Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ሕግ በወፍ በረር ሲታይ

የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ሕግ በወፍ በረር ሲታይ

ቀን:

   በውብሸት ሙላት

ለጋራ ደኅንነት አስፈላጊ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ አንዱ ፖሊስ ነው፡፡ በነፃነት ሰበብ የሌሎችን መብት እንዳንገፋ ጥበቃ ያደርጋል፤ ወንጀልን ይከላከላል፡፡ ፖሊስ፣ የሌሎች ግለሰቦችን ወይንም የወል ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ አገር፣ መንግሥት፣ መሥሪያ ቤቶች የመሳሰሉት ተቋማትን ላይ ጉዳት ሲደርስ የጉዳት አድራሹን ማንነትና የድርጊቱን አፈጻጸም የሚያሳይ ማስረጃ ያፈላልጋል፤ ወይንም የወንጀል ምርመራ ያደርጋል፡፡ ፖሊስ እንደ ተቋም ተልዕኮዎቹ እነዚህ ሁለቱ ወንጀል መከላከልና ምርመራ ናቸው፡፡ 

ወንጀልን የመከላከልም ይሁን የምርመራ ሥራ በባሕርይው የግለሰቦችን መብት ለመጣስ የተመቻቸና የተጋለጠ ነው፡፡ ስለሆነም የግል ነፃነታችንን ሊጋፋ የሚችል ተቋም ቢሆንም እንኳን የጋራ ደኅንነታችን ካልተጠበቀ መልሶ የግል ነፃነታችን ስለሚጣስ እኩይነት ቢጣባውም አማራጭ የሌለው አስፈላጊ ተቋም ነው፡፡ የፖሊሳዊ ሥራ፣ ከላይ እንደተገለጸው አስፈላጊ ቢሆንም የሰብዓዊ መብት ለመጣስ የተጋለጠ ስለሆነ፣ አገሮች በተናጠል ለራሳቸው ብሎም በጋራ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሠራሩን ለማቅናት ሲሉ በርካታ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ የፖሊስ ምልመላ ለማድረግ ጥብቅ መሥፈርቶችን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም ለምልመላ ያመለከተውን ሰው ባሕርዩንና ሰብዕናውን በጥልቅ ለመረዳት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ምልመላው ላይ ይሳተፋሉ፡፡ እንዲህ ከሆነም በኋላ ወንጀል በመከላከልም ይሁን ምርመራ ወቅት የሰብዓዊ መብትን እንዳይጥሱ በቂ ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እንደ ሌሎች ሙያዎችም የፖሊስ የሥነ ምግባር ደንቦችም አሉ፡፡ በርካታ አገሮች የሥነ ምግባር ደንቦቹ በትክክል መተግበራቸውን የሚከታተል በፖሊስ ተቋሙ ውስጥ ሆነ ውጭ የሚገኙ ተቋማትና አሠራር ዘርግተዋል፡፡ አንድ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ዳኛ  ወይም ሌላ ባለሙያ የሙያውን ሥነ ምግባር የሚተላለፍ አድራጎት ከፈጸመ እንደሚጠየቀው ሁሉ ፖሊስም በወንጀል፣ በዲስፕሊንና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂና ኃላፊነት ሊኖርበት ስለሚገባ ይኼው አካሄድ እየዳበረ ስለመሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የመረጃ ነፃነት እንደ ልብ በሚገኝባቸው አገሮች፣ ፖሊስ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ተጠቅሞ ጉዳት ሲያደርስ ትልቅ አጀንዳ እንደሚሆን በየቀኑ እያየን ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቱ ማንኛውንም መረጃ ምሥጥራዊ የማድረግ ባህል በተጠናዎታቸው አገሮች ደግሞ፣ ግለሰቦች ፖሊስ ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢያደርሱ ዜና ሊሆን ይችል እንደሁ እንጂ ፖሊስ ግለሰቦች ላይ አረመኔያዊ የሚባል ተግባር ቢፈጽም እንኳን የመንግሥት ተቋማት ከቻሉ መረጃውን ያፍኑታል፤ ወይንም ደግሞ ድርጊቱ ተገቢ መሆኑን የሚያስረዳ ምክንያት ይፈጥሩለታል፡፡

