Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየዴሞክራሲ ትውልድ ኢትዮጵያን ይታደጋት

የዴሞክራሲ ትውልድ ኢትዮጵያን ይታደጋት

ቀን:

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)

በመጀመርያ በኢሬቻ በዓል በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የተሰማኝን መሪር ሐዘን እየገለጽኩ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጽናናትን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡

የመስቀልን በዓል ተንተርሶ በሻዕቢያ ወረራ ክፉኛ ከተጎዱትና ሰላም ወይ ጦርነት ባለመኖሩ ምክንያት ከደቀቁት አንዷ በሆነችው ጉለመኸዳ (ዛላምበሳ) ጥፋቱን ለማካካስ፣ የወረዳው ተወላጆች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቴሌቪዥን ይዘገብ ነበር፡፡ ዶ/ር ፀጋይ (የአባታቸው ስም አላወኩትም ይቅርታ) 2009 ዓ.ም. ለምን የወጣቶች ዓመት ብለን አንሰይመውም? ብለው ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ እውነት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ (GPT2) ለምን የዴሞክራሲ ትውልድ ዘመን አንለውም?  እላለሁ፡፡ ዓላማውም የዴሞክራሲ ትውልድ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መሪነት የሚቆጣጠርበት ዘመን እንዲሆንና ኢትዮጵያን እንዲታደጋት፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይ ለልሂቃን ፖለቲካው ለመበላሸት መሠረታዊ ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ አነሳለሁ፡፡ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ነው ሊባል ይቻላል፡፡ ፈጣን የሆነ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ባለበት አገር ፖለቲካው ለምን በዚያ ደረጃ ወይም ቀድሞ አይገሰግስም? ፈጣን ለውጥ ባለበት አገር ፈጣን የሆነ  የትውልድ ቅብብሎሽ መኖር የለበትም ወይ? ለምንስ አሽቆለቆለ? በከፍተኛው ፖለቲካዊ አመራር ያሉ የአመፀኛው ትውልድ ልሂቃን በገዥውም ይሁን በተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራችን ሁኔታ ትንተና፣ ችግሮች ዕድሎችና ‹‹The Way Forward›› በጥናት ላይ ተመሥርቶ ማንጠርና በዚያ መሠረት ለመንቀሳቀስ ያልቻሉበት ሁኔታ ለምንድነው?

ለፖለቲካዊ ዝቅጠቱ ምክንያት እዚህም እዚያም ያሉ አመራሮች ላይ ጣት መቀሰር ዋናው መፍትሔ የሚያስገኝልን አይመስለኝም፡፡ ችግሩ ከግለሰቦችና ፓርቲዎች በላይ እንዳይሆን ማጥናቱ ተገቢ ነው፡፡ የመሰለኝን መላምት አቅርቤአለሁ፡፡ እስቲ እንደ ሶሽዮሎጂስት፣ ፖለቲካል ሳይንቲስት፣ ወዘተ ያላችሁ ባለሙያዎችና በተለይ ባለቤቱ የሆነው ወጣት በጥናት ላይ የተመሠረተ ውይይት ያድርግበት፡፡ አሁን ያለው ቀውስ ትክክለኛ አመራሩ ማለት የዴሞክራሲ ትውልድ በቦታው ስላልተቀመጠ ይሆን እንዴ? በሌላ አነጋገር አመፀኛው ትውልድና እሱ የከተባቸው አመራሮች ታሪክ አልቻላችሁም፣ ይብቃችሁ እያለ ነው እንዴ?

