Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጥልቅ ተሃድሶ የማድረጉ ተስፋና የተጋረጠው ፈተና

  በአስፋወሰን በኃይሉ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት ኢትዮጽያን ለ25 ዓመታት አስተዳደሯል፡፡ ይህ አራት አባል ፓርቲዎችንና ቢያንስ አራት አጋር ድርጅቶችን የያዘ ፖለቲካዊ ሥርዓት ፌዴራላዊ አስተዳደርን በመተግበሩም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ይብዛም ይነስም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ታይቷል፡፡ በዚያው ልክ የአገሪቱ ሕዝብ ወደ እጥፍ ገደማ አድጓል፡፡ የፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ ፍላጎቱ በዚያው ልክ ጨምሯል፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂና በመረጃም ወደ አንድ መንደርነት በመምጣቱ ሁሉንም እውነት ገላልጦት አርፏል፡፡

እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች በተንሰራፋባት ሁኔታ በየትኛውም አገር ያሉ መንግሥታትን የሚገጥም ጫና (Challenge) ኢሕአዴግን ገጥሞታል፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የዴሞክራሲ መብት አፈና ከዳር ዳር ይጋለጣል፡፡ ቢሮክራሲ ውስጥ የሚፈጠር የመልካም አስተዳደር ጥሰትና ሙስናም ያስመረረውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን መላውን ሕዝብ የሚያቆስል እስከመሆን ይደርሳል፡፡

ድርጅቱ ከነበረው ታሪካዊ ጉዞ አንፃር የነበረው ‹‹ሚስጥራዊነት›› እንኳን የነገር ወንፊት ተክቶታል፡፡ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በየብሔራዊ ድርጅቱ የተናገሩት ሕዝብ የሚያስከፉ ንግግሮች በቅፅበት እየወጡ አደባባይ ላይ ውለዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ኢሕአዴግን በመሠረቱት ፓርቲዎች መካከል ለ25 ዓመታትና ከዚያ በላይ የነበረው ‹‹ኢእኩልነት›› እየተጋለጠ መጥቷል፡፡ አድርባይነትም ይባል ችሎ ማለፍ ተሸክሞት የኖረው ፖለቲከኛ ሁሉ ‹‹ለምን?›› ማለት ጀምሯል፡፡

ከዚህ የከፋው ነገር ደግሞ ከአንድነትና ኅብረት ይልቅ ልዩነትንና የመንደር ማንነትን ሲያቀነቅን የከረመው አስተሳሰብ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡ ‹‹በእንቁላል ጊዜ በቀጣሽኝ›› እንዲሉ ገና ከመነሻው አንተ የእኔ ብሔር አባል አይደለህም ከክልሌ ውጣ ማለት ሲመጣ ‹‹ተው!›› ባለመባሉ ዛሬ አንዱ ብሔር የሌላውን ሀብት እያወደመ እርቃኑን ማሳደድ ይዟል፡፡ መፍትሔ ካልተበጀለትም ማንም የአገሪቱ ዜጋ ዋስትና ኖሮት በፈለገው ቦታ ሀብት ለማፍራት የሚደፍርበት መብት ጥያቄ አስነስቷል፡፡

እርግጥ ጠባብነትም ይባል ዘረኝነት ለሚባለው ኋላቀር ርዕዮት በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ፅንፈኛ ኃይል የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በራሱ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ሲቀነቀን የኖረውን የቋንቋና የዘር አጀንዳ መሠረት አድርጎ ባለሥልጣናትን (እስከ ቀበሌ አስተዳዳሪ ድረስ)፣ ጄኔራሎችን፣ ባለሀብቶችን፣ ሕንፃዎችንና ትልልቅ ድርጅቶችን መቁጠር ጀምሯል፡፡ በተቃራኒው የታሰረውንና የተሰደደውን ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በብሔር ማንነቱ እየተጠቀሰ ‹‹አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ›› የሚል አገላለጽ ከጓዳ እስከ አደባባይ ያስተጋባል፡፡