በቅርቡ አልጀዚራ በሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አንድ መሬት ላይ የወደቀን ሠልፈኛ ፖሊስ በርግጫ ከአንገቱ በላይ ሲመታው አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ ልጇን የገደለባት እናት አስከሬኑ ላይ እንድትቀመጥ መደረጓን ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ሰምተናል፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በነበሩ ተቃውሞና ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና የአካል ጉዳት መድረሱን መንግሥታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረበበት ጊዜ ፖሊስ በኦሮሚያ የተጠቀመው ኃይል ተመጣጣኝ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ግን እንደነበር ሰምተናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የተወሰኑ ድምፃዊያን የአገራችን ፖሊስ እየወሰደ ያለው የኃይል ዕርምጃ ተገቢ ስላልሆነ እንዲታረም የሚገልጹ ዘፈኖችን አሰምተዋል፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የፖሊስ የኃይል አጠቃቀምን ከሕግ አንፃር መፈተሽ ነው፡፡ ስለሆነም ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ሰነዶችን፣ ሕገ መንግሥቱን፣ ከፖሊስ ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሕጎችና ንድፈ ሐሳቦችን ዋቢ በማድረግ የሚፈቀድ የኃይል አጠቃቀምን ካልተፈቀደው ለመለየት ጥረት ይደረጋል፡፡ ፖሊስ ሕገወጥ  የሆነ ኃይል ሲጠቀም ምን መደረግ እንዳለበት ጥቆማ ያቀርባል፡፡

የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ሲባል

ፖሊስ መደበኛ ተግባሩን በሚያከናውንበት ወቅት ኃይል የሚጠቀምባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ በዋናነት ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተጠረጠረው ሰው ላለመያዝ ኃይል የሚጠቀም ከሆነ፣ ሊያዝ ሲልም ሆነ ከተያዘ በኋለ ለማምለጥ ሲሞክር፣ ወንጀሉ እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ድርጊቱን ካላቆመ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ የሚያስችለውን ያህል ኃይል መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ላለመያዝ ያልሞከረን፣ የማምለጥ ድርጊት ውስጥ ያልገባን፣ የተያዘ ተጠርጣሪ ላይ ኃይል መጠቀም የፖሊሳዊ ሥራን ግብ ለማሳካት ጥቅም የለው፡፡

አሜሪካን አገር የሚገኝ ስለፖሊስ ጥናት በማድረግ የሚታወቅ አንድ ተቋም በያዝነው ዓመት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ ፖሊስ እንደ ተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ መከተል ያለባቸውን 30 መርሆች አሰባስቦ አሳውቋል፡፡ እነዚህን መርሆች የተለያዩ ስለዘርፉ ከተዘጋጁ ድርሳናትም ከሚጠቅሷቸው ንድፈ ሐሳቦች ጋር በማጣጣም ለአራት በመክፈል እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የመጀመሪያ የሰውን ልጅ ሕይወት ክቡርነት መቼም ቢሆን መቼ ማዕከል ማድረግ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፖሊስ በወንጀል መከላከል ሰበብ ሕይወት እንዳያጠፋ፣ የአካል ጉዳት እንዳያደርስ ጥብቅና የዳበሩ ተቋማዊ የኃይል አጠቃቀም መሥፈርቶችን ማበጀት ይመለከታል፡፡ እነዚህ መሥፈርቶችም በትክክል መተግበራቸውን መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ፖሊስ ኃይል ሲጠቀም ሁልጊዜም ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡  

