት የፈጠረውን የውክልና ቀመር አሠራር ክፍተት መጠቀሚያ በማድረግ፣ ዛሬ ወደ ምክር ቤት አመራር የሚወጣ የምክር ቤት መሪ ከአንዱ ምክር ቤት ወደ ሌላኛው ቦታውን እየለዋወጠ ከአሥር ዓመታት በላይ በአመራር ቦታ ላይ ተቀምጦ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡ የንግድ ኩባንያዎችን ወክለው ወደ አመራር ቦታ የወጡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትም ቢሆኑ እንደ ቀድሞዎቹ ‹‹ሁለት ዓመት ካገለገለን በቃን፤ ምክር ቤታችን የተሻሉ አመራር አባላትን ይጠይቃልና ልቀቁን፤›› የሚሉ ሳይሆኑ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ዕድሜና ተጠቃሚነታቸውን ለማራዘም የሚታገሉ እንደሆኑ ሥራዎቻቸው እየመሰከሩ ነው፡፡

ቀድሞ የጠቅላላ ጉባዔዎች ጥሪ ሲደርሳቸው ቢያንስ ከ800 እስከ 1000 የሚሆኑ አባላት ታላላቅ አዳራሾችን እያጨናነቁ በየጉባዔዎች የጎላ ተሳትፎ ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም አዳራሾች በመሙላታቸው የተነሳ ለጉባዔዎች ካላቸው ጉጉትና ፍላጎት ቆመው ሲሳተፉ ማየትም የተለመደ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ደግሞ በአድራሽ ጥበት የተነሳ ወደ የመጡበት ለመመለስ ይገደዱ ነበር፡፡ ዛሬ በአዋጁ ክፍተት እንዲሁም ለጠቅላላ ጉባዔዎች ውክልና ተዘጋጀ የተባለውን አወዛጋቢ ቀመር ተጠቅሞ እንኳ 500 የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊዎችን መጥራትና ማሰባሰብ ከባድ ፈተና ሆኗል፡፡ በቀመሩ መሠረት የንግድ ኩባንያዎች ለጉባዔው መላክ የሚገባቸው ከ300 የማይበልጥ ተሳታፊ ቢሆንም፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ነው ከሚባለው የአባላት ቁጥር መካከል ይህን አነስተኛ የተወካይ መጠን ማሰባሰብ አለመቻሉ ውክልናው የሚሟላው የዘርፍ ማኅበሩ ከቀመር በላይ በሚያቀርበው ተሳታፊ፣ ይህም አልሆን ሲል የሁለቱም ምክር ቤቶች አባል ያልሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ መስክ የተሰማሩ አባላትን ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ጋብዞ የተድበሰበሰ ምልዓተ ጉባዔ በመፍጠር እንደሆነ ሲነገር ይደመጣል፡፡

ለቀድሞው የንግድ ምክር ቤት ጥንካሬ ጽሕፈት ቤቱ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበረው ሁሉ አሁን ለሚታየው ሚናውም ሆነ ደረጃው እያሽቆለቆለ ለሚገኘው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውድቀት ወቅታዊ የጽሕፈት ቤቱ አመራር ድርሻው ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል እየተባለ ይነገራል፡፡ የቀድሞ የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት በአደረጃጀቱ፣ በአቋሙም ሆነ በሥራ አፈጻጸሙ በአገሪቱ ውስጥ ግንባር ቀደም ከሆኑት ተርታ የሚቀመጥ እንደነበር ታሪክ ይመሰክርለታል፡፡ የዕለት ከዕለት ሥራዎቹ የሚመሩት በሥራ መመርያዎች ነበር፡፡ የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣ የዕቃዎች ግዢ፣ የንብረት አስተዳደርና አወጋገድ ወዘተ. መመርያዎችን ተከትሎ ይሠራ ነበር፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ዋና ጸሐፊዎች መልካም ሥነ ምግባር የተላበሱ፣ ሥራቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በሰከነና በረቀቀ መንገድ በብቃት በማከናወን ለዳይሬክተሮች ቦርድ ድጋፍ፣ ለንግድ ኅብረተሰቡም መመኪያና ኩራት ሆነው ማለፋቸው አሁንም ድረስ ይነገርላቸዋል፡፡ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አውታሮች ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቶች ወይም በዋና ጸሐፊዎች አማካይነት ስለምክር ቤቱ ተግባርና ገድል ሳይወሳ የሚታለፍበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ዛሬ በዜና ማሰራጫዎች ስለንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ የምንሰማው በጐ ነገር እምብዛም ነው፡፡ ተዘውትሮ ሲነገርና ሲዘገብ የሚሰማው መበጣበጡ፣ ሕገወጥ ጠቅላላ ጉባዔ መካሄዱን ነው፡፡ ለዚህ ተጠያቂው እገሌ ነው እየተባባሉ መወነጃጀል የተለመደ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከመነሻው ጀምሮ በጥንቃቄና በትጋት የጠቅላላ ጉባዔውን ፕሮግራም በመምራት ለስኬት ማብቃት የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ኃላፊነትና ድርሻ ነበር፡፡ የችግሩ ባለቤት፣ ዋና ጠንሳሽና ተጠያቂ ተደርጐ የሚቀርበው ዋና ጸሐፊው እንደሆነ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች  ከሚያቀርቧቸው ነጥቦች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ በሚዲያዎች ጠያቂነት ወይም በምክር ቤቱ ተነሳሽነት አልፎ አልፎ የሚደመጡ የንግድ ምክር ቤት ዜናዎች ቢኖሩም እውነተኛና ተዓማኒነት ያላቸውን ጉዳዮች ከማቅረብ ይልቅ፣ ፍላጐት ወይም ምኞት ላይ የተንጠለጠሉ፣ ከሀቅ የራቁ መረጃዎች ሲቀርቡ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ የካቲት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፣ ምክር ቤቱ በየሩብ ዓመቱ 800 ነጋዴዎችን በአባልነት ይመዘግባል ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ዓይነቱን ከእውነት የራቀ መረጃ ከየት አግኝተው ሊሰጡ ቻሉ? ለመሆኑ በዓመቱስ 1000 የሚሞላ አባል ይገኛልን?