አሁን መሬት ላይ ያለውን እውነታ የተገነዘበው ገዥው ፓርቲም ችግሩ የውስጣችን ነው ብሎ አምኗል፡፡ በእሱ ብቻ ሳይሆን መፍትሔውም ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ማድረግ ነው በሚል ቢያንስ ከ15 ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተፈጠረውን በጎና መጥፎ ነገር ፈርጅ በፈርጅ መገምገም ጀምሯል፡፡ በሥራ አስፈጻሚ፣ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በአባል ድርጅቶቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የተሰነበተበት ግምገማ፣ ባሳለፍናቸው ሳምንታት ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ መሪዎች አድርሶ ወደ ሕዝቡ ለመውረድ እየተንደረደረ መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡

በመድረኮቹ ከቀረበው መነሻ ጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች ከተነሱ ሐሳቦች አንፃር ውስጥ አዋቂ ምንጮችን መሠረት በማድረግ ለጋዜጣ በሚሆን መንገድ አቀርበዋለሁ፡፡ በዚህ መነሻም ገዢው ፓርቲ ሊያደርገው ያሰበው ተሃድሶ ምን ተግዳሮት ይገጥመዋል፤ እስከምን ድረስስ ሊሄድ ይችላል የሚል ፍተሻ አንባቢዎች እንዲያደርጉ ዕድል ለመስጠት እንሻለን፡፡

የሙስናውና አቋራጭ ብልፅግናው

አሁን ባለው የአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሠራር ሕዝብን እያማረረ ስለመሆኑ ከሪፖርተር ጋዜጣ በላይ ደጋግሞ ያስተጋባ የለም፡፡ እርግጥ ገዢው ፓርቲም ደፍሮ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አይቻል እንጂ ችግሩ እንዳለ ደጋግሞ አንስቷል፡፡ አሁን በተሃድሶው ላይ አዲስ ነገር ሆኖ የመጣው የዝቅጠት አደጋው (ከ1993 ዓ.ም. በላይ) በሥርዓት ደረጃ እየተፈጸመ ነው/አይደለም የሚለው ውዝግብ ነው፡፡

በተለይ ብሔርን፣ በትጥቅ ትግሉ የነበረ አስተዋጽኦን ወይም ‹‹ቀደም ሲል ተበድለናል›› በሚል ሽፋን በሕገወጥ መንገድ ካለውድድርና በአቋራጭ እየበለፀጉ ያሉ ወገኖች መበርከታቸው ተነስቷል፡፡ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጭምር ባለግዙፍ ሕንፃና ትልልቅ ኩባንያ ባለቤት የሆኑ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ማሽነሪዎችን የሚያከራዩ ባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው በሕዝቡ ይታወቃሉ፡፡ በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችም የተያዘ መረጃ እየወጣ ነው፡፡

አሳዛኙ ነገር በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች (ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ 44 ማዞሪያ፣ ሆለታ፣ ዓለም ገና…) የተፈጸመው የመሬት ወረራ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. የኢሕአዴግ በተቃዋሚዎች የመነቅነቅ አደጋ በኋላ በመንግሥት ‹‹አሠራር›› የተደገፈ የሚመስል ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደረጃና በየአካባቢው የተመደቡ ‹‹አመራሮች›› የአምስትና የአሥር ቦታዎች ካርታ እጃቸው አስገቡ፡፡ ለፈለጉት ወገን በርካሽና በስጦታ ጭምር ቸበቸቡ፡፡ በዚህ መሀል በፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት፣ በደኅንነት፣ በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ በተለይ አዛዥነትና መስመራዊ መኮንን ደረጃ ላይ ያለው የድርሻውን አነሳ፡፡