የተወሰኑት መርሆች የሚጠነጥኑት ደግሞ፣ ፖሊስ ኃይል ከመጠቀሙ በፊትና በኋላ ማድረግ ባለበት ዙሪያ ነው፡፡ ፖሊስ ኃይል ከመጠቀሙ በፊት አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ይሄውም ኃይል መጠቀሙ ግጭትን የማያባብስ ስለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና ሠልፍ በሚኖርበት ወቅት በጥብቅ መፈጸም ያለበት አሠራር እንደሆነ ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ፖሊስ የሚወስደው የኃይል ዕርምጃ መረጃ ላይ የተመሠረተ፣ በቦታው ላይ የተከሰቱ ሁኔታዎችን፣ ሥጋቶችንና አደጋዎችን በመገምገም ሌሎች አማራጮችን አለመኖራቸውን አረጋግጦ ነው፡፡ ፖሊስ በተጠቀመው ኃይል ምክንያት ጉዳት ከደረሰም የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ዕርዳታ መስጠት ብሎም በአፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ከእዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ፖሊስ ተገቢ ያልሆነ ኃይል ሲጠቀም ሌላ ፖሊስ ካለ ጣልቃ የመግባት አሠራርን አገሮች ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ጣልቃ ሳይገባ፣ ምን አገባኝ የሚልን ፖሊስ ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡

በሦስተኛነት የሚገኙት ፖሊስ የሚጠቀማቸው መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ፖሊስ ሥራውን በአግባቡ እንዲወጣ ብሎም ተጠርጣሪን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ መሣሪዎችን መጠቀም አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ ተሽከርካሪም (ከተሽከርካሪው ውስጥ ተኩስ የሚከፈት ካልሆነ በስተቀር) ይሁን ተሽከርካሪ ላይ ሆኖ መተኮስ ተገቢ አይደለም፡፡ ዘመናዊና በተቻለ መጠን ጉዳታቸው ዝቅተኛ የሆኑ መሣሪያዎችን፤ ለአብነት ወደ ሰው ግንባር ሲረጩ ተጠርጣሪዎችን ለተወሰኑ ደቂቃ ራሱን እንዳይቆጣጠር የሚያደርጉ ኬሚካሎች መጠቀም አለባቸው፡፡ እነዚህ በበርካታ አገሮች በየሱቁ የሚገኙ ርካሽና በኪስ የሚያዙ፣ በተለይ ሴቶች ከአስገድዶ መደፈር ሙከራ የሚከላከሉባቸው ናቸው፡፡ ሠልፍና ተቃውሞ በሚኖርበት ወቅት የሚሰማሩት ፖሊሶች ራሳቸውን መከላከያ ጋሻ ሊጠቀሙ ግድ ነው፡፡ የኃይል አጠቃቀሙም መለካት ያለበት ከዚህ አንፃርም ጭምር መሆን አለበት፡፡ ጋሻ ላልያዘ ፖሊስ፣ ሠልፈኛ ድንጋይ ቢወረውርበት ሊገድለው ስለሚችል ፖሊስ ሽጉጥ ወይንም ሌላ የሚተኮስ መሣሪያ ሊጠቀም ስለሚችል ጉዳቱ  ይጨምራል፡፡ ጋሻ ከያዘ ግን የድንጋይ ውርወራውን ለመከላከል ዱላ (Baton) በመጠቀም ጉዳቱን መቀነስ ይችላል፡፡ በሠልፍና በሌሎች ሁኔታዎች ወታደርን በከተማ ውስጥ ማሰማራት እንደነዚህ ዓይነት መሣሪያዎችን ስለማይጠቀሙ ወይንም የመጠቀም ልምድ ስለሌላቸው የሚደርሱት ጉዳቶች መናራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

የመጨረሻዎቹ ፖሊስ ኃይል ከተጠቀመ በኋላ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ተግባራት ናቸው፡፡ ፖሊስ የወሰዳቸውን የኃይል ዕርምጃዎች፣ መመዝገብና መሰነድ፣ የመተንተን ብሎም ሪፖርት የማድረግ አሠራር ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡ ፖሊስ እንደ ተቋም በአፋጣኝ መረጃን ለሕዝብ የማሳወቅና ለሚዲያዎችም የመስጠት ግዴታ ሊኖርበት ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳትና ሞት በልዩ ሁኔታ በሠለጠኑ ገለልተኛ ባለሙያዎች ምርመራ እንዲደረግባቸው በማድረግ፣ ፍጥነት የተሞላበት ቁጥጥር በማስፈን ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሥርዓት ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