የኑሮ ውድነትን፣ የመዋቅር ማሻሻልንና አዲስ የሥራ መርሐ ግብርን መነሻ በማድረግ የሥራ ምደባና የደመወዝ ዕድገት የተለመደ የመሥሪያ ቤቶች አሠራር ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤትም ዘንድ ከቀድሞ ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ አልፏል፡፡ ልዩነቱ ቀድሞ ይደረግ የነበረው የደመወዝ ጭማሪ በዝቀተኛ የደመወዝ እርከን ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን ዒላማ ያደረገ፣ ፍትሐዊነትን የተከተለ ሲሆን፣ አሁን ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ግን በዋነኛነት የዋና ጸሐፊውን ደመወዝ በወር ከ12 ብር ሺሕ ወደ 38 ሺሕ በማሳደግ ሠራተኛውን ጉድ ያሰኘ የደመወዝ ጭማሪ የተደረበት ነው፡፡ ለመሆኑ በሥራ ላይ ያለው ቦርድ በኑሮ ውድነት እየተሰበሰበ የሚቀርቡለትን የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄዎች ከማጽደቅ ባለፈ ፍትኃዊ የደመወዝ ዕድገት ስለመደረጉ ይከታተላልን?

አሁን ያለውን አሠራር በተቆርቋሪነት ስሜት የሚታዘቡ ሰዎች ሲናገሩ እንደሚደመጠው፣ ቀድሞ በየሳምንቱ ይካሄዱ የነበሩ የማኔጅመንት ስብሰባዎች ዛሬ የሉም፡፡ ካሉም ለስብሰባዎቹ የሚቀረጽ አጀንዳም ሆነ የሚያዝ የስብሰባ ቃለ ጉባዔ የለም፡፡ ቀደም ባሉት አሠራሮች በጽሕፈት ቤቱ በኩል የሚፈጸም የሠራተኛ ቅጥርን አስመልክቶ መመርያ ይተገበር ነበር፡፡ መመርያው ያልተሻረ ቢሆንም፣ የሚመለከታቸው ክፍሎች በመመርያው መሠረት ለመሥራት ደፋ ቀና ቢሉም፣ በጣልቃ ገብነትና በወገናዊ አሠራሮች ምክንያት ድካማቸው ከንቱ እንደሚቀር ይነገራል፡፡

የምክር ቤቱ ሠራተኞች የጡረታ መመርያ ወጥቶ ተፈጻሚ መሆን ከጀመረ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ረገድም ቢሆን ጣልቃ እየገቡ የራሳቸው ደጋፊዎች ያልሆኑትን ወዲያው እያስወጡ ‹‹ደጋፊዎች›› ለተባሉትም በያመቱ ኮንትራታቸው እየታደሰ ለዓመታት ጡረታቸው እንዲራዘምላቸው እየተደረገ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ‹‹ደጋፊና ደጋፊ ያልሆኑ›› እየተባለ የሚደረገው የሠራተኛ ፍረጃ በጡረታ ጊዜ ማራዘም ጉዳይ ላይ እንደ ምሳሌ ተጠቀሰ እንጂ ለዕድገት፣ ለደመወዝ ጭማሪ ለውጭ አገር ጉዞ፣ ለሥልጠናና ለመሳሰሉት ሁሉ እንደ መስፈርት ሆኖ እንደሚሠራበት የሚያመለክቱ ትዝብቶች ቢኖሩም፣ የምክር ቤቱ ጸሐፊ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ 12 ብር ሺሕ ደመወዝ ሲያገኙ የነበሩት ጸሐፊ አሁን ላይ ደመወዛቸው 38 ሺሕ ብር እንዲሆን ሲደረግ፣ በዚያው ልክ ለጽሕፈት ቤቱ ትጉና ተቆርቋሪ የሆኑ ሠራተኞች መርሳታቸው ግን አሳዛኝ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱን በዋናነት የሚመራው ቦርድም ይኼንን የመዋቅርና የደመወዝ ማስተካከያ እንዲህ ከፍተኛ ርቀት በተስተዋለበትና እሱ ካሳለፈው ውሳኔ ውጭ ዋና በታች ያሉ ኃላፊዎች ቆራጭ ፈላጭ በሆነ አሠራራቸው ይኼ ለእኔ ይጠቅመኛል፣ ይኼኛው አይጠቅመኝም በሚል ኋላ ቀር አሠራር እንደፈለጋቸው ሲሠሩ የቦርዱ ምላሽ ምን ነበር?

እውነታው የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ባለባቸው ኃላፊነት ለንግዱ ኅብረተሰብ የሚጠቅሙ መረጃዎችን እየሰጡ ነው ወይ? የንግዱን ኅብረተሰብ ወክለው በየስብሰባዎች እየተገኙ ነው ወይ? መንግሥት የንግዱን ኅብረተሰብ የሚመለከት ጥሪ ሲያደረግ፣ በስብሰባ ላይ ተገኝተው ሌላው ቢቀር ሐሳብ ሰጥተው ያውቃሉን ወይ? በእነዚህ ጥያቄዎች መፈተሽ ይገባቸዋል፡፡

ምንም ቢሆን ቀደም ሲል የነበሩትን የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊዎች ምን ሠርተው እንዳለፉና ቤቱ በጣም ጥሩ የሥራ ቤት እንደነበረ ከሠሯቸው ሥራዎችና ሰነዶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁን ያሉት ኃላፊዎች ሁልጊዜም ሲሉ እንደሚሰማው የቀድሞውን የምክር ቤቱን ታሪክ መስማት አይፈልጉም፡፡ በስብሰባ ወቅት ጥሩ ሐሳብ ሲቀርብ ይኼ የዱሮ አሠራር ነው በማለት የሚያጣጥሉ ከመሆን አልፈው ስህተቶች በወቅቱ መታረም ስለማይታረሙ፣ የምክር ቤቱ ዕድገት እየወረደ መሄዱን ቀጥሏል፡፡

የምክር ቤቱን ፋይናንስ እንቅስቃሴም በተመለከተ የሚነገሩ ነገሮች አሉ፡፡ ገንዘብ ከፋይናንስ መመሪያ ውጪ እየታዘዘ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ሲነገር እንደሚሰማው የቀድሞ የፋይናንስ መመርያ ኃላፊዎች ሕገወጥ መመርያ አናስፈጽምም በማለት ሥራቸውን ለቀዋል፡፡ አሁን ግን ባልተሟላ ሰነድና የጽሕፈት ቤቱን የፋይናንስ ደንብ ባልጠበቀ አሠራር ከጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ወጪዎች በዘፈቀደ እንዲወጡ ከማድረጋቸው በተለያዩ ጊዜያት እንዲያስተካክሉ በሚመለከታቸው ወገኖች ቢገለጽላቸውም ከድርጊታቸው ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዞዎችን በተመለከተ ጋባዥ አገሮች ወጪዎችን ችለው ግብዣውን የሚያቀርቡ ሆኖ ሳለ፣  ጽሕፈት ቤቱ ወጪያቸውን እንደቻለ በማስመሰል በምክር ቤቱ ገንዘብ ያለአግባብ እንደሚጠቀሙ ይነገራል፡፡

በዚህ መልኩ የሚታየውን አሠራር ለማስተካከል ካልተቻለ ፍርዱን ለንግዱ ኅብረተሰብና በአዋጅ ላቋቋመው የመንግሥት አካል እንተወዋለን፡፡

(ከተቆርቋሪ)   

* * *

መንግሥት በቢሾፍቱ ደረሰውን አደጋ ማስቀረት ይቻለው ነበር

መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የኢሬቻን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡት ዜጎች ላይ የደረሰውን የሞትና የአካል ጉዳት በተባለው መጠን እንዳይሆን ለመከላከል፣ ከአዲስ አበባ የእሳት አደጋ መኪናና በዋና የሠለጠኑ አባላቱ መጠራት ነበረባቸው፡፡ በሌላው ዓለም እንደምናየው የመከላከያ ሄሊኮፕተር ወረቀት መበተን ብቻም ሳይሆን በገመድ ተጎጂዎች እያገዘ የሕይወት አድን ሥራ መሥራት ነበረበት፡፡

የክልሉ መንግሥት በያመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሚሰባሰብበትን ቦታ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብሎ ቀድሞ በማሰብ ገደላማውንና ጥልቅ ጉድጓድ ያለበትን አካባቢ በመሙላት አደጋውን ማስቀረበት ይገባው ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ቢሆኑ የአደጋ ጊዜ ተከላካዮች እንዲገኙ ጥሪ ማድረግ ነበረባቸው፡፡

ስለዚህ ለወደፊቱም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይርስ የክልሉ መንግሥት የአደጋ ማገጃ መከላከያ ግንብ በመገንባት፣ ጉድጓዶችንና ረግረጋማ ቦታዎችን በማተካከል በተቻለው መጠን አደጋ እንዳይፈጠር በመሥራት ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የመጠበቅና የማዳን ሥራን ይሥራ፡፡

(በላይ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...