በዚህ ድርጊት ውስጥ የገቡ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ሕገወጥ ደላሎችና የሕዝብ መሬት አግበስባሾችም ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር ወደ አንድ ወገን (ብሔር) የሚገፋ ሳይሆን የሥርዓቱ ድክመትና ንቅዘት ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ ስለሆነም አሠራርና አደረጃጀትም ዘርግቶ በገፍ የተዘረፈውን ሀብት በሕግ ጠይቆም ሕዝባዊና አብዮታዊ እርምት ሊወስድ የሚችለው ራሱ ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻለም የከፋ ቅሬታና ውድቀት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ እየገነገነ የመጣው ሌላው የሙስናና የኢኮኖሚ ዳባ ተግባር በገቢዎችና ጉምሩክ መስኩ የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ የአንድ አገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዋነኛ መሣሪያ አንዱን ወገን የመበደል፣ ሌላውን ያላግባብ የማበልፀግ በር የሚከፍትበት ነው፡፡ መንግሥት በጠንካራ አሠራርና ሕግ፣ እንዲሁም በሥነ ምግባርና ፍትሐዊ አስተዳደር ካመራው ለአገር ለውጥ በእጅጉ የሚጠቅም ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በአገሪቱ አሁን ለተደረሰበት ለውጥ የሕዝቡ ግብርና ታክስ የመክፈል አቅምና አድማስ መስፋት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ ከቀረጥ ነፃ ታክስ ከገባው ባሻገር በገቢና በወጪ ምርት ላይ የጉምሩክ ቀረጥ ተጠናክሮ መተግበሩም ዋነኛው መሣሪያ ነበር፡፡ በዚህ ሒደትም ውስጥ ግን ‹‹ዘግናኝ›› የሚባሉ የሙስና ወንጀሎች እንደተፈጸመበት ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹ከዓመታት በፊት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የዘርፉ ተጠርጣሪ ባለሥልጣናት (ዋና ዳይሬክተር) ጀምሮ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች፣ የመምርያ ኃላፊዎች፣ ከሳሽ ዓቃብያነ ሕግና ባለሙያዎች በአገር ሀብት አሻጥሩ ውስጥ ተሰማርተዋል፤›› የሚለው መረጃ በአገሪቱ ‹‹አንቱ›› ሲባሉ የከረሙ ባለሀብቶችም በቀረጥና በጉምሩክ አሻጥር ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀው በመገኘታቸው ወህኒ ወርደዋል፡፡

በዚያ ወንጀል ምርመራና ተጠርጣሪዎች መያዝ ወቅት እንደተመለከትነው፣ አንዳንዱ ባለሥልጣን ለአሥር ቤተሰብ የሚያገለግል የቤት ካርታ ብቻ አልነበረም የያዘው፡፡ በርከት ያለ ሕገወጥ መሣሪያና የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ጭምር ተይዟል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ነው አሁን ሙስናውን ገፍቶ ለመታገል የሚያስቸግረው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሙሰኞች በሕገወጥ ድርጊት የሰከሩ በመሆናቸው የግለሰቦችን ጌጣጌጥ ሳይቀር ይነጥቁ እንደበርም እያፈርን ተመልክተናል፡፡

በኮሚሽኑ ድክመትም ይባል በመንግሥት ቁርጠኝነት ማጣት ያልተከሰሱ፣ ተጀምሮ ክሳቸው የተቋረጠ፣ ተከሰውና መረጃ ተደራጅቶባቸውም ውሳኔ ያልተሰጣቸው ሙሰኞችም እንዳሉም ይነገራል፡፡ ለአብነት የብረታ ብረት አስመጪዎችና ‹‹የሪል ስቴት›› አልሚ ተብዬ ነጣቂዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በጥቅም ተካፋይ ባለሥልጣናት እየተደገፉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት ለግል ጥቅም እንዳዋሉም መረጃ አስደግፈው የሚያስረዱ አሉ፡፡

በሲሚንቶ፣ በስኳር፣ በቡና፣ በጫትና በመሳሰሉት ወጪና ገቢ ምርቶች፣ በተሽከርካሪና በማሽነሪ ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሟል፡፡ ለጥቂቶች ብቻ የተፈቀደ በሚመስለው ‹‹ትራንዚተርነት›› በቅፅበት የከበሩትን በየመንደራችን አይተናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ዓመታዋ ክፍያ በመሸሸግና በመቀነስ ሙስና የሚያሳድዱ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አንዳንድ ጥገኞችም ገና ፍትሕ አላገኙም፡፡

እንግዲህ ሙስና ሲነሳ መሬትና ግብርን አነሳን እንጂ በመንግሥት ግዢና ሽያጭ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና የኮንትራት ግዢ ሁሉ የደራ ሌብነት አለ፡፡ መጠኑና ዓይነቱ ከመለያየቱ በስተቀር የሻገተው የሥርዓት ንቅዘትም ገና የሚገታውን ዕርምጃ አላገኘም፡፡

የፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ረገድ

የኢሕአዴግ ተሃድሶ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ እየመጣ ያለው ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ እነ እገሌ በአጭር ጊዜ በለፀጉ እኛ ተጎዳን የሚለው ቅስቀሳ ነው፡፡ በተለይ ሕወሓትን መሠረት አድርገው ያሉ ባለሥልጣናትን ስም በመጥቀስ በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩም የፌዴራሉን ‹‹ቁልፍ›› የሚባሉ ቦታዎች የአንድ ብሔረሰብ ሰዎች እንደያዙ ነው የሚለው ትችት ከምክር ቤቶች እስከ መንደር ቡና መጣጫዎች የሚሰለቅ ሆኗል፡፡

አንዳንድ ተቺዎችም የመሥሪያ ቤቶችን ስምና የኃላፊዎችን ዝርዝር እስከ መጥቀስ ድረስ ይወርዳሉ፡፡ የተለያዩ ተቋማትንና ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡ ይህ ከተግባርና ከሥነ ምግባር ውጤታማነት ውጪ የሆነ አሠራር ባለፉት 60 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚያወዛግቡ ድርጊቶች የተጋለጠ ነው፡፡

ነገር ግን አሁን ላለው ውዝግብ ወደ ዳር የማይገፋ አንድ ጭብጥ ሆኗል ጉዳዩ፡፡ አገሪቱ 25 ዓመታት በዕድገትና ለውጥ ውስጥ እንደመሆኗ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ግለሰቦች ከፍ ያለ ሀብት ማፍራታቸው አይቀርም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ባለተሽከርካሪ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ቤትና ደመወዝ አግኝተዋል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለ ሕንፃ፣ ባለትልቅ ፋብሪካና ባለሰፋፊ እርሻና ማሽነሪ ባለቤቶች የሆኑ ሰዎች ከሕዝብ ሀብት ጋር ያላቸው ቁርኝት ሊመረመር የሚገባው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ከታዳጊ ክልሎች እስከ አዲስ አበባ በመመንዘር ‹‹እገሌ ከየት አምጥቶ!?›› የሚሉ ዜጎች ዋነኛ መከራከሪያቸው ይኼው ነገር ሆኗል፡፡

በተቃራኒው በአገሪቱ ከመነጨው ሰፊ የሚባል ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ በመሠረተ ልማት ሥርጭት፣ በኢንዱስትራላይዜሽን፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ብድርን በማመቻቸት በኩል ‹‹ምን ተደረገልን?!›› የሚሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን በትምህርትና በጤና ተቋማት ፍትሐዊ ክፍፍል ቢኖርም፣ ከላይ በተጠቀሱት ሰፊ ሀብት በሚፈልጉ ተግባራት ሕዝቡን ወደ ማርካት መሄድ ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት ሌሎች አገሮች በሚሄዱበት የነፍስ ወከፍ ገቢና በመሳሰሉት መለኪያዎች ብቻ ዜጎች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አግኝተዋል ሊል አይችልም፡፡ አሁንም አገሪቱ ያላትን ውስን ሀብት በግልጽ፣ ተጠያቂነት በተላበሰና በፍትሐዊነት ሕዝቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን ሁኔታ እንደ አንድ አብነት ብንወስድ ከቀበሌ ቤት፣ ከጋራ ኮንዶሚኒየምና ከጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ጋር የሚያያዙ የአሠራር ክፍተቶች ለዚህ ዓይነቱ ቅሬታ በር ይከፍታሉ፡፡

አሁን እየወጡ እንዳሉት መረጃዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ቤቶች ሁለትና ከዚያ በላይ ባላቸው ሰዎች ተይዘዋል፡፡ ‹‹ሕገወጥ›› ተብለው ወደ መንግሥት የተመለሱት 1,400 ቤቶችም ለእነማን እንደሚሰጡ ግልጽ አሠራር አልተበጀም፡፡ ከ800 የማያንሱቱ ደግሞ አሁንም እየታወቀ ወደ ግል ይዞታነት በንጥቂያ ተዛውረዋል፡፡ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ደረጃ አራት ሺሕ የሚደርሱ ያላግባብ ተይዘው ያሉ ክፍት ቤቶችስ ለምን ጥቅም ማዋሉ? እነማን ናቸው እየገቡባቸው ያሉት?… ዝርዝሩ ብዙና ውስብስብ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከትልቁ አገራዊ ‹‹ኬክ›› በአግባቡ መከፋፈል ያልቻሉ የገጠር ወጣቶችም ወደ አዲስ አበባ እያደረጉት ያለው ፍልሰት መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ በተለይ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ሰፋ ያለ ፍልሰት ለሥራ አጥነትና ለኑሮ ውድነት ብቻ ሳይሆን ለወንጀልና ለከተማ ደኅንነት ዕጦትም ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ በያለበት የአቅሙን ያህል እንዲንቀሳቀስ ዕድሎችን መፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ቢያንስ ፍልሰቱም ወደ ክልሎችና ዞን ከተሞች ቢሆን (ለዚህ የሰው ጉልበት ያለበት ማዕከል መፈጠር ያስፈልጋል) የተሻለ ይሆናል፡፡

ሰላምና መረጋጋትን የመመለስ ጉዳይ

አንድ ታዋቂ ጦማሪ የአሁኑ የኢሕአዴግ አመራር የጂቲፒ ሁለት ትግበራ ‹‹ሠላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ ነው›› ያለውን አባባል እጋራለሁ፡፡ ይነስም ይብዛም ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ጎላ ያለችግር ተፈጥሮ የነበረው በምርጫ 97 ወቅት ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ግፋ ቢል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣  አንዳንዴ በአምልኮ ሥፍራዎች የሚነሳ ወቅታዊ ግርግር ካልሆነ በስተቀር የበረታ የሰላም መደፍረስና የመረጋጋት ሥጋት አጋጥሟል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ እነሆ ወደ አዲሱም የተሸጋገረው ሕዝባዊ እንቢተኘነት ግን ኃይል የተቀላቀለበት ሆኗል፡፡ የቅርብ ጊዜውን በደብረዘይት ኢሬቻ በዓል ላይ ተረጋግጠው ያለቁ ዜገችን ጨምሮ በጣም በርካታ ዜጎች እርስ በርስና ከፀጥታ ኃይል ጋር በመፋለም ወድቀዋል፡፡

እዚህ ላይ ዜጎች ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ማንኛውንም ጥያቄ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ግን አልፈው ንብረት ማውደምና ፀጥታን ማወካቸው ድርጊቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ ማድረጉ አይቀርም፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ቢሆን የዜጎችም ሆነ የንብረት ደኅንነት አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይሁንና ለማደናገጥም ወይም ሆን ተብሎ የሕዝብ ጥያቄን ለመጨፍለቅ የፀጥታ ኃይሉ ተኮሰ እየገደለ ይገኛል፡፡

እውነት ለመናገር ይህ አካሄድ የትም ሊያደርስ አይችልም፡፡ በመንግሥት ላይ የተነሳውን የሕዝብ ቅሬታ ከማባባስና ከማስፋት በስተቀር፡፡ በተለይ በውጭ ያለው ፅንፈኛ ኃይል ሆን ብሎ ዘር እየለየ ለማፋጀት የሚከተለው አደገኛ ሥልት ሲታከልበት መጪው ጊዜ አርማጌዲዮን እንዳይሆን ያሳስባል፡፡ መንግሥትና መሪው ፓርቲም በሆደ ሰፊነትና በጥልቀት ሊመረምሩት ይገባል፡፡

ገና ለጋ በሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ቀላል ግምት የማይሰጠው የሕዝብና የግለሰቦች ንብረት እየወደመ መሆኑም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሞኑ ብቻ በቄለም ወለጋ፣ ደንቢ ዶሎ አምቦ፣ ነጆ፣ ዝዋይ፣ መቂ፣ ሻሸመኔና አገረ ማርያምን በመሳሰሉ ከተሞች በርካታ ተሽከርካሪዎችና የመንግሥትና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋል፡፡

በየአካባቢው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተረጋግተው ሥራ ለመሥራት ተቸግረዋል፡፡ ብጥብጡና ሁከቱ ደግሞ አገረሸ በማለት በተለይ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የሚኖሩ አንዳንድ የሌላ ብሔር ተወላጆች እየተጨነቁ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች (በተለይ አውቶቡሶችና ከባድ የጭነት መኪኖች) ደፍረው የአገር አቋራጭ መንገዶችን መያዝ እየፈሩ ነው፡፡ እየደረሰ ባለው አደጋ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ናቸው (ቢያንስ በቅርቡ በባለሀብቶች ኢንቨስትመንቶች፣ ፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰው አደጋ ይመለከታቸዋልና)፡፡

በመንግሥት በኩል እየተወሰደ የለው ዕርምጃ ግን ጥይትና ስብሰባ ብቻ እየመሰለ ነው፡፡ ‹‹የት አለ እውነተኛው ዳቦ?!›› እንዲሉ ፈጥኖ የእርምትና የማሻሻያ ተግባር ካልታየ የአገርን ሰላምና የሕዝብን አጋርነት መልሶ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ አሁን እንጀመረው ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› እያለ በስብሰባ ጊዜ መብላት ሳይሆን በሌብነት፣ በጠባብነትና ሕዝብን በማገልገል ድክመት የሚወቀሰውን ሁሉ ማራገፍ አለበት፡፡ ዓይን ባወጣ ሌብነት የተዘረፈ የሕዝብ ሀብት ማስመለስና ወንጀለኞችንም በሕግ ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡

እንዳስፈላጊነቱ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥያቅ እያዳመጡ ከሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መወያየት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በአፋጣኝ መፍታትም አለበት፡፡ ባሳለፍነው ጊዜ በተከሰተው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አቅም በፈቀደ መጠን መካስ፣ ካልሆነም ይቅርታ መጠየቅና ዕርቅ መፈጸም የጨዋነት ባህሪ ነው፡፡

ከሁሉ በላይ አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ለማስነሳት የሚደረግን ፀያፍ ድርጊት መከላከልና ራሱም እንደ ሥርዓት መቆጠብ አለበት፡፡ አንዱ ወገን አዛኝ፣ ሌላውን በዳይ እያስመሰሉ በእሳት መጫወት ቀውስን አይፈታም፡፡ አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው የሕዝቢን ጥያቄና አለመርካት ራሱ በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ ያለው፣ አንዳንዱ የመንግሥት ተሿሚና ሠራተኛ በግልጽ እየደገፈው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ከሰሞኑ በመቶ ሺሕ የሚቆጠረው የኢሬቻ በዓል ተሳታፊ በአንድነት ያሰማው ተቃውሞ ነው፡፡

ይህን እውነት ወደ ግራም ቢሉ ወደቀኝ መካድ አይቻልም፡፡ አጉል ከመላላጥ በስተቀርም ለመንግሥት የሚያስገኝለት ፋይዳም አይኖርም፡፡ ስለሆነም የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ይስፋ፣ የፕሬስ ነፃነት ይረጋገጥ፣ ኢፍትሐዊ የሚመስለው የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል በአፋጣኝ ይታረም፡፡ ካልሆነ በየጊዜው አንድ ዓይነት መዝሙር (የኢሕአዴግን ውለታ፣ የውጭ ጠላትን ደባና ‹‹ፀረ ሰላም›› ኃይሎችን በመውቀስ) የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

በአጠቃላይ የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ተስፋ ቢኖረውም የተጋረጠበት ፈተና ከባድ ነው፡፡ በተለይ የድርጅቱ መሪዎችና አባላት እውነተኛ ቁርጠኝነት ካላሳዩ ሥርዓቱን ከሞት ማዳን አይችሉም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles