Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ዘንድሮ በእግር ኳሱ ሰላማዊ የውድድር ማዕቀፎችን እንፈጥራለን የሚል እምነት አለን››

‹‹ዘንድሮ በእግር ኳሱ ሰላማዊ የውድድር ማዕቀፎችን እንፈጥራለን የሚል እምነት አለን››

ቀን:

አቶ አበበ ገላጋይ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮ መርሐ ግብር ጥቅምት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡ የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቱም በይፋ ተከናውኗል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፕሪሚየር ሊጉ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ‹‹ይካሄዳል አይካሄድም›› የሚለው በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንዳንድ የክለብ አመራሮችም ይህንኑ ይጋራሉ፡፡ በፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አበበ ገላጋይ በበኩላቸው ውድድሩ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት መከናወን ይችል ዘንድ በፌዴሬሽኑም ሆነ በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሪሚየር ሊጉ ጥቅምት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚጀመር ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ከሜዳ ዝግጅት፣ ከስፖርታዊ ጨዋነትና በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የተደረገው ዝግጅት እንዴት ይገለጻል?

አቶ አበበ፡- የሜዳ ዝግጅትን በተመለከተ ብዙዎቹ የአገሪቱ ክለቦች ከአንዳንዶቹ የክልል ክለቦች በስተቀር ያሉት ሜዳዎች ውድድሮችን በሚፈለገው መጠን ለማከናወን የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው የአዲስ አበባ ክለቦች የሚጫወቱት በአዲስ አበባ ስታዲየም ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ፌዴሬሽኑ የሜዳ ዝግጅትን በተመለከተ ከክልልና ከክለብ አመራሮች ጋር በመነጋገር ያሉት ሜዳዎች ማሻሻያዎች እንዲደረግላቸው ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለውድድር አመቺ ሆኖ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ቤቶች ያሉዋቸው እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ፌዴሬሽኑም የሜዳ ባለሙያተኞችን ወደ ክልሎች በመላክ ክትትል በማድረግ ላይ ነው፡፡ በጉዳዩ የክልል መንግሥታትንም በማሳተፍ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡ ከፀጥታና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን በተመለከተም ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ከራሳቸው ከክለቦቹ ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እየተሠሩም ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሜዳ ዝግጅቶችን በተመለከተ ከዚህ በፊት በነበሩ ዓመታት ችግሩ ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህ አኳያ ዘንድሮ ተግባራዊ ለመደረጉ ዋስትናው ምንድነው? ምክንያቱም እንግዳ ቡድኖች፣ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ከእንግዲህ ዋስትና ካልተገባላቸው በስተቀር ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት እንደማይችሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየተናገሩ መሆኑ ይነገራል፡፡

አቶ አበበ፡- እያንዳንዱን ነገር መረዳት የሚኖርብን ከአገሪቱ አቅም አኳያ ነው፡፡  ምክንያቱም ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ሜዳዎች የተሟሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን ያሉትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የግድም ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ሌላው በግልጽ መነጋገርና መተማመን የሚኖርብን ክለቦቻችን የቆይታቸውን ያህል በተለይ የሜዳ ዝግጅት ላይ ሠርተዋል ለማለት አይቻልም፡፡ በፌዴሬሽኑ በኩል አሁን ያለውም ሆነ ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ሜዳዎች እንዲኖሩ ጥረት ያላደረጉበት ጊዜ የለም፡፡ እርግጥ ነው በመንግሥት ደረጃ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከመጪው ኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን፣ አንድ ክለብ፣ ክለብ ለመባል የሚያበቃውን መስፈርት ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ መስፈርቶች የሜዳ ዝግጅት ተጠቃሽ ነው ከዚህ አኳያ በፌዴሬሽኑ በኩል ምን ታቅዷል?

አቶ አበበ፡- እንደተባለው መመርያው ክለቦቻችን በካፍም ሆነ በፊፋ ደረጃ የሚጠየቁ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉና ያንን የሚያረጋግጡ ከሆኑ ብቻ ነው ፈቃድ (የክለብ ላይሰንስ) የሚያገኙት፡፡ በውድድር ዓመቱ ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ በአህጉራዊው የክለቦች ውድድር ተሳታፊ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለመወዳደር የክለብ ላይሰንሲንግ ፕሮግራም ውስጥ መግባት ከቻሉ ብቻ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሜዳ ጉዳይ በእኛ ብቻ ሳይሆን የካፍና ፊፋ ጉዳይም እየሆነ መምጣቱ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በፌዴሬሽኑ የክለብ ላይሰንሲንግን የሚመለከት ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት (ክፍል) መሥርቷል፡፡ የማናጀር ቅጥርም ፈጽሟል፡፡ ዲፓርትመንቱስ ምን እየሠራ ነው?

