Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከምንም ነገር በላይ ለአገር ይታሰብ!

  ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች ለአገር የሚበጁ አይደሉም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች በአገር ንብረት ላይ እየደረሱ ያሉ ውድመቶች የአገርን ተስፋ የሚያደበዝዙና የሕዝብን ከድህነት የመውጣት ጽኑ ፍላጎት የሚያጨልሙ ናቸው፡፡ በፋብሪካዎች፣ በንግድ ተቋማት፣ በተሽከርካሪዎች፣ በእርሻዎች፣ በመንግሥታዊ ተቋማትና በመሳሰሉት ላይ እየደረሱ ያሉ ውድመቶች በጊዜ ካልተገቱ አገሪቱንና ሕዝቧን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታሉ፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ንብረቶች በወደሙ ቁጥር ተጎጂው ግብር ከፋዩ ሕዝብ ነው፡፡ የምትጎዳው አገር ናት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከምንም ነገር በላይ መታሰብ ያለበት ለአገር ነው፡፡

  የሕዝብ ቁጣ ገንፍሎ በአገር ላይ ችግር ከመፍጠሩ በፊት መፍትሔ የመፈለግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አቅርቦ አፋጣኝ ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር ከሰላማዊ ሠልፍ አልፎ ወደ ሁከት ይቀየራል፡፡ ሁከቱ ግጭት ይቀሰቅስና ለዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት መንስዔ ይሆናል፡፡ ዓመት ሊሞላው የአንድ ወር ያህል ዕድሜ ባስቆጠረው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት በዚህች አገር በርካቶች ሞተዋል፡፡ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በኢሬቻ በዓል ላይ በደረሰው አደጋ ሳቢያ የበርካታ ዜጎች ሕይወት በማለፉ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞው አገርሽቷል፡፡ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በበርካታ ሥፍራዎች ከፍተኛ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ አገርንና ሕዝብን የማይወጡት ኪሳራ ውስጥ የሚከት የአገር ሀብት ሲወድም ሰላምና መረጋጋትም ይጠፋል፡፡ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትና ሥጋት ይፈጥራል፡፡ በአገር ህልውና ላይም አደጋ ይደቅናል፡፡ ይህም በሰፊው እየታየ ነው፡፡

  መንግሥትን ጨምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ይህ ውድመት በአስቸኳይ እንዲገታ፣ የአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ቀውስ ውስጥ እንዳይገባና ሕዝብ ለአደጋ እንዳይጋለጥ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወቅቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ለዓመታት የሚታየውን የተበላሸ ግንኙነት በማስተካከል አገርና ሕዝብን የሚያረጋጉበት እንጂ፣ ለአገር የማይጠቅሙ ድርጊቶች የሚፈጸሙበት ባይሆን ይመረጣል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ፣ መሠረታዊ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ማየት ተገቢ ነው፡፡ የሕዝቡ ቅሬታና ምሬት እየጨመረ ከፍላጎቱ ጋር የማይመጣጠን ቃል መግባትና አገም ጠቀም ዕርምጃ መውሰድ የፈየደው ከሌለ፣ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ተግባራዊ ዕርምጃ የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር መመካከር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለአገር የሚበጅ እስከሆነ ድረስ መወያየት፣ መደራደር፣ የጋራ መግባባት ላይ መድረስና የመሳሰሉት አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ የሕዝቡ አስተያየቶችም በነፃነት ሊደመጡ ይገባል፡፡

  አሁን በስፋት እየተወሳ ያለው መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር ለማሳየት መዘግየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከገባው ቃል ጋር የሚጣረሱ ድርጊቶች መታየታቸው ነው፡፡ ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ መንግሥት በፍጥነት ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ምላሹ በዘገየ ቁጥር ውጤቱ ግጭት ነው፡፡ ሞት ነው፡፡ ውድመት ነው፡፡ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው፡፡ የዜጎች ሕይወት እንዳይጠፋና የአገር ንብረት እንዳይወድም በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በነፃነት መነጋገር አለባቸው፡፡ ከተቻለም የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ በመግባት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈና የአገር ሀብት እየወደመ የሚቀጥል ከሆነ ግን አገሪቱ የማትወጣበት አረንቋ ውስጥ ትገባለች፡፡ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገው ጥረትም ተስፋው ይመክናል፡፡ የሕዝብም ሆነ የአገር ህልውና አስፈሪ ይሆናል፡፡  

  በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለው አካሄድ ግን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለአገር ዘለቄታ ህልውና አደገኛ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ የማያሳስባቸው ዜጎች በሙሉ የጥፋትና የውድመት ጎዳናዎች እንዲዘጉ መረባረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት ግንባር ቀደሙ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ለመፍትሔ የሚረዱ የፖሊሲ ውሳኔዎች ይጠበቁበታል፡፡ የኃይል ተግባር የሚጠቅም ባለመሆኑም ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚስማሙ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ይዞ ይቅረብ፡፡ በተቃውሞው ጎራ ያሉ ወገኖችም አሁን እየታየ ያለው ድርጊት ለአገር የማይጠቅም መሆኑን በመረዳት በታላቅ ኃላፊነት መንፈስ የተሻለ ሐሳብ ይዘው ይቅረቡ፡፡ በመወቃቀስና በመጨቃጨቅ ምንም ጠብ የሚል ነገር ስለሌለ ለዴሞክራሲያዊ ሒደት የሚረዱ አማራጮችን ይዘው ይቅረቡ፡፡ የሕዝቡን ትግል በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየመራን ነን የሚሉ ወገኖችም በስመ ትግል አገር ከሚያፈርስ ተግባር ቢቆጠቡ ይመረጣል፡፡ በሩቅ ርቀት ሆነው በአግባቡ የማይቆጣጠሩትን ኃይል በርታ ግፋ እያሉ በሚያደርሱት ጥፋት አገርን ማተራመስ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘለቄታውም ሊያጠፉ እንደሚችሉ ከወዲሁ ቢረዱት ይሻላቸዋል፡፡ ሌላው ቢቀር የታሪክ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡

  የሕዝብ ጥያቄ ፈሩን ስቶ አገርን በማፍረስ ሕዝቡን ደግሞ ለዕልቂት እንዳይዳርግ ቢዘገይም መነሳት ተገቢ ነው፡፡ አመፁ እየበረታ ሲሄድ የበለጠ ሞት ይኖራል፡፡ የሕዝቡ ሀብት ይወድማል፡፡ አገርም ለውድቀት ትዳረጋለች፡፡ ነገር ግን ሰላምና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዓውድ እንዲፈጠር ከተፈለገ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለዴሞክራሲያዊ አካሄድ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ወገን ለአገር ይበጃል የሚለውን ሐሳብ ይዞ መነጋገር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህንን ዕድል አሳልፎ መስጠት አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ጥፋት መጋበዝ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ የሚረካባት ታላቋን ኢትዮጵያን እየዘነጉ መተራመስ ሳይሆን፣ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይበገር በፍቅር ፀንቶ የኖረው ኢትዮጵያዊነት በዘለቄታዊነት የሚቀጥለው ከግልና ከቡድን ፍላጎት በላይ ለአገራችን ስናስብ ብቻ ነው፡፡ አገሩን የሚወድ ዜጋ ደግሞ በተሻለ መሠረት ላይ እንድትገነባ ተግቶ ይሠራል እንጂ፣ ፈጽሞ አያወድማትም፡፡ የኢትዮጵያዊነት አኩሪና ጨዋ ልምድም ይህ ነው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት የሆነው የመጠፋፋት ድርጊት ቆሞ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያብብ፡፡ ለዚህም ነው ከአገር በላይ የሚያሳስብ ምንም ነገር የለም የሚባለው! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

  በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ንግግሩን ለማስጀመር ያቀረበውን ጥሪ መንግስት ተቀበለ

  የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር...

  የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች ውዝግብ በኢትዮጵያ

  ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ...