‹‹ዱቤ ነገ እንጂ ዛሬ የለም››፣ ‹‹ዱቤ ክልክል ነው›› የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ ማስታወቂያዎች በመንደር መደብሮች አካባቢ እናያለን፡፡ በሸቀጣ ሸቀጦች መሞላት የነበረበት መደርደሪያ ገጦ፣ የሚሸጥ ዕቃ ያለባት በማትመስለው ያዘመመች ደሳሳ መደብር ውስጥ ሳይቀር በተንጋደደ ጽሑፍ ‹‹ዱቤ ክልክል ነው፤›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያ ይንጠለጠላል፡፡
በቀደሙት ጊዜያት እንዲህ ያለውን መልዕክት የያዘ ማስጠንቀቂያ በርከት ባሉ መደብሮች ውስጥ እንመለከት ነበር፡፡ እንደ ቀድሞው ባይሆንም ዛሬም ይህ መፈክር ጥቂት መደብሮች ውስጥ አሁንም ይታያል፡፡ በግልጽ አይለጠፍ እንጂ የብዙዎቹ የንግድ ድርጅቶች አሠራር ‹‹ዱቤ የለም፤›› በሚል መርህ ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ወይም በዱቤ መሸጥ ፈጽሞ እንደማይታሰብ የሚጠቁም ነገር አለው፡፡
ዱቤ ክልክል መሆኑን የሚያስገነዝቡ ባለመደብሮች ይህንን ማስታወቂያ ያለምክንያት አላኖሩትም፡፡ ምክንያት እንደሚኖራቸው አምናለሁ፡፡ ይህንን ልጽፍ ሳስብ በቅርብ ጊዜ ዱቤ የለም የሚል ጽሑፍ ካነበብኩባቸው መደብሮች አንድ ሁለቱን በማታወስ ወደ አንዱ አቀናሁ፡፡
ከባለመደብሩ ጋር መጠነኛ ትውውቅ ነበረኝና በዘዴ ይህንን መልዕክት ለምን እንሰቀለው ጠየቅሁት፡፡ ለጥያቄዬ መልስ ለመስጠት ካመነታ በኋላ በአጭሩ ‹‹ተቸግሬ›› አለኝ፡፡ ‹‹ዱቤ እየሰጠሁ ደንበኛ ሸሸኝ፡፡ ከሰርኩ…›› አለ፡፡ ሕመሙን ቀሰቀስኩበት መሰል ሦስት ደብተሮችን አውጥቶ ‹‹እይ… ይሄ አልተከፈለኝም፡፡ ይሄም አልተከፈለኝም…›› እያለ ዱቤ ሰጥቶ ሳይከፈል ቀርቷል ያለውንና በደብተሩ የተመዘገበውን የባለ ዕዳ ስም፣ የወሰደውን ዕቃ፣ የወሰዱበትን ቀን፣ ዋጋውንና እያንዳንዱ ባለዕዳ አለበት ያለውን ድምር ዋጋ የሚያመለክተውን የገንዘብ መጠን አሳየኝ፡፡
‹‹ይገርምሃል… አንዳንዱን ዱቤ ጠያቂ እንዲከፍለኝ ወትውቼ፣ ወትውቼ ምንም ስላላገኘሁ ዝም ብዬ ትቻቸዋለሁ፡፡ ዱቤ መስጠቱን ትቼ ደንበኝነታቸውን እንዲቀጥሉ ያደረግኋቸውም አሉ፡፡ ሁሉም ግን በዚያው ቀርቷል፤›› በማለት እያመነታ የጀመረውን ወግ በስሜት ይተርክልኝ ገባ፡፡
ዱቤ ክልክል ነው የሚለውን ማስታወቂያ የጻፈው በዚሁ ምሬት እንደሆነ አስረዳኝ፡፡ ዳግመኛ አንድ ጥያቄ ጣል አደረግኩ፡፡ ‹‹አሁን ለማንም አትሰጥም ማለት ነው?›› አልሰጥም፡፡ አለ ፈርጠም ብሎ ግን ጥሩ ደንበኞች አሉ፡፡ እነሱን ደግሞ አትከለክልም፡፡ አንድ ሦስት ወይም አራት የሚሆኑት በትክክል ስለሚከፍሉኝ ለእነሱ እሰጣለሁ፡፡ ሱቁን ላከራዩት ወይዘሮም ግድ ሆኖበት ዱቤ እንደሚሰጥ አጫወተኝ፡፡ ‹‹አከራይዋ የወሰዱትን ዱቤ በቶሎ አይከፍሉም፡፡ ወጥሬ ከጠየቅኳቸው ደግሞ ነገ ኪራይ ሊጨምሩብኝ ነው ብዬ ስለምሠጋ በሰጡኝ ጊዜ ይስጡኝ እያልኩ ትንሽ ትንሽ እሰጣቸዋለሁ፡፡ የሱቁን ኪራይ የከፈልኳቸው ጊዜ እንኳ ያለባቸውን ዱቤ አስበው መክፈል አይፈልጉም፡፡ ሆኖም ቀስ ብዬ አባብዬ እቀበላቸዋለሁ፡፡››
እንዲህ ያሉትን የዱቤ ደንበኞቹን የተመለከቱ የተለያዩ ገጠመኞችንም አወራኝ፡፡ ባለመደብሩ የተናገረው ትክክል ነው፡፡ እንዲህ ባሉ መደብሮች ሁሌም የሚያጋጥም ነው፡፡ በባለመደብሩና በደንበኛው መካከል ምንም ዓይነት ውል የለም፡፡ በእምነት የሚደረግ፤ በእምነት የሚፈጸም ግብይት ነው፡፡ ወደ ሕግ በመሄድ አቤት የሚባልበት ዕድል የጠበበ ነው፡፡ ክፈለኝ አትክፈለኝ እየተባባሉ ቦክስ መግጠምም ሊከሰት ይችላል፡፡ በአግባቡና በሥርዓቱ ቢሆን ግን የዱቤ ወይም የክሬዲት ግብይት መኖር ያለበት የግብይት ሥርዓቱ አካል ነው፡፡ ችግሩ የዱቤ አሰጣጡና አመላለሱ መንደሬ፣ ወይም እንደ ንግዱና ግብይቱ ሁሉ ኢመደበኛ የመሆኑ ነገር ካልሆነ በቀር በሥርዓት ቢሠራበት ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
ነገሩን ከመንደር መደብሮች ውጭ እንመልከተው፡፡ በዱቤ መገበያየት ያለ ነው፡፡ ለሸማቹም ሆነ ለንግድ ተቋማት ጠቀሜታ አለው፡፡ በሥርዓትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ከሆነም የሸማችና የአገልግሎት ሰጪውን ግንኙነት ያጠነክራል፡፡
በዓለም ላይ አደጉ የምንላቸው አገሮች ኑሯቸው ከዱቤ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት የሚመራም ነው፡፡ ሸማቹ በፕሮግራም እንዲመራ ለማድረግ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ መርጦ እንዲሸምትም ያስችላል፡፡ በዱቤ የወሰደውን ዕቃ ነገ ሊከፍል የሚያስችል ቋሚ ገቢ ካለውም ዛሬ የፈለገውን በመሸመት ፍላጐቱን ያሟላበታል፡፡ ቤት፣ መኪና፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የፍጆታ ሸቀጥ ወዘተ. ለመግዛት ዱቤ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ እርግጥ ይኸው የዱቤ ጣጣ ዓለምን ከስምንት ዓመት በፊት ቀውስ ውስጥ መክተቱ አይዘነጋም፡፡ ባንኮች መክፈል ለሚችለውም ለማይችለውም አበድረው፣ ዱቤ ሰጥተው፣ በዱቤ እንዲሸምቱ ዕድሉን ፈጥረው ኋላ ላይ ዕዳውን የሚመልስ ተበዳሪ በመጥፋቱ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡
ወደ እኛ ልምድ ስንመጣ የሸመታ ሥርዓታችን የተዋጣለት ባለመሆኑ፣ የዱቤ መልካምነት አይታይም፡፡ በፕሮግራም የታገዘ የግብይት ሥርዓት የለንም፡፡ የሸመታ ባህላችን የግብይት ሥርዓታችን ውርስ ነው፡፡ በተዘበራረቀ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ባለንበት ወቅት ሸመታችንን በፕሮግራምና በምርጫ ለማድረግ ከባድ ይሆናል፡፡
መሠረታዊ ፍላጐታችንን ለማሟላት ሁሉም በአቅሙ የዱቤ አገልግሎት የሚሰጥበት ዘመናዊ አሠራር ቢኖር፣ ለግብይት ሥርዓታችን ጤናማነት እገዛ እንደሚያደርግ አንድ ሁለት የለውም፡፡
በንግድ ተቋማት የዱቤ አገልግሎት እንደ አንድ የቢዝነስ አማራጭ እየታየ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊደረግ የሚገባውና መስፋፋትም ያለበት ቢሆንም፣ በአግባቡ አይሠራበትም፡፡ የዱቤ አገልግሎት ከሥጋት ነፃ የሆነ አሠራር እንዲኖረው በማድረግ መሥራት ቢቻልም፣ ጠቀሜታው ታስቦበት በአግባቡ እየተሠራበት አይደለም፡፡ የዱቤ አገልግሎት ለመጀመር ከባንኮች ጋር ተሳስሮ መሥራትም ይችላል፡፡
ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን የፍጆታ ዕቃዎች አለያም ሌሎች ቋሚ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚችሉበት አማራጮች ቢኖሩ፣ በግብይቱ ውስጥ ያሉ ሸማቾች የሽያጭ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትና ባንኮችም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ መንግሥትም የማይቀረውን ድርሻውን እንዲህ ባለው የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ከሚፈጸም ሽያጭ ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንለታል፡፡ ሥርዓቱም በአብዛኛው መደበኛነት ይሰፍንበት ነበር፡፡ በባንክና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠነክርና የገንዘብ ዝውውሩ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ፣ ሞቅ ያለ ገበያ እንዲፈጠር ዕድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ከሁሉም በላይ የዱቤ አገልግሎትን በመስጠት በንግድ ድርጅቶችና በባንኮች መካከል የሚፈጠረው ግንኙነት ሕጋዊ መሠረት ያለው በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ግብይት በሕግ አግባብ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ደረሰኝ ስጠኝ አትስጠኝ የሚል ውዝግብ ይቀረፋል፡፡ በዚህ ሒደትም መንግሥት ከግብይቱ ማግኘት የሚገባውን ድርሻ በሥርዓት እንዲያገኝ በማድረግ ለመንግሥት ግብር ግኝትም አስተዋጽኦ አለው፡፡
ስለዚህ ባንኮችና የንግድ ተቋማት በመተሳሰር ዜጐች የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ቢዘረጉ፣ ለግብይት ሥርዓቱ ትልቅ ትንሳኤ ይሆን ነበር፡፡
ባህላዊና ኋላቀር የሆነውን የግብይት ሥርዓት ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ከተፈለገ፣ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ ሁሉም በአቅሙ እንዲሸምት ለማድረግም ጠቀሜታ ያለው ይህንን አሠራር ቀላልና ቀልጣፋ የሚያደርገው ደግሞ የአገሪቱ ባንኮች በዘመናዊ አደረጃጀት መታጠቅ መጀመራቸው ነው፡፡ ዓለም እየኖረ ያለውም በዚህ መንገድ ነው፡፡