አቶ አበበ፡- ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ዲፓርትመንቱ ከፌዴሬሽኑ ጋር ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ባለው ሁኔታ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን የማስኬድ አቅም አለው ብለው ያምናሉ? በተለይ ስፖርታዊ ጨዋነትን ከማስፈን አኳያ፡፡

አቶ አበበ፡- ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከፌዴሬሽኑ በተጨማሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ ከሁሉም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱም ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስዔዎችን ከነመፍትሔዎቻቸው ጭምር ተለይተው ታውቀዋል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ችግሮቹ መቶ በመቶ ይቀረፋሉ ብለን ባናምንም በተቻለ መጠን ዘንድሮ በእግር ኳሱ ሰላማዊ የውድድር ማዕቀፎችን እንፈጥራለን የሚል እምነት አለን፡፡ ምክንያቱም ከጥናቱ እንደታየው ተጠያቂነቱ የፌዴሬሽን አመራሮች፣ የክልልና የክለብ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ሚኒስቴሩ ጭምር መሆናቸው በዝርዝር ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ሚኒስቴሩ ባቀረበው ጥናት፣ ለችግሮቹ በዋናናት ተጠያቂ ያደረገው የማስፈጸም አቅም ውስንነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአንድ ዓመት በፊት የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አስጠንቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የጥናቱ አተገባበር ምን እንደሚመስል እስካሁን ድረስ አይታወቅም፡፡ ይኼ ብቻውን ሚኒስቴሩ ላስጠናው ጥናት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም?

አቶ አበበ፡- ስትራቴጂክ ዕቅዱ እየተሠራበት ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ የአስተዳደርና ሌሎችም የልማት ሥራዎች የሚሠሩት ዕቅዱን መሠረት አድርገው በወጡ መመርያና ደንቦች ነው፡፡ ዕቅዱ መቶ በመቶ እየተሠራበት ነው የሚል እምነት ግን አይኖረኝም፡፡ ሆኖም  በተጨባጭ የሚታዩ ሥራዎች ግን አሉ፡፡ ሌላው ዕቅዱ የአምስት ዓመት እንደመሆኑ በምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚሠራበት እንደሚሆንም ሊወሰድ ይገባል፡፡ ሌላው እንደነዚህ የመሰሉ ሰነዶች ሲዘጋጁ መቶ በመቶ ፍፁም ናቸው ተብሎ መውሰድም ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ መነሻ ሊሆኑ ይችላል፡፡ መታየት ያለበትም በአንፃራዊነት ሊሆን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሮችን ከመምራት አኳያ በእርስዎ የሚመራው የውድድር ዲፓርትመንት በሙያተኛ ደረጃ የአቅም ውስንነት እንደሚስተዋልበት ይነገራል፡፡ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አበበ፡- በውድድር ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዘርፍ ፍፁም ነው ተብሎ የሚወሰድ ነገር የለም፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚመሩ በርካታ የፕሪሚየር ሊግ፣ የከፍተኛ ሊግ፣ የብሔራዊ ሊግ፣ የሴቶችና በተለያየ ዕድሜ ደረጃ የሚካፈሉ የወጣቶች ውድድሮች አሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ የሚመጥን የሙያተኛ አቅም አለ ወይ? ከሆነ መልሴ የለም ነው፡፡ ምክንያቱም በሙያተኛ ደረጃ በቂ የሰው ኃይል የለንም፡፡ ያሉንን ሙያተኞች እያብቃቃን የምንመራው ውድድር ነው ያለው፡፡ በአጠቀላይ ዓመቱን ሙሉ የሚዘልቁ ውድድሮች ወደ 13 የሚጠጉ ናቸው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ውድድሮች በሙያተኞች አቅም ውስንነት ተስተጓጉለዋል ከተባለ መነጋገር እንችላለን፡፡ እርግጥ ነው ጥራት ላይ ችግሮች እንዳሉ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተጠቀሱት ውድድሮች ፕሪሚየር ሊጉን ብንወስድ፣ የዓመቱ መርሐ ግብር ሳይቆራረጥ የተጠናቀቀበት ጊዜ የለም?

አቶ አበበ፡- ባለፈው የውድድር ዓመት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የዋናው ቡድን ብቻ ሳይሆን በሴቶችና በወጣቶች በተለያየ የዕድሜ ደረጃ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ቡድኖች ግብዓቶቹ ክለቦች ናቸው፡፡ ይህንኑ በሚመለከት በጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀው የፌዴሬሽኑ የውድድር መመርያ፣ አንድ ክለብ ከሦስት በላይ ተጨዋቾችን ካስመረጠ በመደበኛው የሊግ ውድድር ያለመጫወት መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ሲኖራቸው ከሦስት በላይ ተጨዋቾችን የሚያስመርጡ ክለቦች ስለሚኖሩ ውድድሮች የግድ እንዲቋረጡ ይደረጋል፡፡ ለውድድሮች መቆራረጥ በትልቁ ችግር እየሆነ ያለው ይኼ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከኮንሰርት ዝግጅት ጀምሮ ፕሮግራም ሲኖረው ውድድሮች ይቋረጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ባሉበት ለውድድሮች መቆራረጥ የፌዴሬሽን ችግር ብቻ ተደርጎ የሚወሰደው እንዴት ነው? በዚያ ላይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ባለቤት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አለመሆኑ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- መፍትሔ የሚሉት ምንድነው?

አቶ አበበ፡- ለመደበኛ ውድድሮች መቆራረጥ ምክንያት ከሆኑ ችግሮች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ሲኖረው ከሦስት በላይ ያስመረጡ ክለቦች የሚለው የውድድር መመርያ እንደገና መታየት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም አንድ ክለብ ለአንድ የውድድር ዓመት እስከ 30 ተጨዋቾችን ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ክለቡ ከሁለት ጨዋታ በላይ ማሠለፍ የሚችላቸው ተጨዋቾች እንዳሉት ያሳያል፡፡ ይኼ ከሆነ ደግሞ ሦስት ልጅ ያስመረጠ ክለብ ቢጫወት ጉዳት አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ደንቡ እንደገና መጠናት እንደሚኖርበት የተናገርኩት፡፡ ስታዲየሙ የሚያስተናግዳቸው ሌሎች ፕሮግራሞችን ሳያካትት ማለት ነው፡፡ ከሁለት ቡድን በላይ ያለው ክለብ፣ ሦስትና አራት ልጅ ለብሔራዊ ቡድን አስመርጫለሁና አልጫወትም የሚለው ምክንያት በእኔ እምነት ሚዛን የሚደፋ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተቋሙን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲከታተልና እንዲያስፈጽም ከጠቅላላ ጉባኤ አደራ የተሰጠው አካል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ደንብና መመርያዎች አጀንዳ ተይዞላቸው እንዲሻሻሉ ለጉባኤ የማቅረብ መብት ያለው መሆኑን ጭምር ያሳያል፡፡

አቶ አበበ፡- ሥራ አስፈጻሚው በአጀንዳ መልክ ማቅረብ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ያቀረበውን አጀንዳ ተቀብሎ የሚያፀድቀው ጠቅላላ ጉባኤው ስለሆነ ነው መታየት ይኖርበታል ለማለት ያስደፈረኝ፡፡ ምክንያቱም መደበኛ ውድድሮች በሚቆራረጡበት ጊዜ ለምን ብለው ቅሬታ የሚያቀርቡት ራሳቸው ክለቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ለውድድሮች መቆራረጥ ምክንያት መሆኑ ስለሚታመንበት ደንብ ለማውራት አንደበታቸው ለምን እንደሚያዝ ግልጽ አይደለም፡፡ በ2008 የውድድር ዓመት የከፍተኛ ሊግ ፕሮግራም እስከ ነሐሴ ወር ዘልቋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ከከፍተኛ ሊግ ሦስትና ከሦስት በላይ ተጨዋቾችን ያስመረጡ ክለቦች ስላሉ ነው፡፡ ክለቦቹ ደንቡን መሠረት አድርገው ባነሱት ጥያቄ ውድድሮች ለወራት እንዲቋረጡ ሆኗል፡፡ በእርግጥ ፌዴሬሽኑ አሁንም ይኼ ደንብ እንዲሻሻል አጀንዳውን ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዕድሜና ተያያዥነት ባላቸው ምክንያቶች በእግር ኳስ ዳኞችና በጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ላይ የአቅም ውስንነት እንዳለም የሚናገሩ አሉ?