የአፄውን ሥርዓት ለማስወገድ ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለውን አመፅ ለመምራት በከፍተኛ ፉክክር የተነሳሳው ወጣት፣ ኋላም በደርግ ተጨፍጭፎም ሆነ ደርግን አሸንፎ የመጣውን ትውልድ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተለያየ ስም ይሰጡታል፡፡ ታጋይ፣ ቆራጥ፣ ለሕይወቱ የማይሳሳ፣ ለዓላማው የሚሞት፣ ግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም የታጠቀ፣ በሚሉ በርካታ ስሞች ይጠሩታል፡፡ ይኼው ትውልድ አሁን ባለንበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በበርካታ ጽንፎች ተወጥሮ ቅራኔውን ከማጥበብ ይልቅ ይበልጥ እያሰፋ በመሄዱ ላይ የሚገኝ ዋነኛ ተዋናይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ይህንን ለእርቅም ሆነ ለሰላማዊ ውይይት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የአስቸጋሪ ባህል ቁራኛ የሆነውን ትውልድ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ‹‹አመፀኛው ትውልድ›› በሚል አጠቃላይ ስያሜ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ አመፀኛው ትውልድ ተወያይቶ፣ ተከራክሮ፣ እርስ በርሱ ተጫርሶ፣ ተሰዶ፣ ተበትኖ፣ ተደራጅቶ፣ ተታኩሶ፣ ተሸንፎና አሸንፎ አንድ ትውልድ የሚሆን ተሰውቶ መጨረሻ ላይ ግን የኋላቀርነት ዘበኛ የሆነውን ደርግ ደመሰሰ፡፡ እጅግ ጥሩ ሊባል የሚችል ሕገ መንግሥት ቀርጾ ለቀጣዩ ትውልድ አስረክቧል፡፡ ደርግን ያሸነፈባቸው አራት መሠረታዊ ተነፃፃሪ ጥንካሬዎችን እንደ ምክንያት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

  1. የተሻለ ዓላማ ይዞ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በማጥናትና በመገምገም እየጎለበተ የመጣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልትና ስትራቴጂ በመያዙ፣
  2. በራሱና በሕዝቡ የሚተማመን ስለነበረ፣
  3. ለመማር ዝግጁ ስለነበር፣
  4. በተነፃፃሪ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር ስለነበረ ነው፤

እነዚህ ጥንካሬዎች ባለፉት 25 ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በተጨባጭ ሊካዱ የማይችሉና እሰየው የሚያስብሉ ልማታዊና ማኅበራዊ ለውጦችን አስከትለዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ባሉት አሥር ዓመታት በአገሪቱ ገና ሰላምና መረጋጋት ባልተረጋገጡበት ሁኔታ እንኳን አመርቂ ሊባል የሚችል ዕድገት ተመዝግበዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ እንዲህ ይገልጹታል፡፡

‹‹Economic growth during this period (1990/1-1999/00) was quite impressive. Real total and per-capita grew at average rates of 3.7 and 0.7 per annum, respectively, figures that rise to 5.6 and 2.6 respectively, if one excludes the abnormal years 1990-92.›› (The political economy of growth in Ethiopia. Chapter 4 of volume two, A/Professor Alemayoh Geda, 2006)

ባለፉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ከዓለማችን ፈጣን ኢኮኖሚዎች በመጀመርያ ረድፍ የምትጠራ አገር ሆናለች፡፡ ይህ ዕድገት የተገኘው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ ነበር፡፡ ይህ ሰላም ሕገ መንግሥታችን በተወሰነ ደረጃ  ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ ስለተጀመረ የተገኘ ነው፡፡ ሰላም ላጡ ሕዝቦች የሰላም ኃይል በመሆንና ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ዝቅ ተደርጎ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ እነ ሶሪያና ሊቢያ ከነሙሉ ሀብታቸው ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉም መርሳት የለብንም፡፡ እነ ኬንያና ሶማሊያ በአሸባሪዎች ሲታመሱ በሰላም ተኝተን የምናድረው የሰፈነውን አንፃራዊ ሰላም ተማምነን ነው፡፡ ዋናው የሰላማችን ምንጭ ሕዝቦቻችንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን ቢሆንም መንግሥትም ልዩ ምሥጋና ይገባዋል፡፡

ነገር ግን! አሁን ያ ሰላም በከፍተኛ ደረጃ መታመስ ጀምሯል፡፡ ዜጎቻችን እየሞቱ፣ እየቆሰሉና እየታሰሩ ናቸው፡፡ በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፡፡ በብሔሮች መካከል መጠራጠር እየሰፋ ነው፡፡ ብሔርን ማዕከል ያደረገ ጥቃትም እያየን ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ የአደጋ ደወል እያቃጨለ ነው፡፡ ለምን?

“አመፀኛው ትውልድ” እንደማንኛውም ትውልድ የራሱ የሆነ መሠረታዊ ድክመቶች ነበሩበት፡፡ ወደ መቃብሩም ይዞ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ሁሉም ነገር ነጭ ወይም ጥቁር፣ አብዮታዊ ወይም አድኃሪ አንደኛው ከአንደኛው ጋር ሊታረቅ የማይችል (Mutually Exclusive) ማሳያ ያለው ትውልድ ነው፣ አመፀኛው ትውልድ፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ትክክል የሌሎቹ አፍራሽ ነው በማለት እራሱን ይክባል፡፡ እሱ በሄደበት መንገድ ያልሄደን አሳዶ መቅጣት የሚፈልግና በከፍተኛ ስሜት ቂም በቀለኝነት (Vindictive) የተጠናወተው ትውልድ ነው፡፡ የ‹‹Win Win›› ሳይሆን የ‹‹Win Lose›› ትውልድ ነው ሊባል የሚቻለው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ድክመቶች እየጎሉ እየባሰባቸው መጡ፡፡ በተቃራኒ እነዚያ መሠረታዊ ጥንካሬዎች በከፍተኛ ደረጃ በመዳከም ሒደት ያገኛሉ፡፡

ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሸነፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በጥልቅ  ጥናትና በምርምር የተደገፉ የፖለቲካዊ አመራር አቅጣጫዎች የግድ ይላሉ፡፡ የእኛ አመራር ውሳኔዎች ግምገማ ነው መሠረት የሚያደረገው፡፡ የቅርቡ ምሳሌ እንኳን ብንወስድ በ2008 ዓ.ም. መጀመርያ ዋናው ችግራችን መልካም አስተዳደር ነው ተባለ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነት ሆነ፡፡ የአወሳሰኑ ሁኔታ በጣም እስደንጋጭ ነው፡፡ ማናቸውም ገዥ መደብ የራሱ ምሁራን ሳያኖሩት መምራት አይችልም የሚባለውን የሁልጊዜ ብሂል ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም፡፡ የአመፀኛው ትውልድ ‘ምሁራን አድኃሪ’ ናቸው በማለት እሱ ራሱ የፈጠራቸው ምሁራን በተለያዩ ካባዎች እየቀባ የማያስጠጋ ድርጅት ሆኗል፡፡ የራሳቸው ማንነት ባላቸው የእውነት ምሁራን ለመምራት ብቃቱም ፍላጎቱም የለውም፡፡ ስለዚህ እንደምንም ብሎ የተለያዩ ዲግሪዎች ያገኙ የማንንት ቀውስ ያለባቸውን እያግበሰበሰ ይገኛል፡፡ የሚኒስትሮቻችን፣ የዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁኔታ በዚህ መነጽር ቢታይ ጎልቶ የሚስተዋል ይመስለኛል፡፡ ምሁራዊ አቅም ሳይሆን ተላላኪ ምሁራን የሚፈለጉበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ምሁሩና ምሁራዊ አቅምን ያባከነ አመራር  አገር መምራት አይችልም፡፡

