‹‹ለግል ጉዳዬ ከቢሮ የወጣሁት በምሳ ሰዓት ነበር፡፡ ወደ ስምንት ሰዓት ገደማ ስልክ ተደውሎ አየር ጤና አካባቢ ረብሻ ተነስቷል አሉኝ፡፡ መኪናዬን እንዴት እንዳሽከረከርኩ አላስታውስም፡፡ የታየኝ በዊልቸር የሚሄደው አካል ጉዳተኛ ልጄን ከትምህርት ቤት ማውጣት ነበር፡፡ አየር ጤና አካባቢ ስደርስ ታክሲዎች የጫኑትን ሰው እያወረዱ እልም ይላሉ፡፡ አካባቢው ላይ እገረኛ እንጂ የመኪና ፍሰት ቀንሶ ነበር፡፡ ልጄ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ስደርስ፣ ተማሪዎች ሁሉ ወጥተው ልጄንና ታናሽ ወንድሙን ብቻ አገኘኋቸው፡፡ የዘጠኝ ዓመቱ ትንሹ ልጄ አካል ጉዳተኛውንና የ14 ዓመቱን ወንድሙን ዊልቸር መግፋት አቅቶት አብረው ቆመው ነበር፡፡ በግቢው የተወሰኑ መምህራን ያሉ ቢሆንም፣ ልጆቼ ተደናግጠው ነበር፡፡ በተለይ ትንሹ ልጄ ታላቁን ጥሎ ላለመሄድ አብሮ ሆኖ ሳየው እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ‘ዳገቱን መግፋት ስለማልችል እንጂ ዊልቸሩን እየገፋሁ እወስደው ነበር’ ሲለኝ፣ ውስጤን እምናውቀው እኔና ፈጣሪ ብቻ ነበርን፡፡ ልጆቼን ይዤ ቤት ስገባ ትልቁ ልጄ ‘ምንድነው የተፈጠረው?’ አለኝ፡፡ ወደ ሰበታ አካባቢ ብጥብጥ እንዳለ ነገርኩት››፡፡
ዓይናቸው እንባ እንዳቀረረ ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. የገጠማቸውን የነገሩን አባት፣ በወቅቱ ካራ አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ ከመሃል አዲስ አበባ ተደናግጠው ወደየቤታቸው ለመግባት ያቀኑ ባለመኪኖች፣ ከሁለት ሰዓት ላላነሰ ጊዜ መንገድ ላይ ቆመው እንደበር ይገልጻሉ፡፡ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ ሰበታ አካባቢ ተከስቶ የነበረ ረብሻ አዲስ አበባንም አደናግጧት አምሽቷል፡፡ ችግር ተፈጥሮባቸዋል ተብለው በማኅበራዊ ድረገጽ በተጠቀሱ አየር ጤና፣ ካራ፣ መርካቶ፣ ሰሚትና ሌሎችም ስፍራዎች የሚኖሩ ይበልጥ ተደናግጠዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ከየትምህርት ቤት ለማውጣት ተሯሩጠዋል፡፡ ከምትኖርበት ወይራ ሰፈር አካባቢ እስከ ጦር ኃይሎች በእግሯ በመሮጥ ልጇ የሚማርበት ትምህርት ቤት የደረሰችው እናት ሁኔታውን ታስታውሰዋለች፡፡
ቤት እያለች ነው አዲስ አበባ ላይ ብጥብጥ አለ የሚል ወሬ የሰማችው፡፡ ይህ ሲሆን፣ ከሰዓት ነበር፡፡ ‹‹የሳንቲም ቦርሳዬን ይዤ ሮጥኩ፡፡ ታክሲ ማቆሚያ ስደርስ ታክሲዎች ከቆሙበት ቦታ ባዶዋቸውን እየሄዱ ነበር፡፡ ወዲያውም በአካባቢው ትራንስፖርት ጠፋ፡፡ ከቶታል አካባቢ ጀምሮ መንገዱ በመኪና ተጨናንቋል፡፡ ልጄ የሚማርበት ጦር ኃይሎች ድረስ ዳገቱን እንዴት እየሮጥኩ እንደሄድኩ አላስታውስም›› በማለት በዕለቱ ተፈጥሮ የነበውን መደናገጥ ትገልጻለች፡፡
መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ፣ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በተቃውሞ ከተቋረጠና የብዙዎች ሕይወት ከጠፋ በኋላ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቀጠለ ተቃውሞ ንብረት ወድሟል፣ መንገድ ተዘግቷል፣ ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፡፡ ይህም ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ ክልሎች ለንግድ፣ ለትምህርትና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚንቀሳቀሱ ላይም ሆነ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖውን አሳድሯል፡፡
በ2008 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተለያዩ ሥፍራዎች ተከስቶ የነበረ ተቃውሞ፣ በ2009 ዓ.ም. ቀጥሎ የአገሪቱ ዋና መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ላይም እያጠላ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣ ባይታይም፣ የተለያዩ መረጃዎችና በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ያሉ ተቃውሞዎች ከተሜውን አደናግጠውታል፡፡ ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም. እንኳን በተለያዩ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ድረገጽ በተለቀቁ መረጃዎች ሳቢያ፣ አዲስ አበቤዎች ተደናግጠው አምሽተዋል፡፡ በማግስቱም ቢሆን ለወትሮው በትራፊክ ይጨናነቁ የነበሩ አካባቢዎች ጭር ብለው ውለዋል፡፡ ‹‹በተቃውሞ እየተናጠች ነው›› የሚል መረጃን ከማኅበራዊ ድረገጽ ያነበቡ፣ በወሬ ወሬ የሰሙ በዕለቱ ምሽት ቤታቸው መሆንን መርጠዋል፡፡ ለወትሮው የማያንቀላፉ እንደ ቦሌ፣ ካዛንቺስ የመሳሰሉ አካባቢዎች ጭር ብለው ነበር፡፡ በመስቀል አደባባይና ሜክሲኮ አካባቢ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ማንም አይታይም ነበር፡፡ መኪኖችም እንዲሁ፡፡ ይህ ንዝረት በማግሥቱም አዲስ አበባን አልተለያትም፡፡ በተለይ በማግስቱ ጠዋት በመኪና የሚጨናነቁ መንገዶች ነፃ ነበሩ፡፡ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ያልላኩ ወላጆችም ነበሩ፡፡
የማክሰኞውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ረቡዕ ዕለት ልጆቻቸው ትምህርት ቤት እንዲቀሩ ለማድረግ የሞከሩ አንድ አባት ልጆቻቸው አሻፈረኝ እንዳሉዋቸው ይናገራሉ፡፡ ሁለቱ ልጆቻቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ከትምህርት ቤት እንደማይቀሩ ይገልጹላቸዋል፡፡ ‹‹ነገሮች ሊባባሱ ይችላሉ ብዬ ስለሠጋሁ ትምህርት ቤት ቅሩ ብላቸውም እሺ አላሉም፡፡ ትምህርት ቤቱ ልጆች ላይ አንዳች ነገር ቢከሰት ደውሎ ለቤተሰብ እንደሚያሳውቅ ነግረውኝ አሳመኑኝ፤›› ይላሉ፡፡ ልጆቻቸውን በሰርቪስ ወደ ትምህርት ቤት ቢልኩም ቀኑን ሙሉ ልባቸው ረግቶ አልዋለም፡፡ ልጆቻቸው ማታ ወደ ቤት ሲመለሱ እንደነገሯቸው ከሆነ ግን በልጆቻቸው ክፍል ከትምህርት ገበታቸው የቀሩ ተማሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
ልጃቸውን ከትምህርት ቤት ያስቀሩ ወላጅ ደግሞ፣ በሚኖሩበት የጋራ ግቢ እስከ ከዚህ ቀደም ከአካባቢው ርቀት የተነሳ የግቢው ነዋሪ ከ12፡30 ጀምሮ እንደሚወጣና በዕለቱ ግን እስከ ጠዋቱ 1፡30 ሰዓት ድረስ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆች ከግቢ አለመውጣታቸውን፣ አይተው እሳቸውም ከግል ሥራቸው መቅረታቸውንና ልጆቻቸውንም ከትምህርት ቤት ማስቀረታቸውን ነግረውናል፡፡
በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ ‹‹ጥቂት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቢቀሩም ብዙዎቹ ተገኝተዋል፡፡ ‹‹ከሌላው ጊዜ በተለየ ግን ብዙ ተማሪዎች አርፍደዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታውን ለማጣራት እንዳዘገዩዋቸው እገምታለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ማክሰኞ ከትምህርት በኋላ ብዙ ወላጆች በድንጋጤ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ቢገኙም፣ ረቡዕ ነገሮች ተረጋግተዋል፡፡ በእርግጥ ረቡዕ ጠዋት ልጆቻቸውን ሲያደርሱ ስለ ተማሪዎች ደኅንነት ጉዳይ አጥብቀው የጠየቁ ቤተሰቦች ብዙ ነበሩ፡፡
ግብይትን በተመለከተ ተዘዋውረን ባየንባቸው ሥፍራዎች ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ የተጋነነ ዋጋ የተጫነባቸው ምርቶች አላየንም፡፡ በሾላ ገበያ ብዙዎች ጨው ሲሸምቱ የነበረ ሲሆን፣ በአትክልትና በሸቀጦች ላይ ሰሞኑን ከነበረው ዋጋ የተለየ ጭማሪ አልነበረም፡፡ በሾላ ገበያ ቁምጣ ጨው ሲገዙ ያገኘናቸው ሸማች፣ ጨው ከርቀት ስለሚመጣና፣ በየአካባቢው የትራንስፖርት ችግር ስላለ ለጥንቃቄ መግዛታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በመዝናኛ ዘርፉም ያሳደረው ተፅዕኖ አለ፡፡ ከመስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የታወጀውን ብሔራዊ ሐዘን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለሦስት ቀናት ቴአትትር ማሳየት አቁሞ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ እንደገለጹት፣ ቴአትር ቤቱ ከመስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በኋላ ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ቴአትር ቤቱ ሥራ ከጀመረ በኋላ ቀድሞ ከነበረው ለውጦች አያደርጉም፡፡ ‹‹ቴአትር የሚታደመው ተመልካች ቁጥርም ይቀንሳል ብለው አያስቡም፡፡ ቴአትር በባህሪው መንፈስን የሚያረጋጋ የኪነ ጥበብ ዘርፍ በመሆኑ ተመልካቾች እንደቀድሞው ይመጣሉ፤›› ይላሉ፡፡ ቴአትሮቹ የሚታዩት ምሽት ላይ በመሆኑም በተመልካቹ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለው እንደማይገምቱ ያክላሉ፡፡
አዳዲስ የሆሊውድ ፊልሞችን በማሳየት የሚታወቀው በኤድና ሞል ስር ያለው ማቲ መልቲፕሌክስ በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች በፊልም ተመልካቾች ይጨናነቃል፡፡ ለወትሮው ኤድና ሞል ውስጥ ያለው የጌም ማዕከልም በታዳጊዎችና ወጣቶች ይሞላል፡፡ የኤድና ሞል ሲኒማ ክፍል ኃላፊ አቶ ኤልያስ አብርሃም እንደሚናገረው፣ ከሰኞ ወዲህ ባሉት ቀናት የሲኒማ ቤቱና የጌም ማዕከሉ ተጠቃሚዎችም ቁጥር ቀንሷል፡፡ በሲኒማ ቤቱ የሚያሳዩዋቸውን ፊልሞች ሙሉ በሙሉ ባያቋርጡም የቀነሷቸው መርሀ ግብሮች እንዳሉ ኃላፊው ይገልጻል፡፡ ‹‹የቀነስናቸው መርሀ ግብሮች አሉ፡፡ ፊልም ለማየት የሚመጡ ተመልካቾች ቢኖሩም እንደቀድሞው አይደለም››
በጋ ላይ ትምህርት ቤቶች ስለሚከፈቱ ከክረምቱ የደንበኞቻቸው ቁጥር ይቀንሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በጋ መሆኑ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ጌም ለመጫወት ወደ ማዕከሉ የሚሄዱ ሰዎችን ቁጥር ቀንሶታል፡፡ በሲኒማ አገልግሎቱም የሚስተዋለው ተመሳሳይ ድባብ ነው፡፡ እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ፣ በቅርቡ ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት በተሻለ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችሏቸው ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ከአገሪቱ ሁኔታ አንፃር ግን ፕሮጀክቱን የሚያስተዋውቁበትን መርሀ ግብር ወደፊት ገፍተውታል፡፡
ከመጻሕፍት፣ የሙዚቃ አልበሞችና ፊልሞች ምርቃት ጋር በተያያዘ ለዓመታት የሠራ አንድ አስተያየት ሰጪ እንደገለጸልን፣ በኢሬቻ በዓል የደረሰው እልቂት ሐዘን ሰኞ ዕለት የነበረውን የሥራ ድባብ ለውጦታል፡፡ ማክሰኞ ደግሞ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የተፈጠረውን ሥጋት ተከትሎ ሥራቸው ተቀዛቅዟል፡፡ የሬዲዮና ቴሌቪዥን የመዝናኛ መርሀ ግብሮቻቸውን የሰረዙም ነበሩ፡፡
‹‹አሁን እንደ ቀድሞው የምሽት የሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶች፣ የሥነ ጽሑፍ ክለቦች የውይይት መርሀ ግብር ወይም የፊልም ምርቃት ማዘጋጀት ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ ሰው አንድ ነገር ሊፈጠር ይችላል የሚል ሥጋት ስላለው በጊዜ ወደ ቤቱ ሲገባ ይስተዋላል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ትራንስፖርት ይኖራል ወይስ አይኖርም የሚል ሥጋት በመኖሩም የምሽት መርሀ ግብሮችን ማሰናዳት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ድባቡ ለፊልም ቀረጻ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይም ተፅዕኖ እንዳለውም ይናገራል፡፡ ከሰኞ ወደዚህ ባሉት ቀናት አዲስ አበባ አቅራቢያ ያሉ ከተሞች ከመሄዳቸው በፊት የየአካባቢውን ሁኔታ የሚያጣሩ ፊልም ሠሪዎች ማስተዋሉንም ይገልጻል፡፡
ሰዎች አንዳች ነገር ባይኖርም እንኳን ሕይወታቸውን ባጡና የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ሰዎች ሐዘንና ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ሥጋት፣ ከቦታ ቦታ በነፃነት ከመዘዋወር መገታታቸው አይቀሬ ነው ይላል፡፡
ተመሳሳይ ምላሽ ያገኘነው በህትመትና ማስታወቂያ ድርጅት ከሚሠሩ ግለሰብ ነው፡፡ የዚህ ሳምንት ሥራ እንደቀድሞው እንዳልሆነና ሰው ላይ በሐዘን የመሸበብ ስሜት እንደሚነበብ ገልጸውልናል፡፡ ከሐዘኑ በተጨማሪ ሰው ላይ የተፈጠረው የፍርሃት መንፈስም በዘርፉ ያለውን እንቅስቃሴ በመጠኑ አቀዝቅዞታል፡፡ ሁኔታው የበለጠ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ በመዝናኛ አካባቢዎች ነው፡፡ በተለይ አመሻሽ ላይ የሚዝናኑ ሰዎች ቁጥር እንዳለፉት ሳምንታት ብዙ ነው ብለው ደፍረው መናገር እንደማይችሉ ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥ የአንዱ ሰፈር ከሌላው የተለየ ሊሆን እንደሚችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን አንድ የምሽት ክለብ ሥራ አስኪያጅ፣ ከሙዚቃ ጋር የሚገናኙ መርሀ ግብሮች ከመታጠፋቸው ባሻገር ሰው እንደቀድሞ ወጥቶ እንደማይዝናና ተናግሯል፡፡ ‹‹ሰላም ሳይኖር ስለሙዚቃ ወይም መዝናኛ ቦታዎች ማውራት አግባብ አይደለም፤›› ይላል፡፡ ሰዎች በዚህ ወቅት ከቤታቸው ወጥተው እንዲዝናኑ መጠበቅም ከባድ እንደሆነ ያክላል፡፡ የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ ሥነ ጥበባዊ ውይይቶችና ሌሎችም ጥበብ ነክ ዝግጅቶች የሚያሰናዱ የባህል ተቋሞች በበኩላቸው መርሀ ግብሮችን አላጠፉም፡፡ በባህል ማዕከሎች መግቢያ የተለያዩ መርሀ ግብሮች ማስታወቂያዎች ተለጥፈዋል፡፡
የእሑዱን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ ሰኞ በተለይም ማክሰኞ ዕለት ትራንስፖርት ማግኘት የብዙዎች ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ መንገዶች በመኪናዎች ተጨናንቀዋል፡፡ በመንገዶች ግራና ቀኝ ወጣት፣ አዛውንት፣ ሕንፃ ያቀፉ ሴትና ወንዶች ወደተለያየ አቅጣጫ ይተማል፡፡ የራሱ ሚኒባስ ነው፡፡ የሚሠራው ከቦሌ በአትላስ ካዛንቺዝ መስመር ላይ ነው፡፡ ‹‹የሚታየው ነገር ደስ አይልም፡፡ በአጠቃላይ ጠዋትም ዘግይቼ ሰላም መሆኑን አረጋግጬ ነው የምወጣው፡፡ ማታም በጊዜ ነው የምገባው፡፡ በእንደዚህ ያለ ደስ የማይል ሁኔታ ውስጥ የሚፈጠረው አይታወቅም፣ አለመቀደም ነው፡፡›› በማለት ይገልጻል፡፡
በብዛት ካዛንቺስ፣ ሃያ ሁለትና ቦሌ አካባቢ የሚሠራው የላዳ ታክሲ ሾፌር እንደገለደልን ደግሞ፣ ከማክሰኞ ወዲህ በምሽት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቀንሰዋል፡፡ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና ማክሰኞና ረቡዕ መደበኛ ቀናት መሆናቸው ተደማምሮ የሚዝናኑ ሰዎችን ቁጥር አሳንሶታል፡፡ የተከፈቱ የምሽት መዝናኛዎች እንዳሉ ሁሉ የተዘጉም አሉ፡፡ ‹‹የታክሲ ደንበኞቼ እንዳለፉት ሳምንታት አላመሹም፡፡ በጣም ከመሸ በኋላ ያጓጓዝኳቸው ሰዎች ቁጥርም ቀንሷል፤›› ብሏል፡፡
ሥራቸው ከኢንተርኔት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ተቋሞች መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ተፈትነዋል፡፡ በተለያዩ ተቋሞች የኢንተርኔት አለመኖር ከፈጠረው መስተጓጎል ባሻገር፣ ኢንተርኔት ካፌዎችም አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፡፡ ኢንተርኔት ካፌ ያለው አስተያየት ሰጪ እንደገለጸልን፣ የአንድ ቀንም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ አንዳች ነገር ሲፈጠር ኢንተርኔትን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ የበርካቶች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳረፈ ይገኛል ይላል፡፡
‹‹በዐውደ ዓመት ዕለት እንኳን ከሰዓት ላይ ኢንተርኔት ካፌዎች ይከፈታሉ፡፡ ከዘመድ አዝማዶቻቸው ጋር ስካይፕና ቻት የሚያደርጉ ስላሉ በበዓልም እንሠራለን፡፡ ከበዓል የበለጠ ሥራ ባለባቸው መደበኛ ቀኖች ኢንተርኔት ሲቋረጥ ሥራችን አደጋ ውስጥ ይወድቃል፤›› ይላል፡፡
ያነጋገርነው የሞባይል ሽያጭና ጥገና ሱቅ ባለቤት፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት የሸማቾች ቁጥር እንደቀነሰ ገልጿል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ፊልም የማከራየትና ሶፍትዌር የመጫን አገልግሎት የሚሰጡ ሱቆች ባለቤቶችም ስሜት ተመሳሳይ ነው፡፡
መርካቶ አካባቢ በሚገኝ የልብስ መሸጫ መደብር የምትሠራዋ ወጣት ማክሰኞና ረቡዕ የነበረውን ድባብ ገልጻልናለች፡፡ ማክሰኞ ወደ ከሰዓት አካባቢ በፌስቡክ ላይ የተለቀቁ መረጃዎችን ተከትሎ ብዙ ባለሱቆች መደብራቸውን ከአደጋ ለመከላከል ሱቅ እየዘጉ ወደቤት እንደሄዱ ትናገራለች፡፡ ረቡዕ ዕለት ወደ መደበኛ ሥራቸው ሲመለሱ የሸማቾች ቁጥር ደግሞ ቀነሰ፡፡ ‹‹አብዛኛው ሱቅ ረቡዕ ዕለት ክፍት ቢሆንም ገዢዎች በብዛት አልመጡም፡፡ አንዳንድ ደንበኞቻችን ስላለው ሁኔታ ስልክ እየደወሉም ይጠይቁ ነበር፤›› ትላለች፡፡
ረቡዕ ከሰዓት አካባቢ እሷ በምትሠራበት ሱቅና አጎራባቾቿ ያሉ ሰዎች ገንዘባቸውን ከባንክ ስለማውጣት ያወሩ እንደነበር ገልጻለች፡፡ ገንዘባቸው ባንክ ውስጥ በመቀመጡ ደኅንነት ያልተሰማቸው ነጋዴዎች ገንዘባቸውን ስለማውጣት ቢነጋገሩም ማድረግ አለማድረጋቸውን እርግጠኛ አለመሆኗንም ትናገራለች፡፡ በተለያዩ ክልል ከተሞች ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ሁኔታዎችን አባብሷቸዋልም ትላለች፡፡
በአንድ የአበባ አምራችና ላኪ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ግለሰብ በተለያዩ አካባቢዎች የአበባ እርሻዎች መቃጠል ካሳደረው ተፅዕኖ በተጨማሪ የሰሞኑ የአዲስ አበባ ሁኔታ ሥጋት ላይ እንደጣላቸው ይናገራል፡፡ ቀድሞ ከስምንት እስከ አሥር የሚደርሱ መኪናዎች አበባ ወደ ውጪ ለመላክ ይገኙ ነበር፡፡ ከሰኞ ወዲህ ግን ቁጥራቸው እንደቀነሰ ያስረዳል፡፡
‹‹የውጭ ኢንቨስተሮች አገር ውስጥ መሬት ወስደው ሲሠሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን የሚይዙበት መንገድ ይተቻል፡፡ የአሪቱ ዜጎች ምን ያህል ተጠቃሚ ናቸው ሲሉ የሚጠይቁም አሉ፡፡ በዚህና ሌሎችም ምክንያቶች የአበባ እርሻና መኪኖች ዒላማ ስለተደረጉ ለመሥራት ሠግተናል፤›› ይላል፡፡ ምርት ወደ ውጪ የሚልኩ ድርጅቶች ከተቀባዮቻቸው ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት እንቅፋት እንደገጠመውም ይናገራል፡፡
በአንድ የግል ፋይናንስ ተቋም የሚሠሩ ወይዘሮ፣ በመሥሪያ ቤታቸው የሚወራው ሁሉ ስለ አገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከዛ ውጪ በሥራቸው ላይ ለውጥ እንደሌለም ያክላሉ፡፡ በእርግጥ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ድንበር ላይ ያሉ ሰፈሮች ውጥረት ይታይባቸዋል፡፡ ማክሰኞና ረቡዕ ምሽት አካባቢ ከተማው ጭር ማለቱንም ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮዋ የሚኖሩት ጀሞ አካባቢ ሲሆን፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ አካባቢው ጭር እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ ወደ ፉሪ ያሉ ሱቆች አብዛኞቹ ሁለቱን ቀናት ዝግ ነበሩ፡፡ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር በሁለቱ ቀናት ይደዋወሉም ነበር፡፡ ምሽት ላይ ቤተሰቦች እየተደዋወሉ በቤት መኪና ወደየቤታቸውም እንደሄዱም ይናገራሉ፡፡
ያለውን ሁኔታ በማጤን ሰዎች እንቅስቃሴአቸውን በመገደብና በሌላም መልኩ የወሰዷቸው የጥንቃቄ ዕርምጃዎች መልካም ቢሆኑም፣ በሌላ በኩል እዚያ ጋር እንደዚህ ሆነ ወይም እንደዚያ በሚሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎች መሸበርና ራስን ችግር ውስጥ መክተትም ሊኖር እንደሚችል ሰዎች ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ እዚህ ቦታ እንዲህ ሆነ ሲባል በተቻለ መጠን አካባቢው ላይ ለሚያውቁት ሰው እንኳ ስልክ በመደወል ለማጣራት መሞከር ለራስም ለሌሎችም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህን አለማድረግ ግን አካባቢዎች ላይ ብሎም ከተማ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲሰፍን የድርሻውን ያበረክታል፡፡
በምሕረት ሞገስና በምሕረተሥላሴ መኮንን