አቶ አበበ፡- በ2008 የውድድር ዓመት ዳኞችንና ኮሚሽነሮችን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ የወሰዳቸውን የውሳኔ ሐሳቦች በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህንኑ ታሳቢ ተደርጎ፣ የፌዴሬሽኑ ውድድር ክፍል በዚህ ጉዳይ ማስረጃዎቹን መሠረት በማድረግ የወሰዳቸው የዲሲፕሊን ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ይኼ ወደፊትም የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የአገሪቱ የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ወቅታዊ አቋማቸው በካፍም ሆነ በፌዴሬሽኑ በሚመለከተው አካል የሙያ ማጠናከሪያ ሥልጠናና ያንን የሚያረጋግጥ ፈተና ሳይወሰዱ ምደባ አይከናወንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለክልል ጨዋታዎች፣ ዳኞችና ኮሚሽነሮች እንዲንቀሳቀሱ የሚደረጉት አንድ ላይ ነው፡፡ የጨዋታው የመሀል ዳኛ ግልጽ ስህተት መሥራቱ በቪዲዮ ማስረጃ ጭምር ተረጋግጦ ሳለ ነገር ግን የጨዋታው ታዛቢ ዳኛ ለመሀል ዳኛው የሚሰጠው ነጥብ ከፍተኛ መሆኑ ክለቦች በየጊዜው የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ ይኼስ እንዴት ይታያል?

አቶ አበበ፡- በዚህ ጉዳይ ከሁሉም በላይ ሊታመንበት የሚገባው የሙያ ሥነ ምግባር እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን እነዚህን የሙያ ግድፈቶች ጨምሮ በማስረጃ ተረጋግጦ ከቀረበ ፌዴሬሽኑ መመርያውን መሠረት አድርጎ ዕርምጃ የወሰደባቸው አሉ፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጉዳይ የካፍም ሆነ የፊፋ የሥነ ምግባር ደንብ፣ ጨዋታ ጥሩ ሆኖ ከተጠናቀቀ ጥሩ ነው፣ ካልሆነም የተፈጠረው ክስተት በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ነው የሚደነግገው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የሙያ ሰብዕና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዕድሜውን የሚመጥን ዕድገት ላይ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አበበ፡- በእርግጥ የአገሪቱ እግር ኳስ የረዥም ጊዜ ታሪክ እንዳለው የሚካድ አይደለም፡፡ የዕድሜውን ያህል የሚመጥን ዕድገት አሳይቷል ወይ? ለሚለው ከኋላ ጀምሮ የተቀመጡ ሰነዶችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ የግል አስተያየቴን ከተባልኩ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የአፍሪካ እግር ኳስን ከመሠረቱ ጥቂት አገሮች አንዱ መሆኑ ባያከራክርም ዕድገቱ ግን ያንን የሚመጥን አይደለም፡፡ ለዚያም ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ የተደረጉ የመንግሥትና የሥርዓት ለውጦች በእግር ኳሱ ላይ ተፅዕኖ ያሳረፈበት ወቅት መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡ ለዚህም ቀድሞ የነበሩ የትምህርት ቤቶች ስፖርቶችና ማዘውተሪያዎችን ብንመለከት በጊዜ ሒደት እየጠበቡ የመጡበት ሁኔታ እንዳለ ያሳያል፡፡ ከንጉሡ ሥርዓት ጀምሮ ባሉት ሦስት የመንግሥት ሥርዓቶች በተለይ በደርግ መንግሥት ወጣቱ እግር ኳሱን የሚያዘወትረው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከአገር ለመውጣት ነበር፡፡ በዚያ ሥርዓት አንድ ትውልድ በሚያስችል መልኩ ዕድገቱ እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ ወደ ምንገኝበት ሥርዓት ስንመጣ በአዲስ አበባ በእያንዳንዱ ቀበሌ የነበሩ ማዘውተሪያዎች የሉም፡፡ ይኼ ለእግር ኳሱ ዕድገት ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ እግር ኳሱን በመላ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተደራሽ በማድረግ ረገድ በአሁኑ ወቅት ትልቅና የሚታይ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ማለትም ስፖርቱ ከመዝናኛነት ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንዲሆን ተሠርቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...