ሌላው መገለጫው የነበረው በራሱና በሕዝቡ የሚተማመን ጠንካራ መሠረት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለገጠሙት ችግሮች አንዱና መሠረታዊው ነገር በራሱ የሚተማመን አመራር ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብ ላይ እምነት የሌለው ድርጅት መሆኑ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ  ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከስህተቶቹ በፍጥነት ለመማር የነበረው የአዕምሮ ክፋትና ፈቃደኝነት በተመሳሳይ ሁኔታ ከጊዜው ጋር ሊሄድ የማይችል ዘገምተኛ አስተሳሰብ ባለቤት እየሆነ በመምጣቱ፣ በሩን ከፍቶ ለመማር የነበረው ጠንካራ ባህል ሙሉ ለሙሉ ዝግ በማድረጉ ችግሮቹ እንዲባባሱ ሌላ ምክንያት ሆኗል፡፡

“Progress is impossible without change and those who cannot change their minds cannot bring change” ጆርጅ በርናንድ ሾሙ (2002፡ 13) የሚባል ሙሁርም እንዲህ ይላል፣ ‹‹ሕይወት በመማር ሒደት ስትገባ ሐሳባችንን በነፃ መግለጽ ስንችልና የሌሎች ሐሳባች በነፃነት ማግኘት ስንችል ነው፤››

በየጊዜው የሚወጡ ጨቋኝና አፋኝ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ምክንያት በመላው አገራችን ዴሞክራሲያዊና ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲቀጭጭና በተቃራኒው ኢዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች እንዲነግሡ በመደረጉ፣ አሁን ላለንበት ድንግዝግዝ እንድንዳረግ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡

በስተመጨረሻም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መጀመርያ በፓርቲው እንደ አመለካከት ካስወገድኩኝ በኋላ በተወሰነ የከፋ አመራር ላይ ዕርምጃ በመውሰድና አንዳንድ ማስተካከያዎች እንደሚያደርግ እየገለጸልን ነው፡፡ በፓርቲው ያለውን ጣጣ ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሕዝብ ወርደን የእንቅስቃሴውን ችቦ እናበራለን እያለን ነው፡፡ እነዚህ አማልክት እንደ ሻማ እንዲቀልጡ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ነው፡፡ እነሱ እንደ ሻማ ሲቀልጡ ለእኛ ዕዳ ነው፡፡ ያሉትን ብቻ የመስማት ዕዳ፡፡  የገዥው ፓርቲ አመራሮች እነሱ በመሰላቸውና ባሰቡት ብቻ ነገሮች ሊስተካክሉ ይችላሉ ብለው ያምናሉ፡፡ በእነሱ አረዳድ በእነሱና በሕዝቦች መካከል ያለው የብቃትና ለመስዋዕትነት ያለው ዝግጁነት የሰማይና የመሬት ያህል ይራራቃል፡፡ እነሱ በፈለጉት ጊዜ የሚከፍቱት ወይም የሚዘጉትና ቆሞ የሚጠብቃቸው አድርገው ያያሉ፡፡ 

ላለፉት 40 ዓመታት ሥልጣንን ሲቋምጡ የኖሩ የአመፀኛው ትውልድ አካላት በየጊዜው የብሔራዊ ዕርቅ፣ የሽግግር መንግሥትና የባለአደራ መንግሥት እያሉ ሲያላዝኑ ለዘመናት ያጡትን የሥልጣን ጥማታቸውን ከማለም የዘለለ ራዕይ እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ዓላማውን አንጥሮ ሕዝብን በተራዘመ መንገድ አደራጅቶ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠለትን መብቶች (በአስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን) ሒደቱን ለመገንባት ብቃት ያለው ስትራቴጂና ታክቲክ ቀይሶ ለትግል የተዘጋጁትን ሕዝቦች ትክክለኛ አቅጣጫ መምራት አልቻለም፡፡ ብቃቱም ፍላጎቱም የለውም፡፡

በዚህ 25 ዓመታት ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የለም ብሎ ይክዳል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀን ሌሊት ሠርተው ያመጡትን ልማት በኢሕአዴግ አመራር የተገኘ በመሆኑ ለማንኳሰስ ይሞክራሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ከኢሕአዴግ በተሻለ ፕሮግራም እንዳላቸው ሁሉ፡፡

ኢሕአዴግን አዋርዶ ለማሸነፍ የሚደረገው ቂም በቀለኝነት Vindictive መሆን በሰፊው ይታያል፡፡ የዜሮ ድምር (Zero Sum Game) ነው፡፡ ሥልጣን የጠማው አመፀኛው ትውልድ አባላት በሆነ መንገድ እግሮቻቸው ወደ ጉድጓድ ከመግባታቸው በፊት በአቋራጭ ሥልጣን ለማሽተት በጣዕረ ሞት ይወራጫሉ፡፡ የሕዝቦች ጭራ ሆነው በሕዝቦች ውስጥ ያለውን ኋላቀርነት በመጠቀም ሕዝቦችን እርስ በርሳቸው እንዲጠራጠሩና እየተፋጁም ቢሆን፣ እነሱ ከቢሯቸው ወደ አራት ኪሎ ውጭ ያሉትም ቦሌ አየር ማረፊያ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው ለመግባት እየተዘጋጁ ይመስላሉ፡፡ ከንቱ ህልም፡፡ ይሳካለት አይሳካለት ኢሕአዴግ እታደሳለሁ እያለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል ጥቂት ቢሆንም የማሸነፍ ዕድሉ ዜሮ አይደለም፡፡ የአመፀኛው ትውልድ ተቀዋሚ ፓርቲዎችስ መታደስ አይገባቸውም?

የጠፋው (አብዮት የበላው) ትውልድ ደርግ ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜ ከ10 እስከ 15 ዓመት የነበረው ሲሆን፣ በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎችና ብሔር ብሔረሰቦች ሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሞ፣ ወዘተ በምሥራቅና በምዕራብ በደቡብ የብሔር፣ ብሔረሰብ በመሀል አገርና በሰሜን በትጥቅ ትግል ምክንያት የሞተው፣ የተሰደደው፣ ማንነቱን ያጣና በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ያለቀውም ጭምር ነው፡፡ ይህ ትውልድ የአመፀኛው ትውልድና የዴሞክራሲያው ትውልድ መሸጋገርያ ሆኖ ወጣቱ ተሞክሮውን እየቀመረ የትውልድ ሚናው እንዳይጫወት ትልቅ ክፍተት የፈጠረ ነው፡፡ ይህ ሸክም ለዴሞክራሲያዊው ትውልድ ትርጉሙ ትልቅ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊው ትውልድ በኢሕአዴግ በተለይ በብአዴንና በሕወሓት ሥልጣንን ሙጭጭ ብለው ለዘለዓለም መያዝ ፍላጎትና እንዲሁም በተመሳሳይ ተቃዋሚዎች የሥልጣን ጥማት መካከል (Sandwiched) ሆኗል፡፡  ወጣቱ ትውልድ የራሱን ድርሻ በግልጽ ማስቀመጥ ያለበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከአመፀኛው ትውልድ አፍላ በነበረበት ጊዜ መውረስ ያለበት ነበር ቢኖር በራስህና በሕዝብ መተማመን ነው፡፡ እንደማንኛውም ትውልድ  አዲሱ ትውልድ ላይ ጥርጣሬ፣ ንቀትና እምነት አለመጣል ማሳየቱ ነባራዊ ነገር ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ይህንን በመረዳት በሌሎች አስተያየት ሳይደናገጥ አገር ተረክቦ ጉዞውን መቀጠል ይኖርበታል፡፡

      ይህ ትውልድ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በጥናት መለየት አለበት፡፡ የራሱን ማንነት ማወቅ አለበት፡፡ “This extensive study validates that generations create their own traditions and culture by a shared field of emotions, attitudes preferences, and dispositions”. (Presensaul, 2004:01) validating generations differences: a legitimate diversity and leader issue, leoubrshy of organization development journal Vol. 25 issue 2 pages 124-141.)

ካለፉት ትውልዶች በላይ የተማረ በውጭም በውስጥም እየሠራ ያለ ምሁር ያለበት ነው፡፡ ከፍተኛ የመረጃ፣ የዕውቀት ክህሎት ያለውና የተለያዩ ሐሳቦችን የማቻቻል፣ የሌላውን ሐሳብ የማዳመጥና መተንተን የሚችል ነው፡፡ ገና በሕፃንነቱ ስለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ስለምርጫ፣ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማወቅ የጀመረ ግሎባላይዜሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተሻለ የሚረዳ አፍላ ወጣት/ጎልማሳ በመሆኑ፣ በቀጣይነት ለመማርና ለመመራመር የሚችል ብቃቱ ጉልበትም ያለው ነው፡፡ ከአሁኑ ትውልድ ውስጥ  ከአመፀኛ ትውልድ በምንም መንገድ የማይሻሉ ኢዴሞክራሲያውን  ጥቀቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህንም መታገል ያስፈልግ ይሆናል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት በአመፀኛ ትውልድ ሊገነባ አይችልም፡፡ ሥርዓቱ የራሱ ትውልድ ያስፈልገዋል፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሥልጣኑን ለመንጠቅ መታገል አለበት፡፡ ማማረር ብቻ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ያሉትን አደረጃጀቶች ውስጥ በመግባት በመቀየር ወይም የራሱን አዲስ ድርጅት በማቋቋም መታገል ይኖርበታል፡፡ ይህች አገር የወጣቱ ናት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አመራሩ የወጣቱን ችግሮች፣ ተስፋዎች፣ ሐሳቦችና ፍላጎቶች ተረድቶ በሚፈልገው ፍጥነት መፍታት አይችልም፡፡

አመፀኛው ትውልድ እታደሳለሁ ቢልም በራሱ አድማስ ነው፡፡ መመዘኛው የራሱ ፍጥነት ነው፡፡ የራሱን ብሎም ሥልጣኑን የመጠበቅ እንዳይሆን በውስጡ የሚገኙት የዴሞክራሲ ኃይሎች ዋና ዓላማ  “የጥልቅ ተሃድሶው” የዴሞክራሲ ትውልድ የሥልጣን ቅብብሎሽ ጊዜ ማሳጠርና ማንነቱን ያረጋገጠ ምሁር የላይኛውን አመራር እንዲረከብ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ በሥጦታና በመልካም ፈቃድ የሚሰጥ አይደለም፣ በትግል እንጂ፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ የዴሞክራሲ  ኃይል  ካሸነፈ ከ“የጥልቅ ተሃድሶው” የሚጠበቀው አንድና አንድ  ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማክበር!!

ሕገ መንግሥቱ ይከበር ስንል

 ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ይረጋገጡ፡፡ እነዚህ መብቶችን ለማረጋገጥ የተደራጁ ተቋማት በሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት መርሆዎች ይሥሩ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሕገ መንግሥቱ፣ ለመረጣቸው ሕዝብና ለሕሊናቸው ብቻ ተገዥ ይሁኑ፡፡ የፍርድ ቤት ነፃነት ይረጋገጥ፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እነዚህን መብቶች ብቻ በሚያረጋግጥ መልኩ ብቻ ይሥሩ፡፡ ነፃ የምርጫ ቦርድና ኮሚሽኖች ይቋቋሙ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ይረጋገጥ፡፡

እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት በሙሉ ነፃነት ይንቀሳቀሱ፡፡ ፓርቲና መንግሥት ይለያዩ፡፡ የገዥው ፓርቲ መዥገርነት ይቁም፡፡

ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚፃረሩ ሕጎች ይታገዱ ወይም ይሻሻሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፖለቲካዊ አቋሙ ሰው መታሰር የለበትም ስለሚል የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነባር የኢሕአዴግ ታጋይና የቀድሞ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...