  • ይል አጠቃቀም ፈርጆች

አንድ ፖሊስ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ሳለ ሥራው የሚጠይቀውንና በሕግ የተፈቀደውን ኃይል ሊጠቀም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ሆነ ነገር ግን ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይልም ሊጠቀም ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው የተመጣጣኝነትን ልኬት የዘለለ ኃይል ነው፡፡ አለመመጣጠኑን በአስተዳደራዊ መንገድ ወይም በፍርድ ቤት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡

ሌላው ደግሞ ኃይል መጠቀም በማያስፈልግበት ሁኔታ ኃይል ሲጠቀም፣ ወይንም የሕግ ክልከላን በመተላለፍ ኃይል መጠቀም፤ ሕገወጥ የኃይል አጠቃቀም ይባላል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ደግሞ፣ ፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል ዕርምጃ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ለአብነት አንድ ተጠርጣሪ ከተያዘ በኋላ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች በዚህ ምድብ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ፖሊስ ግዴታውን በሚያከናውንበት ጊዜ፣ ኃይል መጠቀም ሊፈቀድ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች በመለኪያነት እዲያገለግሉ፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአንድ ወቅት የሚከተሉትን መሥፈርቶች አስቀምጧል፡፡ እነዚህም የወንጀሉ አደገኝነት፣ ተጠርጣሪው ፖሊስ ወይንም ሌላ ሰው ላይ ቅርብ የሆነ አደጋ የሚያደርስ መሆኑ፣ ተጠርጣሪው ላለመያዝ በግልጽና በአካላዊ እንቅስቃሴ ከተቃወመ፣ ከተያዘ በኋላ ለማምለጥ ከሞከረ፤ የሚሉት ናቸው፡፡ በመሆኑም በሕጋዊ መከላከል (አልሞት ባይ ተጋዳይ) እና የሌሎችን መብት ለማስጠበቅ ሲባል እንኳንስ ፖሊስ ሌላም ግለሰብ ኃይል ሊጠቀም ይችላል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ የወንጀሉ ድርጊት ቀረቤታና አደገኛነት፣ በሌላ መንገድ ሊቀለበስ የማይችል መሆኑን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መሥፈርቶችና መለኪያዎች በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 78 እና 79 ላይ ተገልጸዋል፡፡

ኃይል መጠቀምን የሚገሩ ሕጎች

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ እንደተገለጸው ማንኛውም የሰው ልጅ የማይደፈር በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብት አለው፡፡ በሕይወት የመኖር መብቱ በሕግ በተፈቀደው ሁኔታ (ለምሳሌ በሞት ፍርድ፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት) ሊገድብ ቢችልም፣ በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 16 መሠረት ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ገደብ ሳይደረግበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ልንል የሚገባን የሰው ልጅ አካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ዕውቅና የተሰጠው መብቱ ፍጹማዊ መሆኑን ነው፡፡ ሌላው አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮም ይሁን ተፈርዶበት በእስር ላይ በሚገኝበት ጊዜ ኢሰብዓዊ ከሆኑ አያያዞች የመጠበቅ ፍጹም መብት አለው፡፡ በተለይ ይህ መብት በአስቸኳይ ጊዜ እንኳን የሚገደብ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ማንኛውም የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት መጠበቅና ከኢሰብዓዊ አያያዝ የመጠበቅ መብቶችን ጥበቃ አድርገዋል፡፡

ከላይ የተገለጹትን መብቶች ሥራ ላይ ለማዋል የበለጠ እንዲረዳ፣ እነዚህን መብቶች የጣሰ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ፣ ፖሊስንም ጨምሮ፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 422(2) መሠረት ከተገቢው በላይ ኃይል ከተጠቀመና በ424 መሠረት ደግሞ ጭካኔ የተሞላበትና ለሰብዓዊ ክብር ተቃራኒ የሆኑ አድራጎት ከተፈጸሙ በወንጀል የሚጠየቁበት ሕግ አለ፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም የደረሰው የአካል ጉዳትንም በተመለከተ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 555 በከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወይንም በ556 መሠረት በቀላል የአካል ጉዳት ወንጀል ፖሊሱን መክሰስ ይቻላል፡፡ ከሞተ ደግሞ እንደ ግድያው ዓይነት ከ539 እስከ 541 ድረስ ባሉት አንቀጾች ሊከሰስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ያልተገባ ኃይልን ይከለክላል፡፡ ሕጉ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ ያልተገባ ኃይል እንዲጠቀም የሚገፋፉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የተወሰኑትን ብቻ እንመለከት፡፡

የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት በፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ላይ ያለው አንድምታ

በወንጀል መከላከል፣ ምርመራ፣ ክስ፣ የፍርድ ሒደትና እርማት ውስጥ የሚሳተፉ ተቋማት፣ አወቃቀራቸው፣ አሠራራቸውና የሚተገብሩትን ሕግ ጨምሮ በአንድነት የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ይባላል፡፡ የተለያዩ አገሮች የፍትሕ ባህላቸውንና ማሳካት የሚፈልጉት ማኅበራዊ ግብ መሠረት በማድረግ የተለያዩ አካሄዶችን ተልመዋል፡፡ የዘርፉ ምሁራንም አገሮች የሚከተሏቸውን አካሄዶች በማጤንና የራሳቸውን በመጨመር በርካታ ሞዴሎችን አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኸርበርት ፓከር የወንጀል ቁጥጥር (Crime Control) እና በሕጉ መሠረት (Due Process) የተሰኙ ሞዴሎችን አስተዋውቋል፡፡

‘የወንጀል ቁጥጥር’ ሞዴል፣ ግቡ ወንጀልን መቆጣጠርና ወንጀለኞችን የሚይዝበት፣ የሚመረምርበት፣ የሚከስበትና ውሳኔ የሚሰጡት ተቋማት የሚከተላቸው አሠራር ወጥነት፣ ቀልጣፋነት፣ ብቃት ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ሒደት ውስጥ ፍትሕ የሚያዛቡ ውሳኔዎች ቢፈጸሙ እንኳን በይግባኝ ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ‘በሕጉ መሠረት’ የሚባለው አሠራር ደግሞ ዋና ትኩረቱ የተጠርጣሪዎች መብት ስለሆነ አጽንኦት የሚሰጠው በወንጀል የተጠረጠረው ሰው ከምርመራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ባለው ሒደት ውስጥ መብቱን እንዲጠበቅለት ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያውን በርካታ የአውሮፓ አገሮች የሚከተሉት ሲሆን፣ ሁለተኛውን እንግሊዝና አሜሪካ በዋናነት ይከተሉታል፡፡

የሕግ ሥርዓታችንምና ሕጎቻችን በዋናነት የተቀዱት ከአውሮፓው ሥርዓት በመሆኑ፤ የእኛም አገር የወንጀል ቁጥጥር ሞዴልን ወደሚከተሉት ጎራ ልትካተት ትችላለች፡፡ ስለሆነም ፖሊስን የሚመለከቱት አተገባበር በዚሁ የተቃኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወንጀለኞችን የመያዝ፣ የመመርመር፣ የማስቀጣትና የመሳሰሉት ተግባራት በወጥነት፣ በተቀላጠፈና በብቃት መወጣት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በተቃራኒው በሕጉ መሠረት የተሰኘውን ሞዴል መርጧል፡፡ በተለይም የአካል ደኅንነት ሊገደብ የሚችልበት ምንም ዓይነት ቀዳዳ አለመኖሩ እንዲሁም የተጠርጣሪ የተያዘና የተከሰሰ ሰው መብቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

በፍትሕ ተቋማት ውስጥ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (Business Process Re-engineering)፣ ሲተገበር የተስተዋለው በዋናነት የወንጀል ቁጥጥር ሞዴልንና ተዋረዳዊ የውሳኔ አሰጣጥ የሚባለውን የመንግሥት ሥራ የማከናወን አዝማሚያ ነው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ልክ እንደ ኮሚኒስታዊ የፖለቲካ ፓርቲ አሠራር ከላይ ወደታች የሚሰጥ የውሳኔ መርህን ይከተላል፡፡ እነዚህ የወንጀል ቁጥጥርና ተዋረዳዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሞዴሎች እንደ ማንኛውንም የፍትሕ ተቋማት ለፖሊስም ሰፊ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ትኩረቱም የግለሰቦችን መብት ከማስከበር ይልቅ ወንጀልን መቆጣጠር ነው፡፡ ስለሆነም ከፖሊስ ኃይል አጠቃቀም አንፃር እንደ እንግሊዝና አሜሪካን የመቀየድ አዝማሚያ የለውም፡፡

የፖሊስ አወቃቀርና የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም

ፌዴራላዊም ይሁኑ አሃዳዊ አወቃቀር የሚከተሉ አገሮች በአንድ እዝ ሥር ያለ ፖሊስ ወይንም ደግሞ በተለያዩ እዞች ሥር የሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ ተቋማት አሏቸው፡፡ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ያሏቸው በጥምረትና በቅንጅት የሚሠሩበት መጠን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዱ ፖሊስ ተቋማትም ተግባርና ኃላፊነት ግልጽ ድንበር ከመኖር አንፃር የተለያዩ አሠራሮች አሏቸው፡፡ የፖሊስ ተቋማት ብዛትና የዳበረ ቅንጅታዊ አሠራር መኖር ወይንም አለመኖር፣ ከግለሰብ መብት መከበር፣ ከመልካም አስተዳደርና ከተጠያቂነት ጋር ግንኙነት አለው፡፡

የኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የክልሎችና የፌዴራል ፖሊስ አሉ፡፡ የክልሎች ደግሞ መደበኛና ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ የአካባቢ ፖሊስም (ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) አለ፡፡ በፌዴራልም ከልዩ ኃይሉ በተጨማሪ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ፖሊስ አለ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባርና ሌሎችም የፖሊስ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ደግሞ የክልሎችና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃይል ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

በተለይ ሕዝብ ሰልፍ በሚያደርግበትና ተቃውሞዎች በሚኖሩበት ወቅት፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እንደሆነው፣ ሰልፉንና ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሎቹ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱም ጭምር በአንድ ጊዜ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ ችግሮችን ይፈጥራሉ፡፡ ተገቢ ያልሆነ ኃይል የተጠቀመውን ፖሊስ መለየት ያዳግታል፡፡ እንዲሁም ተጠያቂነት እንዳይሰፍን እንቅፋት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ቅንጅት የጎደለው የእዝ ሰንሰለቱ የተዘበራረቀና የተለያዩ ትዕዛዝ ሰጪዎች መብዛት ፖሊስ የሚጠቀመውን ኃይል መመዘን ይቅርና ተጎጂዎች አቤቱታም ሆነ ክስ የሚያቀርቡበትንና ምርመራው የሚከናወንበትን ፖሊስ ማንነቱንም ይሁን ተጠሪነቱን ስለማያውቁት ደመ ከልብ ይሆናሉ፡፡

ፖሊስ አገልግሎት መስጠት ያለበት ተወልዶ ባደገበት ወይንም በመኖሪያ አድራሻው አካባቢ መሆን አለበት፡፡ ተጠያቂነትን ለማስፈንና ጭካኔ የተሞላበት ኃይል እንዳይጠቀምም ይረዳል፡፡ እዚህ ላይ በጥንት ጊዜ የነበረው የፖሊስና ወታደራዊ አሠራራችን ትምህርት ሰጪ ስለሆነ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም፣ በ14ኛውና 15ኛው ብሎም እስከ አፄ ልብነ ድንግል የንግሥና አዝማናት ድረስ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው የሚገኙ እንደ ወታደርም እንደ ፖሊስም የሚያገለግሉ የጨዋ ሠራዊት ነበሩ፡፡ እነዚህ የተለያዩ መጠሪያ የነበሯቸው የጨዋ ሠራዊት በዋናነት የሚመለመሉት ከአካባቢው ነበር፡፡ ለምሳሌ በአፄ በዕደ ማርያም (1460-1470 ዓ.ም.)፣ የዶባ (አሁን ራያ የሚባለው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች) ሕዝብ እያመጸ ቢያስቸግር የንጉሡ ሠራዊትና በጠለምት አካባቢ ሰፍረው ይኖሩ የነበሩ ጃን አሞራ ተብለው የሚጠሩት ከወጓቸው በኋላ አመጹ ተረጋጋ፡፡ ከዚያም ንጉሡ ከዶባ ሕዝቦች ከራሳቸው የጨዋ ሠራዊት እንደሠሩላቸውና ከመካከላቸው ለእነሱ የሚስማማቸውን ሰው አስተዳዳሪ እንዲሆናቸው እንደሾሙላቸው የዜና መዋዕላቸው ያስረዳል፡፡ ይህንን እንደ ማሳያ የተነሳው ምንም ዓይነት ሌላ ንድፈ ሐሳብ ዋቢ ማድረግ ሳያስፈልግ የታሪካችን አካልም እንደነበር ነው፡፡ በተለይ የጭካኔ ተግባርን ለመቀነስና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲህ ዓይነቱን አሠራርን ማስፈን ተገቢ መሆኑን ጥናቶችም ያስረዳሉ፡፡

ከላይ በወፍ በረር እንዳየነው ሕገ መንግሥቱ፣ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችና የወንጀል ሕጉ ፖሊስ ያልተመጣጠነም ሆነ ሕገወጥና ጭካኔ የተሞላበት ኃይል እንዳይጠቀም ይከለክላል፡፡ በተቃራኒው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ቅኝት የፖሊስ ተቋማት አወቃቀርና ቅጥ ያጣው በየክልሉና በየከተማ አስተዳደሮቹ የስምሪት ሥርዓት ፖሊስ ኃይል እንዲጠቀም እንደ ማትጊያ ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪም ከመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ አተገባበርና ውጤት ተኮር የሥራ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ወንጀልን በማንኛውም መንገድ መከላከልና ምርመራም እንዲሳካ ስለሚያበረታታ ሰብዓዊ መብትን ከማክበር ይልቅ ወደ ተቃራኒው ለማዘንበል የተመቸ ነው፡፡

ፖሊሳዊ አሠራርን የሚያጎለብት ባህርይን የሚገራ ዝርዝር የሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖርና በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የፖሊስ ሕገወጥ ተግባር የሰብዓዊ መብትን ከመጣሱም በተጨማሪ የመልካም አስተዳዳር እጦትንም ያስከትላል፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ሕግ እንዲኖርና የሚቆጣጠሩ ተቋማት ማስፈን ተገቢ ነው፡፡

የፖሊስን የኃይል አጠቃቀም በመጀመሪያ ራሱ የፖሊስ ተቋሙ ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡ መረጃ በመያዝ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በማሟላትና እነዚህን መሣሪያዎች ሳያስታጥቁ አድማና ሠልፍ በሚኖረበት ጊዜ ፖሊስን አለማሰማራት የተቀናጀ የፖሊስ አሠራር ማስፈን የሕዝብን ብሶት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ እንደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎና ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ እንደተባሉት ዓይነቶቹ የፖሊስ አድራጎት ሲኖሩ ዝርዝርና ወቅታዊ መረጃን በፍጥነት ለሕዝብ የማድረስ አሠራር መተግበር ግድ ነው፡፡

በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ከተጣሉበት ኃላፊነቶች አንዱ ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ሲጥሱ ሕግን በጣሰ ሁኔታ የፌዴራል ፖሊስ ክልሎች ውስጥ ሲገባና የመከላከያ ሠራዊቱ በአገር ውስጥ የፀጥታ ጉዳይ ሲሰማራ ተገቢውን ማጣራትና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም የሚለካው እያንዳንዱ ተናጠል ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ መሆኑ እየታወቀ፣ በጅምላ በኦሮሚያ የተወሰደው ተመጣጣኝ በአማራ የነበረው ያልተመጣጣነ በማለት የሚቀርበውን አሠራር ሳይንሳዊ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...